Tuesday, October 3, 2023

ኢትዮጵያና ጂቡቲ ወዴት?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፉ ሕፃናት ሁሉ አልፎ አልፎ በአፈ ታሪክና በተረት መካከል ላይ ያሉ አወዛጋቢ የታሪክ ትርክቶችን ይማራሉ፡፡ በመሠረቱ እነዚህ ታሪኮች ለሕፃናቱ የሚሰጡት በጥንት ዘመን እንደተከናወኑ የተረጋገጡ የታሪክ እውነታዎች ተደርገው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በኢትዮጵያ ዘመናዊነትን በማስተዋወቅና አገሪቱን ከቅኝ ግዛት ጥቃት በመጠበቅ የሚመሰገኑ ቢሆኑም፣ ታሪካቸው ከእነዚህ አወዛጋቢ ትርክቶች የሚካተት ነው፡፡ ስለዚህ የታሪክን እውነታ ከልብ ወለድ መለየት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ አፄ ምኒሊክ ከቅኝ ገዥው የጣሊያን ወራሪ ኃይል ጋር መዋጋታቸውና በዓድዋ ጦርነት ማሸነፋቸው እውነት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባን መቆርቆራቸውም እንዲሁ፡፡

ታዲያ የልብ ወለድ ታሪክ የቱ ነው? እንደ ልብ ወለድ ከሚቆጠሩ ሕፃናት በትምህርት ቤት ስለ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ከተማሯቸው ታሪኮች አንዱ፣ ቀድሞ የኢትዮጵያ ግዛት የሆነችውን ጂቡቲን በመስጠት ከአዲስ አበባ በምሥራቅ ኢትዮጵያ አድርጎ እስከ ጂቡቲ ወደብ የሚዘልቀውን የባቡር መሠረተ ልማት ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምነት መፈረማቸውን ያትታል፡፡ ትረካው እውነት ብሎ የሚያቀርበው አንዱ ጉዳይ፣ በወቅቱ ከነበሩት ዋነኛ የአፍሪካ ቅኝ ገዥዎች አንዷ የነበረችው ፈረንሣይ አፄ ምኒሊክ መብታቸውን ለ99 ዓመታት (ከሊዝ ስምምነት ጋር ይመሳሰላል) አሳልፈው በመስጠት፣ ለባቡር ፕሮጀክቱ ገንዘብ እንዲያገኙና ግንባታውን እንዲያከናውኑ ግፊት ማድረጓን ነው፡፡

ይሁንና ይኼንን ታሪክ እውነት እንደሆነ የሚያስቀምጥ ታሪካዊ ሰነድም ሆነ ሌላ አስተማማኝ ማስረጃ ማቅረብ እንዳልተቻለ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አንዳንድ የታሪክ ባለሙያዎች ይህ እንዳለ አያምኑም፡፡ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት የታሪክ ባለሙያው አቶ ታምራት ኃይሌ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ጥናታቸውን እያካሄዱ ሲሆን፣ ጂቡቲ በየትኛውም ጊዜ የኢትዮጵያ ሕጋዊ  ግዛት እንደነበረች የሚያስቀምጥ ታሪካዊ ማስረጃ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ፈረንሣይን ይመሩ የነበሩት ታዋቂው ሻርል ደጎል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሁሉንም ቅኝ ግዛቶች ነፃ የሚያደርገውን ስምምነት ካፀደቀ በኋላ፣ ጂቡቲን ከኢትዮጵያ ጋር ለመቀላቀል ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር መነጋገራቸው እንደሚታመን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ታምራት ገለጻ፣ ከአዲስ አበባ ተነስቶ እስከ ጂቡቲ የሚዘልቀውን የባቡር መሠረተ ልማት ለማካሄድ ኢትዮጵያና ፈረንሣይ በጋራ የፈረንሣይ – ኢትዮጵያ  የባቡር ኩባንያን ለመመሥረትና ለፈረንሣይ ለ99 ዓመታት የመጠቀም መብት ለመስጠት የተፈረመው ስምምነት የሚያምታታ ነው፡፡ ከስምምነቱ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1917 ሥራ የጀመረው የባቡር መስመር 784 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ነበረው፡፡ በኢትዮጵያና በጂቡቲ መካከል ላለው ግንኙንት ታሪካዊ ምልክት ነው፡፡ ከባቡር መስመሩ ባሻገር የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ተመሳሳይ ባህል፣ ብሔር፣ ቋንቋና ደም ይጋራሉ፡፡ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ማኅበራዊና ባህላዊ ትስስር በየትኛውም ጊዜ ያልተለወጠ ቢሆንም፣ ይህንን ለጋራ ጥቅም ለማዋል ያለፉት መንግሥታት ያደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እ.ኤ.አ. ከ1998 እስከ 2000 ድረስ ተከስቶ የነበረው አውዳሚ ጦርነት፣ አሁን በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት ይህን ግንኙነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ጥረት እንዲያደርግ ምክንያት ሆኖታል፡፡

የሁለቱ አገሮች ጦርነት ኢትዮጵያ ስትጠቀምባቸው የነበሩትንና በኤርትራ የሚገኙትን የምፅዋና የአሰብ ወደቦችን እንዳትጠቀም ከልክሏታል፡፡ ይህ ክስተት የኢትዮጵያ መንግሥት ከጂቡቲ አቻው ጋር በቀጥታ በመደራደር የጂቡቲን ወደብ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ እንድትጠቀም እንድትስማማ አድርጓታል፡፡

‹‹ኢትዮጵያና ጂቡቲ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ልዩነት እንዳላቸው በግልጽ ካሳዩት ጥቂት ገጠመኞች ውጪ፣ ዘላቂ ተፅዕኖ ያለው ግጭት ውስጥ ገብተው አያውቁም፡፡ ይህ እውነታ ቢኖርም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው መጠን ጠንካራና ጤነኛ አይደለም፤›› በማለት በኢሕአዴግ ተረቅቆ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሆነው ሰነድ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ጠቅለል አድርጎ ይገልጸዋል፡፡  

 ጂቡቲና ኢትዮጵያ የነበራቸውን ታሪካዊና የተሳለጠ ግንኙነት ዋጋ በመስጠት የጂቡቲ ወደብ ለኢትዮጵያ ተመራጭ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹የጂቡቲ ወደብ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ለኢትዮጵያ አገልግሎት ለመስጠት ያለመ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ተፈጥሯዊ ምርጫ የሚሆነው ወደቡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ለአብዛኛዎቹ ክልሎች ቅርብ በመሆኑ ነው፤›› በማለትም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ሰነድ ያስቀምጣል፡፡ የፖሊሲው ሰነድ ለኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ገበያ የጂቡቲ ወደብ ዘላቂና አስተማማኝ አገልግሎትን በተመጣጣኝ ክፍያ እንደሚሰጥ ያረጋግጣል፡፡ ይሁንና የወደቡን ቀጣይ አገልግሎት ለማረጋገጥ ተጨማሪ የፖሊሲ አቅጣጫ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል፡፡ ይህ ደግሞ በዋናነት ከጂቡቲ ጋር ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲፈጠርና ሒደቱ ጂቡቲያውያኑን ተጠቃሚ አድርጎ የኢትዮጵያን ጥቅም ጂቡቲያውያኑ ጭምር እንዲጠብቁት ለማድረግ፣ ኢትዮጵያ በምትጫወተው ወሳኝ ሚና ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ፖሊሲው በተጨማሪም ይህን ለማሳካት ኢትዮጵያ ለጂቡቲ በርካሽ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ልታቀርብ እንደምትችል፣ የጂቡቲን የመጠጥ ውኃ ችግር ለመቅረፍ ኢትዮጵያ መፍትሔ ልትሆን እንደምትችልና ሌሎች መሰል ስትራቴጂዎችን ያስቀምጣል፡፡

የፖሊሲው አፈጻጸም   

ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ ፖሊሲውን ለመፈጸም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረጓን ማየት ይቻላል፡፡ የቀድሞውን የባቡር መስመር የሚቀይር አዲስ የባቡር መስመር በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡ 700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አዲሱ የባቡር መስመር በአራት ቢሊዮን ዶላር እየተገነባ ሲሆን፣ የቻይናው ኤክስፖርትና ኢምፖርት ባንክ ብድሩን አቅርቧል፡፡ ፕሮጀክቱ በመጪው ዓመት አጋማሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል፡፡ ኢትዮጵያ ሁለተኛ የባቡር መስመር ግንባታ ለማድረግ እያሰበች ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያን በአፋር በኩል በጂቡቲ እየተገነባ ከሚገኘው ታጁራ ወደብ ጋር የሚያገናኝ ነው፡፡ የታጁራ ወደብ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን የፖታሽ ማዕድን ኤክስፖርት ለማስተላለፍ ብቻ እንደሚውልም ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያና በጂቡቲ ድንበር ላይ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን የሚነሳ 103 ሜትሪክ ኪዩብ ንፁህ የመጠጥ ውኃን በየቀኑ ኢትዮጵያ ለጂቡቲ ማቅረቧም ሌላው ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ለማድረግ እንደ ኬንያና ሱዳን ካሉ አገሮች ጋር ስምምነት የተፈራረመች ቢሆንም፣ ከጂቡቲ ጋር ለማገናኘትና 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ለመጀመር የፈጀባት ጊዜ ጥቂት ወራት ብቻ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያና ጂቡቲ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተፈራረሙት አዲስ ስምምነት በአፋር ብሔራዊ ክልል በኩል ሌላ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ለመዘርጋት የሚያስችል ሲሆን፣ አቅርቦቱንም በእጥፍ ያሳድጋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፈጠረችው ሰፊ የመሠረተ ልማትና የኢኮኖሚ ትስስር ተጠቃሚ የሆነችው ጂቡቲ በበኩሏ፣ 9.8 ቢሊዮን ዶላር በማውጣት የወደብና የአገልግሎት ማስፋፊያ እያደረገች ነው፡፡ ከጂቡቲ ወደብና ነፃ የንግድ ቀጣና ባለሥልጣን (The Port of Djibouti and Free Zones Authority) የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ እ.ኤ.አ. በ2016 ሲጠናቀቅ የታጁራ ወደብ የኢትዮጵያን የፖታሽ ማዕድን ኤክስፖርት ሙሉ በሙሉ ማስተናገድ ይችላል፡፡ ጂቡቲ ከቻይና ኩባንያ ጋር በመተባበር ሰፊ ነፃ የኢንዱስትሪ ዞን ለመገንባትም አቅዳለች፡፡ ዞኑ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን የሚያቅፍ ሲሆን፣ በዋናነት የኢትዮጵያ ኢንቨስተሮች ላይ አነጣጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን አቅሟን ካልተጠቀመችበት ጂቡቲ ከቻይናና ከአውሮፓ አገሮች ኢምፖርት ለማድረግ ትገደዳለች፡፡

የሁለቱ አገሮች ባለሥልጣናት በጥር ወር መጨረሻ በ21ኛው የጋራ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በጂቡቲ በመገናኘት የኢኮኖሚ ውህደቱን የሚያሳልጡ በርካታ ስምምነቶችን ፈርመዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች በትራንስፖርት፣ የጋራ ድንበር የኢንዱስትሪ ዞን ለመፍጠር፣ የጉምሩክ ቢሮዎችን አንድ ለማድረግና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ የጂቡቲ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ኢልያስ ሙሳ ዳዋሌህ ሁለቱ አገሮች ወደ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማምራት አንድ ዕርምጃ መሻገራቸውን ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ አቻቸው አቶ ሱፍያን አህመድ ጋር በጋራ ድንበር ኢንዱስትሪያል ዞን ለመመሥረትና ከጂቡቲ ተነስቶ በአፋር ብሔራዊ ክልል በምትገኘው አዋሽ ከተማ የሚዘልቅ የነዳጅ ማስተላለፊያ ለመዘርጋት የሚያስችሉ ስምምነቶችን በስብሰባው ወቅት ተፈራርመዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ የቀላል አምራች ኢንዱስትሪዎች ማዕከል የመሆን ዕቅድ አላት፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ምርቶች ለተቀረው ዓለም ተደራሽ ለማድረግ ለገበያው ቅርብ መሆንና ተወዳዳሪ ወደብ ሆነን መገኘት አለብን፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የሚኒስትሩ አባባል በአዲስ አበባ የጂቡቲ አምባሳደር በሆኑት አምባሳደር መሐመድ ኢድሪስም ተስተጋብቷል፡፡ አምባሳደር መሐመድ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በሥራው ላይ የነበሩ በመሆናቸው፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት መሠረታዊ ለውጥ ሲያሳይ ለመመልከት በቂ ጊዜ አግኝተዋል፡፡ ‹‹አሁን ኢኮኖሚያዊ ውህደቱን ለማጠናቀቅ እየሠራን ነው፡፡ ተጨባጭ ለማድረግ የሚኒስትሮችን ስብሰባ በየወሩ እያደረግን ነው፤›› በማለትም ግንኙነቱ በሚያበረታታ ሁኔታ እያደገ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ፖለቲካዊ ውህደት

ምንም እንኳን የሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ውህደት ጅማሮ ላይ ቢሆንም፣ የሁለቱን አገሮች መሪዎችን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግን ከፍ ያለውን የፖለቲካ ውህደት አጀንዳ ከማንሳት አልተቆጠቡም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በጂቡቲ ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በጂቡቲ ፓርላማ ፊት ቀርበው ንግግር አድርገው ነበር፡፡ የፓርላማው አባላትን ቀልብ ከሳቡት ጉዳዮች ዋነኛው ለፖለቲካዊ ውህደት ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መናገራቸው ነው፡፡ በየትኛውም መሥፈርት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ታሪካዊ ነበር፡፡ አንደኛው ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ያደረጉት ጉብኝት በኢትዮጵያ መሪ ደረጃ የተደረገ የመጀመርያው ጉብኝት ነው፡፡ ሁለተኛ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በራሱ ታሪካዊ የሚባል ነው፡፡

‹‹እዚህ የተገኘሁበት ዋነኛ አጀንዳ የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ፍላጎትና ጥም ለማርካት ተጨማሪ ሥራዎች እንድንሠራ ጥሪ ለማድረግ ነው፡፡ ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ትብብር በተለይም ታላቅ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነትና ኅብረት ይፈልጋል፡፡ ማን ያውቃል ከጋራ ታሪካዊ እምነታችንና ዕጣ ፈንታችንን ለማሟላት ከምናደርገው ጥረት በመነሳት የፖለቲካ ውህደት ማሳካትም እንችል ይሆናል፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጂቡቲ ፓርላማ አባላት ተናግረዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያዎችና ተንታኞች ለዚህ ግንኙነት ምን ዓይነት ስም እንደሚሰጡት አላውቅም፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ ግን በእርግጠኝነት ለማሳካት እየተጠጋን ነው፡፡ ምክንያቱም የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የሚሹት ነገር በመሆኑና ልጆቻችንንም የሚገባቸው ስለሆነ ነው፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

በተመሳሳይ የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌህ በበኩላቸው፣ ከሁለት ወራት በፊት ጂቡቲን ለጎበኙ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የፖለቲካ ውህደትን የሕዝቦች ፍላጎት ከሆነ አገሮቹ ሊተገብሩት እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

 ‹‹ፖለቲካዊ ውህደት የማይሆንበት ምን ምክንያት አለ?›› በማለት ቀደምት የሆኑት አምባሳደር መሐመድ ኢድሪስ ይጠይቃሉ፡፡ ታሪካዊ እውነትነቱ ይረጋገጥም አይረጋገጥ በአንድ ወቅት አንድ እንደነበሩ የተነገረላቸው የሁለቱ አገሮች አንድነት ቀስ በቀስ ወደ መሆን እየተጓዘ ይመስላል፡፡ ምናልባትም አሁን ታሪክን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዳግም ለመጻፍ ሌላ ዕድል ተገኝቷል፡፡

 

  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -