የምርጫ ዝግጅት ኮሚቴ አዋቀረ
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጊዜያዊ የባለአደራ ቦርድ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሻረውን የንግድ የምክር ቤቱን ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔ በድጋሚ ለማካሄድ ቀን ቆረጠ፡፡ ጉባዔው የሚካሄድበት ሁኔታ ግን አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
ከኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር በነበረ የፍርድ ቤት ክርክር በተሰጠ ውሳኔ መሠረት የተሻረውን ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔ ድጋሚ ለማካሄድ፣ ባለአደራ ቦርዱ መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. መርጧል፡፡
በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ንግድ ምክር ቤቱን የሚመሩ አዳዲስ አመራሮች ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከተሻረው ዘጠነኛ ጉባዔ በተጨማሪ፣ ታኅሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ሊያካሂድ የነበረው 10ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ታግዶ እንዲቆይ ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጠውንና በአቶ ኤልያስ ገነቲ ፕሬዚዳንትነት የሚመራውን ቦርድ፣ እንዲሁም በዕለቱ የተወሰኑ ውሳኔዎችን በመሻሩ ባለአደራ ቦርዱ በሚጠራው ጠቅላላ ጉባዔ እነዚህን ተመራጮች በአዲስ የሚተካ ምርጫ ይካሄዳል፡፡
ለዚህም ምርጫ ባለአደራ ቦርዱ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ አንድ የምርጫ ዝግጅት ኮሚቴ ማዋቀሩንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይሁን እንጂ ጠቅላላው ጉባዔ እንዴት ሊካሄድ ይችላል የሚለው ጉዳይ ግን እያነጋገረ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በፍርድ ቤት በቀረበው ክስ አንዱ ምክንያት የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ሕግን ያልተከተለና በትክክል ምልዓተ ጉባዔውን በማያሟላ ሁኔታ እየተካሄደ ነው በሚል ነው፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ ከ15 ሺሕ በላይ የሚሆኑ አባላት እያሉት የጠቅላላ ጉባዔው ምልዓተ ጉባዔ ሞላ የሚባለው ግን 500+1 ነው መባሉ፣ የንግድ ምክር ቤቶችን ማቋቋሚያ አዋጅ የሚፃረር ነው በማለት ይህ ግድፈት እንዲስተካከል መጠየቁ ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል ንግድ ምክር ቤቱ ከኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር በነበረው ክርክር ይህንን በንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የሰፈረውን አሠራር ትክክል ነው በማለት እንደተፈረደለት በማስታወቁ፣ በጊዜያዊ ባለአደራ ቦርዱ የሚካሄደው ምርጫ ከጠቅላላ አባላቱ 500+1 ከተገኙ ምልዓተ ጉባዔ እንደሞላ ተቆጥሮ በዚሁ ምርጫው ሊካሄድ ይችላል እየተባለ ነው፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው በውክልና ቀመር ይሠራ የሚል እምነት ያላቸው ወገኖች ደግሞ አሁን ባለአደራ ቦርዱ የጠራው ጠቅላላ ጉባዔ እንዴት እንደሚካሄድ ግልጽ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ በተለይ ምልዓተ ጉባዔውን በሚመለከት በፍርድ ቤት በእንጥልጥል ላይ ያለ ጉዳይ መኖሩንም ይጠቁማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጊዜያዊ ባለአደራ ቦርዱ የምርጫው ሒደት ከዚህ ቀደም ከነበረው ወጣ ባለ መንገድ የሚያካሂደው እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው፡፡
በተለይ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የጽሕፈት ቤቱ ሚና ውስን እንዲሆን ማድረጉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ምርጫውን የበለጠ ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ከተፈለገ ደግሞ በተለይ የአባላት ቁጥርን የሚያመለክተው ሰነድ በጥንቃቄ መያዝ እንዳለበት፣ ማን አባል ነው አይደለም የሚለው ጉዳይ ላይ ቦርዱ ትኩረት ያድርግ በማለት የሚያሳስቡ አሉ፡፡