Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየአገሪቱን የሰው ኃይል ለማልማት ውዝፍ የቤት ሥራ አለብን

የአገሪቱን የሰው ኃይል ለማልማት ውዝፍ የቤት ሥራ አለብን

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ከ25 ዓመት በፊት ሁሉም ነገር የሠርቶ አደሩ፣ ስለሠርቶ አደሩ ነበር፡፡ የሁሉም ነገር የጥበብ መጀመሪያ ዕምነቱ፣ ፋሽኑ፣ ምህላው ሁሉ ወዛደሩ፣ ላባደሩ፣ ሠርቶ አደሩ፣ ሠራተኛው ሕዝብ ነበር፡፡ ‹‹ብሔራዊ›› መዝሙሩ ወዛደሩ ወይም ላባደሩ ያሸንፋል ነበር፡፡

በ1980 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት መሠረት መንግሥት ራሱ ‹‹… በሠራተኛውና በገበሬው ኅብረት፣ በምሁሩና በአብዮታዊ ሠራዊት፣ በዕደ ጥበብ ባለሙያውና በሌሎች ዲሞክራሲያዊ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ የሠርቶ አደሩ ሕዝብ መንግሥት›› ነበር፡፡ ሥልጣን ‹‹የሠርቶ አደሩ ሕዝብ›› ነበር፡፡ ግንባር ቀደም ፓርቲው፣ የአገሪቱን የዕድገት አቅጣጫ ቀያሽ፣ የመንግሥትና የመላው ኅብረተሰብ መሪ ኃይል የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ነበር፡፡

በአጠቃላይ ከ1966 ዓ.ም. አብዮት በፊትና ከዚያም በኋላ የሚያዋጣው ፖለቲካ ‹‹ማርክሲዝም ሌኒንዝም›› ነው ተብሎ ኢዲዩ ሲቀር፣ ደርግንና ተቃዋሚ የብሔረሰብ ነፃነት አራማጆችን ጨምሮ የሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ወግና ወገንተኝነት ሠርቶ አደሩ፣ ላብአደሩ፣ ወዛደሩ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሲገባ ወሬው ብዙ አልተሰማም እንጂ፣ የኢትዮጵያ ላብ አደሮች አብዮታዊ ድርጅት (ኢላአድ) የሚባልም ፓርቲ ነበረው፡፡

ኢሕአዴግ ማሌ (ማርክሲስት ሌኒኒስት) ድርጅቶቹንና ኢላአድን አዲስ አበባ መግቢያ በር ላይ ‹‹ትቷቸው›› ቢገባም፣ የሰኔው ኮንፈረንስ ላይ የሠራተኞች ተወካይ ‹‹እንዲሳተፉ›› መፈቀዱ አልቀረም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በቻርተሩ ውስጥ በተወካዮች ምክር ቤት የኃላፊነት (ሥልጣንና ተግባር ሥር) ‹‹የሠራተኛውን መብቶችና ጥቅሞች የሚያስጠብቅ ፍትሐዊ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ እንዲወጣ ያደርጋል፤›› የሚል ድንጋጌ ተካትቶም ነበር፡፡

በደርግ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ሁሉ በሽግግሩ ዘመንም ከዚያም በኋላ ጭምር ሠራተኛው  በተለያዩ ታላላቅ ተቋማት ውስጥ በተለይ በወጡ ሕጎች ይወከል ነበር፡፡ ለምሳሌ በሰኔ 1984 ዓ.ም. በተደረገው የብሔራዊ፣ የክልላዊና የወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫን ለማጣራት የተቋቋመው የምርጫ ጉድለቶች ማረሚያ ቦርድ ውስጥ የላብአደሮች ማኅበር ተወካይ ቦታ ነበረው፡፡ የሠራተኞች ማኅበር ተወካይ የ1984 ዓ.ም. የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ውስጥ አባል ነበር፡፡ በ1984 ዓ.ም. በተቋቋመውና ሕገ መንገሥቱን ባዘጋጀው የሕገ መንግሥት ኮሚሽን ውስጥ ከ29 አባላት መካከል የሠራተኛ ማኅበራት ሦስት ተወካይ ነበራቸው፡፡

ይህን በመሰለ ሁኔታ ይገለጽ የነበረው ሠራተኛውን በየወንዙ ‹‹እወድሃለሁ›› እያሉ ‹‹መሀላ››ን ደግሞ ደጋግሞ የማደስ አሠራር ዛሬ ወደ ‹‹ፅድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ›› ተቀይሯል፡፡ አሁን እንደ ዱሮው ያለሠራተኛው መደብ ተወካይ ተሳትፎ አብዮት ግቡን አይመታም የሚባልበት፣ ለይስሙላ ለአንደበትና ለአዋጅ ወግ ያህል የሚፈከርበት ፋሽን ቀርቷል፡፡ ሠራተኛው በምርጫ ጉዳይ፣ በዳኞች አስተዳደር ጉዳይ፣ በሕገ መንግሥት ጉዳይ፣ ወዘተ በተለይ ውክልና የሚያገኝበት የዱሮው የ‹‹ደጉ ዘመን›› ቀርቶ፣ ‹‹የነጭ ካፒታሊዝም›› መጽሐፍ ነው የተባለው ሕገ መንግሥት የሚፈቅደው የሠራተኛ መብት ድንጋጌ ያቋቋመው እንኳን ከ‹‹እንቁልልጭ›› የተሻለ አልሆነም፡፡ ኢትዮጵያ የመነሻ (መንዕስ) ደመወዝ ሕግ ከሌሏቸው በጣም ጥቂት አገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው በማኅበር የመደራጀትና የመደራደር መብቶች በአሠሪዎች መልካም ፈቃድ ላይ የተተው ናቸው፡፡ አሠሪዎች የመንግሥት አሠሪም ጨምሮ ሲወዱ የሚሰጡት፣ ካልፈቀዱ የሚከለከሉት መብት ነው፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ ይህን በጣም አሳምሮና አምርሮ ያውቀዋል፡፡ መዝግቦታልም፡፡ የዘነጋው ካለ የ‹‹ጁራሲክ ፓርክ››ን ርዕሰ አንቀጽ ያስተውሏል፡፡

በቅርቡ በሪፖርተር ላይ ባነበብነው ዜና እንደተረዳነው በአንድ የቱርክ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ውስጥ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን በማኅበር መደራጀት የቻሉት፣ መነሻ ደመወዛቸውን በኅብረት ስምምነት ድርድር አማካይነት ከፍ ለማስደረግ የበቁት፣ በአገር ውስጥ ሕግና በተፈጻሚነቱ ጥንካሬ ምክንያት አይደለም፡፡ የቱርኩን ምርት ተቀባይ ከሆነው የጀርመን ኩባንያ በስተጀርባ ያሉት ሸማቾች እዚህ አገር የማይታይ እንቅስቃሴ ነው፡፡

ከጠቃቀስናቸው ጉዳዮች ጋር የተያያዘ አንድ አብነት እናሳይ፡፡ ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ያልሞላው የ‹‹አምራች ዘርፍ ተወዳዳሪነት ድጋፍ ምክር ቤት›› የሚባል የመንግሥት ተቋም አለ፡፡ የዚህ ምክር ቤት ዓላማ የአገሪቱ አምራች ዘርፍ በምርታማነት፣ በጥራትና በዋጋ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችል የፖሊሲ ድጋፍ የሚያገኝበትን ሁኔታ የማመቻቸትና የማስተባበር ነው፡፡ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ ብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን ደግሞ ለምክር ቤቱ የሴክሬታሪያት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በሕግ በተደነገገው መሠረት የምክር ቤቱ ተግባርና ኃላፊነት፡-

  •  የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከንግድና ከአገልግሎት ዘርፍ ወደ አምራች ዘርፍ የሚያደርጉትን ሽግግር፣
  • የውጭ ባለሀብቶች በአምራች ዘርፍ እያደረጉ ያሉትን አስተዋጽኦ፣
  •  የአገሪቱ የመሠረተ ልማትና የአገሪቱ የፋይናንስ አቅርቦት ሥርዓት ለተወዳዳሪነት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ፣
  •  የታክስ፣ የጉምሩክና የሎጅስቲክስ ሥርዓቱ የአምራቹን ዘርፍ በመደገፍ የሚጫወቱትን ሚና፣
  •  ሕግና ደንብ የማስከበርና የዳኝነት ሥርዓቱ ለተወዳዳሪነትና ለኢንቨስትመንት ጥበቃ እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ፣
  •  ቴክኒክና ሙያና የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና እንዲሁም የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥርዓቱ ለምርታማነትና ጥራት እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ፣
  •  የጥቃቅንና አነስተኛ ማምረቻ ዘርፍ ከመካከለኛና ከከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸውን ትስስርና ተወዳዳሪነታቸው ያለበትን ደረጃ፣
  •  የወጣቶችና የሴቶች የሥራ ፈጠራ ክህሎት ያለበትን ደረጃ፣
  •  የካይዘን ፍልስፍናና ፖሊሲ በምርታማነትና ጥራት ለመወዳደር እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦና አገራዊ የምርታማነትና ጥራት ንቅናቄ ያለበትን ደረጃ የመገምገም፣ እንቅፋቶችን የመለየትና የመፍትሔና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን የማስቀመጥ ተግባርና ኃላፊነቶች አሉበት፡፡

ሰብሳቢው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ በሦስት ወራት አንድ ጊዜ የሚሰበሰበው የዚህ ምክር ቤት አባላት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰየሙ የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ የሚመለከታቸውን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት ተወካዮችን፣ የግል ዘርፍ ተወካዮችን ‹‹የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች ተወካዮችን›› እና የሌሎች አግባብ ያላቸው ተወካዮችን በአባልነት ያካትታል፡፡

ቀድሞ ይባል እንደነበረው የላባደር/የወዛደር ወይም የሠራተኛ ማኅበር ተወካዮች የሚባሉ አለመኖራቸው ጭምር ልብ ይሏል፡፡ ከዚያም በላይ ከሌሎች መካከል ‹‹አገራዊ የምርታማነትና ጥራት ንቅናቄ ያለበትን ደረጃ›› የመገምገም እንቅፋቶችን የመለየትና የመፍትሔና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን የማስቀመጥ ተግባርና ኃላፊነቶች የተሰጡት ምክር ቤት፣ የአገሪቱን የሥራ ኃይል ባለቤትና ተወካይ የሆነውን ሠራተኛ ከምክር ቤቱ አባላት ውስጥም ሆነ ከምክር ቤቱ ተግባርና ኃላፊነት ውስጥ ሲበዛ ንቆታል ወይም አድበስብሶታል፡፡

የአገር ውስጥ ባለሀብትም ሆነ የውጭ ኢንቨስተር በንግድም ሆነ በአገልግሎት ዘርፍ፣ ከንግድና አገልግሎት ዘርፍ ወደ አምራች ዘርፍ በሚያደርጉት ሽግግር የኢትዮጵያ የሥራ ኃይል (ሌበር ፎርስ) ከፍተኛ ቦታና ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሥራ ኃይል ሲባል የኢትዮጵያ ሠራተኛ ነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡

ኢትዮጵያን የለማ የሰው ኃይል ባለቤት ለማድረግ፣ ተፍጨርጫሪነትንና ታታሪነትን ለማልማት፣ መደረግ ያለበትንም መገንዘብና በዚያው ማዕዘን መነቃነቅ አለብን፡፡ ተፍጨርጫሪነት ችግርን ለማሸነፍ ትልቅ መሣሪያ ነው፡፡ መፍጨርጨር ብልህነትንና ዕውቀትን ያስተምራል፡፡ መፍጨርጨር፣ ብልኃትና ዕውቀት የዕድገት ጉልበት ናቸው፡፡ ያልተነካና ያልታሰበ የሥራ ዕድልን የማየት የመሞከርና የመፍጠር ወላጆች ናቸው፡፡ መፍጨርጨርንና መለኝነትን የተላበሰ ሕዝብ የአዳዲስ ሥራዎችና ፈጠራዎች ጎሬ ነው፡፡

እንዲህ ያለ ሕዝብ መረጃን፣ ዕውቀትንና ሥልጠናን ሲመገብ፣ ሙያዎች ሲባዙ፣ የምርምር ጥናት የቅየሳና የፍልሰፋ ኃይል ተፈጥሮ ከሕዝቡ ጥረቶች ጋር ሲያያዝ ተዓምር ይሠራል፡፡ የለማ ተፍጨርጫሪነትና ሙያ ባልተወደደ ዋጋ የሚገኝበት ኅብረተሰብ ደግሞ ለሥራ ከፋቹ (ለኢንቨስተሮች) ለአገር ወስጥም ለውጭም ፍትፍት ማለት ነው፡፡ (ይህ ፍትፍት ግን የአገር ውስጥ የሕግ ጥበቃ የሌለው፣ ዕድሜ ለፋሽን ኢንዱስትሪው ደንበኞች እንቅስቃሴ የሚል፣ ከዚህ ውጪ ታዳጊ የሌለው የሚደፋና የሚከፋ የሰው ኃይል መሆን የለበትም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ግፍና ጡር አለው)፡፡

ከዚህ አኳያ የአገራችንን የሥራ ኃይል ብንመለከተው በዋጋ በኩል ካለመወደድም ርካሽ ነው፡፡ ወደታች ዝቅ በተባለ ቁጥር ደግሞ ርካሽነቱ የባሰ ነው፡፡ በሙያና በትጋት ረገድ ያለበት የልማት ደረጃ ግን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ዛሬ ከቀድሞው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የመፍጨርጨር፣ የማወቅና ሙያን የማሻሻል ፍላጎት ይታያል፡፡ በተለያየ ደረጃ ክህሎትን የተላበሰ የሥራ ኃይል የማፍራት መንግሥታዊ ጥረትም አለ፡፡ በዲፕሎማ የተመረቁ የግብርና ሙያተኞችን በገበሬው ውስጥ ማሰራጨት (በደንብ የሠለጠኑ እስከሆኑ ድረስ) በአነስተኛ የግብርና ሥራ ላይ አብዮት ለማካሄድ አንድ ሁኔታ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሥልጠናው በራሱ የዘመናዊ ገበሬ ምንጭ መሆን ይችላል፡፡ ለትላልቅ ግብርና ሥራዎች የሚያስፈልገው የሠለጠነ ሙያተኛም በዚህ በኩል እየተሟላ ይሄዳል፡፡ በትምህርትና በሥልጠና የመሻሻል ዕድልን ሳይዘጉ በአካዳሚያዊም ሆነ በሌላ ምክንያት ለሚራገፈው ወጣት በ8ኛ፣ በ10ኛ ደረጃ ላይ የሙያ ሥልጠና መስጠቱ ተገቢ ነው፡፡

ወዲህ ወዲያም ተባለ ግን በየትኛውም ደረጃ የሚሰጥ የአገራችን ትምህርትና ሥልጠና ሥር በሰደደ የጥራት ችግር ውስጥ ይገኛል፡፡ የትምህርት ማስረጃ ማጭበርበር፣ ተገፍቶና አጭበርብሮ ማለፍ፣ የማለፊያ ልልነትና ችሎታን አይመዝኔነት፣ በመማሪያ ቋንቋ የመግባባት ዝቅተኝነትና እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች እስከ ኮሌጅ ድረስ ይታያሉ፡፡

የመንግሥትና የግል ኮሌጆች በትምህርት መሣሪያዎችና በብቁ መምህራን መጓደል የተያዙ ናቸው፡፡ የተማሪን ተወዳጅነት በማርክ ዕደላ የሚገዙና ጥያቄ እያጠራቀሙና ለውጥ ሳያደርጉ ፈተና የሚያወጡ መምህራን በተማሪው ጥራት ላይ በደል እያደረሱ ነው፡፡ የኮሌጅ ወይም ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የፈተና ጥያቄዎች አባራሪ ሆኗል፡፡ ቀድሞ ከተሠሩ የጥናት ወረቀቶች ከመጽሐፍትና ከኢንተርኔት በመስረቅ የጥናት ወረቀት አዘጋጀሁ የሚል ተማሪ እንደ ጉድ እየተራባ ነው፡፡ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር (የግኝትና የፍልሰፋ) ማዕከል ሊሆኑ ይቅርና የተጋ ባለሙያ ለማውጣት ያላቸውም ዕድል ችግር ውስጥ ውድቋል፡፡

በመንግሥት ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች በኩል የይድረስ ይድረስ ሩጫ (የፖለቲካ ንግድ) ትልቅ ጉዳት እንደሚያደርስ ሁሉ፣ በግሎቹ በኩል ደግሞ የገንዘብ ንግዱ ያንኑ ያህል በደል አድርሷል፡፡ የደመወዝ ወጪን ለማቃለል አንድ ሰው የተሟላ ዕውቀት ያላገኘበትንም ትምህርት ደርቦ እንዲያስተምር የሚያደርጉና አዲስ ምሩቅ ወደ መቅጠር የሚያዘነብሉ ኮሌጆች አሉ፡፡ ገምጋሚ ሊመጣ ነው ሲባል ደግሞ ባለሁለተኛ ዲግሪዎችንና ዶክተሮችን ብቅ ብቅ የሚያደርጉ በተራ ነጋዴ ዓይነት ሽወዳ የሚሠሩ አሉ፡፡ ከኮሌጆች ጋር ተያይዞም ሆነ ሳይያዝ የልዩ ልዩ ሙያዎች አጫጭር ሥልጠና እንሰጣለን (የቢሮ ማሽኖች ጥገና፣ የኮምፒዩተር ሀርድዌር ጥገና፣ የሶፍትዌር ጥገና፣ ወዘተ) እየተባለ የተሟላ ብቃት ሳይኖር የተራ ሰው ዕውቀት የሚሰጡ መጻሕፍትንና  ከኢንተርኔት የተቀዱ ምሳሌያዊ ማስተማሪያዎችን ታጥቀው በድፍረት አሠልጣኝ የሚሆኑ፣ ጭራሹን ‹‹ሠልጣኞችን›› ይህ ነው የሚባል ተግባራዊ ልምምድ ውስጥ ሳያስገቡ አጠቃላይ የመግቢያና ቃላዊ ዕውቀት በመስጠት ጊዜ ገድለው ገንዘብ የሚገፉ ተራ አጭበርባሪዎች በርክተዋል፡፡

በማታ ክፍለ ጊዜ ከዝቅተኛ ደረጃ ጀምሮ የሚሰጥ ትምህርትና ሥልጠና ደግሞ በሚቀርበው የትምህርት ማስረጃና በተጨባጭ ችሎታ መካከል የበረታ አለመደራረስ የሚታይበት፣ ‹‹ገንዘቤን ከፍዬ እኮ ነው›› እየተባለ ምስክር ወረቀት በገንዘብ የመግዛት ትግል የሚደረግበትና ከመደበኛው ዘርፍ ይበልጥ የትምህርት ሥራዎችን ሌላ ሰው እያሠሩ መቅረብ፣ ኩረጃና በገፍ ማለፍ ያለበት ቦታ ነው፡፡

ይህን መሳይ ጭምልቅልቆሽ ያለበት የትምህርትና የሥልጠና ሁኔታ በሥራው የሚተማመን፣ ችሎታዬን አሻሽዬና ሠርቼ ላግኝ የሚል የሠለጠነ ሰው ለማፍራት አያስችልም፡፡ ትምህርት ቤቶች መቀበልን ብቻ ሳይሆን፣ መጠየቅንና መመርመርን፣ አቅዶ መሥራትን፣ ትጋትንና የዘሩትን ማጨድን መለማመጃ ሥፍራዎች ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህ በኩል የትምህርት አውታሩ ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የማገዝ፣ የማብቃትና የመከታተል ከባድ ሥራ ተደቅኗል፡፡ ትምህርት ቤቶች የትምህርት መረጃን ከማየት ባሻገር ችሎታን መዝነው (ካስፈለገም የተወሰነ ጊዜ የችሎታ ማስተካከያ ሥርዓት ፈጥረው) የሚቀበሉበት፣ ቀጣሪዎችም ከምስክር ወረቀት ባለፈ ችሎታን የሚያስፈትሹበት ሥርዓት የሚያስፈልግ ይመስላል፡፡

እያምታታና እየተገፋ ምስክር ወረቀት የያዘ ተማሪ በሚቀጠርበት ቦታ እያምታታ ለመኖር እንደሚጥር ሁሉ፣ ከትምህርት ቤቶች የሚወጣው አዲስ የሥራ ኃይልም በሚሰማራበት አካባቢ ባለው የሥራ ባህል በብዙ መልክ ይቃኛል፡፡ ንቅዘት የተባዛው እንደዚያው ነው፡፡ አዲሱን ትውልድ የተሻለ አድርጎ የመቅረፅ ነገር ነባሩን ከማቅናት ጋር በጣሙን የተሳሰረ ነው፡፡ የሠራተኛውን አማራጭ የለሽነት ተጠቅሜ፣ በኮንትራት ሥልት ጉሮሮውን ይዤ ከምግብ ለሥራ በማይሻል ክፍያ ጉልበት ልጋጥ የጥቅም ጥያቄ ሲነሳና በማኅበር የመደራጀት ዝንባሌ ሲታይ፣ በሰበብ እያባረርኩ አፍኜ ከፋፍዬና ተሽቆጥቋጭ አድርጌ ልያዝ ባይነት ቂም፣ ውዝግብና ጥፋት እንዲጠራቀም የሚያደርግ አሮጌ ሥልት ነው፡፡ አንድ መኪና ለረዥም ጊዜ ያለችግር እንዲያገለግል በየጊዜው በጭነት ልኩ፣ በሥራ ብዛቱ፣ በፅዳትና በዕድሳቱ መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ዘላቂ ውጤትን የሚሻ አሠሪ የሠራተኛውን ጉልበት ከማለብ አልፎ ሠራተኛው ለድርጅቱ ያለውን ፍቅርና የሥራ ትጋቱን በተከታታይ ሊያድስና ሊያሳድግ የሚችልበትን ሰጥቶ የመቀበል ዘመናዊ ጥበብ መማርና የሰመረ ተራክቦ ማበጀት ይጠበቅበታል፡፡

በዚህ በኩል መንግሥት እገዛ ሊያደርግ ይቅርና አንዱ ምናልባትም የባሰ ኪሳራነት የሚታይበት አሠሪ ሆኗል፡፡ ወሬ አቀባይነት፣ ስውር ጥቅምና በፖለቲካ መያያዝ ለሥራና ለደመወዝ ዕድገት ዋስትና የሆኑበትን ሁኔታ መበጣጠስ፣ ብልሹ የሥራ አመራርን ማረም ተስኖት በሥሩ ያሉ ድርጅቶች በብልሽቶችና በሠራተኛ ብሶቶች እንደተጠሩ ይገኛሉ፡፡ የሥራ ባህልን የማንሰራራት ዕድል በፖለቲካ ትስስርና በአድሏዊ አሠራር ራሱ እየተቀናቀነ ሠራተኞች አባሮ፣ ሌላ ሠራተኛ በመቅጠር የሥነ ምግባር ችግርን ሊያክም ይሞክራል፡፡ በፋብሪካዎችና በግንባታ ሥራዎች ዘንድ ከጥራት ጋር በተገናዘበ ሁኔታ ሥራዎችን እየለኩ በሠሩት ልክ በመክፈል፣ ታታሪነትን መነቅነቅ እንኳ ዳገት ሆኖ ‹‹ሥራ እንዳያልቅ›› ዛሬም እንደ ኤሊ ይሠራል፡፡

ሠራተኛውም (ንቁ ሳይሆን) ፍዝ ተጎጂ ከመሆን አልወጣም፡፡ ካንዱ ወይም ከሌላው የሠራበት ቦታ መባረር ለሠራተኛው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ ከሥራ ሥራ የማማረጥ ነፃነት (የሥራ ዋስትና) የሚመጣው በኢንዱስትሪያዊ የኢኮኖሚ ዕድገት (በሥራዎች መፍላትና መፍለቅ) ነው፡፡ ይህንን የጥቅም አቅጣጫ ከማወቅ በመለስ በግልም ሆነ በመንግሥት ቤት ያለው ሠራተኛ በሥራ ከመታመን፣ ከመታተር፣ ብቃቱን ከማሻሻል፣ ስለድርጅቱ ደኅንነትና ስኬት ከመቆርቆር የተሻለ የሚያዛልቅ የሥራ ዋስትናና የማደጊያ አማራጭ የለውም፡፡ ይህንን በተግባር ተቀብሎ አፍራሽ አሠራሮችን የመቃወምና ከመንግሥት ድርጅት ሠራተኛነት ጋር የተጣበቀውን መጥፎ ስም የመቀየር የተባበረ የራስ በራስ ትግል ተደቅኖበታል፡፡

የሥራ ክፋቶችና የሥራ አስፋፊዎች (ኢንቨስተሮች) እንቅስቃሴ ከሠራተኛ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአማካሪ ባለሙያዎች፣ ከጥናት፣ ከዲዛይንና ከግንባታ ተቋራጮች ጋር ሁሉ የሚነካካ እንደመሆኑ የሥራ ኃይልን የማልማቱ አድማስ ያንኑ ያህል ሰፊ ነው፡፡ ከዓለማችን ዕድገት ጋር መራመድ የሚችሉ የጥናት፣ የምህንድስናና የሥራ ተቋራጮች መፍጠር ወሳኝ ነው፡፡ ትግሉ በግልና በቡድን ከሚደረግ የራስ መፍጨርጨር ይጀምራል፡፡ ይህም በሙያ ማሻሻያ ትምህርት፣ በውጭ የሰው በሰው ግንኙነት ኢንተርኔትን በማሰስና የውጭ ሥራ ተቋራጮችን በተለያየ ብልኃት ተጠግቶ በመቅሰም ሁሉ ሊካሄድ የሚችል ነው፡፡

ለምሳሌ የአዲስ አበባን የቀለበት መንገድ ሥራ ቻይናዎቹ በተቋረጡ ጊዜ ከኛዎቹ የግንባታ ተቋራጮች ስንቶቹ (ሰው በማስቀጠር ይሁን በሌላ ሥልት) ትንሿንም ዕውቀት አንጠፍጥፎ ለማስቀረት ጥረው ይሆን? ምን አዲስ ነገር አለና በማለት ለመገበዝ የሚሞክሩ ካሉ፣ የአርማታ ምሰሶ ጆንያ አልብሶ ውኃ የማጠጣትን ዘዴ እንኳን ከርቀት ተምረው ሲጠቀሙበት አይተናል፡፡ በቅርብ ደግሞ ስንት ነገር ሊገኝ እንደሚችል የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡

የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ካወቁበት ከራሳቸውም ተርፈው ዕውቀትና ጥበብን መሳቢያና ማዳረሻ መሣሪያ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ሌሎች የሙያ ተቋማት የተያያዙበት የአሠሪዎችንና የሥራ ሠራዊትን ባህል የማንሳት ዘመቻ አገሪቱ ትፈልጋለች፡፡ ከግልና ከመንግሥታዊ ድርጅቶች ችግሮችና ፍላጎቶች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚፈሱበትና መመራመሪያ የሚሆኑበት፣ ውጤቶችም (የመፍትሔ ሐሳቦች፣ ግኝቶችና ፍልሰፋዎች) የሚመለሱበትና የሚሞክሩበት ቅንብርም ሊኖር ይገባል፡፡

በሚደጋገም ፕሮፓጋንዳ፣ በማይገባና በማይረባ ነገር ‹‹የቴክኖሎጂ ሽግግር›› እያለ የሚብከነከነውና የሚባክነውም የኢትዮጵየ ቴሌቪዥን አጠቃላይ የሚባሉ ክህሎቶችን በማሸጋገር ረገድ ብዙ ሊሠራበት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያም ብዙ ችግር ያለበትን የሥራ ኃይሏን ለማልማት ለመጠበቅም ጭምር ከፍ ያለ የተወዘፈ የቤት ሥራ አለባት፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ የተሰጠውን የኢትዮጵያ ሠራተኛን የመደራጀትና የመደራደር መብት ለማስከበር፣ የሠለጠነው አገር የፋሽን ኢንዱስትሪው ደንበኛ እንቅስቃሴና ቁጣ እንዲቀጣጠል መፀለይና መሳል ሊያሳፍረን ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...