በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ አውራ ጐዳናዎች ላይ የሚታዩት አሰቃቂ የተሽከርካሪ አደጋዎች ከቁጥጥር ውጪ እየሆኑ ነው፡፡ የአገሪቱ መውጪያና መግቢያ ከሆነው የአዲስ – አዳማ (ናዝሬት) መንገድ ጀምሮ በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች በየቀኑ ዘግናኝ የሆኑ አደጋዎች ይከሰታሉ፡፡ በእነዚህ አደጋዎች በርካቶች ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ እየተዳረጉም ናቸው፡፡ የአገሪቱ አንጡራ ሀብትም እየወደመ ነው፡፡ ይህንን አሰቃቂ የተሽከርካሪ አደጋ ለመቀነስ ብሎም በቁጥጥር ሥር ለማዋል ለምን ያቅታል? ችግሮቹን በዝርዝር በማየት መፍትሔ ማመላከት ግድ ይለናል፡፡
በቅርቡ የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር መስመር ሙከራ ከቃሊቲ ዴፖ እስከ መስቀል አደባባይ ተጀምሯል፡፡ የባቡር መስመሩን ከተሽከርካሪዎችና ከእግረኞች ለመለየት ተብሎ ግራና ቀኝ አጥር ተሠርቷል፡፡ ነገር ግን ይህንን አጥር እየጣሱ የገቡ ተሽከርካሪዎች ተስተውለዋል፡፡ ይህ ከፍተኛ የአገር ሀብት የፈሰሰበት ፕሮጀክት ሥራ ላይ ሳይውል ካሁኑ እንዲህ ዓይነት አደጋዎችን ማስተናገድ ከጀመረ፣ ነገ ሊደርሱ የሚችሉ አሰቃቂ አደጋዎች ከወዲሁ ሊታሰቡ ይገባል፡፡ በአንድ አቅጣጫ 15 ሺሕ ተሳፋሪዎችን ጭኖ የሚንቀሳቀስ የከተማ ባቡር፣ አጥሩን እየጣሱ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች ጋር ሲላተም ሊፈጠር የሚችለው አደጋ ያሳስባል፡፡ አስፈሪም ነው፡፡
በኢትዮጵያ የተሽከርካሪ አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ የዜጐችን ሕይወት እየቀጠፈ በመሆኑ፣ ሁነኛ መፍትሔ ካልተፈለገለት አደጋው እየተባባሰ ይቀጥላል፡፡ ችግሮቹ ነጥረው ወጥተው ሊታዩ ይገባል፡፡ እስኪ ዋና ዋና የሚባሉ አምስት መሠረታዊ ችግሮችን አንስተን መፍትሔ እንጠቁም፡፡
- ቸልተኝነት
በመላ አገሪቱና በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ለተሽከርካሪ አደጋ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ቸልተኝነት ነው፡፡ ይህ ቸልተኝነት የሚመነጨው የመንገድ ተጠቃሚዎችን ማዕከል ያደረገ የአነዳድ ሥርዓት ባለመኖሩ ነው፡፡ ብዙዎቹ አሽከርካሪዎች መንገድ ውስጥ ከገቡ በኋላ አስፈላጊውን የመንገድ ትራንስፖርት ሕግ ተግባራዊ ከማደረግ ይልቅ በዘፈቀደ ያሽከረክራሉ፡፡ ከፊት፣ ከኋላ፣ ከጐንና ጐን ያሉ ተሽከርካሪዎችን በአስተውሎት እየቃኙ ከማሽከርከር ይልቅ፣ ራሳቸውንና ሌሎችን ለአደጋ እያጋለጡ ይጓዛሉ፡፡ ርቀት አለመጠበቅ፣ አንድ መስመር ይዞ አለመጓዝ፣ በተዛባ ግምት መንቀሳቀስና ከመጠን ያለፈ ፍጥነት ለአደጋ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከመጠን ባለፈ በራስ መተማመን ምክንያት ሰው ሠራሽ የሆነውን ተሽከርካሪ ያላግባብ መጠቀምም ለአደጋ ይዳርጋል፡፡ ቸልተኝነቱ ከዚህ በላይም ሌሎች መገለጫዎች አሉት፡፡
- የችሎታ ማነስ
በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ውስጥ መንጃ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚያሽከረክሩ አሉ፡፡ በቂ የሆነ ልምምድ ሳያደርጉ ልምድ ካላቸው እኩል ለማሽከርከር የሚፈልጉም በብዛት አሉ፡፡ እነዚህ የትራፊክ ሕጉን በበቂ ሁኔታ የማያውቁ፣ የያዙትን ተሽከርካሪ በአግባቡ ማሽከርከር የማይችሉ፣ ድንገተኛ አደጋ ወይም ችግር ሲያጋጥም ምን ማድረግ እንዳለባቸው የማይረዱና በድፍረት ጐዳናውን የወረሩ ናቸው፡፡ ለመንዳት የሚያስችላቸው ፈቃድ ከሕጋዊው አካል ከወሰዱ በኋላ እጃቸውን ሳያፍታቱ ችሎታቸው ካላቸው እኩል ጎዳናው ላይ ይሮጣሉ፡፡ የመንገድ ምልክቶችን፣ የአደባባይ ቅድሚያዎችንና ሌሎች የመንገድ ሥርዓቶችን ጠንቅቀው ስለማያውቁ የእግረኞች ማቋረጫ ላይ ሳይቀር አደጋ ያደርሳሉ፡፡ እነዚህ ችሎታ አልባ አሽከርካሪዎች ከድፍረት በስተቀር ዕውቀቱ ስለሌላቸው የአደጋ ዋነኛ ተዋንያን ናቸው፡፡
- የሥነ ምግባር ጉድለቶች
አሽከርካሪዎች ከመጠጥ፣ ከጫት፣ ከዕፆችና ከመሰል አጓጉል ድርጊቶች መታቀብ አለባቸው፡፡ ይሁንና በየምሽቱ ከየመጠጥ ቤቱ እየተነሱ አደጋ የሚያደርሱ ቁጥራቸው በጣም እያሻቀበ ነው፡፡ በረጅም ጉዞዎች ጫት እየቃሙ የሚያሽከረክሩ ለአደጋ ምክንያት ናቸው፡፡ እነዚህ የሥነ ምግባር ጉድለቶች በጣም በመበራከታቸው በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ ሥፍራዎች በየቀኑ በርካታ አደጋዎች አሉ፡፡ ‹‹ከጠጡ አይንዱ፣ ከነዱ አይጠጡ›› የሚባለው መፈክር ሥራ ላይ ባለመዋሉ በየምሽቱ አደጋ በዝቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በጣም በርካታ ንፁኃን ዜጐች የአደጋ ሰለባ ሆነዋል፡፡ አሁንም እየሆኑ ናቸው፡፡ በአልኮል የደነዘዙና በጫት ምርቃና ሌላ ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ጎዳናውን የደም ማዕበል እያደረጉት ናቸው፡፡
- የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ
በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ እየተስተዋለ ባለው ከፍተኛ የኮንስትራክሽን፣ የወጪና የገቢ ንግድ፣ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ በሚታየው ሰፊ የሥራ እንቅስቃሴ ምክንያት በርካታ ተሽከርካሪዎችና አሽከርካሪዎች ይፈለጋሉ፡፡ ለዚህም ሲባል የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ ተለውጧል፡፡ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ አምስተኛ መንጃ ፈቃድ ማግኘት ይችላል፡፡ ነገር ግን ሥልጠናውም ሆነ ምዘናው ጥራትን የተከተለ ባለመሆኑ ለአደጋ በምክንያትነት እየተጠቀሰ ነው፡፡ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ ጥራት ላይ ትኩረት ካላደረገ፣ አሁን ከሚታዩት በላይ አደጋዎች ያጋጥማሉ፡፡ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ ከሙስና የፀዳ ነው ወይ? ተብሎ ቢጠየቅ ምላሹ አይደለም ነው፡፡ ከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚመደቡ አሽከርካሪዎች ጥራት ያለው ሥልጠና ተሰጥቷቸው፣ ጥራት ባለው ምዘና ወይም ፈተና ውስጥ ካላለፉ በስተቀር ውጤቱ አደጋ ነው፡፡ አሁን የሚታየውም ይህ የጥራት ችግር የፈጠረው አደጋ ነው፡፡ አሽከርካሪዎችን በብዛት ለማምረት የሚደረገው ርብርብ ጥራት አልባ በመሆኑ የብዙ ሺሕ ዜጐችን ሕይወት እየቀሰፈ ነው፡፡ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ ከፍተኛ ግምገማ ያስፈልገዋል፡፡
- የቁጥጥር መላላት
በመላ አገሪቱ የትራፊክ ደንብ ለማስከበር እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ባይስተባበልም፣ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫም ሆነ ክትትልና ቁጥጥሩ በጣም ብዙ ይቀረዋል፡፡ ደንብ በማስከበር ላይ ከተሰማሩት ባለሙያዎች ጀምሮ የሚመለከታቸው ተቋማት በብቁ ሁኔታ አልተደራጁም፡፡ በቂ የትራፊክ መብራቶች፣ የመንገድ ላይ ምልክቶች፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የመቆጣጠሪያ ሥልቶች፣ ተከታታይነትና ወጥነት ያለው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ ተቋማቱ በሠለጠነ የሰው ኃይል፣ በበቂ ተሽከርካሪዎች፣ በራዳር መሣሪያዎችና ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች ስለማይደገፉ አደጋው እየከፋ ነው፡፡ የቁጥጥር መላላቱ ከሥነ ምግባር ችግር ጋር እየተደባለቀ አገሪቱን እያስጨነቃት ነው፡፡
እነዚህ ከላይ የተመለከቱት ችግሮች ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ እነዚህን አሳሳቢ ችግሮች መሠረት በማድረግ መፍትሔ መፈለግ የግድ ነው፡፡ መፍትሔው በመንገድ ደኅንነት የሚመለከታቸው ተቋማት በሰው ኃይል፣ በበቂ መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት አለባቸው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ቀላል የባቡር አገልግሎት ሥራ ሲጀምር በቀንና በምሽት ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ታሳቢ በማድረግ በፍጥነት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ቸልተኞችን በጥንካሬ በመቆጣጠር፣ ብቃት የሌላቸውን ከጐዳናው ላይ በአስቸኳይ በማውጣት፣ ሥነ ምግባር የሌላቸውን መንጃ ፈቃዳቸውን በመሰረዝ፣ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱን ፈር በማስያዝና ጠንካራና ከበድ ያለ ቁጥጥር ማድረግ መጀመር ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ጎዳናዎች የሞት ማምረቻ እየሆኑ መቀጠል ስለማይቻል፣ የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት ኃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡ አዝጋሚ የሆነው አሠራር በፍጥነት ይተካ፡፡ ከቁጥጥር ውጪ የሆነው የተሽከርካሪ አደጋም በቁጥጥር ሥር ይዋል!