Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዲኤንኤ ዋጋ በፍትሕ ሥርዓት

የዲኤንኤ ዋጋ በፍትሕ ሥርዓት

ቀን:

ሳይንስ ለሕዝቡ ካበረከታቸው ስጦታዎች ማንነት የሚለይበት ዲኤንኤ ምርመራ አንዱ ነው፡፡ ዲኤንኤ በማንኛውም የሰውነት ሕዋስ በደም፣ በዘር ፍሳሽ፣ በፀጉር፣ በምራቅና በመሳሰሉት ውስጥ ይገኛል፡፡ የዲኤንኤ ውጤት ውስብስብ የወንጀል ጉዳዮችን ለማወቅ፣ የአባትነት ጥያቄን ለመመለስ ሲውል በጤናው ረገድም ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡

የዲኤንኤ ዓይነትን በመለየትም ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎች፣ በዘር የሚተላለፉ በሽታዎች፣ የፅንስ ጤንነትና ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ምን ዓይነት በሽታ ሊይዙት እንደሚችሉ እንዲሁም በሽታዎችን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ይህ የሳይንስ ውጤት በአገር ውስጥ ተደራሽነቱ እጅግ ውስን ነው፡፡ ስለ ዲኤንኤ በቂ ግንዛቤ ያላቸውን ሰዎች ማግኘትም ከባድ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የዲኤንኤ ቀመር የተገኘው እ.ኤ.አ. በ1985 አሊስ ጄፍሪ በተባለ የእንግሊዝ ሳይንቲስት ነው፡፡ ምርምሩ ከተጠናቀቀ ከአንድ ዓመት በኋላ በአገሪቱ በፍርድ ሒደት ላይ የነበረውን አወዛጋቢ የግድያ ወንጀል ለማጣራት በሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ ወንጀለኛውን በቀላሉ ለመለየት ረድቷል፡፡ በቀጣይም የነፍስ ግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ተጠርጣሪን በዲኤንኤ ለማወቅ ችለዋል፡፡ በመረጃነት ተይዘው የቆዩ ሕዋሳዊ መረጃዎች ከያሉበት ወጥተው እንዲመረመሩ በማድረግም በስህተት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ከእሥር ቤት የሰነበቱ ንፁሐንን ነፃ እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል፡፡

ዛሬ ላይ የፍትሐ ብሔርም ሆነ የወንጀል ጉዳዮችን በማረጋገጥ ረገድ የዲኤንኤ ምርመራ ግንባር ቀደም መረጃ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ከመንትዮች በስተቀር ተመሳሳይ የዲኤንኤ ዓይነት ስለማይከሰት ወንጀለኞችን ከመሀል መንጥሮ በማውጣቱ ረገድ የተመሰገነ ነው፡፡

በአገሪቱ ሕጎች በመረጃነት ከተያዘም ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፡ በወንጀል ሕጉ እና በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በተለይም የአባትነት ጥያቄን በተመለከተ እንደ መጨረሻ የማረጋገጫ መረጃ የሚወሰደው የዲኤንኤ ምርመራ ውጤት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተደራሽነቱ የራቀ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል አይታይም፡፡ ነገር ግን ከሌሎቹ በተሻለ መልኩ በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች የአባትነት ጥያቄን ለመመለስ ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡

በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚገኘው የሕፃናት የሕግ ከለላ ማዕከል ያገኘናቸው ጉዳዮችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡ በማዕከሉ ጥቂት የማይባሉ በዲኤንኤ የተረጋገጡ የአባትነት ጥያቄዎች ለማየት ችለናል፡፡ ካየናቸው መካከልም አንዱ እንደሚከተለው ተቀምጧል፡፡

ምንም እንኳ በመካከለቸው ሕጋዊ ጋብቻ ባይፈጽሙም እንደ ባልና ሚስት በአንድ ጎጆ መኖር ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ መጠነኛ ንብረት ያፈሩ ሲሆን፣ አንድ ልጅም ወልደዋል፡፡ በጎረቤቶች ዘንድም እንደ ባለትዳር ይታዩ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት በመካከላቸው በተከሰተው አለመግባባት ተለያይተው መኖር ጀመሩ፡፡ ልጁ ከወላጅ እናቱ ጋር ይኖር ስለነበር፣ ወላጅ አባቱ የተወሰነ ቀለብ ይሰፍርለት ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ ሳይገፋበት በመሀል አቋረጠው፡፡

በሁኔታው ግራ የተጋባችው እናትም የልጁን ቀለብ እንዲሰጥ ብትወተውተውም አሻፈረኝ አለ፡፡ በመጨረሻም ‹‹የልጁን ቀለብ እንዲቆርጥ›› በሚል  ክስ መሠረተች፡፡ በክሱ መሠረት ቃል እንዲሰጥ የቀረበው አባትም ‹‹ልጄ አይደለም›› ሲል ካደ፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ ልጁ የልደት ሠርቲፍኬት አልነበረውም፡፡ ስለዚህም የተጠርጣሪው ልጅ ስለመሆኑ በቅርበት የሚያውቋቸው ጎረቤቶቻቸው ምስክርነታቸውን ሰጡ፡፡ ነገር ግን አባትነቱን ሊያምን አልቻለም፡፡

ስለዚህም ፍርድ ቤቱ አባትነቱ በዴኤንኤ ምርመራ እንዲረጋገጥ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡  ነገር ግን ግለሰቡ ለመመርመር ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ክርክሩ እልባት እስኪያገኝ ድረስም የሕፃኑ ፍላጎት መሟላት አለበት በሚል ፍርድ ቤቱ ለሕፃኑ ጊዜያዊ ቀለብ እንዲሰጥ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ትዕዛዙ እንዳስከፋው በመግለጽም ‹‹አባትነቴ ሳይረጋገጥ ቀለብ እንድቆርጥ ትዕዛዝ ተላልፎብኛል፤›› ሲል ይግባኝ ጠየቀ፡፡ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱም የግለሰቡ ዲኤንኤ ውጤት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ በመግለጽ የዲኤንኤ ምርመራ እንዲያደርግ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡

የአባትነት ጥያቄውን የማስረዳቱ ግዴታ በከሳሽ (በእናት) ላይ ነበር ያለፈው፡፡ ነገር ግን ቴክኖሎጂው ገና በኢትዮጵያ ውስጥ ባለመጀመሩና ምርመራውን በውጭ አገር ለማድረግ አቅማቸው ስለማይፈቅድ ጉዳዩን ለሕፃናት የሕግ ከላለ ማዕከል አቀረቡ፡፡ ማዕከሉም ምርመራውን በራሱ ወጪ 5,000 ብር በመክፈል በደቡብ አፍሪካ አከናወነ፡፡ የግለሰቡም አባትነት ተረጋገጠ፡፡

እንደ ማዕከሉ የፕሮጀክት ኦፊሰር ቤተልሔም ቲቶ ገለጻ፣ ተመሳሳይ ጉዳዮች በየጊዜው ወደ ማዕከሉ ይመጣሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ሰዎችም አቅሙ ስለሌላቸው አገልግሎቱን በነፃ ወይም በከፊል ክፍያ እንዲያገኙት ይደረጋል፡፡ ብዙ ጊዜም አቅሙ ያላቸውና አባትነታቸው የተረጋገጠ ግለሰቦች ማዕከሉ ያወጣውን ወጪ እንዲሸፍኑ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሠረትም ከላይ በተጠቀሰው ጉዳዩ ተከሳሽ የነበረው ግለሰብ አባትነቱ በመረጋገጡና የወጣውን ወጪ የመሸፈን አቅሙ ስለነበረው ክፍያውን እንዲሸፍን ተገዷል፡፡

ቤተልሔም እንደምትለው፣ ማዕከሉ ግልጋሎቱን የሚሰጠው አቅም ለሌላቸው ግለሰቦች ነው፡፡ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 80 የሚሆኑ የአባትነት ጥያቄዎችን ማስተናገድ ተችሏል፡፡

ነገር ግን ወደ ማዕከሉ የማይመጡ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ‹‹በያንዳንዱ የቤተሰብ ምድብ ችሎት በአማካይ በሳምንት ሁለት መሰል ጥያቄዎች ይከሰታሉ፤›› ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ይገልