በ2006 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ለሁለተኛ ጊዜ ማሻሻያ የተደረገበት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ለሦስተኛ ጊዜ ሊሻሻል መሆኑ ተሰማ፡፡
የንግድ ሚኒስቴር አዋጁን ለመተግበር በርካታ መሰናክሎች እየገጠሙት በመሆኑ፣ አዋጁን እንዲመረምር ያቋቋመው ኮሚቴ የአዋጁን ችግሮች ለይቶ ማውጣቱ ታውቋል፡፡ በዚህ መሠረትም አዋጁ እንዲሻሻል ሐሳብ ማቅረቡን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በርካታ ሰዎች የንግድ ስያሜ ይዘው ለማስመዝገብ ቢመጡም በተደጋጋሚ እየወደቀባቸው በመቸገራቸው የተፈጠረውን ቅሬታ ለማጣራት ባደረገው ሙከራ፣ ከንግድ ምልክትና ስያሜ ጋር በተያያዘ በርካታ የሚጣረሱና ለትርጉም ክፍት የሆኑ አንቀጾች እንዳሉበት የተቋቋመው ኮሚቴ ማረጋገጡን መረጃው ያመለክታል፡፡ በመሆኑም በቅርቡ የማሻሻያ ረቂቁ ተሠርቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ከዚያም ለተወካዮች ምክር ቤት የአሠራር ሒደቱን ተከትሎ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተባለው መሠረት ማሻሻያው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርብ ከሆነ፣ በተሻሻለ በዓመቱ በድጋሚ ለመሻሻል የቀረበ አዋጅ ያደርገዋል፡፡ አዋጁ በ2006 ዓ.ም. ለፓርላማ እንዲቀርብ የተደረገው ከዳግም ምዝገባ ጋር የተፈጠረውን ችግር ለማስተካከል ነበር፡፡
ይኸው አዋጅ በ2004 ዓ.ም. መጨረሻ ላይም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ማሻሻያ ተደርጐበት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ ማሻሻያ የተደረገበት ከፈቃድ ማደስ ጋር ተያይዞ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ከጉምሩክ አዋጁ ጋር ለማጣጣም ሲባል መሆኑን የአዋጁ ማብራሪያ ያመለክታል፡፡