- በቦታ መረጣው ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይወስናል
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ትልቁ የአገር ኩራት ፕሮጀክት እንደሚሆን የተነገረለት፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ሊገነባ የታቀደው አዲሱ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እስከ 50 ቢሊዮን ብር እንደሚወጣበት ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ለመገናኛ ብዙኃን ባለፈው ዓርብ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫና ጉበኝት ላይ ማብራሪያ የሰጡት፣ የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ፕሮጀክትና አዲስ የሚገነባው ኤርፖርት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ኮማንደር ፀጋዬ ቃለአብ፣ እንደተናገሩት፣ አዲሱ ኤርፖርት ከ40 እስከ 50 ቢሊዮን ብር ወጪ ሊያስወጣ ይችላል፡፡ ኤርፖርቱ ከመዲናይቱ ወጣ ብሎ እንደሚገነባ የተናገሩት አቶ ፀጋዬ፣ ጥናቱ ገና በመሠራት ላይ ያለ በመሆኑ የፕሮጀክቱን ወጪና ዝርዝር ጉዳዮች መግለጽ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ከ40 እስከ 50 ቢሊዮን ብር ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችልና የአሥር ዓመት ፕሮጀክት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ ኤርፖርት አራት የአውሮፕላን ማኮብኮቢያዎች እንዲኖሩትና በዓመት እስከ 100 ሚሊዮን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ኤርፖርቱ 12 ኪሎ ሜትር ወርድና ርዝመት በአጠቃላይ 144 ካሬ ኪሎ ሜትር መሬት ላይ የሚያርፍ እንዲሆን የታሰበ ቢሆንም፣ ገና ከውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰ ተገልጿል፡፡ ኤርፖርቱን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኝ የፍጥነት መንገድ ለመገንባት የታሰበ ሲሆን፣ ከኤርፖርቱ ጋር ተያይዞ ራሱን የቻለ ከተማ (ኤርፖርት ሲቲ) ይገነባል፡፡ ኤርፖርቱ አገሪቱን ለመጪው 100 ዓመት የሚያገለግል ይሆናል ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በራሱ ባካሄደው ጥናት ዱከም፣ ሞጆና ተጂ ከተሞች አካባቢ የሚገኙ ሦስት ቦታዎች ለኤርፖርቱ ግንባታ በዕጩነት መርጦ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የቦታው መረጣ ጥናቱ በራሱ አቅም ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ተቀጥሯል፡፡
ጨረታውን አሸንፎ ጥናቱን የሚሠራው ‹‹ኤዲፒአይ›› የተሰኘው የፈረንሳይ ኩባንያ፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የመረጣቸውን ሦስት ቦታዎች በመሉ ውድቅ አድርጎ በሳተላይት ቴክኖሎጂ በመታገዝ ስምንት አዲስ ቦታዎች መርጧል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሦስት ተቀንሰው አምስት ቦታዎች ለውሳኔ ለመንግሥት ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የተመረጡትን አምስት ቦታዎች ለትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በመጪው ሳምንት እንደሚያቀርብ፣ አቶ ወርቅነህ ምክረ ሐሳቡን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ እንደሚያቀርቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዕጩነት የተያዙትን ቦታዎች ከመናገር የተቆጠቡት ኮማንደር ፀጋዬ፣ የኤርፖርቱ ግንባታ የሚካሄድበት ቦታ የመጨረሻ ውሳኔ በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚታወቅና ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ግንባታው የሚካሄድበት ሥፍራ ሰፊፋ የእርሻ ቦታዎች የሚገኙበት ሊሆን እንደሚችል፣ ከ10,000 በላይ ነዋሪዎችን መልሶ ማስፈር ሊያስፈልግ እንደሚችል ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹ይህ ፕሮጀክት ከህዳሴው ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፉ የአገር ፕሮጀክት ይሆናል፡፡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያኮራ፣ ኢትዮጵያን ወደፊት አንድ ትልቅ ዕርምጃ የሚያራምድና መጪውን ትውልድ የሚያገለግል ይሆናል፤›› ብለዋል ኮማንደር ፀጋዬ፡፡
በተያያዘም የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ በመፋጠን ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት አስታውቋል፡፡ በ4.5 ቢሊየን ብር ወጪ የሚካሄደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት የመንገደኞች ተርሚናሉን የማስተናገድ አቅም በዓመት ከሰባት ሚሊዮን ወደ 22 ሚሊዮን ያሳድጋል፡፡ አሁን ያለው ተርሚናል 48,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ አዲስ የሚገነባው ተርሚናል 72,000 ካሬ ሜትር ስፋት ይኖረዋል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ አዲስ የመንገደኞች ተርሚናል፣ ቪአይፒና ከፍተኛ ባለሀብቶች ከፍለው የሚስተናገዱበት ተርሚናል፣ ባለሦስት ፎቅ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ ግንባታ ሥራ አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡
ይኼን ፕሮጀክት በአማካሪነት የሚሠራው ኤዲፒአይ ሲሆን፣ የንድፍ ሥራውን የሠራው ሲፒጂ የተሰኘ ታዋቂ የሲንጋፖር ኩባንያ ነው፡፡ ግንባታው ሦስት ዓመት እንደሚፈጅ ተገልጿል፡፡
በተያያዘም በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ሦስት ፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ እንደሆኑ ለመመልከት ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶ ድርጅት ኤርፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ መኰንን በሰጡት ማብራሪያ፣ በመካሄድ ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች የደኅንነት ካሜራ ማስፋፊያ ሥራ፣ የሻንጣ ማስተላለፊያ ማስፋፊያ ሥራና የፓርኪንግ አውቶሜሽን ሥራ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ አሚራን ኮሙዩኒኬሽን የተሰኘ የእስራኤል ኩባንያ የደኅንነት ካሜራ ማስፋፊያ ሥራ ጨረታውን አሽንፎ ዘመናዊ የሆኑ መሣሪያዎችን በመግጠም ላይ መሆኑን፣ የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ አንድ ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ አቶ ተፈራ ተናግረዋል፡፡
የሻንጣ ማስተላለፊያ መሣሪያዎች ግዢና ተከላ ሥራ ደያፍኩ ሎጋን የተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ በ2.8 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ 20 የመንገደኞች መፈተሻ መሣሪያዎች፣ የሻንጣ መፈተሻ መሣሪያና አንድ የፈንጂ መመርመሪያ ማሽን በ3.6 ሚሊዮን ዩሮ ተገዝተው አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ የእነዚህ መሣሪያዎች ግዢ የኤርፖርቱን ደኅንነት ጥበቃ እንደሚያጠናክረው አቶ ተፈራ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የኤርፖርቱን መኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ አገልግሎት ዘመናዊ ለማድረግ ሥራው ዩስትሪት ፓርኪንግ ለተባለ ተቀማጭነቱ አሜሪካ ለሆነ ኩባንያ ተሰጥቷል፡፡ ‹‹በሰው ይሠራ የነበረው የፓርኪንግ አገልግሎት ለስርቆትና ለወንጀል የተጋለጠ ነበር፤›› ያሉት አቶ ተፈራ፣ ከደንበኞች ብዙ ቅሬታ እንደሚቀርብበት ገልጸዋል፡፡ በሦስት ሚሊየን ብር ወጪ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ተገዝተው እንደሚተከሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያው መሣሪያዎቹን ከተከለ በኋላ ፓርኪንጉን ለሦስት ዓመታት ያስተዳድራል፡፡ ገቢውን የሚሰበስበው ኩባንያው ሲሆን፣ ትርፉን ለሁለት ይካፈላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከትርፉ 70 በመቶ ሲወስድ ኩባንያው 30 በመቶ ይወስዳል፡፡