Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርስለ ኮንዶሚኒየም በእኔ የደረሰ እንዳይደርስባችሁ

ስለ ኮንዶሚኒየም በእኔ የደረሰ እንዳይደርስባችሁ

ቀን:

የወርሐ መጋቢት የ7ተኛ ዙር የኮንዶሚኒየም ዕጣ ሲወጣ እጅግ በጣም ደስ አለኝ፡፡ የምኖረው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ 5 ቀበሌ 07 ውስጥ ሲሆን፣ ዕጣውን ያየሁት ግን በድንገት በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 20 የሕዝብ መዝናኛ ክበብ ጊቢ ውስጥ ተለጥፎ ነው፡፡ የዚያች ቀን ደስታዬ ቢለካ ለ22 ዓመት በኪራይ የኖርኩበትን የስቃይ ዘመን በደቂቃ ያጠፋው ስሜት መግለጽ እስከማይቻለኝ ድረስ ነበር፡፡ ወደ ሰፈሬ ስሄድ በመኪና እንዳልሆነ አውቃለሁ 20 ግን ደቂቃ አለፈጀብኝም፡፡ ቅርብ ለሆኑ ጓደኞቼ ሁሉ ስልክ እየደወልኩ ነገርኳቸው፡፡ አብዛኛዎቹ የደስታዬ ተካፋይ ሆኑ፡፡ እድለኛነቴን የነገሩኝ የማውቃቸውም፣ የማላዋቃቸውም ነበሩ፡፡

ታዲያ ቀኑ ደረሰና ክፍለ ከተማ ቅረቡ በተባለበት ጊዜ ካርዴን ይዤ ቀረብኩ፡፡ ጀሞ የሕንፃ ብሎክ 3 -15/11፣ የቤት ቁጥሩ ደግሞ 120/60 ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ፎርም ተሰጥቶኝ ስሞላ በፎርሙ ላይ በአምስት ቀን ውስጥ ባንክ ቅድመ ክፍያ ከፍለው ይምጡ ይላል፡፡ ባለ ሁለት መኝታ፣ ካሬ ሜትሩ 70.72 ነው፡፡ ቅድመ ክፍያው ደግሞ 33,000 ብር ከልዩ ልዩ ወጪዎች ጋር በድምሩ 36,000 ብር ይላል፡፡ በዚህ ጊዜ በጣም ትልቅ ሥጋት ተፈጠረ፡፡ ይህ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ለእኔ ከ1,000 ብር በታች ደመወዝተኛ ለሆነ ሰው የሚቀመስ አይደለም፤ ተራራ ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎችን ጠየኩ፣ በጣም ግራ ተጋባሁ፡፡ ደስታዬን የሚያደበዝዝ እየሆነ መጣብኝ፡፡ ክፍለ ከተማ ሄጄ ችግሬን ልገልፅ ሞከርኩ መፍትሔ ግን አላገኘሁም፡፡ በዚያው ሳምንት መክፈል ያልቻሉ አንድ ወር ጊዜ ይሰጣቸውና ከዚያ በኋላ እንደገና ዕጣ ይወጣበታል፤ ባለዕጣነታቸውም ይሰረዛል የሚባል ነገር እየታሰበ መሆኑን ሰማሁ፤ አነበብኩም፡፡ ደስታዬ ሁሉ ወደ ሐዘን ተለወጠ፡፡ መሸብኝ፣ ተስፋ አጣሁ፡፡ ምርር ብዬ አለቀስኩ፡፡ ለተቀጠረንበት ቀን ሦስት ቀን ሲቀረው ደግሞ አንድ አዲስ ነገር ተፈጠረ፡፡

- Advertisement -

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር፣ አዋቂና የትውልድ አደራ ያለበት፣ ለብዙኃን የሚያስብና የሚያዝን ተቆርቋሪ ከሚፈጠርበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ ሰው ተገኘ፡፡ እኔ መፍትሔ አለኝ አለ፡፡ ባዶህን ከምትወጣ በብድር ትፈርምልኛለህ፤ ገንዘብም ታገኛለህ እኔም እጠቀምበታለሁ አለና አግባባኝ፡፡ ችግር ቢፈጠርስ ስለው ለእኔ ተወው አለኝ . . . ዕውቀት አለው፣ ዘመድ አለው፣ ገንዘብም አለው አልኩና አመንኩት፡፡ ዘመዶቹ ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ምሁራንና ደላሎች ጭምር ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ዕውቂያው ብዙ ነው፡፡ ሀብታሞች፣ ልዩ ልዩ የመሥሪያ ቤት ሰዎች አሉት፡፡ በትርፍ ጊዜውም ያስተምራል በጥሩ ቦታ ወታደሮችን፣ መኮንኖችን አባሎችን ሳይቀር ሌትም ቀንም ለሥጋና ለነፍሳቸው እንዲሁም ለአገራቸው የሚፀልዩትን ክርስቲያኖችም ያስተምራል፡፡

