Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበአገዛዝ እንጂ በሕዝብ የሚፈጸም በደል የለም

በአገዛዝ እንጂ በሕዝብ የሚፈጸም በደል የለም

ቀን:

በብርቱካን ወለቃ

ለዚህ መጣጥፍ መነሻ ምክንያት የሆነኝ በየነ አስማረና ሊቁ እጅጉ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በኢሳት ቴሌቪዥን ቀርበው በክፉም በደጉም ለዘመናት አብሮ የኖረውን ‹‹የቅማንትና የአማራ ሕዝቦች ስለተጣሉ ደም ከመፋሰሱ በፊት ተቀራርበው ሊታረቁ ይገባል›› የሚል ዲስኩር ቢጤ ቃለ ምልልስ ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ግለሰቦች ማንነት በትክክል ለሚያውቅ ሰው በማንኛውም የሕዝብ ሜዲያ አይደለም በተናጠል ጎን ለጎን ተቀምጦ ለመነጋገር የሞራል ብቃት፣ ዕውቀትና አቅም የሌላቸው ከመሆናቸውም በላይ ሁለቱም ቢሆን በትልቅና በትንሽ  ወንጀል ውስጥ ሲዋኙ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በተለይ ሊቁ የሚባለው ግለሰብ በምንም ዓይነት መለኪያ ስለአብሮነት የመስበክም ሆነ የመናገር ብቃትና ሞራል የለውም፡፡ ከዚያ አለፍ ሲል ደግሞ የቅማንት ጉዳይ የቅማንትና የቅማንት ብቻ እንጂ እንደሱ ዓይነት ‹‹ቅማንት ገዳይ›› እያለ የሚፎክር የወረደ ግለሰብ፣  በምንም ዓይነት መንገድ የቅማንት ሕዝብ ጉዳይ የእሱ ጉዳዩ እንዳልሆነ ቀድሞውንምን መረዳት ነበረበት፡፡ የቅማንት ሕዝብ ጥያቄ ሁለቱ ግለሰቦች እንደሚያወሩት የቦታ ሽሚያ ሳይሆን የማንነት ጉዳይ መሆኑን ዕውቀቱና ግንዛቤው ቢኖራቸው ኖሮ እንደዚህ ዓይነት ተራ ንግግር ለማድረግ አይሞክሩም ነበር፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት እንዲሁም ማንነት ያላቸው ሕዝቦች ለዘመናት ጎን ለጎን ክፉውንና በጎውን በጋራ የተካፈሉ፣ በውጭ ጠላቶች በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ላይ የሚቃጣባቸውን የወረራ ጦርነት በጋራ ከምሥራቅ አስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ በመጠራራት፣ ወረራ በተከሰተበት አቅጣጫ ቀፎው አንደተነካበት ንብ በመትመም ጠላትን ድባቅ ሲያደርጉ የነበሩ ሕዝቦች ለመሆናቸው ታሪክ ይመስክራል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊ የሆነውን መገለጫቸውን የጋራ በማድረግ፣ የውስጥ ግላዊ  ማንነታቸውን አንዱ ያንዱን አክብሮ ሌላ ጊዜ ደግሞ በቋንቋ መሰል ልዩነቶች ምክንያት የሚፈጠሩ መናናቆችና የተዛቡ አመለካከቶችን እንደ ሕዝብ አቻችሎና አስማምተው የኖሩ ሕዝቦች ለመሆናቸው ብዙ የታሪክ ድርሳናት የሚመሰክሩት ሀቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋና መሰል ልዩነቶች ሳያግዳቸው የሰሜኑ ወደ ደቡብ የደቡቡ ወደ ሰሜን፣ ምሥራቁ ወደ ምዕራብ በአጠቃላይ ወደየፈለገው አቅጣጫ በመዘዋወር ተከባብሮና ተስማምቶ፣ አለፍም ሲል አንዱ ከሌላኛው ጋር በደምና በአጥንት በመተሳሰር ለዘመናት አብረው ኖረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በተለያዩ ዘመናት የሚነሱ ገዥዎችና የዚያ ሥርዓት ተራ አሽቃባጭ ቡድኖች የጭቆና ዘመናቸውን ለማራዘምና የቡድን ጥቅማቸውን ለማሳካት አንዱ ሕዝብ በአንዱ ላይ እንዲዘምት በሃይማኖት በማነሳሳት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶች በመምዘዝና አጉልቶ በማሳየት እርስ በእርሱ ጦር እንዲማዘዝና በጠላትነት እንዲተያይ አገዛዝ ሠራሽ ጦርነቶች ሲያካሂዱ ኖረዋል፡፡ በዚህ በገዥዎች አማካይነት በተለኮሰው ጦርነት ተሸናፊው ሕዝብ በአሸናፊው ወገን በባርነት እንዲያገለግል፣ ንብረቱ እንዲዘረፍ፣ መሬቱ ተቀምቶ ገባር እንዲሆን፣ ማንነቱና ቋንቋው ተንቋሾ የሌላ ማንነትና ቋንቋ በኃይል ተገዶ እንዲቀበል ይደረጋል፡፡ በአንድ ዘመን የበላይ የነበረው ግፈኛ ከተበዳይ ወገን በሚነሳ ኃይል በተራው ሲሸነፍ ደግሞ የዚያ ሥርዓት አገልጋዮችና ተከታዮች በተራቸው በሠፈሩት ቁና ግፍ ይሠፈርላቸዋል፡፡

በዚህ የረዥም ዘመን የማስገበርና የመገበር ሒደት ውስጥ የተከናወነው ጦርነት በሕዝቦች ዘንድ የሚታሰበው በግፈኛ የጦር መሪዎች የተፈጸመ በደል እንጂ አንድም ቀን በተለየ ሕዝብ አማካይነት በሌላኛው ላይ የተቃጣ የሕዝብ በቀል ተደርጎ አይታሰብም፡፡ ሕዝቡም ያለፈ ታሪኩን ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፈው ‹‹በዚህኛው ገዥ (ንጉሥ)  ወይም የአካባቢ የጦር መሪ ዘመን በእኛ ላይ እንዲህ ዓይነት በደል በሕዝባችን ላይ ደረሰብን›› ይላል እንጂ፣ ‹‹እንትና ተብሎ በሚጠራ ሕዝብ ተወረን ነበር›› ብሎ አያውቅም፡፡

ነገር ግን የሕዝቦች የአብሮነትና የአንድነት አስተሳሰብ በየዘመኑ ለሚነሱ ገዥዎች ስለማይመቻቸውና የግፍ የሥልጣን ዘመናቸውን ያሳጥርብናል ብለው ስለሚያስቡ፣ በአመራሮች የሚበጠበጥ መርዝ የግድ በሕዝቦች መካከል መረጨት   አስፈላጊ ይመስላቸዋል፡፡ በሕዝቦች መካከል ያለውን የባህል፣ የቋንቋና የሃይማኖት ልዩነቶች መሠረት በማድረግ አንዱ ሕዝብ ሌላኛውን እንዲንቀው፣ እንዲያንቋሽሸው ብሎም በጠላትነት እንዲተያይና አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ ይቆሰቁሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ጦርነቱ ከተቋጨ በኋላ ሕዝቦች ያለምንም ቂም በቀል አብሮነታቸውን እንደገና ይቀጥላሉ፡፡ በአንደኛው የአገሪቱ አካባቢ ረሃብና ችጋር ሲከሰት ችጋሩ ከተከሰተበት  አካባቢ የሚኖረው  ሕዝብ ችጋር ወዳልተከሰተበት ወገኑ በመሄድ፣ ያን የመከራ ዘመን ካሳለፈ በኋላ ችግሩ ሲወገድ ወደ ቀየው ይመለስና ኑሮውን እንደገና ይጀምራል፡፡ በተራው ደግሞ በአንድ ወቅት ለተቸገረው አካባቢ መጠጊያ ሆኖ የነበረው በተራው ተመሳሳይ ችግር ሲደርስበት በፊት አስጠግቶት ወደ ነበረው፣ ወይም ወደሌላ አካባቢ በመሄድ የተከሰተው የተፈጥሮ ወይም ሰው ሠራሽ ችግር አስኪያልፍ በመቆየት ይመለሳል፡፡ ወይም በዚያው ለምዶ ይቀርና ከሌላኛው ሕዝብ ጋር አብሮ ኑሮውን  ይገፋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝምድናውን ወይም አብሮነቱን የሚያቆራኘው በሚኖርበት መልከዓ ምድራዊ ቅርርቦሽ እንጂ አጥንትና ዘር በመቁጠር ከሱ ርቆ ለሚገኘው በተመሳሳይ የጎሳ ስም የሚጠራውን ሕዝብ ‹‹የእኔ ወገን ነው›› ለማለት ብዙም አይደፍርም፡፡ ይህን በምሳሌ  ለማስደገፍ ጎንደር አካባቢ የሚኖርና ራሱን ‹አማራ› ብሎ የሚጠራ ሕዝብ ሸዋ ወይም ጎጃም ከሚገኘው ራሱን ‹አማራ› ብሎ ከሚጠራው ሕዝብ ይልቅ፣ በቅርብ ርቀት የሚገኘውን ትግርኛ ተናጋሪ ሕዝብ ወገኑና በችግር ጊዜ ደራሽ እንደሆነ አድርጎ ይሰማዋል፡፡ በተመሳሳይ የሰሜን ሸዋ ኦሮሞ አርሲና ወለጋ አካባቢ ካለው አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ሕዝብ ይልቅ ለሰሜን ሸዋና ለጎጃም አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ ይበልጥ እንደሚቀርበው ይሰማዋል፡፡ ይህ ማንም የማይክደው ሀቅ ነው፡፡ እንደ ሕዝብ ለይተን ካየነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ገጽታ ይህ ነው፡፡ ሕዝብ ማለት ደግሞ የጭቆናና የግፍ ቀንበርን በሕዝብ ላይ የሚጭኑ ውስን የጦር አበጋዞች ጠመንጃ አንጋች ማለት አይደልም፡፡ ድሮም ሆነ አሁን ድረስ ቢሆን ሥርዓቶችን እንጂ፣ አንድን ሕዝብ በጠላትነት በመፈረጅ የሚናገር አንድም የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለ አይመስለኝም፡፡ ሕዝብን በሕዝብ ለማነሳሳት የሚያቀነቅነው እኩይ ተግባር የተጫጫናቸውና የሥርዓቱን ቁንጮ በተቆጣጠሩት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ብቻ ነው፡፡

የቅማንት ሕዝብ በገዥዎች ከጥንት አስከዛሬ የደረሰበት ግፍ

የቅማንት ሕዝብም እንደ አንድ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር እንደሚኖሩ ሌሎች  ሕዝቦች ሁሉ ለዘመናት የደረሰበትና አሁንም ድረስ እየደረሰበት ያለው ግፍ በተለያዩ ጊዜያት በተነሱ ገዥዎችና የጥቅም አራማጆች ምክንያት እንጂ፣ በሕዝብ የተፈጸመበት በደል እንደሌለ ታሪክ ይመሰክራል፡፡  በኢትዮጵያ አንደ አማራ (የሰሜን የጎንደር አማራ) እና ቅማንት ሕዝብ አብሮና ተቀራርቦ ተጋብቶና ተዛምዶ የሚኖር ሕዝብ ያለ አይመስለኝም፡፡ ወደ አጥንት መቋጠር ዝቅ ስንል ደግሞ የአማራ ደምና አጥንት  በቅማንቱ ውስጥ አለ፡፡ አለመታደል ሆኖ ሃይማኖትና ፖለቲካ ይህን ሕዝብ ለሁለት ሰነጠቁት እንጂ፣ የአንድ እናት ልጆች ለመሆናቸው ማንም በየቤቱ የሚያወራው ሀቅ ነው፡፡ በደርግ ዘመን አንዲት የአብዮት ቀልድ በመጥቀስ የቅማንትንና በጎንደር አካባቢ ስለሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ ያላቸውን ዝምድና ላመላክት፡፡ አንድ የደርግ ካድሬ ሕዝቡን ሰብስቦ ‹‹አብዮተኛ ማነው?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ አንዱ ተሰብሳቢ ትንሽ አሰብ በማድረግ እጁን ያወጣና ‹‹ቀድሞ አድኃሪ ያለ›› በማለት ይመልሳል፡፡ በተመሳሳይም የቅማንትና የአማራ ሕዝብ ልዩነትም ቢሆን ቀድሞ ክርስትናን ከመቀበል ያለፈ ልዩነት ያለው አይመስለኝም፡፡

