ባለሥልጣኑ ለመጀመርያ ጊዜ ተጨማሪ በጀት ሳይጠይቅ ቀርቷል
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ለባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች የ2008 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ትልቁ ባለበጀት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሆኗል፡፡ ሚኒስቴሩ በመንግሥት ግምጃ ቤት ገንዘብ ለሚተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች የበጀት ጣሪያ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የበጀት ጣሪያቸውን በማሳወቅ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ምንጮች እንደገለጹት ገንዘብ ሚኒስቴር ለመሥሪያ ቤቶች ከሰጠው በጀት ጣሪያ ትልቁ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ነው፡፡ የሚመራው ኃላፊ ያላገኘው የኢትዮጵያ ባለሥልጣን፣ ለሚቀጥለው ዓመት ከመንግሥት ግምጃ ቤት 24 ቢሊዮን ብር ተፈቅዶለታል፡፡ ባለሥልጣኑ በ2007 ዓ.ም. በጀት ዓመት 20 ቢሊዮን ብር ከመንግሥት ግምጃ ቤት፣ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ደግሞ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ የተመደበለት በመሆኑ በአጠቃላይ 29 ቢሊዮን ብር ተበጅቶለታል፡፡ ይህ ገንዘብ ከፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ትልቁ ያደርገዋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመትም እንዲሁ ከመንግሥት ግምጃ ቤት የተበጀተለት ገንዘብ ከ2007 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር በአራት ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው በመሆኑ፣ አሁንም የፌዴራል መንግሥት ትልቁ የበጀት ተጠቃሚ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርገዋል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
መንገዶች ባለሥልጣን የሚመደብለትን በጀት ለዘጠኝ ፕሮግራሞች እንደሚያውለው ታውቋል፡፡ ከዘጠኙ ፕሮግራሞች ውስጥ ዋና ዋና መንገዶች ማጠናከርና ማሻሻል፣ አገናኝ መንገዶችን ማሻሻል፣ የአገናኝ መንገዶችን ግንባታና የመንገዶችና ድልድዮች ግንባታ ይገኙበታል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ምንጮች እንደገለጹት፣ መንገዶች ባለሥልጣን ባልተለመደ ሁኔታ ለመጀመርያ ጊዜ በዚህ ዓመት ተጨማሪ በጀት ጥያቄ አላቀረበም፡፡ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አሕመድ መንገዶች ባለሥልጣን የተጨማሪ በጀት ጥያቄ እንዳያቀርብ በወተወቱባቸው ያለፉት ሁለት ዓመታት እንኳ ባለሥልጣኑ ተጨማሪ በጀት መጠየቁን ያስታወሱት ምንጮች፣ ከመስከረም 27 ቀን 1996 ዓ.ም. ጀምሮ ለ11 ዓመታት ሲመሩ የቆዩት አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፊርማ ከቦታቸው ከተነሱ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ባለሥልጣኑ ተጨማሪ በጀት ሳይጠይቅ ቀርቷል ብለዋል፡፡ ባለፉት አራት ወራት በተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር እየተመራ የሚገኘው መንገዶች ባለሥልጣን ተጨማሪ በጀት ሳያቀርብ የቀረበት ምክንያት በግልጽ ማወቅ አልተቻለም፡፡ ነገር ግን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ኃላፊ አቶ ሐጂ ኢብሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚኒስቴሩ ከላይን በጀት አሠራር ወጥቶ የፕሮግራም በጀት አሠራር እየተከተለ በመሆኑና በፕሮግራም በጀት አሠራር ደግሞ ተጨማሪ በጀት የማይፈቀድ በመሆኑ የመጣ ውሳኔ ነው፡፡
ምንጮች እንደሚጠቁሙት ግን ገንዘብ ሚኒስቴር ከላይን በጀት ወጥቶ ፕሮግራም በጀት መጠቀም ከጀመረ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ስለዚህ በአቶ ሐጂ የቀረበው ምክንያት አሳማኝ አይደለም ይላሉ፡፡ አቶ ዛይድ ከተነሱ በኋላ ባለሥልጣኑ ውስጥ ብዥታ በመፈጠሩና መሪ ስለሌለው ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠትና በጀት ለመጠየቅ ባለሥልጣኑ እንደተቸገረ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አቶ ዛይድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምሥጋና አቅርበው፣ ጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲነሱ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
በአቶ ዛይድ መነሳት በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር የሚናገሩት ምንጮች፣ ከአቶ ዛይድ በኋላ የተለያዩ ግለሰቦች የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ይሾማሉ እየተባለ ስማቸው ቢነሳም፣ እስካሁን ውሳኔ እንዳልተሰጠ አመልክተዋል፡፡