ይህ ሰው ሰዎችን ይጎዳል ቢባል ተናጋሪውን ነው ሐሰተኛ  የሚያስብለው፡፡ ይህ ግለሰብ ደስ ያለውን የገንዘብ ቁጥር መጠን ጠቅሶ አስፈረመኝ፡፡ ይህን አድራጎቴን ብዙዎች ትልቅ ስህተት ብለው ይፈርጁታል፡፡ አንድ መቶ ሺሕ ብርም ሰጠኝ፡፡  መጀመርያ ደስታ ከዚያ በኋላ ሐዘን፣ አሁን ደግሞ ተመልሶ ደስታ መጣ ተባለ፡፡ ይኸው ደስታ ግን ከጥቂት ወራት ሳይቆይ ግለሰቡ የተሰጠኝን ገንዘብ አብረን ባንክ ያስገባነውን በፍርድ ቤት ቀድሞ በማሳገድ ብድር አበድሬው አልመለሰልኝም በማለት የክስ ቻርጅ ሰጠኝ፡፡ ደስ የሚለው ገንዘቡን አልነካሁትም ነበር፡፡ ያልመለስኩት ግን መጠኑ ልብ ወለዳዊ የሆነውና ያስፈረመኝን ነው፡፡ በቀጠሮው ቀን ስሄድ የመከላከያ ማስፈቀጃ እንጂ መልስ አልተባልክም ተብዬ ወዲያው ተፈረደብኝ፡፡ ዕድለኛ ነው፡፡ ለብዙዎቹ ፍርድ ቶሎ አይደርስም እሱ ግን በአሥር ቀን ውስጥ BPR ችሎት ነው ፈጥኖ የደረሰለት አሉ፡፡ ስለዚህ ተፈረደለት፡፡ የሰጠኝንም ገንዘብ እንዲወስድ ለባንኩ ተጻፈለት፡፡ ቤቱም ገንዘቡንም ለራሱ አደረገ፡፡

 በተጨማሪም የሚያስፈራሩ፣ መደበኛ ሥራቸውን ወደ ጎን አድነው የሚያንገላቱትን ላከብኝ፡፡ በጣም የሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ገባሁ፡፡ ይኽም አልበቃ ብሎ ሌቦችና ወንበዴዎች የእኔን ቤት አጥንተው ልብሴን፣ ሰነዴንና የትምህርት ቤት ማስረጃዬን፣ በቤት ውስጥ ያሉኝን ቁሳቁሶች ሁሉ አስጠርጎ አስወሰደብኝ፡፡ የእኔ ዕጣ ፈንታ እንደነገርኳችሁ ማዘን ብቻ ነው፡፡ ወደ ጎፋ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ አመለከትኩ፡፡ በCR-679 ተመዝግቦ ነበር እንዲሁ ቀረ እንጂ፡፡ በወገኔ ላይ ምንም ባይደርስበት ደስ ይለኛል፡፡ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ቤቴን፣ የልጆቼን ዕጣ ፈንታ፣ ባለቤቴን፣ የሰጠኝን ገንዘብና የነበረኝን የራሴ የሆኑትን መጠቀሚያ ዕቃዎችና ሽልማት ጭምር አጣሁ፡፡

ዛሬ እጥፍ በበዛ ሐዘን ላይ ነኝና የኮንዶሚኒየም ዕጣ የሚደርሳችሁ ወገኖቼ ትምህርት እንዲሆናችሁ በሚል ሕይወቴን አካፈልኳችሁ፡፡

(ተጎጂ አማረ መኮንን ተሰማ፣ ከአዲስ አበባ)

******

የንብ ትራንስፖርት ነባር ቦርድ አባላት በኪራይ ሰብሳቢነት አንፈረጅም

ጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ዕትም ‹‹ንግድ ሚኒስቴር አክሲዮን ማኅበራትን እየከታተልኩ ነው›› በሚል የዜና ዘገባ ንዑስ ርዕስ ሥር፣ በንግድ ሚኒስትሩ የንብ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ቦርድ አመራር ላይ የኪራይ ሰብሳቢነትና የግልጽነት ችግር እንዳለ ተገልጿል፡፡

ንብ አክሲዮን ማኅበር የትራንስፖርት ዘርፍ ማሟላት ያለበትን አሟልቶ ሥራ አስኪያጅና የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ የሥራውን ሒደት በተጨማሪ የሚከታተል የኦዲትና የኢንስፔክሽን ክፍል አለው፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ከሌላው ቦርድ በተሻለ ሁኔታ ለውጥ ማምጣቱን መጋቢት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደረገው የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ታይቷል፡፡ ባቀረብነው ሪፖርት ሥራችን በመደነቁ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት እንድንቀጥል ተደርጓል፡፡

ስለዚህ ነባሩ ቦርድ በኪራይ ሰብሳቢነት የሚያስፈርጅ ሥራ ያልሠራ መሆኑን ለአክሲዮን ማኅበሩ አባላት እናሳውቃለን፡፡

(ነባር የቦርድ አባላት)

******

የሥራ መሪዎች ልማትንም ጥፋትንም ሊያፋጥኑ ይችላሉ

በሪፖርተር ስለ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ አጠቃላይ ሁኔታ ሁለት ጊዜ የተዘገበውን አንብቤ ይህን አስተያየት ለመስጠት ተገድጃለሁ፡፡ በቀድሞ ስሙ ሞርጌጅ ባንክ እየተባለ የሚጠራው፣ ለመዲናችን ግርማ ሞገስ የነበረው ሕንፃ ላይ የተመሠረተው ይህ ባንክ፣ በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መንትያ የሕንፃ ዲዛይን አሠርቶ አንዱን በመገንባት ለአዲስ አበባ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ማበብ ፈር ቀዳጅ ነበር፡፡

የደርግ መንግሥት ለ17 ዓመታት ባያሰናክለው ኑሮ ዛሬ መዲናችን የት ትደርስ እንደነበር ለመገመት ያስችላል፡፡ ሞርጌጅ ባንክ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዞው ቢቀጭጭም ለበርካታ ልማታዊ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች እንዲሁም ለመንግሥት ሠራተኞች ቤት በማስገንባት እንከን የለሽ ሥራ የሠራ የሕዝብ ባንክ ለመሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ፤ ስለውድቀቱም ሲሰሙ ይቆጫሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

 ስለሆነም በዚህ የነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ የባንኩ ውድቀት አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ ማንም ስለባንኩ የሚያውቅ ዜጋ የአሠራር ብልሹነቱን በማጋለጥ ባንኩን ማዳን ይጠበቅበታል፡፡ ትናንት የተመረሠቱ ባንኮች ከየት ተነስተው የት እንደደረሱ በግልጽ ስለሚታወቅ፣ የባንኩ ችግር የተሻለ የአሠራር ለውጥ እንዲያመጣልን በሚል የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትን በሶፍትዌር ግዥ፣ በኤቲኤምና ጄኔሬተር ግዥ ስም የግል ኪሳቸውን አደልበው፣ በብድር አሰጣጥ አድሎዓዊ አሠራር ምክንያት የማይመለስ ብድር በመስጠት ባንኩን ችግር ላይ የጣሉ፣ ለውድቀቱ ሺሕ ምክንያት የሚደረድሩ የሥራ መሪዎች መሰሪ ሥራቸውን በማጋለጥ ትክክለኛ ችግሩን ነቅሶ በማውጣት የባንኩን ውድቀት ባለውለታዎቹ እንድትታደጉት አደራ እላለሁ፡፡

መንግሥትም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሀቁን የማውጣት አደራ እንዳለበት አስገነዝባሁ፡፡ በአፈጮሌነትና በማስመሰል ባህርያቸው በባንኩ የሥልጣን እርከን ላይ የሠፈሩት፣ ለባንኩ ከማሰብ ይልቅ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ ኃላፊዎች ስለሚመሩት ለባንኩ ውድቀት መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በያዙት ኃላፊነት ሳቢያ ባልተገቡ አሠራሮች መዘፈቃቸው ሳይጣራና ዋጋ ሳይከፍሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ባንኩን ለማዋሃድ ማሰብ መደበቂያ ዋሻ መፍጠር ይሆናል፡፡ ያገባኛል የሚል ሁሉ መንግሥትንም ጨምሮ ውድቀቱን ጉዳዬ ብለው እንዲይዙት አቤት እንላለን፡፡

(ከባንኩ ሠራተኞች)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...