Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልኤፍኤሞችን ያደመቁ ዲጄዎች

ኤፍኤሞችን ያደመቁ ዲጄዎች

ቀን:

ፍሬሕይወት ታደሰ (ዲጄ ሊ) በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በሚተላለፈው ሄሎ ሌዲስ ዝግጅቷ ትታወቃለች፡፡ ዝግጅቱ ዋነኛ ትኩረቱን ፊልምና ሙዚቃ አድርጎ  ሌሎችም ኪነ ጥበባዊ ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡ እንደ እሷ ገለጻ፣ በመገናኛ ብዙኃን የሚሰራጩ መርሐ ግብሮች በብዛት በወንዶች የሚመሩ ሲሆን፣ ሴቶች እንደ ማጀቢያ ይካተታሉ፡፡ ሴቶች የመሪነት ሚና የሚጫወቱበት ዝግጅት ባለማስተዋሏ ሄሎ ሌዲስ የጀመረች ሲሆን፣ በሴት አዘጋጆች እየተመራ ሴቶች የሚያልፉበትን ውጣ ውረድና ስኬት የሚያንፀባርቁ ዜናዎች ያስደምጣል፡፡

የሬዲዮ ጣቢያዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ እንደ ሄሎ ሌዲስ በዲጄ (ዲስክ ጆከሪ) የሚመሩ መርሐ ግብሮችም በየጣቢያው ተበራክተዋል፡፡ የአየር ሰዓት ገዝተው ዝግጅት ከሚያቀርቡ ዲጄዎች ውጪ በተለያየ መርሐ ግብር ሙዚቃ ለመጋበዝ የሚገቡ ዲጄዎች አሉ፡፡

ዲጄ ሊ ራፐር ከመሆን ተነስታ በክለብ ዲጄነት ለሁለት ዓመት ከሠራች በኋላ ነው ወደ መገናኛ ብዙኃን የመጣችው፡፡ ቀድሞ የዲጄ ኪንን ዝግጅት ትከታተል ነበር፡፡ የሬዲዮ ዲጄ የመሆን ፍላጎቷ መሠረትም የሱ ዝግጅት እንደሆነ ትናገራለች፡፡ በሬዲዮ አምስት ዓመት ያስቆጠረችው ዲጄዋ፣ ሴት ዲጄ ለመቀበል የሚያስቸግራቸው እንዳሉ ሁሉ ‹‹የሴት ዲጄ›› ብለው በመገረም ቶሎ ዲጄዋን የሚያገኑም አሉ ትላለች፡፡

 የሬዲዮ ዲጄነት በገቢ አንፃርና በሥራ ሒደት ከሌሎች ዲጄዎች ስላለው ልዩነት  ጠይቀናት ነበር፡፡ እሷ እንደምትለው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዲጄዎች ጥረት ለውጥ ቢታይም የዲጄ ዝግጅቶችን ስፖንሰር ለማድረግ የማይፈቅዱ ተቋሞች ብዙ ናቸው፡፡ አሁን ዝግጅቶቹ ተደማጭ መሆናቸውን ስለተገነዘቡ ስፖንሰር እየሆኑ ነው፡፡ ዲጄዎችን ወደ መገናኛ ብዙኃን ሲመጡ የተለየ ድባብ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከነዚህ አንዱ ታዳሚን ፊት ለፊት እያዩ ሙዚቃ መምረጥ አለመቻላቸው ነው፡፡ ለታዳሚው የሚሆነውን ሙዚቃ አስቀድመው ተገንዝበው ስሜቱን መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡ ዲጄዎች የብዙኃኑን ስሜት የሚኮረኩሩ ሙዚቃዎችን የማወቅ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑ የሬዲዮ ተደማጭነታቸውን አስፍቶታል ብላ ታምናለች፡፡ በዲጄዎች የሚመሩ ዝግጅቶች ከሙዚቃ ባለፈ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አዘውትረው አይዳስሱም የሚል አስተያየት ይደመጣል፡፡ በዚህ ረገድ ምንም እንኳን ሙዚቃው ጎልቶ ቢታይም ለአድማጮች መረጃ መስጠት አስፈላጊነቱንም ሳትጠቅስ አላለፈችም፡፡

ማንኛውም የሬዲዮ አዘጋጅ ሊገጥመው ቢችልም የኮፒራይት ችግር ለዲጄዎችም  አንዱ አሉታዊ ነገር የሆነው የአንድ ሙዚቃ ባለቤት እውቅና ሳይሰጥ በድጋሚ የሚሠሩ ዘፈኖች በተደጋጋሚ መደመጣቸው ነው፡፡ እንደ ዲጄዋ አገላለጽ፣ ጥንቃቄ የሚገባው በኮፒ ራይት ብቻ ሳይሆን በዘፈኖች መልዕክት ጭምርም ነው፡፡ አደንዛዥ ዕፅና ሌሎችን የሚያስተዋውቁ ሙዚቃዎች በሬዲዮ ተለቀው መስማቷን ተገቢ እንዳልሆነ ትጠቅሳለች፡፡

ሌላው የሬዲዮ ዲጄ ይግረም ስንታየሁ (ዲጄ ቤቢ) በዛሚ ኤፍ ኤም 90.7 የአዲስ ሚውዚክ አዘጋጅ ነው፡፡ በ2001 ዓ.ም. ወደ ሬዲዮ ከመምጣቱ በፊት በክለቦችና በተለያዩ መድረኮች ሠርቷል፡፡ እንደ ዲጄ ሊ ሁሉ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ብቸኛ ሬዲዮ ጣቢያ በነበረበት ጊዜ የታወቁ ዲጄዎችን  መነሻው አድርጓል፡፡ ዝግጅቱ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ያሉ አንጋፋዎችን እየዘከረ ለአማተሮች ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ ያመቻቻል፡፡ በመዝናኛ ዘርፍ ያሉ ወቅታዊ መረጃዎችንም ያቀብላል፡፡

የሬዲዮ ጣቢያዎች ቁጥር መጨመሩ የመዝናኛ ወይም ሌላ ይዘት ያለው ዝግጅትን ከሙዚቃ ጋር አዋሕደው ለሚያቀርቡ ዲጄዎች መድረክ እንደሰጠ በማስረገጥ፣ የሬዲዮ ዲጄነት ከሌሎች ያለውን ልዩነት ያብራራል፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሰው የሠርግ ዲጄነት፣ በሠርግ የተለመዱ ዘፈኖች የሚከፈትበት ነው፡፡ በሠርግ ላይ ዲጄው የሚያጫውታቸውን ሙዚቃዎች ማን ሊታደም እንደሚችል ለማወቅ ይችላል፡፡ ወደ ሬዲዮ ሲመጣ የአድማጩ ዕድሜና አመለካከት ልዩነት ሙዚቃ ምርጫው ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ይላል፡፡ በተጨማሪም በሙዚቃ ምርጫ ወቅት ሬዲዮ ኤዲት የሆኑ ሙዚቃዎችን መለየት አስፈላጊ ስለሆነ የሬዲዮ ዲጄነት ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡

ከሙዚቃ መረጣ ጋር በተያያዘ በአንድ ሳምንት ከአንድ ቀን በላይ ዝግጅቶች ሲኖሩ የተለያየ ዓይነት ዘዬ ያላቸው ሙዚቃዎች ለማሰማት ይቻላል፡፡ የአድማጮችን ምላሽ በአጭር የጽሑፍ መልዕክትና በስልክ ጥሪ ከሚገኘው አስተያየት መረዳት እንደሚቻልና ከጊዜ በኋላ የብዙኃኑን ስሜት ያማከሉ ሙዚቃዎች መለየት እንደሚለመድ ያምናል፡፡

የዲጄዎች አቀራረብ በሬዲዮ የሚተላለፉ መልዕክቶችን አለሳልሶ ተደማጭ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ዲጄ ቤቢ ይናገራል፡፡ ሙያው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቀባይነቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ ዲጄዎች የሚያገኙት ገቢም የዛኑ ያህል እየዳጎሰ ነው ይላል፡፡ ሙያው በኢኮኖሚ ያደጉ የሚባሉ አገሮች መስፋፋቱን የሚናገረው ዲጄው፣ በኢትዮጵያ ብዙ የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ ያስረዳል፡፡ አሁን በአንድ ጣቢያ ሁለትና ከዛ በላይ ዲጄዎች መኖራቸው አበረታች ቢሆንም በቂ አይደለም ይላል፡፡

የሬዲዮ ዲጄዎች ካላቸው ሚና አንፃር ቁጥራቸው መጨመር እንዳለበት የሚስማማው ሼሪ መስፍን (ዲጄ ሼሪ) በሸገር 102.1 ከሚተላለፈው ታዲያስ አዲስ ዝግጅት በተጨማሪ በተለያዩ  ተቋማት ክለቦች ይሠራል፡፡ ከትምህርት ቤት ሚኒሚዲያ ተነስቶ በቤት ውስጥ ፓርቲዎች ሙዚቃ በማጫወትና የክለብ ሥራዎችን እየሠራ በዲጄነት 16 ዓመት ቆይቷል፡፡ አስተያየት ከሰጡን ዲጄዎች ጋር የሚጋራው ሌላው ሐሳብ በሬዲዮ ዲጄነት የታዳሚን ስሜት በቀጥታ ለማየት ስለማይቻል በመጠኑ ፈታኝ መሆኑ ነው፡፡

የሬዲዮ አድማጭ በቁጥር ብዙ በዓይነትም የተለያየ ከመሆኑ አንፃር የእያንዳንዱን ፍላጎት ለመረዳት ሊያስቸግር ይችላል ይላል፡፡ ስለዚህ ዲጄዎቹ በብዙኃኑ የሚወደድና አዳዲስ ዘፈኖች ላይ ያተኩራሉ፡፡ ከሱ ተሞክሮ በመነሳት በሬዲዮ ሙዚቃዎችን በተከታታይ ሚክስ አድርጎ ማቅረብ ስለማይቻል ከክለብ ይለያል ይላል፡፡

በመገናኛ ብዙኃን ከአዳዲስ መረጃ ባሻገር የተለያዩ ጉዳዮች እየተነሱ ውይይት ይደረጋል፡፡ እንደ ዲጄው ገለጻ፣ የአየር ሰዓት ሙሉ በሙሉ ከአንድ ጣቢያ የሚወሰዱ ዲጄዎች ልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮችን ቢቃኙ ይመረጣል፡፡ በተቃራኒው በሌላ ሰው መርሐ ግብር የሚገቡ ከሆነ ትኩረታቸው ሙዚቃው ላይ ብቻ ሲሆን፣ ውጤታማ ይሆናሉ ይላል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ የሬዲዮ ዲጄነትን ከአንድ አገር የሥልጣኔ ደረጃ ጋር አያይዞ መመልከት ይቻላል፡፡ ዘመን አመጣሽ መሣሪያዎችን በመጠቀምም ይሁን መደበኛ ትምህርት በመከታተል የተሻሉ አገሮች የሬዲዮ ዲጄነትን የተራቀቀ ገጽታ አላብሰውታል፡፡ በሌሎች አገሮች በእያንዳንዱ የሙዚቃ ዘዬ የተካኑ (ማስተር ያደረጉ) እና ሙሉ ጊዜአቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ያዋሉ ዲጄዎችም አሉ፡፡ እነዚህ ዲጄዎች ሁሉንም ዓይነት ሙዚቃ ከሚያጫውቱ ዲጄዎች የተሻለ እንደሚሠሩ እሙን ነው ይላል፡፡ ዲጄዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታየው በክለብ፣ በሠርግ ወይም በሌላ ሥራ ሳይወጠሩና በአንዱ ዘርፍ ሲያተኩሩ ፍሬያማ እንደሚሆኑ ያክላል፡፡

የሬዲዮ ዲጄነት ገቢ በከፊል ስፖንሰሮች ላይ ይመረኮዛል፡፡ በክለብ ወይም በሠርግ በሰዓታት የሚገኘው ገንዘብ ከሬዲዮ ጋር ለማወዳደር እንደሚያስቸግር ገልጾ፣ ዝግጅቶችን ተደማጭ እንዲሆኑ ማድረግ እስከተቻለ ድረስ ዲጄዎች ስፖንሰር ለማግኘት አያዳግታቸውም ይላል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰው ዝቅተኛ አመለካከት በመለወጡ በመጠኑ መንገዱን ምቹ እንዳደረገላቸው ያስረዳል፡፡

ተስፋዬ ገብረእግዚ (ፕሮሞተር ቤቢ) በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሚተላለፈው አበሻ ሁድ ዝግጅት ፕሮሞተር ነው፡፡ መዝናኛና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚያነሳው መርሐ ግብሩ አራት ዓመት አስቆጥሯል፡፡ እሱ የዲጄዎች ዝግጅቶች  ሙዚቃ ላይ ማተኮር አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ አድማጭ በተከታታይ መረጃ ይፈልጋል በሚል ልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮች ይነሳሉ፡፡ ጉዳዮቹ ግን ከአየር ሰዓቱ አብላጫውን ጊዜ እንደሚወሰዱ ገልጾ፣ ሙዚቃው የበለጠ ቢጎላ እንደሚመርጥ ያስረዳል፡፡

አንዳንድ ዝግጅቶች የሚተላለፉበትን ሰዓት ያላገናዘበ የሙዚቃ ምርጫና መስመሩን የለቀቀ የማስታወቂያ ሰዓት ድልደላ ይታይባቸዋል ይላል፡፡ ዲጄዎች አዳዲስና ጥሩ ሙዚቃዎችን ለአድማጭ በማስተዋወቅ እንዲሁም ጊዜ የማይቀይራቸው የሚባሉ ጥዑመ ዜማዎችን ለማስደመጥ የሚያስችል ሙያዊ ብቃት እያላቸው ዝግጅታቸውን በማስታወቂያ ሲፈጁ ይታያል፡፡ ስፖንሰሮችን ከተመደበው ሰዓት በላይ ማስተዋወቅና ምርቶችን በተዛባ መልኩ ማቅረብ መቅረት አለባቸው ከሚላቸው ጥቂቱ ናቸው፡፡

በሬዲዮ ዲጄነት ሙዚቃ ከሚሰጠው ሰፊ ጊዜ ውጪ ባለው ክፍተት ኪነ ጥበባዊ ይዘት ያላቸው መረጃዎችን እንዲያቀርቡ ያሳስባል፡፡ ከኪነ ጥበብ ውጪ የሆኑ አያሌ ጉዳዮች አንስተው የሚያወያዩ ጋዜጠኞችና ሌሎች ባለሙያዎች የሚያቀርቡት ዝግጅት በየጣቢያው ስላለ ዲጄዎች ሙዚቃው ላይ ቢያተኩሩ ይሻላል ይላል፡፡

በጉዳዩ ካነጋገርናቸው አንዱ የዲጄዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አሮን ከበደ (ዲጄ አሮን) ነው፡፡ የኤፍኤም ጣቢያዎች ሥራ በጀመሩበት ወቅት ብዙውን አየር ሰዓት የወሰዱና ጣቢያዎችንም ያስተዋወቁ ዲጄዎች እንደሆኑ ይናገራል፡፡ ማንኛውም ሰው ከሚያሰማው ሙዚቃ በተለየ የዲጄዎች ሙዚቃ ምርጫ ተመራጭ እንደሚሆን ከሙያ አጋሮቹ ጋር ይስማማበታል፡፡ ከቀደምቱ ዲጄ ዚ፣ ዲጄ ፒንክ፣ ዲጄ ሮክሲ፣ ዲጄ ኪንና ሌሎችም በዘርፉ ተጠቃሽ ናቸው ይላል፡፡

ዲጄነት በኢትዮጵያ በክለብ፣ በስቱዲዮ፣ በሬዲዮም ይሁን በሌላ ዘርፍ የሚሠራው በልምድ መሆኑ ሙያውን እንደሚጎዳው ይገልጻል፡፡ ማኅበር መመሥረቱ የዲጄዎችን ጥቅም በማስከበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግሮ፣ በተለይም በቅርብ የፀደቀውን የሮያሊቲ ክፍያ ከሬዲዮ ዲጄዎች ጋር አያይዞ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ አሠራሩ የሬዲዮ ዲጄዎች እንደሌሎች ዲጄዎች ያሉባቸው ኃላፊነቶች እንዲወጡ ያስገድዳል፡፡ ዲጂዎቹ ሙዚቃውን ለማጫወት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ መገናኛ ብዙኃን የሚከፍሉ ሲሆን፣ አሠራሩ አዳዲስ ሙዚቃዎችን በማስተዋወቅ የሚጠቅም ይሆናል ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...