Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአፍዴራ ጨው አምራቾች የመሠረተ ልማት ችግር ተፅዕኖ አሳድሮብናል አሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱን የጨው ፍጆታ ከ90 በመቶ በላይ የሚሸፍኑት የአፍዴራ ጨው አምራቾች፣ ለዓመታት ምላሽ ሳያገኝ የቆየው የአካባቢው የመሠረተ ልማት ችግር በምርታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገለጹ፡፡

ባለፈው ሳምንት ከአይሪሽ ኤይድ በዕርዳታ የተበረከቱላቸውን የአዮዲን መደባለቂያ ማሽኖች በተረከቡበት ወቅት አምራቾቹ እንደተናገሩት፣ እስካሁን ድረስ ምላሽ ያልተሰጣቸው የኤሌክትሪክ፣ የመንገድ፣ የውኃና የቴሌኮም አገልግሎቶች በምርታቸው ላይ ተፅዕኖ እያደረሱ ናቸው፡፡

በአፍዴራ ከሚገኙት የጨው አምራች ማኅበራት መካከል ካዳባ የተሰኘውና ከ500 በላይ አባላት ያሉት ማኅበር ውስጥ አባል የሆኑት አቶ ጣሂር ውሃብረቢ እንደገለጹት፣ በዕርዳታ የተገኙትና ማኅበራቱም የተወሰነ ወጪ ያወጡባቸው የአዮዲን መደባለቂያ ማሽኖች በጄኔሬተር የሚሠሩ በመሆናቸው ለረዥም ጊዜ ማገልገላቸውን እንደሚጠራጠሩ ጠቁመዋል፡፡ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሲሆን ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የማሽኖቹን መለዋወጫዎች እንኳን እንዴት ብለን ማግኘት እንደምንችል አናውቅም፤›› ሲሉ ለሪፖርተር የተናገሩት አቶ ጣሂር፣ የውኃና የመንገድ አቅርቦቱ ሙሉ ለሙሉ ካልተሟላ በቀር መንግሥትና ሕዝብ የጣለባቸውን የጨው አዮዳይዜሽን ኃላፊነት በሚፈለገው መጠን ለማሟላት እንደሚከብዳቸው ገልጸዋል፡፡

ከአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ እስከ አፍዴራ ድረስ የሚደርሰው አስፓልት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንና የኤሌክትሪክና የውኃ አገልግሎቶችን ለማዳረስ ሥራዎች መጀመራቸውን የሚገልጹት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሙሳ አህመድ፣ መንግሥት ምላሽ መስጠት መጀመሩን ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና አምራቾቹን በፅኑ እየፈተኑ የሚገኙት የኤሌክትሪክና የቴሌኮም እንዲሁም የውኃ አቅርቦት ችግሮች አምራቾቹ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በኃላፊነት እየተወጡት የሚገኘውን ጨውን ከአዮዲን ጋር አመጣጥኖ የማምረት ሥራ፣ በተገቢው ሁኔታ እንዳይወጡ እንቅፋት እንደሆነባቸው የተሰነዘረውን አስተያየት እንደሚጋሩት ገልጸዋል፡፡

የአካባቢው ውኃ በቂ ባለመሆኑና የጨው ይዘቱም ከፍተኛ በመሆኑ አንዳንድ አምራቾች ለአዮዲን መደባለቂያ የሚሆን ውኃ 270 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የሎጊያ ከተማ ጭምር በማስመጣት የሕዝቡን ጤንነት ይበልጥ ለመጠበቅ እየተጣረ መሆኑን የሚገልጹት አምራቾቹ፣ የመሠረተ ልማት ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ ሲቀረፉ የሚፈለገውን ለውጥ ሙሉ በሙሉ ማምጣት እንደሚቻልም ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያ በአፈሯ ዝቅተኛ የአዮዲን ይዘት የተነሳ በዓለም በአዮዲን እጥረት በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ከሚጠቁት ቀዳሚዎቹ አገሮች አንዷ ናት፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በሕዝብ ጤና አጠባበቅ ተቋማትና ዩኒሴፍን በመሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተካሄደ ጥናት፣ ከአምስት ዓመት በፊት 15 በመቶ ብቻ የነበረው አዮዲን የተቀላቀለበት ጨው አምና ወደ 88 በመቶ እንዳደገ ይጠቁማል፡፡ ይሁንና ትክክለኛውና አገሪቱ ያፀደቀችውን ከ33 እስከ 36 በመቶ የሚጠበቀውን የአዮዲን መጠን በማሟላት ደረጃ ግን 23 በመቶ ብቻ መድረሱ አሁንም ብዙ ሥራ ከሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ አምራቾችና ተባባሪ ድርጅቶች እንደሚጠበቅ የዓለም አቀፉ ቃል ኪዳን ለተሻሻለ ንጥረ ምግብ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ዓለም ሐደራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች