አገር በቀሉ የአሉሙኒየም ኩባንያ በኢትዮጵያ የደቡብ አካባቢዎች በአሉሙኒየም ማዕድን ቁፋሮ ለማድረግ የሚያስችለውን የዳሰሳ ጥናት አጠናቆ የፍለጋ ሥራ ለመጀመር፣ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑ አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃይማኖት አባተ እንደገለጹት ኢንተር አፍሪካ ኤክስትሩዥን በሚል መጠሪያ የሚታወቀውና ከአምስት ዓመት በፊት ቃሊቲ አካባቢ ማምረቻውን ያቋቋመው ድርጅት፣ ወደ አሉሙኒየም ሥራ የገባው ምርቶቹን ከዱባይ በማስመጣት ነው፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ምርቱን በአገር ውስጥ ማምረት መጀመሩን አቶ ሃይማኖት ይገልጻሉ፡፡ ለአሉሙኒየም ማምረቻ የሚያገለግሉ ጥሬ ዕቃዎችን (ስክራፖችን) ከአገር ውስጥ መሰብሰብ ቢቻልም፣ መቶ በመቶ የአሉሙኒየም ይዘቱን ለማስጠበቅ ሲባል ጥሬ ዕቃውን አሁንም ከውጪ ማስገባቱ እንዳልቆመ ተናግርዋል፡፡
በቅርቡ ግን ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር በመተባበር ደቡብ ክልል በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የአሉሙኒየም ማዕድን መኖሩ በመረጋገጡ፣ ድርጅቱ የቅድመ ትግበራ ሰነዱን ለማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር አቅርቦ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኩባንያው ባለቤት አቶ ብሩክ ኃይሌ በሙያቸው አርክቴክት እንደሆኑ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ጥራቱ የተረጋገጠለትንና ከውጪ ከሚመጣው አሉሙኒየም ጋር ሊወዳደር የሚችል ምርት በአገር ውስጥ እንዲመረት በነበራቸው ፍላጎት፣ በ45 ሚሊዮን ብር ድርጅቱን ማቋቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ በ40/60 የቤቶች ግንባታም ተሳታፊ እንደሆነ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ሰንጋ ተራና ቃሊቲ አካባቢ እየተገነቡ ያሉትን ቤቶች የበር፣ የመስኮትና የፓርትሽን ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