Thursday, September 21, 2023

ዝርዝር ጉዳዮችን ያላካተተው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአባላትና የሥራ አመራር ሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት፣ የሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል የበላይ ማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ የመንግሥትን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ በዚህ መሠረት ባለፈው ሳምንት ጥር 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የ2007 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ባለ 18 ገጽ ሰነድ ቢሆንም፣ በጀት ዓመቱ አገሪቱ ላለፉት ዓምስት ዓመታት ስትመራበት የነበረው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማጠናቀቂያ እንደመሆኑ መጠን፣ ዝርዝር ትንታኔዎችን እንደሚይዝ  ለመገመት ይቻል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሪፖርቱ የመንግሥትን የሥራ አፈጻጸም ከመሪ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ ጋር ያነፃፀረ ነው ለማለት የሚያስደፍር ካለመሆኑም በላይ፣ ጥልቅ ትንተናዎች የጎደሉትና የወደፊት አቅጣጫዎችን  የማያሳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሪፖርታቸውን ይዘትና ጥልቀት ቀድመው የተረዱት ቢመስልም፣ በሪፖርታቸው የመጀመሪያ ገጽ ላይ ‹‹የእያንዳንዱ ዘርፍ ኃላፊዎች ለተከበረው ምክር ቤትና ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በዝርዝር ያቀረቡት እንደተጠበቀ ሆኖ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የተዘጋጀ ሪፖርት መሆኑን ለመግለጽ እሞክራለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ ፓርላማው ከየካቲት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለእረፍት ከመበተኑ በፊት በነበሩ የመደበኛ ስብሰባ ጊዜያት ለጠቅላላ ጉባዔው በሥራ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የቀረቡት ሦስት ሪፖርቶች ብቻ ናቸው፡፡ በመሆኑም ሪፖርታቸው ዝርዝር ላለመሆኑ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ የሚገባ ነጥብ ነው ብሎ መቀበል ይከብዳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው የመረጧቸው ዋና ዋና ነጥቦች በራሳቸው ማብራሪያ የጎደላቸው መሆናቸውን መመልከት ይቻላል፡፡

ኢኮኖሚ

በኢኮኖሚው ዘርፍ የቀረበው ሪፖርት የ2003 ዓ.ም. የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን መነሻ ያደረገ ሲሆን፣ በዕቅዱ ዓመታት እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአጠቃላይ በ10.1 በመቶ ማደጉን ያሳያል፡፡ ዕድገቱ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎችና ማለትም በግብርናው ዘርፍ የ5.4 በመቶ፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች በቅደም ተከተል የ21.2 እና የ11.9 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል ይላል፡፡ የተመዘገበው ሁለንተናዊ ዕድገት ፈጣንና ከተያዙ ግቦች በአብዛኞቹ እንዲሳኩ ያስቻለ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ የተመዘገበው ዕድገት ኢኮኖሚው ከ1996 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. በነበሩት 11 ተከታታይ ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ በ10.9 በመቶ እንዳደገ ያስረዳል፡፡ በ2006 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በወቅቱ የገበያ ዋጋ መሠረት 1.1 ትረሊዮን ብር ወይም 55 ቢሊዮን ዶላር እንደተገመተ ያትታል፡፡

በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ አወቃቀሩም መጠነኛ ሽግግር ማሳየቱን ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት የግብርና ዘርፍ በ2003 ዓ.ም. በጠቅላላ ኢኮኖሚ ውስጥ የ45 በመቶ ድርሻ የነበረው ሲሆን፣ በ2006 ዓ.ም. ወደ 40 በመቶ ዝቅ ብሏል ይላል፡፡ ኢንዱስትሪ በሌላ በኩል በ2003 ከነበረው የ11 በመቶ ድርሻ በ2006 ዓ.ም. ወደ 14 በመቶ ከፍ ማለቱን፣ የአገልግሎት ዘርፉ በተመሳሳይ ወቅት ድርሻው ከ45 በመቶ ወደ 46 በመቶ ከፍ በማለት ትልቁ የኢኮኖሚ ዘርፍ ለመሆን እንደበቃ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ከማረጋገጥ አንፃር ትልቅ ግምት የሚሰጠው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ድርሻ ማደግ ሲሆን፣ ላለፉት አራት ዓመታት ዘርፉ በአማካይ በየዓመቱ በ13 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ይገልጻል፡፡ ስለሆነም እየታየ ያለውን ጅምር የኢኮኖሚ አወቃቀር ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን የአቅም አጠቃቀምና ምርታማነት ማሳደግም ሆነ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንትን ከእስካሁኑ በላቀ ደረጃ ማስፋፋት እንደሚጠይቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክቷል፡፡

በተያያዘው የ2007 በጀት ዓመት የአገሪቱ ኢኮኖሚ የ11.4 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ የተተነበየ ሲሆን፣ በግብርናው 8.7 በመቶ፣ በኢንዱስትሪው 23.7 በመቶ እና በአገልግሎት ዘርፎች 9.0 በመቶ እንደሚሆን ታሳቢ መደረጉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ከላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ ዘርፍ  ሪፖርት ላይ የተመለከቱት በሙሉ የበጀት ዓመቱን አጋማሽ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ እንዳልሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ብዙዎቹ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም. ያሉ መረጃዎች እንጂ፣ የ2007 በጀት ዓመት በኢኮኖሚ ዘርፍ የመንግሥትን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የሚያሳዩ መረጃዎች አይደሉም፡፡ የ2007 በጀት ዓመት አጠቃላይ የዕድገት ትንበያ እንጂ፣ በትንበያው መሠረት እንዲሁም በአምስት ዓመቱ ዕቅድ ለ2007 በጀት ዓመት የተጣለውን ዕቅድ መነሻ በማድረግ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸምን የሚያሳይም አይደለም፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረታዊ የአወቃቀር ለውጥ በመጠኑ ማሳየቱን ለመግለጽ የተቀመጠው መረጃ የ2006 ዓ.ም. ከመሆኑ ባለፈም፣ በትክክል መንግሥት በአምስት ዓመቱ ዕቅድ ወዳስቀመጠው መዋቅራዊ ለውጥ እየሄደ ነው? የሚለውንም የገመገመ እንዲሁም የወደፊት አቅጣጫን የሚያመላክት እንዳልሆነ ማየት ይቻላል፡፡

