Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን አገር አቋራጭ ባቡሮች ማምረት ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በቅርቡ ግንባታው ለተጀመረው አገር አቋራጭ የባቡር መስመር ጥቅም ላይ የሚውሉ ባቡሮችን በብዛት በአገር ውስጥ ለማምረት፣ የመጀመሪያውን የሙከራ ባቡር (ፕሮቶታይፕ) ዲዛይን አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታወቀ፡፡

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን የሚያድኑ ወታደራዊና የሲቪል ምርቶችን ለማምረት አቅዶ የተነሳው ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ የሕዝብና የዕቃ ማመላለሻ አገር አቋራጭ ባቡሮችን በአገር ውስጥ በብዛት ለማምረት የመጀመሪያውን የሙከራ ዲዛይን አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ በባህር ዳር ከተማ የተከበረውን ሦስተኛውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ የመከላከያ ተቋማት ጋር በመተባበር የሠራቸውን አዳዲስ ምርቶች ለሕዝብ ዕይታ ክፍት አድርጓል፡፡ ከእነዚህም መካከል ግንባታው በመጀመር ላይ የሚገኘው ግዙፉ የአገር አቋራጭ የባቡር ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ፣ አገልገሎት የሚሰጡ የሕዝብና የዕቃ ማመላለሻ ባቡሮች ኮርፖሬሽኑ ሠርቶ ለማቅረብ የሚያስችል ሙከራ ማሳየቱ ይገኝበታል፡፡ ሠርቶ ያጠናቀቀው የከተማ ቀላል ባቡርም እንዲሁ፡፡

በኮርፖሬሽኑ ሥር ከሚገኙት ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ በሆነው በሎኮሞቲቭ ኢንዱስትሪ እየተሞከረ ያለውን ባቡር በአገር ውስጥ የማምረት ጥረት የተጀመረው፣ የኢንዱስትሪው ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት በአዲስ አበባ ለገሐር የኢትዮ – ጂቡቲ ምድር ባቡር ግቢ ውስጥ ነው፡፡

ኢንዱስትሪው በዚሁ ግቢ የቀላል ባቡር ማምረቻ ፋብሪካ ሲኖረው፣ በድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የአገር አቋራጭ ባቡሮች ፋብሪካ አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ከድርጅቱ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኢንዱስትሪው ሎኮሞቲቭን (የባቡር ጎታች) ጨምሮ ቀላል ባቡሮችና አገር አቋራጭ ዋገን ባቡሮችን ማምረት ይችላል ተብሏል፡፡ ተሠርቶ የተጠናቀቀው ቀላል የከተማ ባቡር በሰዓት ፍጥነቱ 70 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ የመጫን አቅሙ እስከ 300 ሰው ይደርሳል፡፡

በኤሌክትሪክ የሚሠራ አገር አቋራጭ የጭነት መጎተቻ ባቡር (ሎኮሞቲቭ) ፍጥነት በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ እንደ ዓይነታቸው ከሦስት ሺሕ እስከ አራት ሺሕ ቶን ዕቃ ማጓጓዝ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ ሥራው የተጀመረው በኤሌክትሪክ የሚሠራው አገር አቋራጭ የሕዝብ ማጓጓዣ በበኩሉ ፍጥነቱ በሰዓት 160 ኪሎ ሜትር ሆኖ፣ እስከ 1,300 ሰው የመጫን አቅም እንደሚኖረው ታውቋል፡፡

በተጨማሪም ኢንዱስትሪው እስከ 70 ቶን የመጫን አቅም ያላቸው የዕቃ መጫኛ ጋሪ፣ የማቀባበያ ባቡርና በኤሌክትሪክ የሚሠራ አውቶቡስ ለማምረት አቅዷል፡፡

በሥፍራው የነበሩ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሙከራ ሥራውን ለማጠናቀቅ ወደ አራት ዓመት ጊዜ የፈጀ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በብዛት ለማምረት ታቅዷል፡፡ ቀደም ሲል ለአዲስ አበባ ቀላል የከተማ ባቡር አገልገሎት መንግሥት 49 ቀላል ባቡሮች ከቻይና ያስመጣ ሲሆን፣ በቀጣይነት በተያዘው ፕሮግራም በአገር ውስጥ ማምረት እንደሚጀመር ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

ኮረፖሬሽኑ ቀደም ሲል ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን)፣ ‹‹ዚላ›› የተሰኘ ጥይት የማይበሳው ወታደራዊ ተሽከርካሪ፣ እንዲሁም ትራክተሮችና የተለያዩ መጠን ያላቸው የጭነት ተሽከርካሪዎችን ማምረቱ ይታወሳል፡፡   

በየማነ ናግሽ፣ ከባህር ዳር  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች