Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሲያኮበኩብ አደጋ በደረሰበት የኢትዮጵያ አውሮፕላን ላይ ጋና የቅድመ ምርመራ ሪፖርት ይፋ አደረገች

ሲያኮበኩብ አደጋ በደረሰበት የኢትዮጵያ አውሮፕላን ላይ ጋና የቅድመ ምርመራ ሪፖርት ይፋ አደረገች

ቀን:

ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ሪፖርቱን እገመግማለሁ ብሏል

በጋና ኮቶካ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ካረፈ በኋላ ሲንደረደር ባጋጠመው መጥፎ የአየር ፀባይ ምክንያት መስመሩን ስቶ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በሚመለከት፣ ጋና የቅደመ ምርመራ ሪፖርት ይፋ አደረገች፡፡ ሪፖርቱ የደረሰው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በምርመራው ሒደት ተሳታፊ እንደነበር ገልጾ፣ ይፋ የተደረገውን ሪፖርት እንደሚመረምር አስታውቋል፡፡

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737-400 ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን፣ ከቶጎ ወደ ጋና በማምራት ቅዳሜ ጥር 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ማለዳ ላይ በማረፍ ላይ እያለ ነበር ጉዳት የደረሰበት፡፡ በወቅቱ በሦስት የበረራ ሠራተኞች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው በወታደራዊ ሆስፒታል ሕክምና ማግኘታቸውም ይታወሳል፡፡

የአየር መንገዱ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ በማጣራት ላይ የነበረው ኮሚቴ፣ በቅደመ ምርመራ ሪፖርቱ አውሮፕላኑ ለደረሰበት ጉዳት መጥፎ የአየር ፀባይ አስተዋጽኦ አድርጓል ከማለት ውጪ የገለጸው ነገር የለም፡፡ ባለ16 ገጹ ሪፖርት ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እንደደረሰውና በምርመራው ሒደትም ተሳታፊ እንደነበር ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው አረጋግጠዋል፡፡

ዋናው የምርመራ ሪፖርት ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ የአጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጋናዊው ካፒቴን ሳሙኤል ቶምሰን መግለጻቸውን የጋና መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

ኮሎኔል ወሰንየለህ እንደገለጹት፣ የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ የተደረገውን ቅደመ ምርመራ ሪፖርት በመንተራስ ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ሆኖም የችግሩ መንስዔ በወቅቱ የነበረው ተለዋዋጭ የአየር ፀባይ ሊሆን እንደሚችል እንደሚገመት፣ ሆኖም ግን ይፋ የተደረገውን ሪፖርት ባለሥልጣኑ ከተመለከተው በኋላ አስተያየት እንደሚሰጥበት ገልጸዋል፡፡

የበረራ ቁጥሩ “ETAQV-KP-4030” የሆነው ይህ አውሮፕላን ለማረፍ ሲሞክር መንገዱን በመሳቱ በቀኝ ክንፉ፣ በታችኛውና በፊተኛው ክፍሎቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ለጋና ትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዚፋ አቲቮር የቀረበው ጊዜያዊ ሪፖርት ካካተታቸው ጥሬ ግኝቶች መካከል የአውሮፕላኑ ይዞታ፣ የተመረተበት ጊዜ፣ አደጋው የደረሰበት ጊዜና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎች ተተንትነው እንደሚጠኑ መገለጹና ዋናው ሪፖርት ይፋ ከመደረጉ በፊት የወጣውን የግኝት ውጤት መንግሥታቸው በጥንቃቄ እንደሚመለከተው አስታውቀዋል፡፡

አውሮፕላኑ አደጋ ባጋጠመው ወቅት ጎማዎቹ በመተንፈሳቸው ምክንያት መንገዱን ስቶ መውጣቱና በወቅቱ የነበረው መጥፎ የአየር ፀባይ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ቢገለጽም፣ ትክክለኛው የአደጋው መንስዔ ገና በመጣራት ላይ መሆኑን የጋናም ሆኑ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...