‹‹ሕወሓት እንደ መኢሶን ቢሸነፍ፣ እንደ ኢሕአፓ በትግል ስልት ስህተት ቢንኮታኮት፣ እንዲሁም እንደ ኦነግ የስደት ድርጅት ቢሆን ኖሮ የዛሬዋ ኢትዮጵያ እውን አትሆንም፡፡››
አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ፣ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የተመሠረተበትና የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 40ኛ ዓመት አስመልክቶ በመቐለ ከተማ በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ የተናገሩት፡፡ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም. በምዕራብ ትግራይ ደደቢት በረሃ የትጥቅ ትግሉን፣ ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ (ተሓሕት) በሚል መጠርያ የጀመረው ሕወሓት የአራት አሠርታት ዕድሜውን በሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ የካቲት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ባካሄደው ሲምፖዚየም ሲዘክር ከቀረቡት ሦስት ወረቀቶች አንዱ የአፈ ጉባኤ አባዱላ ‹‹የኢሕአዴግ የጋራ ትግል ከምሥረታው እስከ ደርግ መደምሰስ›› የሚለው ሲሆን፣ አንጋፋ ታጋዮቹ አቶ ሥዩም መስፍን ‹‹ከተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ሕወሓት 1ኛ ጉባኤ››፣ እንዲሁም አቶ ዓባይ ፀሐዬ ‹‹ከሕወሓት 1ኛ ጉባኤ እስከ ኢሕአዴግ ምሥረታ›› በሚሉ ርእሶች የመወያያ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