ያም ሆነ ይህ ድሮ አንድ የነበሩ ሕዝቦች በአገዛዝና ሃይማኖት ጥምር ደባ አማካይነት እንደ ሁለት የተለያዩ ሕዝቦች መቆጠር ከጀመሩ ዘመናትን አሳልፈዋል፡፡ የአማራው ሕዝብም የቅማንትን ሕዝብ ‹‹ቅማንቶች›› ቅማንቱም የአማራን ሕዝብ ‹‹አማራ›› በማለት  አብረው ለዘመናት ኑረዋል፣ አሁንም እየኖሩ ይገኛሉ፣ ወደፊትም ይህ አብሮነታቸው ይቀጥላል፡፡  ይህ ሲባል የቅማንት ሕዝብ በአገዛዙ አማካይነት በደል አልደረሰበትም ማለት አይደለም፡፡ ቋንቋውን እንዳይናገር ቋንቋው የወፍ ቋንቋ፣ ሃይማኖቱ አረማዊ፣ ባህሉና ወጉ ኋላ ቀር ብሎ በማንቋሸሽ ገዥዎች ወደሚፈልጉት የሕዝብ መደብ ለመውሰድ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት ከፊሉ ተሸንፎ ራሱን ወደ አማራነት ቀይሯል፣ ግማሹ ወደ ተራራና በረሃ ተሰዷል፣ ግማሹ ደግሞ የመከራ መስቀሉን ተሸክሞ አሁን ያለበት ላይ ደርሷል፡፡

በዚህ ሕዝብ ላይ ጦርነት በገዥዎች ታውጆበታል፡፡ ይሁን እንጂ መከራን በዘዴ ማሳለፍ የሚችለው ሕዝብ አንዳንዴ ጦርነቱን በመከላከል ሌላ ጊዜ በመሰደድ ማንነቱን እዚህ ድረስ አድርሶታል፡፡ እነዚህ ጦርነቶች በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የተፈጸሙ ቢሆን ኖሮ አንዱ አንደኛውን ሙሉ በሙሉ አጥፍቶ ይኖር ነበር እንጂ፣ አሁን እንደሚገኘው በጉርብትና በፍቅር መኖር አይችሉም ነበር፡፡ ይህ ሕዝብ በአገዛዙ የደረሰበትን በደልና መከራ አገዛዙ እንጂ፣ ጎረቤት የሆነው የአማራ ሕዝብ በደል አደረሰብኝ ብሎ ፍፁም አያውቅም፡፡ ምክንያቱ ከአገዛዙ ጋር በቁጥር ደረጃ እኩል አይሁኑ እንጂ፣ ቅማንቱም አማራውም በጋራ የሥርዓቱ መሣሪያ በመሆን በሁለቱ ሕዝቦች ላይ በደል አድርሰዋል፡፡ የጭቆና ሥነ ልቦናው ዓይነት ይለያይ ካልሆነ በስተቀር የአማራው ሕዝብም ቢሆን ከጭቆና አገዛዙ በደል ፍፁም ነፃ  አልነበረም፡፡ ይህም ማለት በተለያዩ ዘመናት በነበሩት የግፍ አገዛዞች የቅማንትና የአማራ ሕዝብ እኩል ተጠቂ ነበሩ፡፡ ልዩነቱ የአማራው ሕዝብ በማንነቱ ምክያት እንደ ቅማንት ሕዝብ የሚደርስበት በደል አልነበረም፡፡ አማራው በአማራነቱ በኩራት አንገቱን ቀና አድርጎ ሲናገር ቅማንት በቅማንትነቱ ምክንያት እንዲሸማቀቅ ተደርጓል፡፡ በዚህ ረገድ በጎንደርና አካባቢው የሚኖረው አማራ ነኝ የሚለው ሕዝብም  በቅማንቱ ላይ በተለያዩ ሥነ ቃሎችና አባባሎች የሥነ ልቦና ጫና ፍፁም አላደረሰም ባይባልም፣ የዚህ ግፍ ምንጭ መሠረቱ አገዛዙ በመሆኑ በመገንዘብ የቅማንት ሕዝብ በአማራ ሕዝብ ላይ ፍፁም ቂም ቋጥሮ አያውቅም፡፡

የቅማንት ሕዝብ በተወሰኑ ግለቦችና የአገዛዙ የአጥቢያ ሹሞች ዛሬም ድረስ ከትምህክት አመለካከትና ከግፍ አገዛዝ ነፃ ሊወጣ አልቻለም፡፡ ያለፈው የግፍና የመከራ ዘመን እንደ ሥርዓት ቢወገድም፣ አሁንም ድረስ በተወሰኑ የመንግሥት ሹመኞች ዘንድ ያለው የትምህክት አመለካከትና ይህን ሕዝብ በዘሩ ምክንያት የመለየት ሥራው እንደቀጠለ ነው፡፡ የቅማንትን ሕዝብ ከኢትዮጵያ የብሔረሰብ መዝገብ ሙሉ በሙሉ አንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ በክልሉ ቅማንትኛ ቋንቋ እየሞተ እያዩ የሥርዓቱ ሰዎች ለማዳን ጥረት ለማድረግ አልሞከሩም፡፡ ይባስ ብለው ‹‹ቅማንት የሚባል ሕዝብ በግዛታችን የለም›› በሚል የክልሉ መንግሥት በምክር ቤቱ ድምፅ አሰጥቷል፡፡

የቅማንት ሕዝብ ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ ላነሳው የዕውቅና ጥያቄ የክልሉ መንግሥት ከሚገባው በላይ እንዲንዛዛ ከማድረጉም በላይ፣ በመጨረሻ ጥያቄውን ሳይመልስ አልፎታል፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት የቅማንት ሕዝብ በአማራው ሕዝብ አንድም ቂምና ጥላቻ አልቋጠረም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ በአጎራባች ቀበሌና ወረዳ የሚኖር  የአማራ ሕዝብ የቅማንትን የመብት ጥያቄ በመደገፍ ስብሰባ አብሮ ተሠልፏል፣ ሰላማዊ ሠልፍ ወጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ድርጊታቸው ለአንዳንድ የብአዴን አመራሮች አልተመቻቸውም፡፡

በክልሉ መንግሥት የተነፈገውን የመብት ጥያቄ የቅማንት ሕዝብ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ በማለቱ ምክንያት የክልሉ መንግሥት ውሳኔውን እንደገና እንዲመረምር ተገደደ፡፡ በዚህም ምክንያት የክልሉ መንግሥት ‹‹የፌደሬሽን ምክር ቤት ለቅማንት ጥያቄ ወሰነ ከሚባል ጥያቄው በክልሉ መንግሥት ተመለሰ ለማስባል በመጨረሻ ሰዓት ጥያቄውን ብአዴን ይመልሳል›› በሚል ለሕዝቡ ቃል ተገባ፡፡  በእርግጥ አንዳንድ የትምህክት ቡድኖች ጥያቄው ‹‹የጥቂት ኪራይ ሰብሳቢዎቸና ሥልጣን ፈላጊዎች ነው›› በማለት ማናናቃቸውን አላቋረጡም ነበር፡፡ እነዚህ  የቅማንት መብት ጥያቄ መከበር የማይዋጥላቸው አንዳንድ የዞንና የወረዳ ኃላፊዎች አመራር ሰጪነትና የቅማንትን የመብት ጥያቄ የሚቃወሙ ‹‹የአማራ ኅብረት ኮሚቴ›› በሚል በማደራጀት የቅማንት ሕዝብ ጥያቄ አቅጣጫውን እንዲስት መሥራት ጀመሩ፡፡ በዚህም ምክንያት በዚህ የአማራ ኅብረት ኮሚቴ አማካይነት ከታኅሳስ ወር 2007 ዓ.ም እስካሁን ድረስ በመተማ፣ በጭልጋ፣ በቋራ፣ በላይና በታች አርማጭሆ ወረዳዎች በአማራ ቀበሌዎች የሚሠሩ ወደ 400 የሚጠጉ የቅማንት የመንግሥት ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮችና ኢንቨሰተሮች በግፍ ተባረሩ፡፡ ለእነዚህ ቡድኖች የገንዘብና የትጥቅ መሣሪያ እገዛ የሚያደርጉ ግለሰቦች መሣሪያ እየገዙ በቅማንት ሕዝብ ላይ የሚዘምት ቡድን አደራጁ፡፡ በዚህ ረገድ የተወሰኑ በውጭ አገር የሚኖሩ ግለሰቦችም በዚህ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ለዚህ ወራሪ ቡድን ከተሰጠው ዋነኛ ተልዕኮ አንደኛውና መነገር ያለበት የላይ አርማጭሆን ወረዳ ዋና ከተማ ትክል ድንጋይን ለመውረር ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ 500 የሚሆን የታጠቀ ኃይል ወደ ትክል ድንጋይ ተንቀሳቀሰ፡፡ ይሁን እንጂ በንቃት ሲከታተል የነበረው የቅማንት ሕዝብ ይህን ቀማኛ የወንበዴ ቡደን በማፈን ያለምንም ጉዳት ወደመጡበት እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ በዚህ ዘመቻ አንዳንድ የዞንና የወረዳ  አመራሮች ጭምር ለመሳተፋቸው በቂ መረጃ አለ፡፡ ይህ ምክንያት ነው እንግዲህ  ለበየነ አስማረና ለሊቁ እጅጉ ‹‹የአማራና ቅማንት ሕዝብ ተጣልቷልና እርቅ ይውረድ›› ልፈፋ፡፡ ጠቡ የአማራና የቅማነት ቢሆን ኑሮ ትክል ድንጋይን ለመውረር የመጣው ወራሪ ኃይል በ500 ቁጥር ባልተወሰነ ነበር፡፡ የቅማንትና የአማራ ሕዝብ ፀብ ቢሆን ኖሮ ለወረራ የመጡትን አንድም ሳያስቀር የቅማንት ሕዝብ ወደ ግባተ መሬታቸው ይቀላቅላቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ግማሹ የቅማንት ሕዝብ ሽማግሌ በመሆን ‹‹እነዚህ ወሮበላዎች ብንረሽናቸው ከወላጆቻውና ከዘመዶቻቸው ጋር ቂም ስለምንጋባ ለዛሬ ወደመጡበት ያለምንም ጉዳት ይመለሱና ሁለተኛ ከመጡ ግን ልካቸውን እናሳያቸዋለን፤››  በማለት እንዲመለሱ አድርጓል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ግፎች በቅማንት ሕዝብ ላይ የደረሱትና እየደረሱ ያሉት በዘመኑ በሚነሱ ገዥዎች መሆኑን አንባቢያን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ በዚህ ሕዝብ ላይ ከድሮ እስከዛሬ የሚደርስበት መከራ በገዥዎች እንጂ በሕዝብ የሚፈጸም አይደለም፡፡

የእነበየነ አስማረና የሊቁ እጅጉ መልስ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ

በመጀመርያ ደረጃ እነዚህ ግለሰቦች ለማንኛውም ዓይነት ሚዲያ ብቁ አለመሆናቸውን ጠያቂ ጋዜጠኛው ጭምር የተረዳ ይመስለኛል፡፡ የእነዚህ ግለሰቦች ሰብዕናም ሆነ ዕውቀትና ክህሎት ለእንደዚህ ዓይነት መድረክ አይመጥንም፡፡ ዞሮ ዞሮ የሚያውቀው የሚዲያ ባለቤቱ በመሆኑ የእኔ ጉዳይ አይሆንም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ጎንደር ተበታተነች፣ አማራና ቅማንት ወደ ጦርነት እያመሩ ነው፣ የቅማንት ሕዝብ በ12ኛው ሰዓት የወያኔ መጠቀሚያ ለመሆን እየሠራ ነው ለማለት ያስቻላቸው ዋና ምክንያት ምን ይሆን? ጎንደር አንድ የምትሆነው በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ቅማንትና አማራ እንዲሁም ሌሎች ሕዝቦች በእኩልነት ሲኖሩ እንጂ፣ አንዱ በአንዱ የማንነት ሥር ተጠልሎና ተጨፍልቆ ሲኖር እንዳልሆነ መገንዘብ እንኳን ተስኗቸዋል፡፡ የሊቁ እጅጉ ግድ የለም፡፡ ድሮም በቅማንት ሕዝብ ላይ የነበረውን ጥላቻ ሳያጥብ አሜሪካ በመሻገሩ ኃጢያቱ የተሰረየለት መስሎት ስለሚሆን ግድ የለም ይሁን፡፡ የበየነ አስማረ ጉዳይ  ግን እጅግ ያሳዝናል፡፡ በየነ አስማረ ወደ ጎንደር ከተማ ሲገባ በቅማንትነቱ እየተሰደበና እየተሸማቀቀ መኖሩን አሜሪካ ሲሻገር ረስቶ፣ በቅማንት የመብት ጥያቄ በተቃራኒው መሠለፉ የሰውየውን ከዜሮ በታች የማንነት ቀውስ ውስጥ መሆኑን ዓብይ ማሳያ ነው፡፡

ጎንደር እንድትበታተን ቅማንት ምን አደረገ? የቅማንት ጥያቄ ‹‹እኔ ቅማንት እንጅ አማራ አይደለሁም፣ በመሆኑም በስሜ ልጠራ፤›› አለ እንጂ ጎንደርን ለመበታተን ምን የተለየ ነገር አከናወነ? ሁለቱ ግለሰቦች ቅማንት የሚባል ሕዝብ እንዳለ አያውቁም? ጎንደር ተወለድኩ የሚል ግለሰብ ቅማንትን ካላወቀ ሌላ ምን እንዲያውቅ ይጠበቃል? የቅማንት ሕዝብ የቦታ ማስፋፋት ጥያቄ አነሳ ወይስ ደግሞ ድሮ ቅማንት የነበሩና ዛሬ በአማራነታቸው የሚጠሩ ሕዝቦችን እንደገና ቅማንት ለማድረግ ተንቀሳቀሰ? ታዲያ በምን ሥሌት ነው ጎንደር የምትበታተነው? የአማራ ሕዝብ የቅማንትን ማንነት ሊቀበል ባለመቻሉ ይሆን ሁለቱ ሕዝቦች ወደ ጦርነት የሚገቡት? አቶ ሊቁና አቶ በየነ የቅማንት ሕዝብ የማንም መንግሥት አሽከርና አገልጋይ አልነበረም፣ ለወደፊትም አይሆንም፡፡ እናንተ ‹‹ወያኔ›› እያላችሁ የምትጠሩት የኢሕአዴግ መንግሥት አገሪቱን ከመቆጣጠሩ በፊት ቅማንት በኢትዮጵያ በጎንደር ክፍለ አገር ይኖር የነበረ ሕዝብ ነው፡፡ ለወደፊትም የሚኖር ነው፡፡ ቅማንትን በወያኔ የፖለቲካ ሙቀት የተፈለፈለ ሕዝብ ሳይሆን ጥንታዊ ጎንደሬ መሆኑን ዓለም ያውቀዋል፡፡ ምን ለማለት እንደምትፈልጉ ለቅማንት ሕዝብ ቢገባውም፣ የቅማንት ሕዝብ ጥያቄ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተጎናፀፉትን የማንነት የመብት ጥያቄ በስማዕት መስዋዕትነት ከፀደቀው ሕገ መንግሥት እንጂ፣ ከማንም እንዳልሆነ አለመገንዘባችሁ እጅግ ያሳዝናል፡፡

 አቶ ሊቁና መሰሎችህ የቅማንትን ሕዝብ በጣሊያን ወረራ ጊዜ በዱር በገደል በአርበኝነት እንዳልታገለ፣ የራሳችሁን የባንዳነት ተግባር ለመሸፈን የቅማንትን ሕዝብ በባእዳነት ከሰሳችሁት፡፡ በትክክል ግን ማን ባንዳ እንደነበር (Ethiopia Under Mussolini) የሚለውን መጽሐፍ ከቻልክ አንብብ፡፡ ካልቻልክ ደግሞ ለሰዎች አስነብብና እወቅ፡፡ ወያኔ (ኢሕአዴግ) አስካሁን ድረስ በሥልጣን ላይ ያለው በዓላማ ፅናቱና በሕዝባዊነቱ እንጂ፣  በአንድ ሕዝብ የሥርዓቱ ታማኝነት አይደልም፡፡ የቅማንት ሕዝብ እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሥርዓቱ መልካም ነገር ሲያደርግ ያሞግሳል፡፡ ሲሳሳት ደግሞ መሳሳቱን ሕዝባዊ ዕይታውን ያስቀምጣል፡፡ ምንም እንኳ የቅማንት ሕዝብ የመብት ጥያቄ በተወሰኑ ትምህክተኞች መልስ እንዳያገኝ እስከዛሬ ቢደረግም፣ ቅማንት እንደ ቅማንት አንገቱን ቀና አድርጎ መሄድ የጀመረውና ‹‹ቅማንት ነኝ›› ያለው በዘመነ ወያኔ እንጂ በሰለሞናዊ ሥርዓት አልነበረም፡፡

