Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለውጭ ኩባንያ ለመስጠት ታቅዷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ – ሰበታ – ጂቡቲ የባቡር መስመር በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቆ ዝግጁ ሲሆን፣ የትራንስፖርትና የጥገና አገልግሎት የሚሰጥ ልምድ ያለው የውጭ ኩባንያ ለመቅጠር መታሰቡን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በባቡር ትራንስፖርት ትልቁና ከባድ የሆነው የመሠረተ ልማት ዝርጋታው ሳይሆን የአገልግሎትና የጥገና ሥራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የአዲስ አበባ – ሰበታ – ጂቡቲ የባቡር መስመር በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር እንደሚጠናቀቅ፣ ከዚህም በኋላ የትራንስፖርትና የጥገና አገልግሎቱን የሚያከናውን ኩባንያ ለመቅጠር መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

አፍሪካ ውስጥ የባቡር ትራንስፖርት ውጤታማ መሆን ያልቻለው በአገልግሎትና በጥገና በቂ አቅም ባለመኖሩ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያ ይህ ችግር እንዲደገም አይፈቀድም ብለዋል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርትና የጥገና አገልግሎትን ለማካሄድ ሸንዘን ሜትሮ ግሩፕ የተባለው ኩባንያ ከቻይና ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የፈጠረው ጥምረት፣ ለአምስት ዓመት በኮንትራት እንደተቀጠረ ሁሉ በአዲስ አበባ ጂቡቲ መስመር ላይም ኩባንያ ለመቅጠር ከጂቡቲ መንግሥት ጋር እየተመከረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሚቀጠረው ኩባንያ አገልግሎቱን የሚሰጠው ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ የመጨረሻ ጫፍ በመሆኑ፣ ከጂቡቲ መንግሥት ጋር መነጋገርና አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ የግድ እንደሚል ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ይህንንና ሌሎች የባቡሩ መስመሩን በተመለከተ በሁለቱ አገሮች የተቋቋመ ኮሚሽን መኖሩን፣ የኢትዮጵያው ቡድን የሚመራው በእርሳቸው መሆኑንና በየሁለቱ ወሩ ከጂቡቲ አቻው ጋር ተገናኝቶ እንደሚመክርም አክለዋል፡፡

በእስካሁኑ ሒደት የኢትዮጵያና የጂቡቲ መንግሥታት የባቡር ትራንስፖርት በሚካሄድበት መስመር የጋራ ድንበር ላይ የጉምሩክና የደኅንነት ቢሮዎቻቸውን በአንድ ሕንፃ ላይ በማድረግ፣ በአንድ ዶክመንት ሁሉንም አገልግሎቶች ለማከናወን መስማማታቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የባቡር መስመር ተበድሮ እየገነባ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ አገልግሎቱ ሲጀመር የሚያገኘው የአገልግሎት ክፍያ የግንባታ ብድሩን በአግባቡ ለመመለስ ያስችለዋል ብለዋል፡፡

እንደ ዕቅዱ ከሆነ በአንድ ባቡር በአንድ ትራንስፖርት ዘጠና ከባድ ተሽከርካሪዎች የሚያነሱትን ወደብ የሚገኝ ኮንቴነር ወይም ንብረት ማስገባት ይቻላል፡፡ ይህም አገሪቱ ወደብ ለሚቀመጡ ንብረቶች በምታወጣው የዴሜሬጅ ክፍያ፣ የነዳጅና የትራንስፖርት ዋጋዎችን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ የሚያስችል ትልቅ ፕሮጀክት ያደርገዋል ተብሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች