Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየምርጫ ሰሞን የሙስና ግርግርና የመልካም አስተዳደር እጦት ያሳስበናል

የምርጫ ሰሞን የሙስና ግርግርና የመልካም አስተዳደር እጦት ያሳስበናል

ቀን:

በአሳምነው ጐርፉ

ምርጫ በየትኛውም አገር የሚኖሩ ዜጐች ሊያስተዳዳራቸው የሚችለውን መሪ የሚመርጡበት አንድ ክንውን ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች ምርጫ ዓይነቱ ይለያይ እንደሁ እንጂ ስሙ ያው ነው፡፡

በአገራችን ምርጫ መካሄድ ከጀመረ አንስቶ ከስምንት አሥርት ዓመታት በላይ መቆጠሩ አንድ ነገር ሆኖ፣ በዴሞክራሲያዊ አኳኋን የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጐቶች ያላቸው አካላት መወዳደር የጀመሩት ካለፉት ሃያ ዓመታት ወዲህ ነው ቢባል ስህተት አይመስለኝም፡፡

- Advertisement -

በዚህ ጽሑፍ ስለምርጫ ለመሰተረክ እምብዛም ፍላጐት የለኝም፡፡ ይልቁንም ባለፉት 20 ዓመታት በአገራችን ከተካሄዱ አራት ምርጫዎች አንፃር፣ በምርጫ ወቅት በፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ አስተዳደርና በፀረ ሙስና ትግሉ ረገድ የአገራችንና የሌሎች አገሮችን የምርጫ ሰሞን እንቅስቃሴ በወፍ በረር መነካካት፣ ለውይይት በር እንደሚከፍት በመተማመን ጥቂት ልበል፡፡

ሙስና እንደ ምርጫ ሁሉ በየትኛውም ዓለም ያለና የሚኖር አስከፊ ወንጀል ነው፡፡ እዚህም ላይ ዓይነቱ ይለያይ እንደሆነ እንጂ መንግሥታዊ ሥልጣንን በመጨበጥ ያልተገባ ብልፅግናና ዝርፊያ የመፈጸሙ ድርጊት በየትም የሚታይ ነው፡፡ በታዳጊ አገሮች ያለው የሙስና ዓይነትና መጠን በተለይ አገሮቹ ካላቸው ውስን ሀብት አንፃር ሲመዘን ከፍተኛ መሆኑን ማጤን ግን አይከብድም፡፡

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በዓለም ውስጥ በሙስና ወንጀል እ.ኤ.አ. የ2013/14 አፈጻጸምን አጥንቶ ይፋ ባደረገው የሰሞኑ መረጃ፣ በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙ 95 አገሮችን ዳስሷል፡፡ ከእያንዳንዱ አገር አሥር ሺሕ ገደማ ዜጐችን በተለያየ የናሙና ሥልት በመውሰድ ባደረገው ጥናትም የከፋ ሙስና ወንጀል ያላባቸውን አሥር አገሮች ለይቷል፡፡

የጥናቱ ሪፖርት የአፍሪካ አገሮችን በተመለከተ ባወጣው ደረጃ ኬንያ ሙስና በሰፋ ሁኔታ ከሚፈጸምባቸው አሥር አገሮች በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እንዲያውም ከአገሪቱ አሥር ዜጐች ውስጥ ሰባቱ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚዎች ጉቦ እንደሚሰጡ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ በዚህ ጥናት ሴራሊዮን ከ95 አገሮች ውስጥ 84 በመቶ በማምጣት ሌላዋ ሙስና በከፍተኛ ደረጃ የሚፈጸምባቸው አገሮች ውስጥ ተመድባለች፡፡ ላይቤሪያ 75 በመቶ፣ የመን 74 በመቶ ያገኙ ሲሆን ኬንያ 70 በመቶ ሙስና ጠልፏታል ይላል፡፡

እነዚህን መረጃዎች በዚህ ጽሑፍ መመልከት የተፈለገው በዋናነት ሙስና የተፈጸመባቸው ወቅቶች እንዴት ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ እንደሆነ ጥናቱ ስለዳሰሰ ነው፡፡ በየትኛውም አገር ሙስና ፀረ ዴሞክራሲያዊነትን፣ የሰላም እጦትንና ሁከትን አዘውትሮ ይፈልጋል፡፡ በእርግጥ የፀረ ዴሞክራሲያዊነት መገለጫው ብዙ ነው፡፡ ጭፍን ያለ አፋኝ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የጥቂቶች ቆራጭ ፈላጭነትን፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት መጓደል፣ ከዓለም አቀፍ ሕግጋት የወጡ የጨረታና የግዥ አካሄዶችን መከተል ሙስናን አባብሰው ታይተዋል፡፡

በእስያ አገሮች የሙስና ድርጊቶችን በማጥናት በቀረበ የትራንስፓረንሲ ኤዥያ ድረ ገጽ ላይ እንደወጣ መረጃም እንደ ቻይና፣ ታይዋን፣ ሰሜን ኮሪያና ጃፓን ባሉት ፈጣን አዳጊ አገሮች ውስጥ በከፍተኛ የኮንስትራክሽንና የመልሶ ማልማት ዘመቻ ላይ በነበሩበት ጊዜ ሙስና ከፍቶ ታይቷል፡፡ በትልልቆቹ ከተሞች የመሠረተ ልማት ግንባታና የከተማ ቦታ የሊዝ ሽያጭ፣ እንዲሁም ለውጭ ባለሀብቶችና ትልልቅ ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት ግብይት ውስጥም ቱባ የሚባሉ ዘረፋዎች መፈጸማቸውን ዳስሷል፡፡

ወደ አገራችን ጉዳይ ስንመለስ ቀደም ሲል የተጠቀሰው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ጥናት ላይ የኢትዮጵያ ሙስና እየቀነሰ መምጣት ብቻ ሳይሆን፣ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮችም በአንፃሩ ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡ እንደ ጥናቱ ከቀጣናው ኡጋንዳ ከኬንያ በመቀጠል ሁለተኛ ከፍተኛ የሙስና ወንጀል የሚፈጸምባት አገር ሆናለች፡፡ ታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ሊቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሞዛምቢክ፣ ሞሮኮ፣ ዚምባብዌ፣ ጋናና ማዳጋስካር እንደ ቅደም ተከተላቸው ሙስና የተስፋፋባቸው አገሮች ተብለዋል፡፡ ከእነዚህ ኋላ የኢትዮጵያ መገኘት በአንፃሩም ቢሆን ‹‹ተመስገን!›› የሚያስብል ነው፡፡

እዚህ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› ይበለው ‹‹ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት›› አጥፊ እንደሆነና ሊታገሰው እንደማይችል ደጋግሞ ይናገራል፡፡ ዋነኞቹ የዘረፋ ችግር የሚስተዋልባቸው ማለትም መሬት፣ የገቢ ግብር፣ የመንግሥት ግዥና አገልግሎት፣ ሽያጭ እንደሆኑ ያስረዳል፡፡ መለስ ባለ ደረጃም ዋነኞቹ የሙስና መታያዎችና መከማቻዎች ማዘጋጃ ቤቶች፣ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይልና መጠጥ ውኃ ያሉ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የመሠረተ ልማትና የኮንስትራክሽን መስክ ተዋናዮች ናቸው፡፡

በጠለቀ ጥናት ላይ መመሥረት ባይቻልም በኢትዮጵያ የከፋ የመልካም አስተዳደር ጥፋትና ጉድለት እንዲሁም መሬትን የመሰለ የሕዝብ ሀብት ወደ መሸጥ የሚስተዋለው በምርጫ ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀደም ሲል በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መሥሪያ ቤቶች በምርመራ ሥራ ላይ የነበረ አንድ ባለሙያን የቅርብ ጊዜ ገለጻ መጥቀስ ይገባል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ሙስናና የመልካም አስተዳደር በደልን ከሕዝብ እንደሚነጥለው አደገኛ ተግባር ያስባል፡፡ እናም በተለይ በምርጫ ወቅት ‹የሕዝብ ጫጫታ› ባይነሳ ይወዳል፡፡ ነገር ግን ምርጫን ተከትሎ ከፍተኛ የሙስና ወንጀሎች ይፈጸማሉ፡፡ የተጋለጡም አሉ፡፡ ተድበስብሰው የቀሩትም ቀላል አይደሉም፤›› ይላል፡፡ ለአብነት ሲጠቅስም በዋናነት በምርጫ 97 ዋዜማና ማግሥት በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የተቸበቸበውን የሕዝብ መሬት ይጠቅሳል፡፡

በእርግጥም እንደ ቅርብ ጊዜ ታሪክ በተለያዩ መጽሐፎችና ከሥርዓቱ ባፈነገጡ አንዳንድ ሰዎች እየተገለጸ ያለው፣ በራሱ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መዝገብ እስካሁን ችሎቶችን ያጨናነቁት ጉዳዮች ከ1997 አጋማሽ እስከ 1999 ዓ.ም. የተፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ ቅንጅት የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ ከተማዋን ሊያስተዳድር ነው በሚል በራሱ በሥርዓቱ የመካከለኛው ደረጃ ካድሬዎች ውስጥ ከተፈጠረው የዝርፊያ ዘመቻ በላይ፣ በቅድመ ምርጫው ወቅት የሕዝቡን ስሜት በመረዳት ምንም ቦታ ሳንይዝ ‹‹የሥርዓት ለውጥ ሊመጣ ነው›› በሚል፣ የአዲስ አበባ ዙሪያ ብዛት ያለው መሬት ተቸብችቧል፡፡ ጥቂት ግለሰቦችም እስከ አሥርና ሃያ ካርታ ሸጠዋል ይላል፡፡

በተመሳሳይ በምርጫ 1992 ወቅት የከፉ የሙስና ችግሮች እንደታዩም ይጠቁማል፡፡ አንደኛው አገሪቱ በአንድ በኩል በባድመ ጦርነት ፍጥጫ ማግሥት፣ በሌላ በኩል በሕወሓት መከፋፈል የውስጥ ለውስጥ ንትርክ አይሎ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም ነበር በመከላከያ ሚኒስቴርና በክልል ርዕሰ መስተዳደር ደረጃ የነበሩ ቱባ ባለሥልጣናት በሙስና የተጠረጠሩት፡፡ ሰፊ የሕዝብ አገልገሎት በሚሰጠው ቴሌኮሙዩኒኬሽን ውስጥ በዓለም አቀፍ ገበያ የተፈጸመ ወንጀል ተጋኖ ባይነገርም፣ በወቅቱ በኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የተበላሹ ግዥዎች መታየታቸውን ከተጋለጡት መካከል መጥቀስ ይቻላል፡፡

በፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርምራ ተሞክረው በሕግ ውሳኔ ያላገኙ እንደ አዳማ፣ መቀሌና አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የተገነቡ ሕንፃዎች ሕዝብና መንግሥት ‹‹ምርጫ ምርጫ›› ሲሉ፣ ውስጥ ውስጡን አገርን ብል እንደበላው አገዳ የሚበታትኑ የኮንትሮባንድ ወንጀሎች ተስፋፍተው መፈጸማቸውም በተለያዩ አጋጣሚዎች ታይተዋል፡፡

በምርጫ ሰሞን ሙስናዎችና የመልካም አስተዳደር በደሎች በየትም አገር የሚፈጸሙ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ጐልተው የሚነሱበት ሁኔታ አለ፡፡ በተለይ ከአነስተኛ ሙስናና ከዜጎች መጉላላት ጋር በተያያዘ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልተበጀ የሚያስረዱም አሉ፡፡ በምክንያትነት የሚነሳው ገዥው ፓርቲ መላውን የመንግሥት መዋቅር፣ ሀብትና አሠራር ጨምሮ ምርጫ ላይ እንዲያነጣጥር ማድረጉ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከክልል የካቢኔ አባላት እስከ ገጠር ወረዳ አመራሮች ድረስ ለምርጫ ቅስቀሳ ለወራት ወደ መንደራቸው መውረዳቸው በመደበኛው ሥራ ላይ የሚፈጥረው ክፍተት አለ፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን በየመሥሪያ ቤቱ አንገታቸውን ቀብረው በአቋራጭ ለመበልፀግ ያሰፈሰፉ ‹‹ሌቦች!›› ምቹ መደላደል ይፈጠርላቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከትንንሿ ግዥና ለአገልግሎት ጉቦ በመጠየቅ ሕዝብን ተስፋ ማስቆረጥና ማማረር ይጀምራሉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ከምርጫ ሰሞን የሙስና ግርግርና የመልካም አስተዳደር ክፍተት በር የሚከፈተው በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ተሰግስጎ አገዛዙን ለማድከም የሚሠራው ‹‹ደባ›› (ሳቦታጅ) ነው፡፡ ይኼ ዓይነቱ አሻጥር በሌሎች አገሮች ውስጥም ያለና የሚኖር ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይልና የመጠጥ ውኃ ባሉ አገልግሎት ሰጪዎችና በአንዳንድ የፀጥታ አካላትና ፍርድ ቤቶች ላይ የሚታዩ አነስተኛ ሙስናዎች ሕዝብን ክፉኛ የሚያማርሩ እየሆኑ ናቸው፡፡ በ1997 ዓ.ም. ‹‹ምርጫ ምርጫ ስንል›› ያበላሸነው ብዙ ነገር ነበር ያሉ አንድ የገዥው ፓርቲ የሥራ ኃላፊ፣ አሁን ያለውን ሁኔታ እየተገነዘቡ መሆኑንም ማረጋገጥ ያዳግታል፡፡

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በርሊን ከሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ባወጣው መረጃ በሙስና የተዘፈቁ አገሮችን ሲመዝን ከዜሮ እስከ 100 የሚል መለኪያ አበጅቷል፡፡ 100 ነጥብ ያገኙት በአገራቸው ውስጥ የሚፈጸመው የሙስና ወንጀል እጅግ ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ እንደ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ጃፓንና አውስትራሊያ ያሉት ናቸው፡፡ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት፣ ለነቃ የሕዝብ ተሳትፎና ለዴሞክራሲያዊ ባህል የሰጡት ትኩረት ረድቷቸዋል፡፡ በመለኪያው መሠረት ወደ ዜሮ የወረዱት ደግሞ ሙስና በብዛት የሚፈጸምባቸው አገሮች ሆነው ተቀምጠዋል፡፡

እርግጥ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናልም ሆነ የሌሎች መሰል መረጃዎች ውጤት የተለያየ ነው፡፡ አገራችንንም በአንድ ወቅት በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ያሳየች፣ በዚያው ልክ የገነነ ሙስና የሚስተዋልባት ሲል ያስቀመጠው መረጃ አለ፡፡ ለዚህም የእነ አይኤምኤፍ (ዓለም የገንዘብ ድርጅት) የቅርብ አጋር የሚባሉ አጥኚዎች በአሥር ዓመታት ውስጥ 11 ቢሊዮን ዶላር (200 ቢሊዮን ብር ገደማ) ከኢትዮጵያ ወጥቶ አልተመለሰም የሚል መረጃ ማውጣታቸውን በመጥቀስ ነበር፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሙስና (Grand Corruption) የለም፡፡ ነገር ግን ሕዝብ የሚያማርሩና የግል ፅናትና የተጠያቂነት ባህል ያልተላበሱ የመልካም አስተዳደር ጥሰቶችና አነስተኛ ሙስናዎች (Petty Corruption) ሥር እየሰደዱ ነው ሲል ደምድሟል፡፡ ይህንኑ መረጃ ከዓመታት በፊት አረጋግጦት ይገኛል፡፡

የጉዳያችን መነሻ ማጠንጠኛ ‹‹የምርጫ ዘመቻ ሲመጣ የመልካም አስተዳደር ችግር ይባባሳል፣ ሙስናም ያገረሻል፤›› የሚለውን የተደጋገመ የዜጐች አስተያየት ነው፡፡ በእርግጥ ጭራሹኑ ምርጫም ሆነ ሰላምና ዴሞክራሲ በሌለባቸው አገሮች ሙስና እንደሚበረታ አይተናል፡፡ ለምሳሌ ባለፉት አሥር ዓመታት ለኢመንግሥታዊ ሥርዓት፣ ወሮበላነትና ለሙስና የተጋለጡ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት የተበተባቸው አገሮች መካከል ሶማሊያ ቀዳሚ ሆና ትጠቀሳለች፡፡ ሰሜን ኮሪያ በፍፁም አምባገነናዊ ሥርዓት (Absolute Dictatorship) መተብተብ ሙስናን አባብሶታል፡፡ አፍጋኒስታን፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ፣ ኡዝቤኪስታን፣ ቱርክሜኒስታንና ሶሪያ ተጠቅሰው ይገኛሉ፡፡

ለእነዚህ አገሮች ሙስናና አጭበርባሪነት እንዲበረታባቸው ያደረጉት ምክንያቶች የፀጥታና የደኅንነት መንጠፍ፣ ሽብርተኝነትና በፖለቲካ ሥልጣን ሀብት ለማጋበስ የሚቀሰቀስ ምኞት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት የግልጽነትና የተጠያቂነት አለመስፋፋት፣ እንዲሁም ሕዝብ ሲፈቅድ የሚሾመውና የሚሽረው መንግሥት ማጣታቸው ነው፡፡ ጉልበትና ኃይል አገር ወደ መምራት ከገባ መጨረሻው ግልጽና የታወቀ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አገር ልማት ማረጋገጧ መልካም ነው፡፡ ‹‹የድህነት ተራራ›› መሸርሸሩም በጐ ነው አይጠላም፡፡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የምትሰጠው ትኩረት መሻሻል አለበት የሚባልበት ዋናው ምክንያት ግን፣ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ካላከበረና በድፍረት ውስጡን እያጠራ ካልሄደ ተጠልፎ መውደቁ ስለማይቀር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ‹‹ሲሾም ያልበላ…›› የሚለው ተረት ሥር እየሰደደ ከሄደና ሕዝብ አመኔታ እያጣ ስግብግቦችም በሥርዓቱ ላይ እየተንጠላጠሉ፣ ‹‹ያልደከሙበትን በስፋት ማግበስበስ›› ከጀመሩ አገር የሚበትን ይሆናል፡፡

በአገር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ መንግሥት ሲዘጋጅም የሠራውን በጐ ነገር ለሕዝብ በማሳየትና ጉድለቱንና ጥፋቱን ማመን ይበልጥ ይበጀዋል፡፡ በሥነ ምግባር፣ በብቃትም ሆነ በዓላማ ፅናት ችግር ያለባቸው የመንግሥትም ሆነ የፓርቲው ሰዎችን ሕዝብ እየሸነገለ ተሸክሞ ከመሄድም ሊወጣ የግድ ይለዋል፡፡ በተለይ ሕዝቡ በግላጭ የሚያውቃቸውን የሙስናና የማጭበርበር ድርጊቶችን ማጋለጥ ተገቢ ነው፡፡ የሕዝብ ሀብት ሲዘረፍ እንዳላዩ በማየት ማለፍ ማንንም ሊጠቅም አይችልም፡፡ ራሱ ዘራፊውንም ቢሆን፡፡

መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ሥልጣን ላይ እንዳለ አካል ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንም ሆነ ተወዳድረው ለማሸነፍ ከፍ ያለ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለምርጫ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መገኘትም ያስፈልጋል፡፡ ተገቢውን የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት ዘንግቶ፣ ለሕዝብ ሊሰጥ የሚገባውን ፍትሐዊና ግልጽ ረስቶ በር ዘግቶ ‹‹ምርጫ ምርጫ›› ማለት ያልታሰበ ዋጋ ያስከፍላል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከውጭ ባለሀብቶች እስከ መንደር ነዋሪዎች ድረስ በከተሞች ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ አይደሉም፡፡ ‹‹በስብሰባ ብዛት›› ያልተከፈቱ በሮች አሉ፡፡ ቅስቀሳ በወጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የባለጉዳይ ሠልፍ የበዛባቸው ቢሮዎች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ ‹‹ኔትወርክ መጨናነቅ ወይም አለመኖር›› የሚለው ምክንያት በምርጫ ሰሞን በርከት ብሎ መደመጥ የቅሬታ ምንጭ ሆኗል፡፡ ያለቅድመ ማስጠንቀቂያ በተከታታይ የሚጠፋው የኤሌክትሪክ ኃይል፣ በከተሞች ሳይቀር በስፋት እያማረረ ያለው የውኃ እጥረት ተፈጥሯዊ ችግር እንኳን ቢሆኑ ሕዝቡ በምርጫ ሰሞን ሊሰማቸው አይሻም፡፡

በምርጫ ወቅት ሕዝቡ ሰማው፣ ሰለቸውም በየመንደሩ እየወረደ ‹‹ኢሕአዴግን ምረጡ!›› የሚለው ሁሉ እውን ለማስመረጥ ነው ብሎ ማየትም ያስፈልጋል፡፡ ራሱን አብዮተኛ በማድረግ ‹‹ሌብነቱ›› እና ዜጋ አማራሪነቱ እንዳይታወቅ፣ በተጨባጭ ለሕዝብ ካለው አጋርነት ወይስ ሌላ ምክንያት አለው ማለት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም የመንግሥት ሹመኛና ባለሙያ ግን በየተመደበበት ሕዝብን በታማኝነት፣ በቅንነት፣ በግልጽነት፣ በተጠያቂነት፣ ወዘተ ቢያገለግል ከምርጫ ቅስቀሳም በላይ ይመስለኛል፡፡ ቢሮ እየዘጋ፣ በጉዳይ ገዳይና በደላላ በየቀዳዳው እየወሰነ፣ እየተደራደረና እየዘረፈ ‹‹ምርጫ ላይ ነን!›› ካለ ተያይዞ መስጠም ነው፡፡

ለፓርቲው ወይም ለሥርዓቱ ወግኛለሁ እያለ የሌሎችን መብት እየጣሰ፣ ሕግና ሥርዓትን ባልተጻፈ ሕግ እየደፈጠጠ መቀጠል የሚሻ ‹‹ቁም!›› ሊባል ይገባዋል፡፡ ይህን ለማለትም የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ወይም ገለልተኛ ዜጋ መሆን ሳያስፈልግ፣ ራሱ በሥርዓቱ ውስጥ እንደ ቀደመው ባለታሪክ ትግል ሊደረግበት ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን ‹‹ምርጫ ምርጫ›› ሲባል ሕዝብን ለሚጐዱ በር እንዳይከፈት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...