ባለቀ ሰዓት የሚለው ንግግር በራሱ በአየር ላይ የሚለቀቅ ቀቢፀ ተስፋ ይሆን ካልሆነ በስተቀር፣ ለኢሕአዴግ በሥልጣን መቀጠልም ሆነ መውረድ ወሳኙ በእናንተ ወደ ሰማይ የሚለቀቅ በአየር የተሞላ ባዶ ፊኛ  ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሰፊው ሕዝብ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሰዓት 12 ሰዓት ነው እንኳ ብለን ብንቀበል፣ የቅማንትን ሕዝብ ቅማንት ሆኖ ከመቀጠል የሚያግደው አንዳች ነገር እንደሌለ እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ፡፡ መሰሎችህ እንኳን ዛሬ በዚያ የጨለማ ዘመን የቅማንትን ሕዝብ ከቶም ሊያጠፉት አልቻሉም፡፡

የእናንተ ጥያቄ የግዛት አንድነት ለመሆኑ ካሁን በፊት ጽፌላችኋለሁ፡፡ አሁንም ልድገመው ጥያቄያችሁ ሰው አልባ አንድነት እየሰበካችሁ መሆኑ ማረጋገጫው ርዕዮተ ዓላማችሁን ሕዝቡ ባለመቀበሉ፣ በየጊዜው የምትክቡት የእንቧይ ካብ እየተናደ ናዳው  ራሳችሁን ወደ ምድር እያወረዳችሁ ለመሆኑ ራሳችሁ ጭምር የምታውቁት ሀቅ ነው፡፡ ነፃነት የማክዶናልድ የዶሮ ክንፍ እየነጩና በቢራ ጭንቅላትን እያናወዙ አይገኝም፡፡ ነፃነት የሚገኘው በሕዝብ ውስጥ ሆኖ የሕዝብን ብሶት ሰምቶ በቁርጠኝነት መታገልን ይጠይቃል፡፡ ነፃነት የዋይት ሐውስንና የተባበሩት መንግሥታትን በር በማጨናነቅ አይገኝም፡፡ ከቻላችሁ ወደ ሕዝብ ውስጥ ግቡና ሕዝቡ የሚቀበላችሁ ከሆነ ሕዝባዊ ትግል አቀጣጥሉ፡፡ ካልቻላችሁ አፋችሁን ልጉም አድርጋችሁ ቁጭ በሉ፡፡ ኢሕአዴግ ደርግን የገረሰሰው በአውሮፓና በአሜሪካ ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ ሳይሆን በሕዝቡ ውስጥ ሆኖ ነው፡፡

በመጨረሻ አንድ ነገር ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡ ሁለቱ የቅማንትና የአማራ ሕዝቦች እንደተጣሉ አድርጋችሁ የምትደሰኩሩትና እርቅ ያስፈልጋል የምትሉት እውን ሁለቱ ሕዝቦች ተጣልተው ሳይሆን፣ በዚህ ሰበብ የቅማንት ጥያቄ እንዲቋረጥ አልማችሁ ለመሆኑ ከዚህ ያሉ የእናተ ጋሻ ጃግሬዎች በግልጽ ይነግሩናል፡፡ ‹‹የቅማንትን ሕዝብ በየአቅጣጫው በማፈናቀል ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄውን ሊተወው ይችላል፤›› የሚል የተሳሳተ ሥሌት መሆኑን እናውቀዋለን፡፡ ይልቅ በቅማንትና በሌሎች አጎራባች ሕዝቦች ላይ የሚቃጣ የጦር መሣሪያ እየገዛችሁ ከምታስታጥቁ መንገድ፣ ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ለሕዝቦቻችሁ በማሠራት ሕዝባችሁን የልማቱ ተቋዳሽ ለማድረግ ሥሩ፡፡ በጦርነት ያሸነፈ ወይም የተሸነፈ መንግሥት እንጂ ሕዝብ በዓለም ላይ የለምና ሁለቱን ሕዝቦች ሰላም ባትነሱ መልካም ነው፡፡ ‹‹ከቅማንት ጋር ተጣልቻለሁ›› የሚል ሕዝብ ምናልባት ካለ ደግሞ ከማንነት ጥያቄ ባሻገር ባለው ማንኛውም ነገር ለመነጋገር የቅማንት ሕዝብ ዝግጁ ነው፡፡ ቅማንት በድሎኛል የሚል ሕዝብ ግን ያለ አይመስለኝም፡፡

 ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...