Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናሰማያዊ ፓርቲ ኢሕአዴግንና ምርጫ ቦርድን ወቀሰ

ሰማያዊ ፓርቲ ኢሕአዴግንና ምርጫ ቦርድን ወቀሰ

ቀን:

400 ዕጩዎችን ማስመዝገቡን አስታወቀ

‹‹በፓርቲው የመወዳደሪያ ምልክት ሌላ ፓርቲ ለመጠቀም ሕጋዊ መሠረት የለውም›› ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

በ2007 ጠቅላላ ምርጫ ተወዳድሮ በማሸነፍ ሥልጣን ለመያዝ የሚያበቃውን ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የሚናገረው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢሕአዴግና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ሒደቱ ላይ ከፍተኛ ችግር እያደረሱበት መሆኑን አስታወቀ፡፡

- Advertisement -

ሰማያዊ ፓርቲ በቦርዱና በኢሕአዴግ ላይ ወቀሳ ያቀረበው የካቲት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን፣ በሁሉም ክልሎች ዕጩ ተወዳዳሪዎቹን ለማስመዝገብ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁለቱ አካላት በዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ላይ እንግልትና እንቅፋት እንደፈጠሩበት አሳውቋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ በገዢው ፓርቲ አባላትና በምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች ከፍተኛ እንግልትና እንቅፋት እየተፈጠረበት መሆኑን የጠቆሙት የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ በፓርቲው ዕጩዎች ላይ እየደረሱ ናቸው ያሉዋቸውን ችግሮች አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ዕጩ ተመዝጋቢዎች የተወለዱበት ዞን መሆኑ እየታወቀ፣ ‹‹ምስክር አምጡ›› በማለት እንዳይመዘገቡ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ ወረዳዎች ያሉ ምርጫ አስፈጻሚዎች ጽሕፈት ቤታቸውን ዘግተው በመጥፋታቸው፣ ዕጩ ተመዝጋቢዎች ሳይመዘገቡ ጊዜው እንዲያልፍ መደረጉንም አክለዋል፡፡

አንድ ዕጩ ተመዝጋቢ ቅሬታ እስካልቀረበበት ድረስ መመዝገብ የሚችል ቢሆንም፣ የምርጫ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ‹‹የሌላ ፓርቲ አባል ናችሁ፣ ከፓርቲያችሁ መልቀቂያ ካላመጣችሁ አትመዘገቡም፤›› ስላሏቸው፣ የፓርቲው አባላት ሳይመዘገቡ መቅረታቸውን አቶ ስለሺ ገልጸዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በጋሞጎፋ፣ በምሥራቅና በምዕራብ ጎጃም አካባቢዎች ዕጩ ተመዝጋቢዎችን የገዢው ፓርቲ ታጣቂዎች በማስፈራራት፣ በአካባቢ ሽማግሌዎችና የእምነት አባቶች በማስወገዝ ራሳቸውን ከዕጩነት እንዲያገሉ ተፅዕኖና ግፊት እንደተደረገባቸውም አብራርተዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር፣ በሲዳማና በከንባታ ዞኖች የፓርቲው ዕጩዎች በታጣቂዎች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው የጠቆሙት አቶ ስለሺ፣ በደቡብ ኦሞ ዞን ሁሉንም ነገር አሟልተው የተመዘገቡ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቁጥር ደ/ቁ – አ573/ፖአ/ጠ470 የካቲት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ለደቡብ ክልል ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት በተጻፈ ደብዳቤ፣ 18 የክልል ምክር ቤትና ስድስት የተወካዮች ምክር ቤት በድምሩ 24 ዕጩዎች እንዲሰረዙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ምርጫ ቦርድና ገዢው ፓርቲ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነፃና ፍትሐዊ በሆነ የምርጫ ሜዳ እንዳይሳተፉ በማድረግ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት የሥልጣን ዘመን እንዲራዘም እያደረጉ መሆናቸውን ምክትል ሊቀመንበሩ አክለዋል፡፡

