Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትቅዱስ ጊዮርጊስና ደደቢት የመልስ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ስታዲየም አልታወቀም

ቅዱስ ጊዮርጊስና ደደቢት የመልስ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ስታዲየም አልታወቀም

ቀን:

‹‹የካፍን ውሳኔ እየጠበቅን ነው›› የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮናና በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አገሪቱን ወክለው ተሳትፎዋቸውን የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊስና ደደቢት ከሜዳቸው ውጪ ካስመዘገቡት ውጤት በኋላ በሜዳቸው የሚያደርጉት ጨዋታ በየትኛው ስታዲየም እንደሚያካሒዱ ገና አለየለትም፡፡
‹‹አንድ ለእናቱ›› በሚል በብዙኃኑ የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ የሚገለጸው የአዲስ አበባ ስታዲዮም ለእድሳት በመዘጋቱ ክስተቱ መፈጠሩ ክለቦች አሁንም ቢሆን የራሳቸው ስታዲየም ያለመኖሩ ፕሮፌሽናሊዝምን የሚያሳይ ደረጃ ላይ አለመገኘታቸውን የሚያመላክት መሆኑን ነው፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ጨዋታው የሚደረግበትን ስታዲዮም ለመለየት የካፍን ውሳኔ ‹‹እየጠበቅን ነው›› ይላል፡፡
79 ዓመታትን ያስቆጠረው አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህ አጋጣሚ እስከተከሰተበት ለ20 ዓመታት ሲወራለት የነበረውን የክለቡን የስታዲየም ግንባታ እውን አለማድረጉ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የገጠመው የሜዳ እጦት ከክለቡ ክብር ጋር ሲተያይ የሚያስተቸው እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ከሜዳው ውጪ ከአልጀሪያው ኦልማ ጋር የተጫወተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1ለ0 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ተመልሷል፡፡ የመልሱ ጨዋታ የሚደረግበት ስታዲየም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ፣ የት እንደሚከናወን የተረጋገጠ ነገር ባይኖርም፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ የቡድኑ ተጋጣሚ እንግዳው ቡድን አዲስ አበባ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡
የአዲስ አበባ ስታዲየም ከየካቲት 25 እስከ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ለ12ኛ ጊዜ የሚከናወነውን የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ስታዲየሙም ለዚሁ ሲባል እድሳት እየተደረገለት መሆኑን ተከትሎ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች እንዳያስተናግድ ክልከላ ተደርጎበታል፡፡
በሻምፒዮናው ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የባሕር ዳር ስታዲየምና የድሬዳዋን ስታዲየም በካፍ ዕውቅና ለማሰጠት እንቅስቃሴ መጀመሩ የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደ ኃላፊው አገላለጽ፣ ሁለቱ ስታዲየሞች የሚገኙበት ሁኔታ አስመልክቶ ካፍ የሚያጣራ ሙያተኛ (ኢንስፔክተር) ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ባለሙያውም አስፈላጊ ያላቸውን መረጃዎች አሰባስቦ መሔዱንና ይህንኑ ካፍ ውሳኔ እንዲሰጥበት መላኩን ለፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በዚህ ብቻ ዝም ብሎ እንዳልተቀመጠ የተናገሩት አቶ ዘሪሁን፣ ጉዳዩ አስቸኳይ ውሳኔ የሚያስፈልገው መሆኑን በመጥቀስ ደብዳቤ መጻፉንም ተናግረዋል፡፡
የመልስ ጨዋታዎቻቸውን በአዲስ አበባ ስታዲዮም እንደሚያደርጉ ቀደም ሲል ይጠብቁ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስና ደደቢት ካፍ ጨዋታውን በባሕር ዳር አልያም በድሬዳዋ ስታዲየም እንዲያከናውኑ ቢፈቅድ የሜዳ ገቢን በተመለከተ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ እንዴት ሊሆን ነው? ለሚለው አቶ ዘሪሁን፣ ‹‹ለጊዜው ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ሁለቱ ስታዲየሞች በካፍ ዕውቅና የሚያገኙበትን ጉዳይ ነው፡፡ የሜዳ ገቢ ስለሚባለው ነገር በሁለተኛ ደረጃ የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ የሜዳ ገቢን በተመለከተና ስታዲየሞቹም ዕውቅና ካገኙ በኋላ ግን ፌዴሬሽኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር የሚነጋገርበት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑት የቅዱስ ጊዮርጊስና የደደቢት ክለብ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ ካፍ የባሕር ዳርንም ሆነ የድሬዳዋን ስታዲየሞች ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደሚችሉ ባልተወሰነበት ሁኔታ ምንም የሚሉት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ለአፍሪካ የክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሲሼልሱን ኮት ዲ ኦርን ከሜዳው ውጪ የገጠመው ደደቢት 3ለ2 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወቃል፡፡
 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...