Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ስኳር እና ዘይት ከሕዝብ ሱቅ ለማግኘት ፀሐይ ያልበገረው የካዛንቺስ ነዋሪ

ትኩስ ፅሁፎች

 ፎቶ በመስፍን ሰለሞን

****************

ዋዜማ

የተድላ የሥቃይ

ሀገር ከሚመስለው እንሥራው ገላችን

ሞላ የማር ጠጅ ተጠጣ ተብላላ

አንዳችም አልቀረን ካረቄም ከጠላ፡፡

ከበርሜል ልባችን

ባንድነት ካሉበት የበቀልና ቂም አምቡላና አተላ

ሲጠጣ ሲበላ

ያራዳዋ እሳት

ኮኛክ እንኳ ሳትቀር ገፍትራ ልትጥለን

ባጭር ልታስቀረን

ትፈጀው ጀመረ ባቢሎን ገላችን፡፡

  • ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ በ1930ዎቹ የተቀኙትን ግእዝ ከአማርኛ ያጣቀሰ ዋዜማ ቅኔ ኤፍሬም ሥዩም ተሰማ ‹‹ተዋናይ ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና›› በሚለው መድበሉ በውርስ ትርጉም እንዳስማማው፡፡

****************

ፈተና

በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ አንድ ሰው ለተፈለገበት መደብ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ወጥቶ በርካታ ሥራ ፈላጊዎች ይመዘገባሉ፡፡ ከብዙዎቹ ግን በመጨረሻው ዙር የደረሱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከጥቂቶቹ ደግሞ በተለያዩ መስፈርቶች ተጣርተው ሁለት ይቀራሉ፡፡

የመጨረሻዎቹ ተፈታኞች ወንድና ሴት ነበሩና አንድ ላይ ፈታኙ ፊት እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡ ፈታኙ ቀድሞውኑም ቀልባቸው ልጅቱ ላይ አርፎ ኖሮ መጀመሪያ ሴቷን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ስንት ነው›› አሏት፡፡ ልጅቱም ሳትቆይ ‹‹75 ሚሊዮን›› ትላለች፡፡ ቀጠሉና ወንዱን ተፈታኝ ‹‹አንተ ደግሞ ስማቸውን ጥራ›› ብለው ለዩት፡፡

  • ዘመን (2001)

****************

አማልክቱን የታደገው ፍጡር

በድሮ ጊዜ አንድ አትሬዉስ የሚባል ሰው የግሪክ አማልክትን በኃይል ለመብለጥ ይገዳደራል፡፡ በዚህም የተነሣ አማልክቱ ተቆጥተው የእርሱ ውላጆች በሙሉ ሕይወት የቀናች እንዳትሆንላቸው “አትሬዉስና ቤቱ የተረገሙ ይሁኑ!” የሚል እርግማን አስተላለፉ፡፡ይህ እርግማን በትዕቢቱ ያስቆጣቸውን አትሬዉስን ብቻ ሳይሆን ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን ሁሉ የሚመለከት ነበረ፡፡  

ጊዜ ነጎደ፡፡ እርግማኑም ተረሳና ከአትሬዉስ ልጆች መካከል አንዱ የሆነው አጋሜምኖን ክሊቴምኔስትራ ከምትሰኝ ሴት ጋር በፍቅር ይወድቃል፡፡ በመጨረሻም ያገባትና ኦሬስተስ የተባለ ልጅ ይወልዳሉ፡፡ ይህቺ ክሊቴምኔስትራ ግን በልጇ አባት ላይ ሌላ ሰው ወሸመችበት፡፡ መወሸሙም ሳይበቃት አጋሜምኖን ከጦርነት ሲመለስ ከውሽማዋ ጋር ተባብራ ገደለችው- የልጇን አባት! እርሷ ለውሽማዋ ፍቅር ብላ አጋሜምኖንን ስትገድል እርግማኑን ወደ ልጇ ማተላለፏን አላየችም፡፡ የአፍቃሪ ነገር! ያውም የውሽማ ፍቅር ችግር እኮ ነው፡፡ አማልክቱ ይህንን ሁሉ ከኦሊምፐስ ተራራ ላይ ተጎልተው ይመለከታሉ፡፡ እርግማናቸው በመሥራቱም “ቺርስ!” እየተባባሉ አማልክታዊ ጽዋቸውን ይቀባበላሉ፡፡ አባትየው ላይ የወደቀው እርግማን በገዛ ሚስቱ በመገደል ሲጠናቀቅ ያልተባረከ ሕይወት የመመምራት አማልክታዊው እርግማን ግን ወደ ልጁ ወደ ኦሬስተስ ተላለፈ፡፡

ኦሬስተስ እናቱ የፈጸመችውን ይህንን ወንጀል ሲያውቅ ነፍሱ አጣብቂኝ ውስጥ ወደቀች፡፡ ከፊቱም ሁለት አማራጮች ብቻ ቀረቡለት፡፡ አማራጭ አንድ በግሪኮች ባህል ወንድ ልጅ የአባቱን ገዳይ መግደል አለበት፡፡ አማራጭ ሁለት አንድ ግሪካዊ ሊፈጽማቸው ከሚችሉ ኃጢኣቶች ሁሉ እጅግ ከባዱ የገዛ እናቱን መግደል ነው፡፡ (ያኔ የአማርኛ ሙሾ አውራጅ ከግሪክ ከተሞች በአንዷ ብትኖር ኖሮ ‹‹ሟቹ አባትህ ገዳይዋ እናትህ ሐዘንህ ቅጥ አጣ ከቤትህ አልወጣ›› ብላ ልቡ እስኪፈርጥ ታስለቅሰው ነበረ፡፡)

የአባቱን ገዳይ አለመበቀል ከባድ ነውር ነው፡፡ የወለደችውን እናቱን መግደልም ታላቅ ኃጢኣት ነው፡፡ ምን ይሻላል? ኦሬስተስ ብዙ ካወጣና ካወረደ በኋላ የመጀመሪያውን አማራጭ በመውሰድ የአባቱን ደም ለመበቀል የወለደችውን እናቱን ሲጥ አደረጋት፡፡ እርግማኑ ሠራ! አማልክቱ አሁንም ተደስተው “ቺርስ!” ተባባሉ፡፡

Anchorምንም እንኳ ይህ ሁሉ ዕቅዳቸው ቢሆንምና በዕቅዳቸው አፈጻጸምም ቢደሰቱም የአማልክትነት ሥልጣናቸው የተፈጸመውን ኃጢኣት እንዲቀጡ ያስገድዳቸዋልና በግሪክ ውስጥ እናቱን የገደለ ኃጢኣተኛን ለኃጢኣቱ የሚገባውን ፍዳ የሚከፍሉትን ፍዩሪዎች በመባል የሚጠሩ ሦስት አስጠሊታ የስቃይ መናፍስትን ወደ ኦሬስተስ ላኩበት፡፡ እነዚህ መናፍስትም ኦሬስተስን በሔደበት ሁሉ እየተከተሉ የሠራውን ኃጢኣት እያስታወሱ ይወቅሱታል፡፡ በአሰቃቂ ገጽታቸውም ያስፈራሩት ጀመር፡፡ ሕይወቱ ሲዖል ሆነችበት፡፡ ከኃኣቱ ሊያመልጥ ብዙ ሞከረ፤ ግን አልቻለም፡፡ የኃጢኣቱን ሥርየት ለማግኘት ብዙ ማሰነ፡፡ ግን አልሳካልህ አለው፡፡ ከብዙ ዓመታት ስቃይና መፍትሔ ፍለጋ በኋላ አንድ ቀን አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ- አማልክቱን ከእርግማኑ እንዲፈቱት መጠየቅ፡፡ በዚህም መሠረት አማልክቱን በአያቱ ላይ ካስተላለፉትና በእርሱም ላይ ተነግሮ የማያልቅ ስቃይን ካስከተለበት ከዚህ እንደስኳር በሽታ በዘር የሚተላለፍ እርግማን እንዲፈቱት ይጠይቃቸዋል፡፡

አማልክቱም ጉዳዩን በችሎት ለማየት ተስማሙ፡፡ በችሎቱም ላይ አፖሎ የተባለው አምላክ ለኦሬስተስ እንዲህ ሲል ይሟገትለት ጀመር፡፡

“ሁሉንም ነገር ያቀድሁትና ኦሬስተስ እናቱን እንዲገድል ያደረግሁት እኔ ነኝ፡፡ ስለሆነም ኦሬስተስ ስለተፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ ሊሆን አይገባም፡፡”

በዚህ ጊዜ ኦሬስተስ ከመቀመጫው ዘልሎ በመነሣት

“ተቃውሞ አለኝ!” አለ፡፡

“ተቃውሞህ ምንድነው?” ዳኞቹ አማልክት ጠየቁት፡፡

“እናቴን የገደለው አፖሎ ሳይሆን እኔ ራሴ መሆኔ እንዲያዝልኝ፡፡” 

አማልክቱ ተገረሙ፡፡ ከአቴሬዉስ ቤተሰብ መካከል አንድም ሰው እንዲህ አማልክቱን ከማማረርና ከመርገም ውጪ ለኃጢኣቱ ራሱን በተጠያቂነት ያስቀመጠ ሰው አይተው አያውቁም፡፡ በዚህም የተነሣ ኦሬስተስ ሙሉ በሙሉ ከእርግማኑም ከኃጢኣቱም ነጻ እንዲሆን ወሰኑለት፡፡ እነዚያ ያሰቃዩት የነበሩ መናፍስትም የምክርና የፍቅር መናፍስት ወደመሆን ተቀየሩለት፡፡ በእነርሱ ምክርም ሕይወት የአልጋ ላይ ጉዞ ሁናለት ዓለሙን ሲቀጭ ኖረ፡፡

  • (የአጉስጢን ጦማር ከግሪክ ሚቶሎጂ የተገኘ ተረክ)

 

****************

ሕይወት ቀጣፊው ሥራ አጥነት

በዓመት ውስጥ 45,000 ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉት ሥራ አጥ በመሆናቸው እንደሆነ ተመለከተ፡፡ ዙሪክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በ63 አገሮች የተሠራ ጥናትን መነሻ ያደረገው የዘ ላንሴት ሳይኪያትሪ ዘገባ እንደሚያትተው፣ ሥራ አጥነት ከሚፈጥረው የኢኮኖሚ ቀውስ ባሻገር ራስ የማጥፋት መንስኤ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2000 – 2011 ባለው ጊዜ በዓመት 233,000 ሰዎች  ራሳቸውን ያጠፉ ሲሆን፣ የ45,000ው ምክንያት ከሥራ አጥነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ወቅቱ በዓለም ኢኮኖሚያዊ ልቀት የታየበት መሆኑን ጥናቱ ጠቅሶ፣ ከ2008 – 2009 የኢኮኖሚ ቀውስ ባጋጠመበት ወቅት የሟቾች ቁጥር ወደ 5,000 እንዳደገ ያሳያል፡፡

ከ2000 – 2011 በየአገሩ ከተመዘገቡ ሟቾች ከ20 ከመቶ – 30 የሚሆኑት ሥራ ኖሯቸው ያጡ ናቸው፡፡ ጥናቱን ከመሰል ጥናቶች የሚለየው በየትኛውም ዕድሜ ክልል ያሉ ሴቶችም ይሁን ወንዶች ለራስ ማጥፋት እኩል ተጋላጭ መሆናቸውን በማሳየቱ እንደሆነ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ እንደ አጥኝዎቹ፣ ሰዎች ራሳቸውን እንዳያጠፉ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ሥራ አጥነት ሲስፋፋ ብቻ ሳይሆን በተረጋጋ ኢኮኖሚ ወቅትም መሆን አለበት፡፡

የጥናቱ መሪ ካርሎስ ኖርጅት እንደተናገሩት፣ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር ሥራ አጥነት ከመስፋፋቱ ስድስት ወራት አስቀድሞ ይጨምራል፡፡ ተመራማሪው ‹‹ሥራ አጥነት ባልተለመደባቸው አገሮች ከሌሎች አገሮች በበለጠ የሞት መንስዔ ነው፤›› ይላሉ፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች