Sunday, June 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚነሳው ሽብርተኝነትና ኢትዮጵያ

በያሲን ባህሩ

መካከለኛው ምሥራቅ የቀደምት ሥልጣኔ መሠረት ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ሃይማኖቶች መነሻ መሆኑ በታሪክ ተከትቦ ይገኛል፡፡ ክርስትና፣ እስልምናም ሆነ አይሁድ ምንጫቸው እዚያው ነው፡፡ የኢትዮጵያ የእስልምና ግንኙነትም ከብዙዎቹ እስላማዊ የታሪክ ክንውኖች በፊት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እስልምና ‹‹ሱኒ›› እና ‹‹ሺኣ›› ተብሎ ከመከፋፈሉ በጣም በፊትም ነው፡፡ አራቱ ታላላቅ የሕዝበ ሙስሊሙ (ኡማ) መሪዎች (አቡበከር፣ ዑመር፣ ዑስማንና ዓሊ) እንደመሪ ከመከሰታቸው በፊት እንደሆነም ይታወቃል፡፡

በቅርቡ በወጣ አንድ ሃይማኖታዊ የጥናት ጽሑፍ እንደተገለጸው፣ የኢትዮጵያና የእስልምና ግንኙነት የተጀመረው ኸዋሪድ፣ ወሃቢ፣ ሰለፊ፣ ወዘተ የሚባሉ አክራሪዎች ከመፈጠራቸው በፊት ነው፡፡ ግንኙነታችን የሚጀምረው ከረጂም ዓመታት በፊት ነው፡፡ ይኸውም በእስልምና የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የነበሩ የራሳቸው ወገኖች የሆኑት ቁሬያሾች ‹‹የመሐመድን ነብይነት አንቀበልም›› ብለው ተከታዮቻቸውን መውጪያ መግቢያ ባሰጡበት ጊዜ፣ ጓዶቻቸውን (ሰሃበዎቻቸውን) ወደ ሐበሻ አገር ስደት እንዲሄዱ ካዘዙበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

እንግዲህ ወደ ሃይማኖታዊ ታሪኩ ቢገባ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን የእስልምናም አገር መሆኗን ለመንደርደርያ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ እንኳን ዛሬ በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ሃይማኖቶች ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝተው፣ የነፃነትና የእኩልነት ካባ ተጎናጽፈው ይቅርና ጥንትም ቢሆን ኢትዮጵያዊያን ሙስሊም ክርስቲያኖች ተከባብረው ባየባዕታቸው የሚኖሩባት አገር መሆኗን ማንም ሊክደው አይችልም፡፡

በመሠረቱ የተከበረው የእስልምና ዕምነት ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ሚስጥር ጥልቅ መሆኑን አለማጤን የሚያስከትለው ውርደትን ነው፡፡ ነብዩ መሐመድ (ሰአወ) ወገኖቻቸው በደረሰባቸው ጥቃት ሲሸሹ ወደ ሐበሻ ምድር እንዲሄዱ የመከሩበት ምክንያት ነበራቸው፡፡ አንደኛው የንጉሡን መልካምነት ሲሆን፣ ‹‹ከሰው ጥግ የማይደርስና ካልነኩት የማይነካ፣ ፈጣሪውን የሚፈራ ሕዝብ መኖሩን ነግረው ነው፤›› ይላሉ የታሪክ ድርሳናት፡፡ ከዚህ የምንረዳው ኢትዮጵያ ለእስልምና መጠለያነት ከዓለም አገሮች ሁሉ በቅድሚያ የተመረጠች ቅዱስ ሕዝብና ንጉሥ የነበረባት መሆኗን ነው፡፡

በእስልምና ታሪክ የመጀመርያው የመስጊድ የሶላት ጥሪ አዋጅ (አዛን) ነጋሪና የነብዩ (ሰዐወ) በጣም የቅርብ ወዳጅ የነበረ ቢላል ሐበሻ ነው፡፡ ‹‹አዛን›› ማለት በጥሩ የድምፅ አወራረድና በርጋታ ፈጣሪን የማመስገን ተምሳሌት በመሆኑም እስካሁን እየተሠራበት ያለ ሃይማኖታዊ ክዋኔም ነው፡፡ በዚህም ዛሬ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ከጥንት ከመሠረቱ ከመጣው ሃይማኖታዊ መርሆዎች ላይ ተመሥርተው ዕምነቱን በማስፋፋት፣ በማስተማርና ፈጣሪያቸውን በማምለክ ላይ ይገኛሉ፡፡ የአገራችን የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ቁጥርም በዝቶና በርክቶ መገኘቱ ይታወቃል፡፡

መካከለኛው ምሥራቅን ያስጨነቀው ሽብርተኝነት

ሽብርተኝነት (Terrorism) የዓለማችን ዋንኛ ሥጋት ቢሆንም ጎልቶ የማታየው በመካከለኛው ምሥራቅ መሆኑ አይካድም፡፡ በመሆኑም የአደጋው ሰበቦችም ሆነ ሰለባዎች ሙስሊሞች ሆነዋል፡፡ (እስልምና ግን በፍፁም የሰላም ሃይማኖት ብቻ መሆኑን መጠራጠር አይገባንም!)

ዛሬ በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በአፍጋኒስታን፣ በፓኪስታን (አልፎ አልፎ) እንደዚሁም እንደ ግብፅና ሊቢያ ባሉት የሰሜን አፍሪካ አገሮች ንፁኃንን እየፈጀ ያለው ሽብርተኝነት መሆኑን መጠራጠር ያስቸግራል፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ ናይጄሪያና ካሜሩን ባሉት ከምዕራብ አፍሪካ እስከ ምሥራቆቹ ሶማሊያና ኬንያ ድረስ ከዚያም አልፎ አሜሪካና አውሮፓ (የቅርቡን የፈሪንሣይ አደጋ ልብ ይሏል) ማጤን ይገባል፡፡ አሳዛኙ እውነት ደግሞ በሽብር ጥቃት ውስጥ ዋነኛ ተጎጂዎች የሆኑ ንፁኃን የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የመሆናቸው ነገር ነው፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ብሔራዊ ፀረ ሽብር ማዕከል (NCTC) እ.ኤ.አ. 2012 ባወጣው አንድ ሪፖርት የሽብርተኝነት ሰለባ የሆኑ ወገኖች በሃይማኖት ዘውግ ተለይተው ሲታዩ ከ82 እስከ 97 በመቶ የሚሆኑት ሙስሊሞች ናቸው፡፡ (Incase where the religious affiliation of terrorism casualties could be determined, muslims suffered between 82-97% terrorism related fatalities over the past five years) ይህንኑ መረጃም ‹‹Global Terrorism Database›› (GTD) የተባለ ተቋም በቅርቡ አረጋግጦታል፡፡

በመረጃዎቹ መሠረት ዋነኛ የሽብርተኝነት ጥቃት ሰላባ የሆኑ አገሮችም ተለይተዋል፡፡ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ ናይጄሪያ፣ ሶማሊያ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ሲሪላንካና ታይላንድ ከአንድ እስከ አሥር ተራ የወጣላቸው ሲሆን፣ እነዚህ አገሮች ደግሞ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የሚበዛባቸው መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በተለያዩ ጥናቶች እንደተረጋገጠው መካከለኛው ምሥራቅን መነሻው አድርጎ ብዙዎችን እያስጨነቀ ያለው ሽብርተኝነት እስላማዊ አክራሪነት ነው፡፡ በዓለማችን የሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት የለም፡፡ የዓለም ሙስሊሞች ተጨቁነውና ነፃነት አጥተዋል ከሚል ይነሳል፡፡ እየጠበቀ ሲሄድ እስልምና ዓለምን ሙሉ መያዝ አለበት፡፡ መንግሥታት ከሃይማኖት ነፃ (ሴኩላር) ከመሆን ይልቅ እስላማዊ መሆን አለባቸው የሚል አባዜ የተጠናወታቸው ናቸው፡፡ ኃይል፣ የፖለቲካ ሥልጣንና ሀብትን ካልተቆጣጠርን ሃይማኖታችን አይስፋፋም የሚል አጉል ፀለምተኛ ጽንፈኝነት የተጠናወታቸው ኃይሎችም ናቸው፡፡ ፀለምተኛ ጽንፈኝነት የተፀናወታቸው በንፁኃን የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችና በሰላሙ ሃይማኖት ስም የሚነግዱት እነዚህ ዓለም አቀፍ ኃይሎች፣ ‹‹ነባሩን የዕምነቱ መርሆ እንደተበከለ ይቆጥራሉ›› ይላሉ ጥናቶች፡፡ ‹‹እስልምና በጊዜ ሒደት ከእስልምና በፊት በነበረ የጨለማ ዘመናት (ጀሂሊያ) በነባሩ አሠራሮች፣ ባህሎችና አፈ ታሪኮች እየተበከለ ስለሆነ ማጥራት አለብን፡፡ ወደ ቀድሞው የነቢዩና የአራቱ ካሊፎች (አቡበከር፣ ዑመር፣ ዑስማን፣ ዓሊ) ወደነበሩባት ወርቃማ ዘመን እስልምናን መመለስ አለብንም፤›› ይላሉ፡፡

ከዚህ በመነሳት ዴሞክራሲያዊነትና ውይይት፣ የሌሎች ዕምነት ተከታዮችን መብቶች መጠበቅን ችላ የሚሉ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ይፈጠራሉ፡፡ መገለል፣ መሸሽና መነጠል እየተፈጠረም ሽብርተኝነት ከሕግና ሥርዓት የወጣ የኃይል ዕርምጃ ይዘወተራል፡፡ በመሆኑም ስሙ ይለያይ እንጂ ሁሉም ንፁኃንን የሚቀጥፍ፣ የአገርን ሀብት የሚያወድም፣ ሥጋትና አስፈሪነትን የሚፈጥር ተግባር ይሆናል፡፡ መሠረታዊያን (Fundamentalists)፣ ሥር ነቀሎች (Radicals)፣ አክራሪዎች (Fanatics)፣ የሃይማኖት ጦረኞችና ጀሃዲስቶች (Jihadists)፣ እስላማዊያን (Islamists)፣ ወዘተ እየተባሉ ቢጠሩም የሁሉም መንገድ መጠፋፋት ሆኗል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እ.ኤ.አ. ከ2004 እስከ 2013 ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ብቻ እንግሊዝ 400 የሽብር ጥቃቶች በአብዘኛው በሰሜን አየርላንድ ተፈጽሞባታል፡፡ እርግጥ ብዙዎቹ ሽብሮች አውዳሚ አልነበሩም፡፡ በአሜሪካ 131 የሽብር ጥቃቶች አጋጥመዋል፡፡ 20 የሚሆኑት አውዳሚዎች ነበሩ፡፡ በፈረንሣይ የቅርቡን የፓሪሱን የሽብር ጥቃት ሳይጨምር 47 የሽብር ጥቃቶች ተሰንዝረዋል፡፡ በአንፃሩ ኢራቅ ውስጥ 12,000 የሽብር ጥቃቶች ሲመዘገቡ፣ ከእነዚህ ውስጥ 8,000 ያህሉ አውዳሚዎች፣ ንብረትና ሕይወት የጠፋባቸው ናቸው፡፡ ሽብርተኝነት ዓላማው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ማኅበራዊ ግቦችን በፍረኃት፣ በማሸበርና በማስገደድ መቀዳጀት ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እስልምናን መጠለያ ያደረጉ አሸባሪዎች መብዛታቸው ነው ሁነቱን ከሃይማኖቱ ጋር ያስተሳሰረው፡፡

በየትኛውም ዓለም ቢሆን እስልምና ሰላም እንጂ ሽብርና ጥቃት አይደለም የሚባለው ግን ለአፍ ብቻ አይደለም፡፡ በተጨባጭ በሃይማኖታዊ ፍልስፍናውም ሆነ በሐዲስ በግልፅ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ውስጥ ደግነት፣ ሰላምና ፍቅር እንጂ ጥቃትና ጥላቻን የሚሰብክ ሕግጋት ያለመኖሩ ነው፡፡ አንድ ምሳሌን ወስደን ብንመለከት በእስልምና ዕምነት ውስጥ ከፍተኛ አክብሮትና ግምት ከሚሰጣቸው ግብረ ገባዊ እሴቶች (Moral Values) መካከል ይቅር ባይነት፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ መከባበርና መቻቻል የሚባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የሞራል እሴቶችን ሙስሊም የሆነ ሰው ሁሉ ቢያንስ በቀን አምስት ጊዜ በመደበኛ ሶላቱ (ስግደቱና ፀሎቱ) ውስጥ የሚገለጹ ናቸው፡፡

በድምሩ ይኼን ታላቅ የዓለም ሃይማኖት ተገን በማድረግ ዓለምን እያሸበረ ያለው ሽብርተኝነት ውስጡ ፖለቲካዊ ፍላጎት የገነቡበትና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ገፅታን የተላበሰ መሆኑ ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ የሽብርተኝነት ሰለባ ነች

ቀደም ሲል በዝርዝር ለመግለጽ እንደተሞከረው ዓለም አቀፉ ሽብርተኝነት በዋናነት እስልምናን ምሽግ አድርጎ የተለያዩ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች የሚስተናገዱበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም እስልምናን ‹‹ሱኒ›› እና ‹‹ሺአ›› በሚል ርዕዮት በመከፋፈሉ ወላፈኑ በእኛ አገር እስልምና ውስጥም መንፀባረቁ አልቀረም፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይ ሳዑዲ ዓረቢያ ነዳጅ ከተገኘ ካለፉት ሰባና ሰማኒያ ዓመታት ወዲህ፣ ፔትሮ ዶላሩን ለሃይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት የማዋሉ ዘመቻም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በአካባቢው ባሉት ሁለት ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች መካና መዲና ማዕከላት ድረስ የሃይማኖቱ አክራሪዎች የራሳቸውን ሕግ እያወጡ ኃይላቸውን በማጠናከር ‹‹ሙጥዋዕ›› የሚባሉትን ጢም አስረዛሚና ሱሪ አሳጣሪ የሃይማኖት ‹‹ፖሊሶች›› እስከ ማደረጀት ደርሰዋል፡፡ ወሃቢያን በማስፋፋትም ፀረ ውሃቢያና ፀረ ሳዑዲ ትምህርቶችን የሚያፍን ራቢጣ አል ኢስላሚያ የተባለ መቺ ኃይል እስከ ማቋቋም ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ይኼ አካሄድ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች እንዲስፋፋም ቢያንስ ላለፉት 25 ዓመታት ሠርተዋል፡፡

በአገራችን በተለይ ባለፉት አሥር ዓመታት ገደማ ውስጥ ውስጡን የሚደመጡ የዕምነት ተቋማት መቃጠል፣ የነባር መስኪዶች መፈራረስ፣ ከክርስትና ሃይማኖት አማኞች ጋር የመፋጠጥ ድርጊቶች ሁሉ መነሻው የወሃቢያ አስተሳሰብ መስፋፋት ነበር፡፡ መንግሥት ሕግና ሕገ መንግሥት ከሚፈቅድለት ውጪ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ከገባ መታረም ያለበት ነው፡፡ ይኼ ማለት ግን ሌላውን ዓለም እያመሰ እንዳለው ያለ የሽብርተኝነት ተግባር እንዲያቆጠቁጥ ዕድል ይሰጥ ማለት አይደለም፡፡

መንግሥት በአገሪቱ የፖለቲካ ሥልጣንን በአቋራጭ ለመጨበጥ የእስልምና ሃይማኖትን ተገን አድርገዋል የሚላቸው ወገኖች አሉ፡፡ በተለይ ከአወሊያ ትምህርት ቤት አንስቶ ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ገደማ በየመስኪዱ የተደበላለቀ ስሜት ሲንፀባረቅ ታይቷል፡፡ እስካሁንም ድርጊቱን መርተዋል የተባሉ ግለሰቦች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዞ ማረሚያ ቤት ይገኛሉ፡፡ ዛሬም ቢሆን ግን ጉዳዩን ‹‹ድምፃችን ይሰማ!›› በሚል መፍክር ውስጥ ለውስጥ የሚያራምዱት የእስልምና ሃይማኖት ወጣት ተከታዮች እንዳሉ መሸፈን አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይተዋል፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶችም እኩል ዕውቅና ያላቸው ሲሆን፣ ዜጎች የፈለጉትን የማመንና የማምለክ መብታቸውም ካለፉት ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ተቀይሯል፡፡ ከዚህ አንፃር ሃይማኖትን ምሽግ በማድረግ ለምን ወጣ ያሉና የከረሩ አስተሳሰቦች ማቀንቀን ጀመሩ ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በተለይ እስልምና ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ከዚያ በፊት ከነበሩት በእጥፍ የማምለኪያና የማስተማሪያ የዕምነት ተቋማትን ገንብቶ፣ በነፃና በራሱ በሃይማኖቱ መርሆዎች መሪዎቹን እየመረጠ፣ የተለያዩ አስተምሮዎችን በሲዲ፣ በመጽሐፍና በጋዜጣ በስፋት ማዘጋጀት እየተቻለ፣ ሴቶችና ወጣቶች በየትኛውም ቦታ መስገድ ሃይማኖታዊ ተግባራትን እየፈጸሙ፣ ስለምን የጨለማውን ዘመንና የጥፋቱን መንገድ የሚመኙ ወጣቶች አቆጠቆጡ? በማለት አጥብቆ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል፣ ሃይማኖታችን እንዳይስፋፋ ሆኗል፣ መሪዎቻችን በነፃነት መምረጥ አልቻልንም፣ የአገሪቱ መንግሥት ክርስቲያናዊ በመሆኑ ተፅኖ ተደርጎብናል፣ የዕምነት ተቋማትን ማስፋፋት አልቻልንም፣ አል-ሐበሻ የሚባል እስላማዊ አስተምህሮ ተጭኖብናል፣ አወሊያ የትምህርት ተቋም ለዋናው መጅሊስ መተላለፍ ትክክል አይደለም…›› የሚሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡

እነዚህና ሌሎች አስተሳሰቦች እንደ ጥያቄ መነሳታቸው ነውር አይደለም፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን ግን አፈታታቸው በውይይትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ሊሆን የግድ ነው፡፡ ያለበለዚያ በሁከት፣ በአመፅና በነውጥ ወይም ሌሎች ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን በማደናቀፍ ሊሆን አይገባም፡፡ ለምሳሌ ተሞክሮ እንደነበረው (በደሴ፣ በሶማሌ ክልል፣ በአርሲና ባሌ እንዲሁም በስልጤ አካባቢ) አለፍ ያለ ግብረ ሽበራ በመፈጸም አይደለም፡፡ ይኼ ከሆነም የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክም ሆነ የሌሎች የተለያዩ ዕምነቶች ተከታይ ሕዝብ አገር የሆነችው ኢትዮጵያ ፈረሰች፡፡ ኢራቅና አፍጋኒስታን ሆነች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ መታየት ያለበት በዚህ ደረጃ ነው፡፡

ሌላው ኢትዮጵያ አሁንም ለግበረ ሽበራ የተጋለጠች አገር ነች የሚባለው ተጠናክሮ የቀጠለው የዓለም አቀፍ እስላማዊ ሽብርተኝነት ዒላማ ውስጥ ያለች በመሆኗ ነው፡፡ ለዚህም በአንድ በኩል ያለንበት ቀጣና አስተዋፅኦ ያደረገ ሲሆን፣ ጽንፈኞች ‹‹የክርስቲያን ደሴት›› በሚል ታፔላ የምዕራባዊያንና የፅዮናዊያን እህት አገር አድርገው በመሳላቸው እንደሆነ የሚያስረዱ ብዙ አስተያየቶች አሉ፡፡

ከሶማሊያ መፈርጠም ጀምሮ የነበረው አልሸባብ መሪ አህመድ አብዲ ጎዳኔ (ከወራት በፊት በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ተገድሏል) በአንድ ወቅት የሰጠው መግለጫ አባባሉን ያረጋግጣል፡፡ አልሸባብ ሶማሊያዊያንን አስታጥቶ ለፍጅት ከመዳረጉም በላይ ከአፍጋኒስታን፣ ከፓኪስታን፣ ከአሜሪካና ከጀርመን እየመለመለ ባስገባቸው ሽብርተኛ ጀሌዎቹ በመመካት በተለይ ከካምፓላው የቦምብ ጥቃት በኋላ እንዲህ ብሏል፡፡ ‹‹በካምፓላ የደረሰው ጥቃት የመጀመርያው ነው፡፡ ገና ምን ዓይታችሁ ጦርነቱን በኬንያና በኢትዮጵያ ምድር እናደርገዋለን፡፡ አይደለም እዚህ ጎረቤት አሜሪካም እንድትለበለብ እናደርጋለን፡፡ ሸሪዓ በመላው ዓለም አገሮች ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ ጦርነቱ ሊያበራ አይችልም፤›› ነበር ያለው፡፡

ይህን ሰው ሞት ቢቀድመውም፣ አልሸባብም ተንኮታክቶ የመጨረሻዎቹ እስትንፋሶቹ መቆሚያ ሰዓት ላይ በደመ ነፍስ ቢወራጭም፣ ምኞቹ አንድ ነገር ያሳያል፡፡ ልክ እንደ አልቃይዳ፣ አይኤስ፣ ቦኮ ሐራም፣ የአፍጋኒስታን ታሊባንና ሌሎችም ሁሉ ተቀራራቢ ጽንፈኛና አውዳሚ ዓላማን የሰነቀ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን ከዘመናት ጦርነትና መተላለቅ ወጥተው ባለፉት ሃያ ዓመታት አገራቸው የተስፋ ጉዞ እንድትጀምር የረዳትን ዋንኛ ሰላም አሳልፈው ለመስጠት እንደማይፈልጉ መታወቅ አለበት፡፡ አልሸባብን ተረዳድቶ ጓዳ ጎድጓዳው ገብቶ መቀጥቀጥና ከምድረ ገጽ የማጥፋት ዘመቻ ቅዱስና ትክክለኛ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የክርስቲያንም የእስልምናም አገር ነች፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ ሕዝቦችም ሰላማቸውን የምንመኝላቸው ወገኖቻችን ናቸው፡፡ በየትም ሥፍራ ይገኝ በምንም ሰበብ ይነሳ ሽብርተኝነትን ግን ልንታገስም ሆነ ልንሽከም አይገባም፣ አይቻለንም፡፡  ፈጣሪ ለዓለም ሰላም ይስጣት! ኢትዮጵያንም ይጠብቃት!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles