Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ምርጫ 2002 የሚደገም ከሆነ የመድበለ ፓርቲ ነገር ያበቃለታል›› ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የመድረክ የወቅቱ ሊቀመንበር

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ከሚሳተፉት ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሊቀ መንበር ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በመምህርነት ያገለግላሉ፡፡ ሰለሞን ጎሹ ለበርካታ ዓመታት ካስተማሩበት ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ በተለምዶ አምስተኛ በር ከሚባለው ተሻግሮ በሚገኘው ጽሕፈት ቤታቸው በመገኘት በምርጫ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡ ፕሮፌሰር በየነ ምልከታቸውን ካካፈሉባቸው ጉዳዮች መካከል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛነት፣ መድረክ ለመራጮች ስላቀረበው አማራጭ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ስላለው የርዕዮተ ዓለም ልዩነት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተባብረው እንዳይሠሩ ያደረጉዋቸው ምክንያቶችና ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በሁሉም ምርጫዎች በመሳተፍ ያገኙት ልምድና የቀሰሙት ትምህርት ይገኙበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠንካራ ተቃዋሚ ከሚባሉ ፓርቲዎች አንዱ የሆነውን መድረክን በሊቀ መንበርነት እየመሩ ነው፡፡ በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ እንዴት እየተዘጋጃችሁ ነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ፓርቲያችን ለምርጫዎች ከፍተኛ ግምት ይሰጣል፡፡ ምርጫ ለማሸነፍ የተሰባሰብን ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ መሆናችን በየምርጫው ከፍተኛ ባለድርሻዎች ነን፡፡ ከ2002ቱ የቧልት ምርጫ በኋላ በምርጫ ምኅዳሩ ዙሪያ ከገዥው ፓርቲ ጋር በመደራደር መድረክን ጨምሮ ለሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራሽ የሆነ የምርጫ ምኅዳር እንዲፈጠር ስንጥር ነበር፡፡ ጥረታችን በእርግጥ ውጤት አላስመዘገበም፡፡ ሆኖም ለዚህ ምርጫ ዝግጅታችንን የጀመርነው በዚህ ጥረት ነበር፡፡ ገዥው ፓርቲ የምርጫ ምኅዳሩ ሁሉንም ፓርቲዎች በእኩልነት እንዲያገለግል ላቀረብነው ጥሪ ፈቃደኝነት አላሳየም፡፡ በዋነኛነት ለድርድር ያቀረብነው ሁለት ጉዳዮችን ነው፡፡ አንደኛ የምርጫ አስተዳደሩ ያቀፋቸው ሰዎች የገዥው ፓርቲ አባላትና በተለያዩ ተዋረዶች በኃላፊነት የሚያገለግሉ ካድሬዎች መሆናቸው እንዲቆም ጠይቀናል፡፡ ሁለተኛ የምርጫ ታዛቢዎች እጥረት እንዲቀረፍ ነው የጠየቅነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተደረጉ የኢትዮጵያ ምርጫዎችን በመደበኛነት የታዘበው የአውሮፓ ኅብረት መጪውን ምርጫ እንዲታዘብ መንግሥት ጥሪ አላደረገም፡፡ አሜሪካኖችም ምርጫውን የሚታዘብ ቡድን ለመላክ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው ነበር፡፡ ለዚህም ምላሽ አላገኙም፡፡ በዚህ ምክንያት የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ ምርጫውን እንዳይታዘቡ ተከልክለዋል ማለት ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- በመድረክ ዕይታ የመንግሥት ቸልተኝነት ወይም እነዚህን ታዛቢዎች ያልፈለገበት ምክንያት ምንድነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ማንኛውም የሚያገናዝብ ሰው መገመት እንደሚችለው መንግሥት ለሦስተኛ ወገኖች ሊገለጥ የማይገባ በምርጫው ሒደት የሚደብቀው አንድ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ለነገሩ አጠቃላይ የምርጫ ሒደቱ ለተወዳዳሪ ፓርቲዎችም ጭምር ግልጽ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የምርጫ አስተዳደሩ አካል እንቅስቃሴዎች የምርጫ ካርድ ቆጠራውን ጨምሮ ለፓርቲዎቹ ተደራሽ አይደሉም፡፡ ብቸኛው የፓርቲ ተወካይ ያካሄድ ጥሰት አለ የሚል ቅሬታ ሲያቀርብ ወዲያው ይባረራል፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት መከራከሪያ ግን የተለየ ነው፡፡ የምርጫውን ተዓማኒነት በአገር ውስጥ ኃይሎችና በአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች መለካት ዴሞክራሲን ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለማዛመድ ተመራጭ እንደሆነ ይከራከራል፡፡ ምርጫውን አገር በቀል ሲቪል ማኅበራትና የአፍሪካ ኅብረት መታዘባቸው የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካን ከመጋበዝ የተሻለ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ ለዚህ መከራከሪያ ምላሽዎት ምንድነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እያንዳንዱ ምርጫ ለታዛቢ ክፍት መሆን አለበት፡፡ ይኼ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው አሠራር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የምርጫ ሒደት ዴሞክራሲያዊ ነው ብለን የምናስብ ከሆነ ዴሞከራሲን ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማዛመድ የሚል ሰበብ መስጠት ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም፡፡ የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ የምርጫ ታዛቢዎች እኮ በምርጫው ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ ከለጋሽ አገሮች ነው የሚመጡት፡፡ የለጋሽ አገሮች አንዱ ተልዕኮ በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ በልማትና በመሰል ጉዳዮች ላይ በመተባበር ይሠራሉ፡፡ በምርጫ ጉዳይ ላይ ግን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ አትረዱም ማለት ስሜት አይሰጥም፡፡ ለታዛቢዎች የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያወጣው ወጪ የለም፡፡ በአንፃሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዛቢዎች ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ አልጋዎችን ይይዛሉ፣ አገልግሎቶችን ይጠቀማሉ፡፡ ይኼ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ጥቅም ይሰጥ ነበር፡፡ ስለምርጫው የተለየ ፍላጎት የሌላቸው ገለልተኛ ግለሰቦች ካልመሰከሩም በምርጫው ውጤት ላይ ስምምነት ለመፍጠር አስቸጋሪ ነው፡፡

ከእያንዳንዱ ምርጫ በኋላ የሚፈጠረውን ውዝግብ ለማቆም ምን ያህል ጊዜ መጠበቅ አለብን? በነገራችን ላይ ምርጫ የሚታዘቡ አገር በቀል ሲቪል ማኅበራት የሉም፡፡ አብዛኛዎቹ ምርጫ 97ትን የታዘቡ ገለልተኛ ሲቪል ማኅበራት የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ከፀደቀ በኋላ ጠፍተዋል፡፡ አሁን በአገር በቀል ሲቪል ማኅበራት የተመዘገቡት እንደ ሴቶች፣ ወጣቶችና ንግድ ማኅበራት ያሉት አካላት የኢሕአዴግ አካላት በመሆናቸው ትክክለኛ ሲቪል ማኅበራት አይደሉም፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታቢዛዎችም ስህተቶችን ለመደበቅ ብቻ የሚመጡ ናቸው፡፡ የሚመጡት ለገዥው ፓርቲ ለመመስከር ነው፡፡ በእነዚህ ግለሰቦች ላይ እምነት የለንም፡፡ ባለሙያዎች አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ እንዲዝናኑ አፍሪካ ኅብረት ስፖንሰር ያደረጋቸው ቱሪስቶች ነው የሚመስሉት፡፡

ሪፖርተር፡- የመድረክ የመጨረሻ ጋዜጣዊ መግለጫ ፓርቲው በቅድመ ምርጫ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ እየደረሰበት ያለውን ፈተና ይተነትናል፡፡ በአባላት ላይ የደረሰው ወከባና የዕጩዎች ምዝገባ ላይ ያለው አድሎአዊ አሠራርን በዝርዝር ጠቅሳችኋል፡፡ በአጠቃላይ ምን ዓይነት ተግዳሮቶች ናቸው ፓርቲያችሁን እየገጠሙት ያሉት?

ፕሮፌሰር በየነ፡- በአጠቃላይ በሒደቱ ላይ ቀናነት ይጎላል፡፡ የዕጩዎችን ምዝገባ ለማደናቀፍ የአስተዳደር አካላት ሰበብ ሲፈልጉ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ በቀውስ መካከል ነው የምንገኘው፡፡ [ቃለ ምልልሱ የተደረገው ረቡዕ የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ማምሻ ላይ ሲሆን፣ ይኼው ቀን የዕጩዎች ምዘገባ የሚካሄድበት የመጨረሻ ቀን ነበር] በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጋሞ ዞን በሚገኙ አራት የምርጫ ክልሎች ዕጩዎቻችንን ለመመዝገብ የአካባቢው የምርጫ አስተዳደር ኃላፊዎች ፈቃደኛ መሆን አልቻሉም፡፡ የማያሳምነው ምክንያታቸው ደግሞ የዕጩዎች ቅጽ ላይ የሰፈረው ፊርማ ኦሪጅናል ሳይሆን ኮፒ ነው የሚል ነው፡፡ ዕጩዎችን የምናስተዋውቅበት ቅጽ ደረጃውን የጠበቀና ወጥ ነው፡፡ ቅጹ ላይ ፊርማዬን ካኖርኩ በኋላ እሱ ይባዛል፡፡ የተባዛው ላይ ኦሪጅናል ማኅተም ይደረግበታል፡፡ በእያንዳንዱ የዕጩ ቅጽ ላይ ልፈርም አልችልም፡፡ ይኼ ደግሞ በመላው አገሪቱ የምንሠራበት መንገድ ነው፡፡ አሁን ግን በ11ኛው ሰዓት ይኼን እንደ ሰበብ በመጥቀስ ዕጩዎችን አንመዘግብም ተባለ፡፡ በምርጫ ሒደት የምናደርገውን ተሳትፎ ለመገደብ እነዚህ አካላት ይኼን መሰል ሰበቦችና ታክቲኮችን ይጠቀማሉ፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ መሠረታዊ ጉዳዮችን የሚገነዘብ አይመስልም፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ እንቅፋቶች ቢኖሩም መድረክ በምርጫው ተሳታፊ ነው፡፡ በምን ያህል የምርጫ ክልሎች ላይ ትሳተፋላችሁ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አሁን ቁጥሮቹ በእጄ ላይ አይገኙም ምናልባት ነገ ሙሉ ሪፖርት ይኖረናል፡፡ ነገር ግን መድረክ በተቻለው መጠን ብዙ ቦታ ለመሸፈን ሞክሯል፡፡ የኦሮሚያን፣ የደቡብንና የትግራይ ክልሎችን ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ሸፍነናል፡፡ በአማራ ክልል የተወሰኑ ቦታዎችም ላይ ተሳታፊ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- በ2002 ዓ.ም. የፀደቀውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ መድረክ አለመቀበሉ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ነበር፡፡ ሕጉን በመፈረም አባል ለመሆን ዕድሉ ያለ ቢሆንም መድረክ አሁንም አባል አይደለም፡፡ በፓርቲያችሁ ግምገማ ሰነዱ ምንን የተመለከተ ነው? ፓርቲያችሁ አቋሙን እንዲቀይር የገፋፋችሁ ምክንያት የለም?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አቋማችንን ለመቀየር አስቀድመን ሞክረናል፡፡ በሁለት ጉዳዮች ላይ ከመድረክ ጋር ለመወያየት ኢሕአዴግ ፈቃደኛ ከሆነ መድረክ ሕጉን አሁኑኑ ያፀድቃል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የምርጫ ቦርድ አደረጃጀትና የምርጫ ታዛቢዎችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ዋነኛ የምርጫ ማነቆዎች ናቸው፡፡ የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁ ፓርቲዎች በምርጫው ቅስቀሳ ወቅት ሊኖራቸው ስለሚገባው ባህርይ ነው የሚደነግገው፡፡ የምርጫ ሕጉ ጭማሪ ነው፡፡ እንደ አንድ ሕግ አክባሪ ፖለቲካ ፓርቲ የሚወጡ ሕጎችን እንገነዘባቸዋለን፡፡ ነገር ግን ሕጉን ያልፈረመ ፓርቲ ‹‹የጋራ ምክር ቤት›› (በየደረጃው የሚመሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት) አባል መሆን እንደማይቻል ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን እኛ ይኼን የምናደርገው ኢሕአዴግ በምርጫ ማነቆዎች ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ሲሆን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት መድረክ ብቻውን ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚደራደርበት ምክንያት የለም  ይላሉ፡፡ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚነኩ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር የጋራ ምክር ቤቱ ተስማሚ መድረክ እንደሆነም ይከራከራሉ፡፡ መድረክ በተለየ መንገድ ለመታየት ይሞክራል በሚልም ይተቻሉ፡፡ ለዚህ ምላሽዎት ምንድነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- መድረክ ተለይቶ ለመታየት አይሞክርም፡፡ መብታችንን ለመጠቀም ነው የጠየቅነው፡፡ ይኼን የመጠየቅም ሆነ ያለመጠየቅ ምርጫ አለን፡፡ በእኛና በሌሎች የጋራ ምክር ቤቱ አባል ባልሆኑ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት እነሱ በሁለቱ ጉዳዮች ላይ እንደኛ የሚጨነቁ ባለመሆናቸው ነው፡፡ በጋራ ምክር ቤቱ ከኢሕአዴግ ጋር አባል የሆኑ ፓርቲዎች ደግሞ የገዥው ፓርቲ ተባባሪዎች ናቸው፡፡ በምርጫው ለማሸነፍ የሚፎካከሩ አይደሉም፡፡ ይኼን ካስመዘገቡት የዕጩዎች ቁጥር ብዛት መረዳት ይቻላል፡፡ እኛ ከኢሕአዴግ ቀጥሎ በርካታ ዕጩዎችን አስመዝግበናል፡፡ ለዚህ ነው በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ የምናነሳው፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተቋቋመ በኋላ በአሠራሩ ላይ ለውጥ አይተዋል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- በምርጫ ጉዳይ ላይ ራሴን እንደ ጥንት ሰው ነው የምቆጥረው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ሒደቱ ውስጥ አለሁበት፡፡ በአንድ ወቅት በሽግግሩ ወቅት የምርጫ ኮሚሽኑ አባል ነበርኩ፡፡ ለውጡ መጥፎ የሚባል ነው፡፡ አቶ አሰፋ ብሩ የምርጫ ቦርድ ዋና ጸሐፊ በነበሩበት ወቅት እርስ በርስ እንገዳደር ነበር፡፡ በቦርዱ አሠራር ላይ ስህተት ስናገኝና መድልኦ ተፈጽሟል ብለን ስናምን ማስረጃ ይዘን ወደ ቦርዱ እንቀርብ ነበር፡፡ ለምሳሌ የኢሕአዴግ አባላት የምርጫ አስተዳዳሪዎች ሆነው መመደባቸውን ለይተን እናቀርብ ነበር፡፡ በአብዛኛው ለቅሬታዎቻችን በጎ ምላሽ አግኝተን ግለሰቦቹን እናስቀይር ነበር፡፡ የአቶ አሰፋ ቢሮ የተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ ማስረጃ ያሰባስብ ነበር፡፡ አቶ አሰፋ በምርጫ ቅስቀሳና በምርጫው ዕለት ሁሌም በመስክ ላይ በሥራ ነበር የሚያሳልፉት፡፡ ኢሕአዴግ ሁሉንም የምርጫ ክልሎች በሕገወጥ መንገድ ለመቆጣጠር የነበረውን ፍላጎት የገቱና የቀለበሱ ወሳኝ ውሳኔዎችን አቶ አሰፋ ይሰጡ ነበር፡፡ የሚገርመው ይህን እያገኘንም ቦርዱ ላይ ጠንከር ያሉ ቃላትን ተጠቅመን ቅሬታ እናቀርብ ነበር፡፡ ይሁንና ነገሮችን ግን ማስፈጸም እንችል ነበር፡፡ በምርጫ 92 እና 97 ማስረጃ ባቀረብንባቸው ቦታዎች ላይ በድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ሁሉ አድርገን ነበር፡፡ በምርጫ 2002 ግን ለቦርዱ በማስረጃ የተፈጠሩ ችግሮችን ብናቀርብም ሁሉንም ውድቅ አድርጎብናል፡፡ ስለዚህ የምርጫ ቦርድ አቅም እየወረደ ነው የመጣው፡፡ አሁን ስለማስረጃና እውነታ ቦርዱ ደንታ የለውም፡፡ ተመሳሳይ ስህተቶችን ነው እየደጋገመ የሚገኘው፡፡ በቦርዱ ውስጥ አሁን ከላይ እስከታች የመታመን ክብር ያለው ሰውን አጥቻለሁ፡፡ ይኼ መሆኑ ደግሞ ለአገሪቱም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ጥቅም አይሰጥም፡፡

ሪፖርተር፡- በአመራር ይገባኛል ዙሪያ በአንድነትና በመኢአድ ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው ውዝግብ ላይ ቦርዱ በቅርቡ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ለብዙኃኑ የወገነ ውሳኔ አልሰጠም በሚል የቦርዱ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ዳግም ተነስቷል፡፡ መድረክ ውሳኔውን እንዴት አየው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- መድረክ በአንድነትና በመኢአድ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ ተመልካች ነው፡፡ ነገር ግን በውሳኔው ፓርቲዎችን እንዴት ማዳከም እንደሚቻልና ማፍረስ እንደሚቻል ታዝበናል፡፡ ዛሬ ይኼ ነገር በአንድነትና በመኢአድ ላይ ተከስቷል፡፡ ማን ያውቃል ነገ እኛ ላይ ሊፈጸም ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት (ኅብረት)ን በምናንቀሳቅስበት ወቅት መሰል ነገር ገጥሞን ነበር፡፡ በአንዱ አባላችን (ኦብኮ) ላይ በገዥው ፓርቲ የተደገፈ መፈንቅለ ድርጅት ተካሂዶ ነበር፡፡  ኦብኮ በወቅቱ የኅብረት አባል በመሆኑ ዕድለኛ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ አባላትና አመራሮች በኅብረት ሥር እንደ ፓርቲ መንቀሳቀሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ አንድነት የመድረክ አባል ነበር፡፡ በመድረክ አባልነታቸው ቀጥለው ቢሆን ኖሮ በዚህ ችግር ውስጥም ቢሆኑ አባሎቻቸውን በመድረክ ስም ለምርጫ ማዘጋጀት ይችሉ ነበር፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ሰርጎ ገቦች የመበጥበጥና የመከፋፈል አደጋ ሁሌም አለባቸው፡፡ በአንድነትና በመኢአድ ጉዳይ የገዥው ፓርቲ እጅ እንዳለበት እጠረጥራለሁ፡፡ የትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ ተጠናክሮ እንዲወጣ  ገዥው ፓርቲ አይፈልግም፡፡ አንድነት ከመድረክ ለመውጣት ሲወስን የገዥው ፓርቲ እጅ እንዳለበት ጠርጥረናል፡፡ አንድነት ለሁለት የተከፈለው መቶ በመቶ በውስጣዊ ልዩነት የተነሳ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የገዥው ፓርቲና የዳያስፖራ ውጫዊ ተፅዕኖዎች እንደሚኖሩበት አስባለሁ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላትን ሲቀበሉና አመራሮችን ሲመርጡ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ክስተቱ ለሁሉም ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትምህርት ይሰጣል፡፡  

ሪፖርተር፡- በአንድነትና በሌሎች የመድረክ አባል ፓርቲዎች መካከል ያለውን የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ከግምት ውስጥ በማስገባት አንዳንዶች ጥምረቱ ላይ ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ጥቂቶች እንዲያውም ‹ያልተቀደሰ ጥምረት› ሲሉ ይጠሩት ነበር፡፡ በተለይ በግለሰቦች መብት ላይ የሚያተኩረውን የአንድነትን ፍልስፍና በቡድን መብት ላይ ትኩረት ከሚያደርገው የሌሎች ፍልስፍና ጋር ማስታረቅ እጅግ ከባድ እንደሆነ ሲገልጹ ነበር፡፡ አንድነት ከመድረክ ሲለይ ጥምረቱ ዘለቄታዊ እንደማይኖረው ከጅምሩ የገለጹ ሰዎች ልክ መሆናቸው ተረጋግጧል ማለት ይቻላል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አይቻልም፡፡ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች የመድረክን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ያልተገነዘቡ ናቸው፡፡ ከአንድነት ጋር የነበረን ታክቲካዊ ጥምረት እንጂ ስትራቴጂካዊ ጥምረት አልነበረም፡፡ ታክቲካዊ ጥምረት ማለት በአንገብጋቢ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አብረን ለመሥራት የምናደርገው ስምምነት ነው፡፡ ስትራቴጂካዊ ጥምረት ግን የርዕዮተ ዓለም ልዩነትን ማጣጣም ይጠይቃል፡፡ መድረክ የተፈጠረበት ታክቲካዊ ጉዳዮች በኢትዮጵያ አንድነት፣ በዴሞክራሲያዊ ሽግግር፣ በመልካም አስተዳደርና በግለሰቦች የሰብዓዊ መብት ላይ ያተኩራሉ፡፡ ፓርቲዎቹ የግለሰብ መብትን፣ የቡድን መብትን፣ ሊበራል ዴሞክራሲን ወይም ሌላ ርዕዮተ ዓለምን መከተላቸው ወይም አለመከተላቸው ላይ ክርክር አልነበረንም፡፡ እኔ ለምሳሌ ሶሻል ዴሞክራት ነኝ፡፡ ሌላው አባል ፓርቲም የመረጠው ርዕዮተ ዓለም ሊኖረው ይችላል፡፡ መድረክ ምርጫ ቢያሸንፍ የሚመሠርተው መንግሥት የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ነው፡፡ ይኼ ፕሮግራማችን ላይ በግልጽ የተቀመጠ ነው፡፡ ይኼ መንግሥት ሰላም የሚያረጋግጥ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያስፋፋና ለሁሉም ተደራሽ የሚያደርግ፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በተለይ የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩት ላይ ማሻሻያዎችን የሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ ወጥ ርዕዮተ ዓለም መፍጠር የመድረክ ዓላማ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ እንደ አንድነት ያሉ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ከብሔር ተኮር ፓርቲዎች ጋር ያለ ምንም ችግር በጋራ መሥራት ይችላሉ እያሉ ነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አይችሉም፡፡ በቅድሚያ በዴሞክራሲያዊ ባህል ሊያምኑ ይገባል፡፡ ይህን እስከተቀበሉ ድረስ ብሔር ተኮር ወይም ኅብረ ብሔራዊ መሆናቸው ችግር የለውም፡፡ የሁላችንም ልዩነት ተጣጥሞ መቀጠል የሚችለው በቅድሚያ የዴሞክራሲ ባህል መገንባት ስንችል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ዶ/ር አሰፋ ፍስሐ ያሉ ተመራማሪዎች የኢሕአዴግና የመድረክ ፕሮግራሞች ላይ ከአፈጻጸም ስትራቴጂ ልዩነት ባሻገር መሠረታዊ ልዩነት እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ይስማማሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አልስማማም፡፡ መድረክ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን አጀንዳ በጣም ይቃወማል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ኮሙዩኒዝምና አክራሪ የሶሻሊዝም ሐሳቦችን ያቀፈ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ይኼ የገዥው ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም በአገሪቱ ውስጥ ላሉ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ ነው፡፡ በዚህ ርዕዮተ ዓለም መሠረት ሌሎች ፓርቲዎችን መስማት አይፈልግም፣ ከሌሎች ጋር ተቻችሎ አይደኖርም፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን አይከፍትም፣ ከሌሎች ጋር አይደራደርም፡፡ የአባላቱ ባህሪ ጎጂ የሆነው ርዕዮተ ዓለሙ በሌላ መንገድ እንዳያስቡና ግትር እንዲሆኑ ስለሚሰብካቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ሁሉም የመድረክ አባላት ይኼን አቀራረብ ይቃወማሉ፡፡ ኢሕአዴግ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሕይወት የሚመዘብርበት መንገድም የርዕዮተ ዓለሙ ውጤት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በተግባር በመንግሥት የሚመራ የሶሻሊስት ሥርዓት እየፈጠረ ነው፡፡ በተጨማሪም አቅም ያለው ፓርቲ ከሚፎካከረው ፓርቲ ጋር የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሊኖረው ግድ ነው፡፡ እኛም ከኢሕአዴግ ጋር የርዕዮተ ዓለም ልዩነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ገዢው ፓርቲንና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማነፃፀር ያጠኑ ምሑራን ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ከነበረበት ሁኔታ ዛሬ ፈጽሞ የተለየ አካል መሆኑንና በአንፃሩ ተቃዋሚዎች አሁንም በሽግግሩ ወቅት ያነሱት የነበረውን ጥያቄ እንደሚያነሱ  ይደመድማሉ፡፡ የኢሕአዴግን ርዕዮተ ዓለምና የአገር ግንባታ መንገድ በእውቀትና በመረጃ ከመተንተንና አማራጭ ከማቅረብ ይልቅ ሁሉንም የኢሕአደግ ድርጊቶች በጭፍን ይቃወማሉ በማለትም ይተቻሉ፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ ምርጫ በመጣ ቁጥር አዲስ ነገር ይዞ ብቅ ሲል ተቃዋሚዎቹ ይኼን ማድረግ አልቻሉም በሚልም ይከራከራሉ፡፡ በእነዚህ ነጥቦች ላይ ይስማማሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አልስማማም፡፡ በመጪው ምርጫ ኢሕአዴግ ይዞት የሚቀርበው አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ምን እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ የልማታዊ መንግሥት ሞዴል እንደሆነ ከማኦ ዜዶንግ ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ በልማት ዙሪያ የመንግሥት ንቁ ተሳትፎ ብዙ ዘመን ያስቆጠረ አካሄድ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ዋነኛ ሐሳብ አመንጪዎች በጣም አዳዲስ ነገር ፈጣሪዎች እንደሆኑና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርም ብዙ ነገሮችን እንደፈጠሩ ለራሳቸው ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ ኢሕአዴግ ለልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም የጨመረው ነገር ምንድነው? የኢሕአዴግ አመራሮች ለአገር ግንባታና ሕዝቦችን ከድህነት ለማውጣት ቁርጠኛና ታታሪ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ በተግባር ግን ይኼ የለም፡፡ ስለዚህ የአጥኚዎቹ ድምጻሜ ተዓማኒነት የጎለደው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መድረክ የምርጫ ማኒፊስቶውን እየከለሰ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ማኒፌስቶው ምን አካቷል? በመጪው ምርጫ ለመራጮች መድረክ የሚያቀርበው አማራጭ ምንድነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ለመራጩ የምናቀርበው አማራጭ እስከ ዛሬ የተፈጠሩ ስህተቶችን ለማስተካከል ከእኛ ጋር አብሮ እንዲሆን ነው፡፡ በተለይ በአፈጻጸም ዙሪያ ትኩረት አድርገናል፡፡ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መልካም አስተዳዳር፣ የቢሮክራሲው አደረጃጀት፣ ሙስና፣ የመሬት አስተዳደር፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ሰብዓዊ መብትና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ይገኙበታል፡፡ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ብቁ ኢትዮጵያዊያንን በማግለል ቢሮክራሲውን ተቆጣጥረዋል፡፡ የገዢው ፓርቲ አባላት ያልሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ‹‹በዘመናዊ ባርነት›› ሥር ነው እየኖሩ ያሉት፡፡ በእዚህም የተነሳ የመንግሥት ሠራተኛው የመሥራት ፍላጎቱ ሞቷል፡፡ ሙስናን እናጠፋለን ብለን ቃል አንገባም፣ ለመቀነስ ግን እንሠራለን፡፡ መድረክ በጤና፣ በትምህርትና በመሳሰሉት ማኅበራዊ ጉዳዮችም ላይ አማራጮች አሉት፡፡

ሪፖርተር፡- ያለፈው ምርጫ ሽንፈታችሁን በዚህ ምርጫ የምታስተካክሱ ይመስልዎታል? ድምፅ ነፍገዋችሁ የነበሩትን መራጮች መልሳችሁ ለማሳመን ምን ዓይነት ስትራቴጂ ነድፋችኋል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- እሱን መድረክ ሳይሆን መራጩ ነው የሚወስነው፡፡ መድረክ የማይያዝ የማይጨበጥ መንፈስ አይደለም፡፡ መራጩ ሕዝብ ድምፁን ለመጠበቅ ሊቆም ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩ ምርጫዎች ያሸነፍነው ሕዝቡ የምርጫ ካርዱን ስለጠበቀና የምርጫ አስተዳዳሪዎች ያልተገባ ነገር እንዳያደርጉ በጉልበት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ቁጥጥር በማድረጉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ያለው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እውነተኛ ውድድር እንዲካሄድባት ካስፈለገ፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አቀራረብና አደረጃጀት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሊደረግ እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሚሰጡ በርካቶች ናቸው፡፡ አሁን ያለው አካሄድ ከቀጠለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አያስፈልጉም የሚሉም አሉ፡፡ እነዚህን አመለካከቶች ይጋራሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አስፈላጊ ሆነን የቀጠልነው እኛ ባንኖር ኖሮ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ አሁን ካለበት የባሰ ይሆን ስለነበር ነው፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ነህ ማለት ሁሌ ማሸነፍ አለብህ ማለት አይደለም፡፡ የውትወታ ሥራ እንሠራለን፣ መንግሥትን እንተቻለን፣ አማራጮች እናቀርባለን፣ ሰላማዊ ስብሰባና ፖለቲካዊ ስብሳዎችን እናካሂዳለን፣ ሕዝቡን እናስተምራለን፡፡ በሕዝቡ አስተሳሰብ ላይ በርካታ ለውጦችን አምጥተናል፡፡ ሕዝቡ አሁን ተወዳዳሪ ነው፡፡ የተሰጠው አስተያየት ሊያስተላልፍ የሞከረው መልዕክት ተቃዋሚዎች ተከፋፍለዋል፣ አንድ ላይ በመሆን በአንድ ፓርቲ ኢሕአዴግን መወዳዳር አለባቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ይኼ የሚቻል ነገር አይደለም፡፡ የተለያዩ ኅብረቶችን፣ ጥምረቶችንና መድረኮችን ለመፍጠር ብዙ ጥሬያለሁ፡፡ የኢትዮጵያዊያን ፍላጎት ሲታይ የተለያየ በመሆኑ የተሳካ ውህደት መፍጠር አልተቻለም፡፡ ቢመሠረትም ዘላቂ መሆን አልቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት በነበሩት ሁሉም ጠቅላላ ምርጫዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህ ምርጫዎች ምን ተማሩ? ለእርስዎና ለፓርቲዎ እጅግ ፈታኝ የነበረው የትኛው ምርጫ ነበር?

ፕሮፌሰር በየነ፡- እጅግ በጣም ከባድ የነበረው ምርጫ የ1992 ምርጫ ነው፡፡ ሐዲያ ዞንን አሸነፍን፡፡ ነገር ግን ብዙ ዋጋ ከፍለንበታል፡፡ ብዙ ሕይወት ጠፍቶበታል፡፡ ከገዢው ፓርቲ በተሰነዘረ የበቀል ጥቃት የምርጫ ክልሉ ከፍተኛ ስቃይ የተቀበለ ነው፡፡ በተለይ ከ1992 እስከ 1994 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜ በእኔ የፖለቲካ ሕይወት እጅግ ከባዱ ነበር፡፡ ድምፃቸውን ለእኛ የሰጡ ሰዎች እንግልት፣ አካላዊ ጉዳት፣ እስርና ሞትን ተቀብለዋል፡፡ አንዳንዶችም ሕይወታቸውን ለማዳን ተሰደዋል፡፡ በርካታዎቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ አሁን በደቡብ አፍሪካ ጎዳናዎች ላይ ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በተቃዋሚው ጎራ በጣም ቆይተዋል፡፡ በሆነ ወቅት ለመተው ተቃርበው ነበር? አሁንስ አልደከመዎትም?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አሁን በጣም ደክሞኛል፡፡ የእኔ ትልቁ ሽክም የሕዝቡ ፍላጎት ነው፡፡ አሁንም ለውጥ እናመጣለን ብለው ያምናሉ፡፡ እንዴት ልተዋቸው እችላለሁ? እስከምችለው ድረስ አብሬአቸው ለመጓዘ እሞክራለሁ፡፡ የአሁኑ ምርጫ የመጨረሻዬ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በምርጫ 2002 ኢሕአዴግ የምርጫ ምኅዳሩን ቁልቁል ፈጥፍጦታል፡፡ ፓርላማውን መቶ በመቶ በመቆጣጠር እንደማይቀብረው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ ከሆነ ሁሉንም ነገር ሞክሬያለሁ ብዬ አቆማለሁ፡፡ ምርጫ 2002 የሚደገም ከሆነ የመድበለ ፓርቲ ነገር ያበቃለታል፡፡ ከዚያ ባሻገር ለመሄድ መሞከር በጣም ተስፈኛ መሆን ነው፡፡

 

 

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...