ዶ/ር ዮሐንስ ወዳጄ የተወለዱት የአንደኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ ገብተው በሕክምና የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በሥራ ዓለም ቀብሪደሃርና የካቲት 12 ሆስፒታሎች በጠቅላላ ሐኪምነት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በ8896 ሃሎ ዶክተር በተለያዩ የሕክምና ዘርፍ በቀን ለ24 ሰዓት፣ በሳምንት ለሰባት ሰዓት የማማከርና መረጃ አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማራ ቴሌሜድ የሕክምና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (ኩባንያ) ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ታደሰ ገብረማርያም በኩባንያው የሥራ እንቅስቃሴ ዙሪያ አነጋግሮአቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ዓይነቱ ተቋም ለማቋቋም ምንድነው ያነሳሳዎት?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- አጋጣሚዎች ናቸው ወደዚህ የወሰዱኝ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሐኪም ከሆንክ ሁልጊዜ በውጥረት ውስጥ ወይም ነገሮችን እያብቃቃህ ነው የምትሠራው፡፡ ሁልጊዜ ደግሞ ለቴክኖሎጂ ቀረቤታ (ኤክስፖዠር) ስለነበረኝና ጓደኞቼም የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ስለሆኑ ለምንድነው ድረ ገጽ የማይኖረን እያልኩ አስብ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ መጀመሪያ ያከናወነው ነገር ቢኖር በአማርኛ ስለሕክምና ጉዳዮች የሚያብራራ ‹‹አዲስ ሔልዝ›› ድረ ገጽ መክፈታችን ነው፡፡ ስንቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢንተርኔት ከፍቶ ድረ ገጹን ያነባል? የሚል ጥያቄ በመነሳቱ ኅብረተሰቡ ላይ ለመድረስ የስልክ አገልግሎቱን ጀምረናል፡፡
ሪፖርተር፡- ሥራችሁን እንዴት ታከናውናላችሁ?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- ኩባንያችን በሕክምና ዙሪያ በጠቅላላ ሐኪሞች አማካይነት የማማከርና መረጃ የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ ሥራውን የሚያከናውነውም ከጋሮቹ ጋር ነው፡፡ ፓርትነሮቹም ኢትዮ ቴሌኮምና ቤልካሽ ሶሉሽንስ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸውም የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮ ቴሌኮም የሚደውልበትን ቁጥር ያቀርባል፡፡ ቤልካሽ ሶሉሽንስ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ደግሞ የቴክኖሎጂ ሥራውን ያከናውናል፡፡ ኩባንያው በስልክ ላይ የተመሠረተና በሕክምና ላይ ያተኮረ የማማከርና መረጃ የመስጠት አገልግሎት ያከናውናል፡፡ ይህንን አገልግሎት ለመጠቀም ሰዎች ሲደውሉ ለአገልግሎቱ የሚከፍሉት ከስልክ ክሬዲታቸው ነው፡፡ በተረፈ ሃሎ ዶክተር የማኅበሩ የአገልግሎቱ ብራንድ (ምልክት) ነው፡፡ ሰዎች በሚደውሉበት ጊዜ ጥሪው በኢትዮ ቴሌኮም አድርጎ ወደ ኩባንያው ይመጣል፡፡ ከዚህ በኋላ በዕለቱ ተረኛ ወደ ሆኑ ወይም ወደሚሠሩ ጠቅላላ ሐኪሞች ጥሪው ይተላለፋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ የቴክኖሎጂው አካል በመሆኑ ሐኪም ማማከር በሚችልበት ሰዓት ‹‹ሳይን ኢን›› አድርጎ ማማከር ይችላል፡፡ የማማከሩን ሥራ አጠናቆ ወደ ሌላ ሥራ በሚንቀሳቀስበት፣ ወይም አገልግሎት መስጠት በማይቻልበት ሰዓት ሳይን አውት አድርጎ ይወጣል፡፡
ሪፖርተር፡- በስልክ የሚደውሉ የጥያቄዎችን ዓይነት ከፋፍሎ ማየት ይቻላል?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- አዎ ማየት ይቻላል፡፡ የሕመም ወይም ጥሩ ያለመሰማት ስሜት ኖሯቸው ስለዛ ስሜት ማብራሪያ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ፡፡ ሰውየው የራስ ምታት፣ የሆድ ሕመም፣ የትኩሳት ስሜት ሊኖረው ይችል ይሆናል፡፡ አለበለዚያ ደግሞ እናት ልጅዋ ታሞባት ይሆናል፡፡ ነፍሰጡር መጥፎ ስሜት ተሰምቷት ልትደውል ትችላለች፡፡ ስለዚህ ክሊኒክ ሲኬድ ማንኛውም ሐኪም እንደሚያደርገው ሁሉ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን እንጠይቃለን፡፡ ከምናቀርባቸው ጥያቄዎች በሚሰጡት መልሶች ላይ ተመሥርተን በሽታው ቀላል ከሆነ ፕሪስክሪብሽን የማይፈልጉ መድኃኒቶችን ተጠቅሞ መዳንና ወይም ደግሞ በጣም የሚያጣድፍ ከሆነ ሐኪም ዘንድ ሄዶ ማማከር እንደሚቻል እንነግራቸዋለን፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ጥሪ ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ወይም ልጃቸውን ያሳከሙ አባቶች፣ ሐኪም ቤት ሄደው ሕክምና አግኝተውና መድኃኒት ተሰጥቷቸውና ሳይሰጣቸውም ምርመራ ብቻ ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው የተመለሱ ሰዎች ግልጽ ያልሆኑላቸው ጥያቄዎች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች እኛ ዘንድ ደውለው ቢያቀርቡልን ትክክለኛውን መረጃ እንሰጣቸዋለን፡፡
ሪፖርተር፡- በሕክምና አሰጣጥ ረገድ ያለውን ክፍተት እንዴት ትሞሉታላችሁ?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- በአገራችን ካለው እጥረት አንፃር ሐኪሞችም አንዳንዴ በቂ ጊዜ ወስደን ነገሮችን አብራርተን ለደንበኛው ወይም ለበሽተኛው አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በደንብ አድርገን እስኪጠግብ ድረስ ሰጥተን የመላክ ዕድሉ ላይኖር ይችላል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ካለው መጨናነቅና የሥራ ሸክም የተነሳ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ኩባንያው ይህንን ክፍተት ይሞላል፡፡ ስለሆነም ደንበኛው ከተሰጠው ሕክምና በተጨማሪ ስላለው ሁኔታ በደንብ ይረዳል፡፡ መድኃኒቱን በትክክል መውሰድ፣ ምን ዓይነት የአወሳሰድ ዘዴ መጠቀምና ችግር ቢያጋጥም ምን ማድረግ እንዳለበት ሊረዳ ይችላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ መድኃኒቱ ላይ ብቻ ያተኮረ ጥያቄ ሊኖር ይችላል፡፡ አንዲት ነፍሰጡር ሕክምና ተቋም ሄዳ፣ መድኃኒት ተሰጥቷት ካበቃ በኋላ ለሐኪሜ ነፍሰጡር መሆኔን አልነገርኩትም ነበር፡፡ እረሳሁ ብላ ልትደውል ትችላለች፡፡ የሰጠኝ መድኃኒት ይህ ነው፤ ከእርግዝና ጋር አብሮ ይሄዳል? አይሄድም? ብላም ልትጠይቅ ትችላለች፡፡ አንድ ሰው ደግሞ ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት መድኃኒት እወስድ ነበር፡፡ ሐኪሜን ግን ሳልነግረው ቀረሁኝ፣ አሁን ሌላ መድኃኒት ታዞልኝ መጥቼያለሁ ሊለን ይችላል፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር የታመመ ብቻ ሳይሆን ሕክምናም ያገኘ ወይም እያገኘ ያለ ሰውም ሊጠይቀን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ጥያቄው ከኩባንያው አቅም በላይ ሆኖ ከተገኘስ?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- ወደ ሕክምና ተቋም ልንጠቁም እንችላለን፡፡ ግን በተለየ መልኩ እዚህ ቦታ ወይም ተቋም ሂድ የምንለው አይኖርም፡፡ ለምሳሌ ጉዳዩ የተለየ ከሆነና ሰብ ስፔሻሊስት የሚያስፈልጋቸው ማለትም ሐኪም ዓይቶ ኒውሮሰርጂን ያስፈልግሃል ተብሎ ኒውሮሰርጂን የት አገኛለሁ ብሎ አንድ ሰው ቢጠይቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ኒውሮሰርጂን ያሉባቸው የሕክምና ተቋማት ውስን ስለሆኑ ያሉበትን ቦታ እንነግረዋለን፡፡ በተረፈ ጠቅላላ ሐኪም የሚያስፈልገው ነገር ከሆነ በአብዛኛው በአካባቢው ያሉት ወይም የሚቀርቡትን ተቋማት ነው የምንጠቀመው፡፡ ምክንያቱም ስፔሻሊቲ ስላልሆነ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአንድ የሕክምና ተቋም ውስጥ ላለው ሐኪም እንዲህ ዓይነት በሽተኛ ልከንልሃል ብላችሁ እንዴት ነው የምትነግሩት?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- አሁን ባለን አገልግሎት በየሆስፒታሉም ሆነ በየጤና ጣቢያው ከሚገኙ አገልግሎት ሰጪዎች ወይም ሐኪሞች ጋር ግንኙነት የለንም፡፡ ይህ በደንብ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ለበሽተኛው እንዲህ ዓይነቱ የሕክምና ተቋም ብትሄድ ይሻልሃል እያልን እንጠቁመዋለን እንጂ እገሌ ከተባለው ሐኪም ጋር ተገናኝ አንለውም፡፡ ወደፊት ግን በደንብ ስንጠናከር ወደዚህ የምናመራበት መንገድ ሊኖር ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- በስልክ የማማከርና መረጃ የመስጠት አገልግሎት ከጀመራችሁ ስንት ዓመት ይሆናችኋል?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- ይህንን አገልግሎት የጀመርነው በ2005 ዓ.ም. ነው፡፡ አሁን ላይ ሆኖ ሲታይ ግን ሁለት ዓመት ይሆነዋል፡፡ የመጀመሪያው ስምንት ወራት የሙከራ ጊዜ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- በእነዚህ ዓመታት የማማከርና መረጃ የማግኘት አገልግሎት ፍለጋ የደወሉትን በዕድሜ ለያይቶ ማየት ይቻላል?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- ያሉንን የተለያዩ ጥያቄዎች ከፋፍለን ስናያቸው ከሁሉም ኅብረተሰብ ይመጣል፡፡ ከአምስት ቀን የጨቅላ ሕፃን እስከ 96 ዓመት አዛውንት ድረስ ይደውሉልናል፡፡ ግን አብላጫው ደዋዮቻችን ከ20 እስከ 40 ዓመት የሆኑ ወጣቶች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የሚጠይቁት ጥያቄዎች ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት በእናቶች እና በልጆች ጤና ዙሪያ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አገልግሎታችንን ትንሽ ለየት የሚያደርገው ነው ብለን የምናምነው አንዳንድ ሰዎች ከሐኪም ዘንድ ሄደው ፊት ለፊት ስለበሽታቸው ለማውራት ብዙ ምቾት የማይሰማቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህም ከባህላችን አንጻር ማለትም የሚያሳፍሩ ነገሮች የተባሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የኛ አገልግሎት ግን የጠያቂዎቹ ስማቸውን መግለጽ ሳያስፈልግና ማንነታቸው ሳይታወቅ ዝም ብለው ደውለው የሚፈልጉትን የማማከርና የመረጃ አገልግሎት ሊያገኙ ይችላሉ፤ ይህ ዓይነቱ አካሄድም ምቾት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
ሪፖርተር፡- በቀን ምን ያህል የስልክ ጥሪ ይደርሳችኋል?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- በአሁኑ ጊዜ በቀን እስከ 150 ጥሪ እናስተናግዳለን፡፡
ሪፖርተር፡- ደንበኞች በደቂቃ ስንት ብር ከፍለው ነው የሚደውሉት?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- ደንበኞች የሚደውሉት በአነስተኛ ክፍያ ነው፡፡ ወይም በደቂቃ ስምንት ብር ከፍለው ነው የሚደውሉት፡፡ ብዙ ጥሪዎች የሚቆዩት ሦስት ደቂቃ አካባቢ ነው፡፡ ከአምስት ደቂቃ የሚያልፉ ጥሪዎች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ደንበኞች የሚፈልጉትን ጠይቀውና አስፈላጊው ማብራሪያ ለመስጠት አምስት ደቂቃ ይበቃቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ደንበኛው ሲደውል ጥያቄህን ከአምስት ደቂቃ በላይ አታሳልፍ ተብሎ ተወስኖ ይነገረዋል እንዴ?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- አንወሰንም፡፡ ባሕሪው ሲታይ ግን ከሐኪም ጋር አምስት ደቂቃ ማውራት ይበቃል፡፡ ብዙውን ጊዜ በጣም ብዙ ምርመራ አድርጎና በምርመራዎቹ ላይ ካልተወያዩ በስተቀር አምስት ደቂቃ በጣም በቂ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በ40 ብር ዋጋ ሐኪሙን ማናገር ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- በአገልግሎታችሁ ያጋጠማችሁ ተግዳሮት ምን ይመስላል?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ይህ ነገር አዲስ ሐሳብ ነው፡፡ ሕክምና እንዴት በስልክ ይሆናል ብሎ የሚያስቡ ነበሩ፡፡ ይህንን የማሳመኑ ሥራ ነበር ትልቁ ፈተና፡፡ ይህ ዓይነቱ አገልግሎት ሕክምናን የሚያግዝ እንጂ የሚተካ አለመሆኑንም ለማስረዳት ብዙ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ ለምሳሌ ያህል ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮ ቴሌኮም መረብ (ኔትወርክ) የሚሻሻልበት ወቅት ነበር፡፡ በእነዚህም ወቅት የቴሌ የአገልግሎት መቋረጥ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ግን ጊዜያዊ በመሆናቸው የፈጠሩት እንቅፋት ይህን ያህል ከባድ አልነበረም፡፡ ሲስተሙ ከተሻሻለ በኋላ ግን አገልግሎቱ በአሁኑ ጊዜ በጣም ተስተካክሏል፡፡
ሪፖርተር፡- በስልክ ላይ የተመሠረተ የሕክምና ማማከር አገልግሎት የምትሰጡበት ወጥ መመሪያ አላችሁ?
ዶ/ር ዮሐንስ፡- በአጠቃላይ እንደዚህ ዓይነት አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ ከአንድ ሐኪም ወደ አንድ ሐኪም የሚሰጠው ምክር ዩኒፎርም፣ ደረጃውን የጠበቀና ወጥነት እንዲኖረውና በሳይንስ ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም የተነሳ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል ጋር በመተባበር መመሪያውን በረቂቀ ደረጃ አዘጋጀን፡፡ ከዛም የሰርጀሪ፣ የጽንስና ማህፀን፣ የሳይካትሪ፣ የውስጥ ደዌ ሐኪሞች ጋር በረቂቁ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ በውይይቱም የተንፀባረቁትን ጠቃሚ ሐሳቦችና ግብረ መልሶች ሁሉ በግብዓትነት ተጠቅመንበታል፡፡ ይኸው መመሪያ በቅርቡ ታትሞ ለሐኪሞች ሁሉ ይሠራጫል፡፡