Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የአገር መከላከያ ሠራዊት ተዋጽኦ እንደ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የሚከፋፈል አይደለም›› ...

‹‹የአገር መከላከያ ሠራዊት ተዋጽኦ እንደ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የሚከፋፈል አይደለም›› ጄኔራል ሳሞራ የኑስ

ቀን:

የአገር መከላከያ ሠራዊት ብሔራዊ ተዋጽኦ የጠበቀና የተመጣጠነ መሆን ያለበት ቢሆንም እንደ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የሚከፋፈል እንዳልሆነ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላላ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ተናገሩ፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ በሆነችው በባህር ዳር ከተማ የተከበረውን ሦስተኛውን የሠራዊት ቀን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ (ሲምፖዝየም)፣ ‹‹የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ከየት ወዴት?›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ጄኔራል ሳሞራ የመከላከያ ሠራዊት አመጣጥ፣ ዕድገትና አሁን የሚገኝበትን ደረጃ ተንትነዋል፡፡

ቀደም ሲል ደርግን ያሸነፈው የኢሕአዴግ ሠራዊት የአሁኑ መከላከያ ሠራዊት መሠረት እንደሆነ አስታውሰው፣ ለማመጣጠን ሲባል ከ30 ሺሕ በላይ ነባር ታጋዮች እንዲቀነሱ የተደረገበት ምክንያት ብሔራዊ አስተዋጽኦን ለማጠናከር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለታጋዮችም ሆነ ለአመራሮች ፈታኝና ከባድ ውሳኔ የነበረ ቢሆንም ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ወስነናል፤›› በማለት የገለጹት ጄኔራል ሳሞራ፣ በመከላከያ ሠራዊት አነስተኛ ተሳትፎ ከነበራቸው ብሔር ብሔረሰቦች አዲስ አባላት በመመልመል፣ ከወንጀል ነፃ የሆኑ ተፈላጊ ችሎታና ሙያ የነበራቸው የደርግ ሠራዊት አባላትም ታክለውበት ሠራዊቱ እንደ አዲስ መደራጀቱን አብራርተዋል፡፡ በወቅቱ ካልተቀነሱት የሕወሓት ታጋዮች ላይ ሁለት ማዕረግ እንደተቀነሰ፣ በአንፃሩ ደግሞ ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ ሁለት ማዕረግ እንዲጨመር መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ ከተፈጠረው መከፋፈል በኋላ በተደረገው የተሃድሶ እንቅስቃሴ መሠረት የሠራዊቱ ማነቆ የነበሩ ችግሮችና አስተሳሰቦች መወገዳቸውንም አውስተዋል፡፡ አዲሱ የሠራዊት ግንባታ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮዎችን የሚያሳካ፣ የመከላከል ቁመናው የማይደፈር ሆኖ በዋናነት የሻዕቢያ ተላላኪዎችን ጨምሮ ማናቸውም የደኅንነት ሥጋት መቆጣጠር የሚችልና የጦርነት አደጋን ከሩቁ የሚገታ ስትራቴጂ የተከተለ እንደነበርም ጄኔራሉ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኤርትራ ጦርነትን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት ጄኔራል ሳሞራ፣ ‹‹ጦርነቱን ባንፈልገውም በውጊያ የተፈተነና ብቃት ያለው የተመጣጠነ ሠራዊት ለመገንባት አስተዋጽኦ አድርጎልናል፤›› ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ተዋጽኦን በተመለከተ እንደ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ያነሱት ጄኔራል ሳሞራ ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችን መሠረት ያደረገ፣ ለመስዋዕትነት ዝግጁ የሆነና ለውትድርና የሚያስፈልጉ ሙያ፣ ዕውቀት፣ ችሎታና ልምድን መሠረት ባደረገ ምልመላና ዕድገት ሠራዊቱ መደራጀቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹የሠራዊታችን ግንባታ ብሔራዊ ተዋጽኦን ያረጋገጠ መሆን አለበት ሲባልም፣ ይህን ሙያና መሠረታዊ መሥፈርቶችን መነሻ ያደረገውን መርህ በአግባቡ በመረዳት መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከመሠረቱ የታጋዮች ሕዝባዊ ባህርያትን የተላበሰ፣ የሰላምና የልማት ኃይል በመሆኑ ከሌሎች አገሮች እንደሚለይ ገልጸው፣ ‹‹ብሔራዊ አስተዋጽኦ ግን በዋናነት በብቃትና በሙያ የሚለካ እንጂ እንደ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የሚከፋፈል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም የተደረገው ምልመላ ብሔር ብሔረሰቦችን ያሳተፈ ቢሆንም፣ ለአገር ጥቅም ሲባል ብቃትና ችሎታን መሠረት ባደረገና ግልጽነት በሰፈነበት የተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም መከላከያ ሠራዊት ፕሮፌሽናል (ዘመናዊ) ለማድረግ በርካታ የጥናትና የትምህርት ተቋማት ተመሥርተው አባሉ ራሱን እንዲያሳድግና እንዲያድግ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በዚህም ብቃትና አቅም ያለው ሠራዊት በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ጄኔራሉ አክለዋል፡፡ የአመራር መተካካት ሠራዊቱንም የሚመለከተው ሲሆን፣ በዚህ ተቋም መተካካት የተሻለ አመራርን ለመቀየርና ሠራዊቱን በከፍተኛ ደረጃ ያገለገሉ ታጋዮችንም በክብር እንዲተኩ ለማድረግ ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

ከፕሮፌሽናል ሠራዊት ግንባታ አኳያ፣ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው አንዳንድ አዳዲስ መመርያዎች፣ ደንቦችና ማኑዋሎች በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በሲምፖዝየሙ ‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴና መከላከያ ሠራዊታችን›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢፌዲሪ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ቀደምት ሥርዓቶች ሠራዊት በሕገ መንግሥቱም ሳይቀር የንጉሠ ነገሥቱ ተገዢ ነበረ ብለዋል፡፡ የአሁኑ የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ለገዢው ፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተገዢ የሆነ ሕዝባዊ ሠራዊት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለመከላከያ ሠራዊት የሚመደበው በጀት ከሌሎች የዓለም አገሮች ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አብቃቅቶ በመጠቀም ከራሱ ተርፎ በልማት ሠራዊት ላይም በማዋል ውጤታማ ለመሆን ችለዋል ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የመከላከያ ሚኒስትሩ ሪፖርታቸውን ለፓርላማ ሲያቀርቡ የሠራዊቱ ተዋጽኦ ላይ ለውጥ እየታየ ቢሆንም፣ የሌላው የማመጣጠን ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ገልጸው ነበር፡፡ በሠራዊት አባላት ብዛት ቅድሚያ የሚይዘው ክልል አማራ እንደሆነ፣ በመቀጠልም ደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች እንደሚከተሉ አመልክተው ነበር፡፡ ትግራይ ከሁለተኛነት ወደ አራተኛ መውረዱም ተገልጾ ነበር፡፡ ታዳጊ ክልሎችም የማሠልጠኛ ሥራቸውን በማጠናከር ለምልመላ ጥሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ ሪፖርቱ መጠቆሙ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...