የምርጫ አዋጁንና ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት በማድረግ ሰማያዊ ፓርቲ በምርጫ ሒደት ዙሪያ፣ ዕጩዎች እንዴት እንደሚመለመሉ፣ የታዛቢዎች ምርጫን፣ የምርጫ ቅስቀሳ አጠቃቀምን በሚመለከት የተለያዩ መሥፈርቶችን በማዘጋጀት በልዩ ጥንቃቄ ያቀረባቸው ዕጩዎች መሰረዛቸው፣ ከወዲሁ የምርጫው ሒደት ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያመላክት ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችሉት 400 ዕጩዎች ማቅረቡ ለኢሕአዴግ ሥጋት ስለሆነበት፣ በተለያዩ ምክንያቶች ዕጩዎችን እየቀናነሱ ከውድድሩ ውጭ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት መሆኑንም አቶ ስለሺ ገልጸዋል፡፡

ኢሕአዴግና ሌሎች ፓርቲዎች ምን ያህል ዕጩ እንዳስመዘገቡ ቦርዱ በመገናኛ ብዙኃን እየገለጸ ቢሆንም፣ ሰማያዊ ፓርቲ ምን ያህል ዕጩዎችን እንዳስመዘገበ አለመናገሩ አካሄዱ ችግር እንዳለበት አመልካች መሆኑን የገለጹት አቶ ስለሺ፣ ‹‹ምን ያህል ዕጩዎቻችንን እንደተቀበሉና እንዳልተቀበሉ እስካሁን ምንም መረጃ የለንም፤›› ብለዋል፡፡ የተሰረዙትን ዕጩዎች በሚመለከት አጥጋቢ መልስ ባይገኝም፣ በመመርያው መሠረት በአምስት ቀናት ውስጥ አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ሆኖ ፓርቲው ለመንግሥትነት የሚያበቁት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በመላው የአገሪቱ ክፍሎች ማስመዝገቡን ሕዝብ ሊያውቅላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ያቀረበውን ወቀሳ በሚመለከት ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለደቡብ ክልል ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ መጻፉን አረጋግጧል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቦርዱ የማያውቀው የዘጠኝ ፓርቲዎች ‹‹ትብብር›› የሚባለው አካል መሆኑን ገልጾ፣ የደቡብ ኦሞ ሕዝቦች ኅብረት ፓርቲ ለቦርዱ ደብዳቤ በመጻፉ ነው፡፡ ፓርቲው ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹ትብብሩ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት አባሎቼ በሰማያዊ ፓርቲ የመወዳደሪያ ምልክት እንዲመዘገቡ አድርጌያለሁ፤›› በማለቱ ምክንያት፣ ቦርዱ ለክልሉ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ መጻፉን የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ አቶ ወንድሙ ጎላ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ሕዝቦች ኅብረት ፓርቲ የራሱን መወዳደሪያ ምልክት ከወሰደ በኋላ በራሱ ምልክት ዕጩዎቹን ማስመዝገብ ሲችል፣ የሰማያዊ ፓርቲን መወዳደሪያ ምልክት ተጠቅሞ ዕጮዎቹን የሚያስመዘግብበት ሕጋዊ መሠረት ስለሌለው፣ የደቡብ ክልል ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት አጣርቶ እንዲልክ ደብዳቤ መጻፉን አቶ ወንድሙ አስረድተዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ተወዳዳሪ ዕጩዎች ችግር እየገጠማቸው ስለመሆኑ የተጠየቁት አቶ ወንድሙ፣ ‹‹እዚህ ሆኖ እንዲህ ሆንኩና ተደረግኩ ሳይሆን፣ በአካባቢው ላለው የፍትሕ አካል አጣርተው በማቅረብ በሕግ መጠየቅ ይችላሉ፡፡ ለቦርዱም ቢያሳውቁ ይከታተለዋል፤›› ብለዋል፡፡ የዕጩዎችን ብዛት በሚመለከት ተጠቋሚ ዕጩዎች የሚመዘገቡበት ቅጽ (03) ተጣርቶና በዕጩ ማሳወቂያ ቅጽ (04) የተጣራ ዕጩ ሳይደርስ ቦርዱ እንደማይገልጽ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ቦርዱ ተጣርቶ እንደደረሰው ይፋ እንደሚያደርግ አቶ ወንድሙ አክለዋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...