በኅዳር ወር መጨረሻ በአፋር ክልል የሚከበረው 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለእንግዶች ማረፊያ እንዲሆኑ የአፋርን ሕዝብ አኗኗርና ባህል እንዲያሳዩ ተደርገው የተሠሩት ባህላዊ ቤቶች 480 ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ከአምስት እስከ ስምንት ሰዎችን የማስተናገድ አቅም የሚኖራቸው ባህላዊ ቤቶች፣ ውስጣቸው የአፋርን ሕዝብ አኗኗርና ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅ በሚያስችሉ የቤት ውስጥ ዕቃዎች የሚሟላ ነው። በባህላዊ ቤቶቹ በዋናነት ከሁሉም ክልሎች የሚመጡ የባህል ቡድኖች እንደሚያርፉበት ታውቋል፡፡ የመንደሩ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታና የኤሌክትሪክ መብራት መስመር ዝርጋታም ተጠናቋል፡፡ የመታጠቢያና የመጸዳጃ ቤት ግንባታም በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የአፋር ባህላዊ ቤቶችን ግንባታ የክልሉ 16 ወረዳዎች ወጪ መገንባታቸውን፣ አጠቃላይ ወጪው ገና አለመታወቁን በተሰጠው መግለጫ መረዳት ተችሏል፡፡
- ፎቶ በታምራት ጌታቸው
* * *
ሞት በቃኝ አያውቅም
‹‹ሞት›› ለምንድነው በቃኝ የማያቀው
‹ጠገብሁ› ጉድጓድ ሆዴ ሞላ የማይለው
ሴት ሆነ ወንድ ሽማግሌ ሕፃን
ማግበስበስ ነው ሌትም ሆነ ቀን
የሒትለር ተከታዮች በግድያ ከሚያግዙት፣
ምሁራን ኑክሌር ቦምብ እየሠሩ ከሚረዱት
ምናለ ሞትን በቃህ ቢሉት
ከአማኑኤል (ሠራተኛ ሠፈር)
* * *
የኢትዮጵያ ምስክሯ ፈረንጅ!
‹‹ዱሮም አንተ ምግብ የት ታውቃለህ? ይሄኮ በአውሮፓ በጣም ተወዳጅ ምግብ ነው›› የሚባባሉ ሰዎች ሰምቼ አውቃለሁ፡፡ በርካታ ድርጅቶችም ‹‹ይህ ምርታችን በአውሮፓና በአሜሪካ የማንትሴን ድርጅት ሽልማት ያገኘ ነው›› በማለት ምርቶቻቸውን ብንገዛ እንደሚበጀን ሲነግሩን የምንሰማው ነው፡፡ እንትን የሚባለው ዕቃ ‹‹የስልጡኖች ምርጫ ነው›› በማለት ከኋላ ቀርነታችን እንድንላቀቅ የሚገፋፉንም ማስታወቂያዎች አሉ፡፡ ‹‹ጣፋጭነቱ በአውሮፓ የተመሰከረለት›› ኬክ ቢገጥመንም ታዝበን ዝም ከማለት በላይ ለአንድ ቂጣ የሚሰጠውን አርባ ስም ስናይ እናዝን ይሆናል ፒሳን ልብ በሉ፡፡
ይህ ልማድ ወደ ግለሰቦች ሕይወት ታሪክም እየገባ ይመስላል፡፡ በዚህ ዕውቀታቸው ወይም ግኝታቸው የአሜሪካን ማንትስ ዩኒቨርስቲ ሽልማት ያገኙ ናቸው፡፡ እንትን የሚባለው አካዳሚ ወይም አሶሴሽን ሸልሟቸዋል፤ የክብር ስፍራም ሰጥቶአቸዋል፡፡ የመጀመሪይው ጥቁር፣ የመጀመሪያው አፍሪካዊ፣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እየተባለም ብዙ ነገር መባላቸው ይሰማል፡፡ አንዳንድ ምሁራንም እንዲህ ነኝ እንዲህ የተባልኩ ነኝ ሲሉን እንሰማቸዋለን፡፡
ይህ ሁሉ ይሁን፡፡ አገራችን ከእነዚህ ሰዎች ያገኘችው ምንም ነገር የሌለ ከሆነ ታዲያ ምን ይጠበስ? ማለት ተገቢም ላይሆን የችላል፡፡ ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ፈረንጅ የሾመው ያዳነቀውን ሁሉ መቀበልና ማድነቅ አለብን? ወይስ ቢቻል ለአገሩ የፈየደውን እሱ ካልሆነ የተደነቀበትን ነገር መርምረን ማድነቅ አለብን? ፈረንጆቹ ‹‹ጥቁር ይህን ያህል ካሰበ መች አነሰው?›› እያሉ የማርክና የማዕረግ ቁልል እንደሚያሸክሙ አልፎ አልፎ እንሰማለን፡፡ ደግሞ ደርሰውስ እዚህ ስሙንም እንኳ በቅጡ የማናውቀውን ድርጅት የአውሮፓ ተሸላሚዎች ብለው ሾመው ሲልኩብን ምን አስበው ነው?
ይልቅ የራሳችንን ማድነቂያ መስፈርት ብናበጅ አይሻል ይሆን? እኛ ገዝተን የምንጠቀመውን ምርት ጥራት ማረጋገጥ ካልቻልን ‹‹ጥራቱ በመላ ኢትዮጵያ የተረጋገጠ›› ምርት የሚል ማስታወቂያ መስማት ካልቻልን በእጅ አዙር ቅኝ ወደመሆን ማምራታችን እንዳይሆን፡፡ ይህ ብስኩት በአሜሪካ የተወደደ ነው ስለተባለ ብቻ የጣዕም ባለቤትነታችንን አሳልፈን በሌላው ስሜት ማጣጣም ከወደደን አደጋ ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ይህን ፕሮጀክት ‹‹ሰውጭ አገር ኤክስፐርቶች ነው ያስጠናነው›› እያሉ ሲፎክሩ ዝም ብለን ከሰማን ነገሩ እያሰጋ ሊሄድ ይችላል፡፡ በራስ ማፈር በገዛ ምሁርና ዜጋ አለመተማመንንም ያመጣል፡፡ ካለበለዚያ ነገ ይህች ኢትዮጵያዊት ኮረዳ በማንትስ አገር ውበቷ የተመሰከረላት ናትና እንዳታመልጣችሁ ማለትን እንዳያመጣ ያሰጋል፡፡
- ‹‹ሪፖርተር መጽሔት›› (ጥር 1992)