በሪፖርቱ እንደተቀመጠው መዋቅራዊ ለውጡ በመጠኑ እየመጣ መሆኑን ለማሳየት፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት በ2003 ዓ.ም. ከነበረው የ11 በመቶ ድርሻ በ2006 ዓ.ም. ወደ 14 በመቶ ከፍ ማለቱ ተጠቅሷል፡፡

ቀደም ሲል እንደተገለጸው መረጃው በ2006 ዓ.ም. አፈጻጸም ላይ የተመሠረተ ከመሆኑም ባሻገር የአምስት ዓመቱ ዕቅድ ላይ ከተቀመጠው ግብ አንፃር ያልተገመገመ ነው፡፡ መረጃው እንደሚያመለክተው በየዓመቱ መጠነኛ ዕድገት ቢኖርም በዕቅዱ ከተቀመጠው 18 በመቶና በየኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተጣለው ግብ አንፃር በእጅጉ አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑም መዋቅራዊ ለውጡ እየመጣ መሆኑን የሚያሳይ ነው ለማለት አያስችልም፡፡ ምክንያቱም ኢኮኖሚውን እየመሩ ከሚገኙት ግብርናና የአገልግሎት ዘርፍ አንፃር የኢንዱስትሪው አፈጻጸም በእጅጉ ሩቅ ነው፡፡

በመሆኑም መዋቅራዊ ለውጡ እየመጣ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው እጅግ አናሳ ነው ከሚባለው የአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሪፖርቱ የዚህን ሒደት አንድምታ የዳሰሰ አይደለም፡፡ ሪፖርቱ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚካተቱ ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ያላካተተም ነው፡፡

በመሆኑም በግንባታ ላይ ከሚገኙት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክትና የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር፣ እንዲሁም ከአዋሽ ወልዲያ መቀሌ የሚደርሰው የባቡር መስመር ውጪ፣ ታቅደው የነበሩት ፕሮጀክቶች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ሪፖርቱ አያሳይም፡፡ በስኳር ልማት ዘርፍ የታቀዱት ፋብሪካዎችን በሚመለከት በበጀት ዓመቱ አጋማሽ የደረሰበት የአፈጻጸም ደረጃ አልተገለጸም፡፡

በኃይል አቅርቦት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ 10 ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት በዕቅድ የተያዘ ቢሆንም፣ በዓመቱ አጋማሽ የዚህን ዘርፍ እንቅስቃሴ የተመለከተ ሪፖርት አልቀረበም፡፡ አገሪቱ በቱሪዝም ልማት ከፍተኛ ውጥን ይዛ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ቦርድ ብታቋቁም የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት ተስፋ በተጣለበት በቱሪዝም ልማት ዘርፍ ምን ታቅዶ ምን እየተሠራ መሆኑን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡ ዘርፉም ሙሉ በሙሉ በሪፖርታቸው አልተካተተም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ የዳሰሰው አንኳር ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ሳይሆን፣ የካይዘን ሥራ ፍልስፍና ላይ ስለተሰጠው ሥልጠናና በቤት ልማት ፕሮጀክቶች የተገነቡ ቤቶች በቅርቡ የሚተላለፉ መሆኑን ነው፡፡ እንዲሁም በሥራ ፈጠራ ረገድ ለምን ያህል ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ቢገልጹም፣ የዚህም ኢኮኖሚያዊ አንድምታ በሪፖርቱ አልተካተተም፡፡

ፖለቲካ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፖለቲካ ዘርፍ ባቀረቡት ሪፖርት የአገሪቱን የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ ስትራቴጂዎች በተለይም ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን በትብብር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት አይተዋል፡፡

በዚሁም መሠረት የኢትዮ-ጂቡቲ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር እየተደረገ ስለላው ጥረትና የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኬንያን በተመለከተ ልዩ የትብብር ሰነድ መፈረሙንና ሁለቱን አገሮች በኃይልና በመንገድ የማገናኘት ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሶማሊያን በተመለከተ በኢትዮጵያ አደራዳሪነት በማዕከላዊ መንግሥትና በጁባ አስተዳደር መካከል ስምምነት መፈረሙ አንድ ውጤት መሆኑንና እንደዚህ ዓይነቱ ጥረት እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ግብፅን በተመለከተ ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ መመረጥ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል የትብብር መንፈስ መታየት መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በጠቀሷቸው ሁለቱም የጎረቤት አገሮችና የግብፅ የውጭ ግንኙነት ዝርዝር ትንታኔዎች አልተንፀባረቁም፡፡ ለአብነትም ያህል በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ውይይት ቢጀመርም መግባባት ላይ አለመደረሱን፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ኢትዮጵያ የግብፅን ውኃ እንማትጎዳ በሰነድ እንድትፈርም ስለመጠየቁና እስካሁንም ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ አለመደረሱን አላስረዱም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -