Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትምህርት ያልቀናቸው

ትምህርት ያልቀናቸው

ቀን:

በሺቢያምፅ ደምሰው

ሰርኬ ለማ ትባላለች፡፡ ከደብረ ማርቆስ አዲስ አበባ የመጣችው ያሳደጓት አያቷ በመሞታቸው እየሠራች ለመማር ነበር፡፡ ወጣቷ ዘመዶቿ ቤት የምትኖር ጓደኛዋ ደላሎች ታገኛታለች፡፡ ደላሎቹም ስለሙያ፣ ተያዥ እንዳላት፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ ቀደም ብላ ሌሎች ቤቶች እንደሠራች እንደጠየቋት ትናገራለች፡፡

የእሷ ጥያቄ የነበረው ደግሞ ከ6ኛ ክፍል ያቋረጠችውን ትምህርት መቀጠል እንደምትፈለግና ደመወዝዋን ነው፡፡ ደላላውም የቤት ውስጥ አሠሪዎች የምትማር ሠራተኛ እንደማይፈልጉ ነገራት፡፡ ቀን ቀን እየሠራች የማታ መማር እንደምትፈልግ ገልጻለት እየሠራች የማታ የምትማርበትን ቀጣሪዎች እንዲያገኝላት ብትነግረውም፡፡ ደውሎ ከጠየቃቸው ግለሰቦች አንዳቸውም የምትማር የቤት ሠራተኛ እንደማይፈልጉ እንደገለፁላት ታስታውሳለች፡፡ በኋላ ሌሎችንም ደላሎች ከጓደኛዋ ጋር ሆነው ቢጠይቁም፤ የሁሉም ደላሎች ምላሽ ‹‹ቀጣሪዎች የምትማር የቤት ሠራተኛ አይፈልጉም›› ሆነባት፡፡ በመሆኑም የመማር ፍላጐቷን ገድባ ወደ ቤት ሠራተኝነቷ ገባች፡፡

ሰርኬ አዲስ አበባ ከመጣች ስድስት ዓመት ሆኗታል፡፡ እስካሁን ሦስት ቤቶች ሠርታለች፡፡ የገባችባቸውን ቤቶች ባለቤቶችም የማታ እንዲያስተምሯት መጠየቋንና አሠሪዎቿም ፈቃደኛ ሊሆኑላት እንዳልቻሉ ትናገራለች፡፡

ከልጅነት እስከ ወጣትነት የዕድሜ ክልል ያሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ወደ ከተማ ይመጣሉ፡፡ እንስቶቹ ከሚፈልጉት የሥራ ዘርፍ አንዱ የቤት ሠራተኝነት ነው፡፡ ይህንንም የሚፈለጉት ምክንያት የሚኖሩበት ቤት ስለሚያገኙና ሥራውንም በቀላሉ መሥራት ስለሚችሉ እንደሆነ የቤት ሠራተኛ አገናኞችን በጐበኘንበት ወቅት ያነጋገርናቸው ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶች ከመጡበት አካባቢ ያቋረጡትን ትምህርት አንዳንዶችም ያልጀመሩትን ትምህርት እየሠሩ ለመማር ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከአሠሪዎቻቸው አዎንታዊ ምላሽ እንደማያገኙ የሚናገሩት አሉ፡፡ ሰርኬ፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት የገጠማት ይሄ ነበር፡፡ በተለይ መጀመሪያ የገባችበት ቤት መማር እንደምትፈልግ ለሚያስተዳድሯት ወይዘሮ ስትነግራቸው ‹‹አንቺ ትምህርት ቤት ገብተሽ ሥራውን ማን ይሥራው፤ ደግሞ የት ለመድረስ›› እንዳሏት ታስታውሳለች፡፡

አቶ አንመን የሥጋት፣ አሠሪ እና ሠራተኛን በማገናኘት ለስድስት ዓመታት ያህል አዲስ አበባ ውስጥ ሠርቷል፡፡ እንደ አቶ አንመን ገለጻ፣ የቤት ሠራተኝነት ሥራ ፈልገው ወደ እሱ ጋር ከሚመጡት ብዙዎቹ ከገጠራማ አካባቢዎች የመጡ ናቸው፡፡ እየሠሩ መማር የሚፈልጉ ያጋጠሙት በጣም ጥቂቶች ቢሆኑም እነሱም ፍላጐታቸው እንዳልተሳካ ይገልጻል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ደንበኞቹ የልጅ ቤት ነው፣ አይመቸንም፤ ከብዙ ሰው ጋር ሲገናኙና የተሻለ አማራጭ ያለ ሲመስላቸው ድንገት ጥለውን ይሔዳሉ፡፡ የሚል ሥጋት ስላላቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ስርቆት ይለምዳሉ፤ የወንድ ጓደኛም ይይዙና አርግዘው ይጠፋሉ የሚል ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ ደመወዝም እየከፈልን አናስተምርም፣ የተሻለ ዕውቀት እና ችሎታ ሲኖራት ጥላን ትሄዳለች እንደሚሉ ይገልጻል፡፡

አቶ ደሳለኝ ታደለ አራት ዓመት ሠራተኛን እና አሠሪን በማገናኘት ሠርቷል፡፡ በሚሠራበት ሽሮ ሜዳ አካባቢ ሥራ ፈልገው ከሚመጡት ብዙዎቹ ደመወዝ ከመደራደር ውጪ እንዲያስተምሩዋቸው ወይም እየሠሩ መማር እንደሚፈልጉ እንደማይጠይቁት ይናገራል፡፡ አንዲት የቤት ሠራተኛ ብቻ እየሠራች የማታ መማር እንደምትፈልግ እንደጠየቀችው አስታውሶ፣ ለእሷም ብዙ ሰዎች ጋር ከተደዋወለ በኋላ በቅርብ ትዳር የመሠረቱ ጥንዶች ቤት እንዳስቀጠራትም ይገልጻል፡፡

የቤት ሠራተኛን በማታውም ሆነ በቀኑ መርሐ ግብር ትምህርት ገበታ ለማስገባት እንደሚቸገሩ አንዳንድ ያነጋገርናቸው ግለሰቦች ይናገራሉ፡፡ ቦሌ 22 አካባቢ ያነጋገርኳቸው ባለትዳሮች፣ የቤት ሠራተኛ እንዳላቸው ሆኖም እንደማያስተምሯትም ተናግረዋል፡፡ እንደ ምክንያትም ያነሱትም ሁለቱም ባለሥራ መሆናቸውን እና ከሥራ ሰዓት መልስም የማታ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ መሆናቸውን ነው፡፡ ጥንዶቹ ቤት ውስጥ የአራት ዓመት እና የስምንት ዓመት ልጆቻቸውን በተለይ ከትምህርት ቤት ሲመጡ ተቀብሎ የሚንከባከባቸው ሰው ስለሚያስፈልግ የቀጠሯትን ሠራተኛ ለማስተማር እንደሚቸገሩም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ማንኛውም ሰው ቢሆን ደክሞት ከውጪ ሲመጣ አስፈላጊውን ሁሉ የሚታዘዘው ሰው ይፈልጋል፤ የተቀጣሪ ሠራተኞች አስፈላጊነት አንድም በዚህ ምክንያት ነው፣ ደመወዝ የሚከፈለውም ለዚሁ ነው፤›› ይላሉ፡፡

አንዳንድ የቤት ሠራተኞች ደግሞ ሥራ እየሠሩ እንዲማሩ ከአንዳንድ አሠሪዎች ይሁንታን ቢያገኙም፤ ትምህርታቸውን ሲማሩ ተፅዕኖ እንደሚፈጠርባቸው ይገልጻሉ፡፡

ወጣት አስካለም የገጠማት ይኸው ነበር፡፡ ወጣቷ ቀን ቀን የቤት ሥራዋን አጠናቅቃ ማታ እንድትማር አሠሪዎቿ ፈቅደዋል፡፡ በዚህም እንጦጦ አምባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ4ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ ትምህርት በጀመረችበት ወቅት በሰዓቱ ወደ ትምህርት ቤት እየሄደች መማር ችላ ነበር፡፡ ከወራት በኋላ ግን ‹‹ለምን ሥራሽን ሳትጨርሺ ሔድሽ፣ እስካሁን ለምን አመሸሽ፣›› እና ሌሎችም ጥያቄዎችን እያነሳች አሠሪዋ ትናገራት ጀመር፡፡ ‹‹ትምህርት ቤት ሔጄ  በመጣሁ ቁጥር ትናገረኛለች፡፡ ይባስ ብላ ደመወዝሽን አስተካክይ የሥራ ጫና ስለሌለብሽ በማለት ደመወዜን በራሷ ፈቃድ ቀነሰችብኝ፡፡ ራሴን ለማሻሻል ፍላጐቱ ስለነበረኝ ሁሉንም ነገር ችዬ እየተማርኩ ሳለሁ አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ስገባ ‘ወይ ሥራሽን ወይ ትምህርትሽን ምረጪ’ አለችኝ፡፡ እኔም በማግሥቱ ዕቃዬን ይዤ እንዲያሰናብቱኝ ጠየቅኳቸው፡፡ የሠራሁበትን ደመወዜን ሳትከፍለኝ ዕቃዬን ፈትሻ ‘መሄድ ትችያለሽ’ አለችኝ፤›› ትላለች፡፡ በዚህ ምክንያት ትምህርቷን ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት እንዳቋረጠች እና ከዚያም በኋላ በሠራችባቸው ቤቶች የመማር ዕድሉን ጠይቃ እንዳልተሳካላት፣ ሽሮ ሜዳ ከደላሎች ጋር ስትነጋገር ያገኘናት ወ/ሪት አስካለ ትገልጻለች፡፡

በእንጦጦ አምባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአደረጃጀት እና የትምህርት ፕሮግራሞች ክትትል ምክትል ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ስማቸው ጥላሁን፣ በትምህርት ቤቱ በማታ መርሃ ግብር የሚማሩት የቤት ሠራተኞች ቁጥር አናሳ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የመማር ዕድሉን አግኝተው ትምህርት ቤት የሚገቡት አንዳንድ የቤት ሠራተኞችም የተለያዩ ተፅዕኖዎች እንደሚደርስባቸው ይገልጻሉ፡፡ ብዙዎቹ ተማሪዎች የቤት ሥራዎችን የሚሠሩበት ብሎም የሚያጠኑበት ጊዜ እንደማያገኙ፣ ቤት እንደገቡ አሠሪዎቻቸው ብዙ ሥራ አዘጋጅተው እንደሚጠብቋቸው፣ አምሽተው ለመሥራትም የሥራው ድካም ተፅዕኖ እንደሚፈጥርባቸው እንደ ምክንያት እንደሚያቀርቡ ይገልጻሉ፡፡

ከትምህርት ቤት ከወጡ በኋላ እርስ በእርሳቸው የመገናኘት ዕድል ስለሌላቸው የቡድን ሥራ እንደማይሰጣቸው፣ ይህም አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር ዕውቀታቸውን እንዳይለዋወጡ እንደሚያደርጋቸው ምክትል ርዕሰ መምህሩ ይናገራሉ፡፡

ብዙዎቹ የቤት ሠራተኞች በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን እስከመጨረሻው አያጠናቅቁም፡፡ ለዚህም ሠራተኞቹ የሚሠሩበት ቤትን በየጊዜው መቀያየራቸው፣ ቀጣሪዎቻቸው ሊያስተምሯቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸው እንዲሁም በሚሠሩበት ቤት ውስጥ ከአሠሪዎች ጋር በተደጋጋሚ የሚደረግ ጭቅጭቅ ከትምህርታቸው እንዲስተጓጎሉ ማድረጉ እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡

የምትማር የቤት ሠራተኛ የማይፈልጉ እንዳሉ ሁሉ፣ ለልጆቻቸው የሚያደርጉትን እንክብካቤና ድጋፍ ለቤት ሠራተኞቻቸውም የሚያደርጉ አሉ፡፡ ወ/ሮ አልማዝ ተሻለ የባህላዊ አልባሳት ነጋዴ ናቸው፡፡ የሚያስተምሯት፣ ለልጆቻቸው የሚያደርጉላቸውን ሁሉ የሚያደርጉላት በቤታቸው ውስጥ ለአምስት ዓመት የቆየች የ7ኛ ክፍል ተማሪ የቤት ሠራተኛ እንዳለቻቸው ይገልጻሉ፡፡ የቀጠሯት ሠራተኛ እሳቸው ቤት ስትመጣ ከ4ኛ ክፍል አቋርጣ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ያስገቧትም ልጅቷ ጠይቃቸው ሳይሆን እሳቸው ባቀረቡላት ሐሳብ ነው፡፡ ወ/ሮ አልማዝ የሚያስተምሯት ሠራተኛቸው በአሁኑ ጊዜ ቤት ውስጥ ያሉትን ሁለት ልጆች ከመንከባከብ በተጨማሪም የቤት ሥራቸውን እንደምታሠራቸው፣ እንደምታስጠናቸው፣ በትምህርቷም የደረጃ ተማሪ መሆኗን ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የቤቱን ሥራ ተጋግዘው መሥራታቸውና የምታጠናበት ጊዜ በማግኘቷ ነው፡፡

‹‹የምናስተዳድራቸው ሠራተኞች ተምረው፣ ተሻሽለው የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ማድረግ የዜግነት ግዴታችን መሆን አለበት፤›› የሚሉት ወ/ሮ አልማዝ፣ ‹‹እንደ ልጆቼ የማያትን ልጅ ከዳር ደርሳ የማየት ህልሙ አለኝም፤›› ይላሉ፡፡

የቤት ሠራተኞች እየተማሩ የሚሻሻሉበት፣ የተሻለ ገቢ እና ዕውቀት የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት የአሠሪዎች ኃላፊነት መሆን አለበት የሚሉት ደግሞ አቶ ሳሙኤል ዘሪሁን ናቸው፡፡ አቶ ሳሙኤል በኢትዮጵያውያን ላይ በየአገሩ ለሚፈጸመው አሰቃቂ ጥቃትም አንድም የኅብረተሰቡ ተፅዕኖ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በየዓረብ አገሮች በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርስ በደልና ጥቃት ስንሰማ ከንፈር ከመምጠጥ እና እንባን ከማፍሰስ በዘለለ እኛም እዚህ በእህቶቻችን ላይ የምንፈጽመው በደል ሊሰማን ይገባል፡፡ እራሳችንን ማየት አለብን፡፡ እህቶቻችንን ለስደትና ለእንግልት የምንዳርጋቸው እኛው ነን፡፡ ጉልበታቸውን እንበዘብዛለን፣ ደህና መቀየሪያ ልብስ ገዝተው ቤተሰቦቻቸውን እንኳን የሚረዱበት ትንሽ ገንዘብ አይተርፋቸውም፡፡ ብዙዎች መማር እየፈለጉ በፍራቻ ዝም ይላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ‘አስተምሩን’ ሲሉ ‘የቀጠርኩሽ የቤት ሥራን እንድትሠሪ እንጂ ላስተምርሽ አይደለም’፤ ይባላሉ፡፡ ልጆቻቸው በሰው አገር በደረሰባቸው ሥቃይ መሬት አልበቃ የሚላቸው፣ ለምን በአገራቸው ዜጋ ላይ የሚፈጽሙት በደል እና ስቃይ አልታይ አላቸው?›› በማለትም ጥያቄ ይነሳሉ፡፡   

የቤት ሠራተኞች ያላቸው ሙያ በዕውቀት ቢደገፍ ከራሳቸው አልፈው ለሚያገለግሉት ቤተሰብም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ከቤት ሠራተኞች ጋር በተያያዘ የሁለተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ጽሑፏን ያዘጋጀችው ወ/ሪት አቤኔዘር አሰፋ ትገልጻለች፡፡

የቤት ሠራተኞች ትምህርት ቤት ገብተው ቢማሩ ከአሠሪዎቻቸው ጋር በቀላሉ መግባባት ይችላሉ፡፡ የተሻለ ንቃተ ህሊና ይኖራቸዋል፡፡ የቤት ሠራተኞች ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ከጥቅም ውጪ የሚያደርጓቸው አንዳንድ ንብረቶችንም ማዳን ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የቤት ሠራተኞች በአሠሪዎቻቸው የመማር ዕድልም እንደማያገኙ ትገልጻለች፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሱት፣ የአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሥራ ጫና ጋር በተያያዘ ቤታቸውንም ሆነ ልጆቻቸውን ለሠራተኞች ኃላፊነቱን መስጠታቸው፣ ጥቂት የማይባሉ አሠሪዎች ለሠራተኞች ፍላጐት ትኩረት አለመስጠት፣ የራስ ጥቅምን ብቻ ማሰብ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘታቸው የተለያዩ ችግሮችን ይፈጥርብናል ከሚል ሥጋት፤ እንዲሁም የቤት ሠራተኞቹ ወደ ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር ፍላጐቱ በራሱ አናሳ መሆን፣ ወደ ትምህርት ቤት የሚገቡትን የቤት ሠራተኞች ቁጥር ውስን እንደሚያደርገው ወ/ሪት አቤኔዘር ትገልጻለች፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...