በምርጫ ዋዜማ ከሚስተዋሉ ክስተቶች አንደኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ነው፡፡ የምርጫ 2007 ቅስቀሳ የካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ይጀመራል፡፡ በዚህ ቅስቀሳ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መሬት ላይ ከማይታዩ አሰልቺና ግራ የሚያጋቡ ንትርኮች ወጥተው፣ በነጠሩ የፖሊሲ አማራጮች ላይ ነው መከራከር ያለባቸው፡፡ ከዛፍ ላይ ወርደው መሬት ላይ ባለውና ለሕዝቡ በቀረበው ጉዳይ ላይ ነው ቅስቀሳቸውንም ሆነ ክርክራቸውን መመሥረት ያለባቸው፡፡
ሁሌም ምርጫ በመጣ ቁጥር የቅስቀሳው አካል በሆነው የቴሌቪዥን ክርክር የፌዴራሊዝም ጥያቄ ይነሳል፡፡ ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያ ወደ አኃዳዊ ሥርዓት አለመመለሷ እየታወቀና ሕዝቡም እየኖረበት በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜ ማባከን ያሳዝናል፡፡ ለኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ያስፈልጋታል? ወይስ አያስፈልጋትም? እየተባለ የምርጫ ክርክሩን ከማሳከር ይልቅ፣ የፌዴራል ሥርዓቱ በምን ዓይነት አካሄድ ቢመራ ነው ዘላቂና አስተማማኝ የሚሆነው? የሚለው ተመራጭ ይሆናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሕዝቡ ከ20 ዓመታት በላይ እየኖረበት ከመሆኑም በላይ፣ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ፌዴራሊዝም አማራጭ የለውም፡፡ ነገር ግን ፌዴራሊዝምን በቅጡ ጠንቅቀን ተረድተነዋል? በትክክል ገብቶንስ ተርጉመነዋል? ነው መባል ያለበት፡፡
ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ ወንዝ የማያሻግሩ ጭቅጭቆች በተደጋጋሚ ተሰምተዋል፡፡ ላለፉት ሃያ ዓመታት በሥራ ላይ የዋለው ሕገ መንግሥት ሕዝብ የሚተዳደርበት ከመሆኑም በላይ፣ በተገቢው መንገድ ከተከበረ ብዙ ርቀት የሚያስኬድ ነው፡፡ ጥያቄ የሚነሳባቸው አንቀጾች ቢኖሩም እንኳ በጊዜ ሒደት በመቀራረብና በመነጋገር ለአገር ዘለቄታዊ ጥቅም ሲባል መፍትሔ እንዴት እንደሚያገኙ መነጋገሩ ጠቃሚ ነው፡፡ ይልቁንም ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት ዴሞክራሲያዊነቱ እንዴት ተጠናክሮ ይቀጥል ማለት የተሻለ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ ከመዝመት ይልቅ ሕገ መንግሥቱን ማክበር ይቅደም ነው መባል ያለበት፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ በውስጡ የያዛቸው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠቅሙ በርካታ ጉዳዮች ስላሉት ነው፡፡
በመሬት ላይ ለበርካታ ጊዜያት ሙግቶች ተሰምተዋል፡፡ መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው የሚለው የሕገ መንግሥቱ ውሳኔ ነው፡፡ መሬት ይሸጥ ይለወጥ፣ ወይም አይሸጥም አይለወጥም የሚለው ክርክር ከዚህ ዘመን ጋር አይሄድም፡፡ ባለፉት በርካታ ዓመታት አርሶ አደሩ ለሚያርስበት መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ይዞ እያረሰ ሲሆን፣ የከተማ ነዋሪው ደግሞ በሊዝ ሥርዓት ይተዳደራል ተብሏል፡፡ በሊዝ ሥርዓቱ የሕዝብ ሀብት በሆነው መሬት ላይ መፍትሔ የሚኖረው ውይይት ይደረግበት የሚለው ሐሳብ ይቅደም፡፡ ስለዚህ በመሬት ጉዳይ ላይ የሚኖረው ሙግት በሊዝም ሆነ በመሬት ይዞታ ሥርዓት ውስጥ ለሕገወጥነት በር የሚከፍቱ ተግባራት ይወገዱ የሚለው ነው፡፡ መሬትን በወረራ መያዝና በሕገወጥ መንገድ መጠቀም እንዲገታ ነው ሙግቱ መካሄድ ያለበት፡፡ መሬት ላይ ያልወረደና ለመራጩ ሕዝብ በግልጽ ቋንቋ የማይገባ የምርጫ ክርክር ከአሰልቺነቱም በላይ ውጤት የለውም፡፡ ክርክሩ ከሕዝቡ የየዕለት ሕይወትና ከዘለቄታው ጥቅም ጋር ይቆራኝ፡፡
ሌላው የሰብዓዊ መብት ጥበቃን በተመለከተ የሚደረገው ክርክር ነው፡፡ አንደኛው ወገን ከሚያራምደው ርዕዮተ ዓለም አንፃር የግለሰቦች መብት መቅደም አለበት ሲል፣ ሌላኛው ደግሞ ስለቡድን መብት ይሰብካል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች ስለሰብዓዊ መብት መከበር ያገባናል ካሉ፣ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በቡድን እየተባለ ጭቅጭቅና አተካራ ውስጥ እየገቡ መራጩን ሕዝብ ከማወዛገብ ቢታቀቡ ይመረጣል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሰፈሩት የሰብዓዊ መብቶች አንቀጾች ተግባራዊ እንዲደረጉ ነው መወትወት ያለባቸው፡፡ የግለሰብና የቡድን መብት እየተባሉ መሬት ያልረገጡ ንድፈ ሐሳቦች የትም አያደርሱም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የተቀበላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ሁለንተናዊ ድንጋጌዎች ብዙ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ መብቶች በርካታ የሚዳስሷቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ መሠረታዊው ጭብጥ በዚህ ላይ ነው ማጠንጠን ያለበት፡፡
ላለፉት 24 ዓመታት ገደማ መሬት ላይ ባልረገጡ፣ ነገር ግን እጅግ በጣም አታካችና አሰልቺ በሆኑ ክርክሮች ውስጥ የምሁራኑ ተሳትፎም ተመሳሳይ ነው፡፡ በፌዴራሊዝም፣ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ በመሬት ይዞታ፣ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የበሰሉ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ደርዝ ያለው ውይይት እንዲኖር ከመርዳት ይልቅ፣ ጥያቄዎቹን በተደጋጋሚ እንደ አዲስ ያቀርቡዋቸዋል፡፡ የበሰሉና መሬት የረገጡ የፖሊሲ ሐሳቦችን ከማንሳት ይልቅ ጥያቄ ላይ ያተኩራሉ፡፡ ይህ ዘመን ጥያቄዎችን ከመደርደር ይልቅ መፍትሔዎች ላይ መረባረብ ነው የሚፈልገው፡፡ ከሕዝቡ የአኗኗር ዘይቤና መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ጉድለቶችን አይቶ፣ ለመፍትሔ ጠቃሚ ግብዓቶችን ማመንጨት የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በጥያቄ የተሞሉ ሐሳቦች መፍትሔ አልባ ከሆኑ ክርክሩም ሆነ ጭቅጭቁ ሚዛን አይደፋም፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳቸውን ሲያደርጉ ትኩረት ማድረግ ያለባቸው በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚካሄዱ ክርክሮች የተሠሩትን ወይም እየተሠሩ ያሉትን ከመተቸት በዘለለ ቀለል ባለ አቀራረብ የተሻለ የሚባለውን ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ የሠራው በሙሉ እንዲወደስለት ሲፈልግ፣ የነበሩበትን ድክመቶች ያለምንም ይሉኝታ ለሕዝቡ መንገር አለበት፡፡ ልማት ላይ ስታተኩር ዴሞክራሲውን ትተኸዋል ሲባል፣ ለዴሞክራሲውም እንዴት መትጋት እንደሚገባው አብጠርጥሮ ማስረዳት አለበት፡፡ ተቃዋሚዎችም የገዥው ፓርቲ ድክመት ላይ ብቻ ተንጠላጥለው የሕዝቡን ይሁንታ ማግኘት ስለማይችሉ፣ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ተግባራዊ መሆን የሚችሉ አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቦች ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ‹‹ከሕዝቡ ጋር ሆነን የሚበጀንን ይዘን እንመጣለን›› የሚባለው ቀልድ አይሠራም፡፡ በተለይ ለዓመታት የዘለቁት ፋይዳ ቢስ ክርክሮች ወደ ጎን ተገፍተው፣ ለሕዝቡም ሆነ ለአገሪቱ የሚበጁ የተሻሉ የፖሊሲ አማራጮች ይንፀባረቁ፡፡ ግትርነት፣ ሸፍጥ፣ አሉባልታና የራስን ድክመት በሌላው ላይ ማላከክ ይብቃ፡፡ ጊዜው እንዲህ ዓይነቶቹ አቀራረቦች አይመጥኑትም፡፡ በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች የሚደምቁት እጅግ በሚያጓጉና አዕምሮን ወጥረው በሚይዙ የፖሊሲ ክርክሮች ነው፡፡ ውጤቱም የእነዚህ ክርክሮች ነፀብራቅ ነው፡፡
በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ለመራጩ ሕዝብ ቅርብ መሆን አለበት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ይዘው ሲቀርቡ ሕዝቡን ያማከሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ሕዝብ በቀላሉ የሚረዳቸውና ከዕለት ተዕለት ሕይወቱ ጋር የተቆራኙ እንዲሆኑ መጣር ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ውጪ አንዱ ሌላኛውን ጠልፎ ለመጣል በሚደረግ መውተርተር የጥላቻ መገለጫ የሆኑ ውግዘቶችና ስድቦች ውስጥ ሲገቡ አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቦች ይመክናሉ፡፡ ኢኮኖሚው እንዴት ቢመራ ነው የበለጠ ዕድገት የሚመዘገበው? ከዚያም ከድህነት የሚወጣው? የፖለቲካው እንቅስቃሴ እንዴት ቢዘወር ነው ምኅዳሩ ሰፍቶ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዕውን የሚሆነው? ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩትና የሕግ የበላይነት የሚኖረው ምን ቢደረግ ነው? መልካም አስተዳደር የሚሰፍነው ምን ዓይነት አሠራር ተግባራዊ ሲሆን ነው? ሙስናን ከሥሩ መንግሎ መጣል የሚቻለው እንዴት ቢደረግ ነው? ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚኖረው በምን መንገድ ነው? የዜጎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ እንዲኖር ምን መደረግ አለበት? ዘለቄታ ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው እንዴት ነው? ምርጫው ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት እንዲኖረው ምን መደረግ አለበት? ወዘተ የመሳሰሉት መሬት ወርደው በሚገባ መተንተን ይኖርባቸዋል፡፡ መሬት ያልወረዱ ንድፈ ሐሳባዊ ትንተናዎች ጠቀሜታ ስለሌላቸው፣ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዛፍ ላይ ይውረዱ!