Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሰማያዊ ፓርቲ ምልክት መወዳደር አለብኝ የሚለው ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ ጋር ተወዛገበ

በሰማያዊ ፓርቲ ምልክት መወዳደር አለብኝ የሚለው ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ ጋር ተወዛገበ

ቀን:

ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ለመዋሀድ የሚያስችለውን ቅድመ ስምምነት ማድረጉንና በአንድ የምርጫ ምልክት ለመወዳደር መወሰኑን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁን የገለጸው የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኦሕዴኅ)፣ ከቦርዱ ጋር መግባባት ባለመቻሉ ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡

ኦሕዴኅ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ መሥፈርቶችን አሟልቼ ካስገባሁ በኋላ ቦርዱ አፅድቆልኛል ቢልም፣ ምርጫ ቦርድ ግን የደረሰው ሪፖርት እንደሌለ በመግለጽ፣ ፓርቲው በወሰደው ሕጋዊ ሠርቲፊኬት ላይ ለውጥ ማድረጉን እንዳላፀደቀ አስታውቋል፡፡

የኦሕዴኅ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ በቀለ የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰማያዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በሰጡት መግለጫ፣ ፓርቲያቸው በሰማያዊ ፓርቲ ምልክት ለመወዳደር ወስኗል ብለዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ አባሎቼ በምርጫ እንዳይወዳደሩ ጫና እየተደረገባቸውና እየተሰረዙ ነው ለሚለው ወቀሳ፣ ምርጫ ቦርድ የታገዱት ግለሰቦች የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ሳይሆኑ የኦሕዴኅ አባላት ናቸው ማለቱን እንዴት ይታያል ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ  በሰጡበት ማብራሪያ ነው አቶ ግርማ ይህንን የተናገሩት፡፡

ኦሕዴኅ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት ማድረጉን የጠቆሙት አቶ ግርማ፣ በተለይ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር የተናጠል ስምምነት እንዳለውና የስምምነቱ አንዱ መንፈስ ደግሞ የዚህ ስምምነት ፈራሚዎች ለ2007 ጠቅላላ ምርጫ አባላትን በአንድ መወዳደሪያ ምልክት ማቅረብ እንደሆነ መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የአንዱ ፓርቲ አባልና አመራር በሌላው ፓርቲ ስምና ምልክት የሚወዳደርበትን ጉዳይ ማመቻቸትና ስምምነት ሲደረስም ተግባራዊ ለማድረግ፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር መስማማታቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ዕጩዎችን እንዴት ማቅረብ እንዳለብን ምርጫ ቦርድ አይወስንም፤›› ሲሉም ምርጫ ቦርድ የወሰደው የዕግድ ዕርምጃ ሕገወጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ወንድሙ ጎላ ግን፣ ‹‹አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ውህደት፣ ቅንጅትና ግንባር መፍጠር ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች በጠቅላላ ጉባዔ ፀድቀው ለቦርዱ ሲቀርቡና ቦርዱ ሲያፀድቀው ነው ተፈጻሚነት የሚኖራቸው፤›› በማለት ለሪፖርተር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በሰማያዊ ፓርቲ በኩል እየቀረበ ያለው ውንጀላ ግን ሕጉን መሠረት ያላደረገና ተገቢዎቹን የሕግ መሥፈርቶች ያላሟላ ነው፤›› በማለት የሰማያዊ ፓርቲን ክስ አጣጥለውታል፡፡

‹‹የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት የተባለው ድርጅት በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ምልክት ወስዷል፡፡ በመሆኑም ውህደት፣ ግንባር አልያም ቅንጅት መፈጠሩን ቦርዱ ሳያውቀው የፓርቲው ዕጩዎች በሌላ ፓርቲ ምልክት ተመዝገበዋል ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ሕገወጥ ነው፤›› በማለት የተፈጠረውን ውዝግብ አብራርተዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ከኦሕዴኅ ጋር ስለተደረሰው ስምምነት ምንም ነገር ያልተናገሩ ሲሆን፣ ‹‹በተናጠል ሌላ ፓርቲ ውስጥ የነበረ ሰው ያኛውን ፓርቲ ትቶ ሰማያዊን ወክሎ የመወዳደር መብት አለው፤›› በማለት ይሞግታሉ፡፡

የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ግን፣ ማንኛውም ግለሰብ በፈለገው ፓርቲ ውስጥ የመወዳደር መብት እንዳለው ገልጸው፣ ‹‹ነገር ግን እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ የሚከቱ መሆን የለባቸውም፤›› ይላሉ፡፡

ለዚህም እንደ መከራከሪያነት የሚያቀርቡት ደግሞ፣ ‹‹አሁን የታገዱት የኦሕዴኅ አባላት ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ በኦሕዴኅ የተመዘገቡ አባላት ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈም የኦሕዴኅ ፕሬዚዳንት እንኳን ለመወዳደር የተመዘገቡት አዲስ አበባ ውስጥ ነው፤›› በማለት ዕገዳው የመነጨው አባላቱ ከፓርቲው ባለመልቀቃቸው እንጂ፣ ሌላ የተለየ ዓላማም ሆነ ዕቅድ ስላለ አይደለም በማለት መልሰዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የዘጠኝ ፓርቲዎች ትብብር የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በተመረጡ 15 የአገሪቱ ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ለማድረግ ይዞት የነበረውን ዕቅድ ለአንድ ሳምንት ወደፊት በመግፋት፣ የካቲት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቁን በዕለቱ በተሰጠው መግለጫ ይፋ ተደርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...