Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመንግሥትን ተሳትፎ ያሳድጋል የተባለው የውጭ ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት...

የመንግሥትን ተሳትፎ ያሳድጋል የተባለው የውጭ ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተላከ

ቀን:

ረቂቁ ሕገወጦችን እንዳያባብስ መሥጋታቸውን ኤጀንሲዎች ጠቁመዋል

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ›› በሚል ያዘጋጀውና መንግሥት በሴክተሩ ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖረው ያደርጋል የተባለው ረቂቅ አዋጅ፣ ሰሞኑን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩ ተጠቆመ፡፡

ቀደም ብሎ ሲሠራበት የነበረውን አዋጅ ቁጥር 632/2001ን ይተካል የተባለው አዲሱ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ፣ ከባለድርሻ አካላት ማለትም ኤጀንሲዎች ጋር አዳማ ከተማ በተደረገ ውይይት ተነስተው የነበሩ ተቃውሞችንና ግብዓቶችን ተስተካክሎና አካቶ እንደሚቀርብ የተገለጸ ቢሆንም፣ አጥጋቢ የሆነ ማስተካከያ ሳይደረግበት ለምክር ቤቱ መላኩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚኒስትሮች ምክር ቤትና ለሚመለከተው አካል ረቂቁን ሲልክ፣ ስለአዋጁ አጭር ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት በነባሩ ሕግ ሙሉ በሙሉ በግሉ ሴክተር የተያዘ ነበር፡፡ በቀረበው ረቂቅ ሕግ ግን የመንግሥት ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሚሆንና በግል ኤጀንሲዎች ላይ ግዴታዎች በተሻለ ደረጃ ጠንካራ እንደሚሆኑ አካቶ የያዘ መሆኑን ያብራራል፡፡

በቀድሞ ሕግ ለሥራ ወደ ውጪ የሚሄዱ ሠራተኞች በሚሰማሩበት የሥራ መስክ ተገቢውን ሥልጠና የወሰዱና የብቃት ማረጋገጫ ማቅረብ የማያስገድድ እንደነበር የጠቆመው የሚኒስቴሩ ረቂቅ፣ በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ግን አስገዳጅ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቀድሞውን ሕግ ማሻሻል ያስፈለገበትን ሲያብራራ፣ ሌሎች አገሮች በዘርፉ ያላቸውን የሕግ፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ተሞክሮን በስፋት ዳስሷል፡፡ የፊሊፒንስ፣ የህንድ፣ የባንግላዴሽና የሲሪላንካ ተሞክሮን ጠቅሷል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን ኃላፊነት በኤጀንሲዎች ላይ በማድረጉ፣ ኤጀንሲዎች በሚልኩዋቸው ሠራተኞች ላይ ከመጠን በላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ለሪፖርተር ገልጸው፣ ረቂቁ ከመፅደቁ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአትኩሮት ሊመለከቱት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በረቂቁ ውስጥ የተካተቱ አንቀጾች በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩትን በማሸማቀቅ ሕገወጥ ደላሎችን ያስፋፋል ከሚል የተነሳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በረቂቅ ሕጉ አንድ ሠራተኛ መላክ የሚቻለው ሁለቱ አገሮች ስምምነት ላይ ሲደርሱ መሆኑ መካተቱ ጥሩ መሆኑን የሚገልጹት ኤጀንሲዎቹ፣ የተቀባይና ላኪ አገሮች ኤጀንሲዎች ማኅበራት ለሠራተኞቹ የተሻለ ጥቅምና ጥበቃ የሚያደርግ ውል መፈራረም እንዲችሉ ተደርጎ፣ በረቂቁ ውስጥ እንዲካተት ጠይቀዋል፡፡ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር በተገናዘበ ሁኔታ በሥራው ውስጥ ያሉ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ከአቻ ማኅበር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ኮሚሽን እንዲያገኙ ቢደረግ፣ የኮንትራት ጊዜያቸውን ጨርሰው ከአሠሪዎቻቸው ጋር ለመቀጠል የሚስማሙ ሠራተኞች፣ በሄዱበት አገር ካለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ (ቆንስላ) ጽሕፈት ቤት ቀርበው ከአሠሪዎቻቸው ጋር እንዲፈራረሙ የሚል በረቂቁ እንዲካተት ጠይቀዋል፡፡

ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ሠራተኞች፣ በአገር ውስጥ በሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት የባንክ ሒሳብ ከፍተው ቢሄዱና ከደመወዛቸው የተወሰነ መቶኛ በቀጥታ ወደ ሒሳባቸው እንዲገባ ቢደረግ፣ እነሱም ሆኑ አገር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡ ተዋውለው ከሄዱበት አሠሪ ቤት ጠፍተውና በሌላ ቦታ ተቀጥረው ቢገኙ፣ በሕግ ተጠያቂ የሚደረጉበት አንቀጽ በረቂቁ እንዲካተት ኤጀንሲዎቹ መጠየቃቸውንም አክለዋል፡፡

በርካታ በረቂቁ መካተት ያለባቸውን ነጥቦች ያነሱት ኤጀንሲዎቹ ከአዋጁ መውጣት ያለባቸውንም ነጥቦች ጠቁመዋል፡፡ በረቂቁ ‹‹ትርጓሜ›› በሚለው ክፍል ሥር የተካተተው ‹‹የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ›› ትርጉም ግልጽ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሚሠሩት ሥራ አሠሪና ሠራተኛውን ማገናኘት፣ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የተላከን ሠራተኛ መብት ማስከበር በመሆኑ፣ ኃላፊነታቸውና ግዴታቸው እስከምን ድረስ እንደሚዘልቅ በማያሻማ ቋንቋ መገለጽ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት፣ አሠሪ እንደሆነ መቁጠር የሥነ አመክንዮና የሕግ ፍልስፍና (Jurisprudence) መሠረት የሌለው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ኤጀንሲ ዓረብ አገር ለሚሠራ ሠራተኛ አሠሪ ተደርጎ በረቂቁ ውስጥ መካተቱ፣ የሕግና የፍሬ መሠረት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

ፈቃድ ለማግኘት ወይም ብቁ ለመሆን የተቀመጠው ካፒታል መጠን በአገሪቱ የንግድ ሕግ መሠረት ተፈጻሚ እንደሚሆን ጠይቀው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ፈቃድ ለማግኘት መሟላት ስላለባቸው ነገሮች በረቂቁ ውስጥ የተቀባይ አገርን ሕግ፣ ደንብና ፍላጎት ያላገናዘበ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ኤጀንሲዎቹ ሚኒስቴሩ በረቂቅ ሕጉ ማካተት፣ ማውጣትና ግልጽ ማድረግ ያለበትን በዝርዝር በመጥቀስ እንዲያካትት ያሳወቁ ቢሆንም በዝምታ ማለፉን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የትምህርት ደረጃን በረቂቁ ማስፈሩ፣ ቀደም ብለው የሄዱ እንዳይመለሱ የሚያደርግና በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ጉልበታቸውን ተጠቅመው ለመሥራት መሄድ የሚፈልጉት ወደ ሕገወጦች እንዲሄዱ እንዳያደርጋቸው ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

አዋጅ ቁጥር 632/2001 ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ በአሁኑ ወቅት 400 ያህል የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ፈቃድ መውሰዳቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ በእነሱ አማካይነትና በግላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለሥራ ተሰማርተዋል፡፡

በሕጋዊም ይሁን በሕገወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ ማለትም የመብት ጥሰት፣ የጉልበት ብዝበዛ፣ ሞት፣ የአካል ጉዳትና የአካል መጉደልና እንግልት መድረሱን በመጥቀስ፣ አዋጅ 632/2001ን ማሻሻል እንዳስፈለገ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ መውሰዱንና በቀጣይ የተሻለ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳለውም ገልጿል፡፡ 95 አንቀጾች ያሉት ረቂቅ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት በተለይ የሕግ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲያደርጉበት ተጠቁሟል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...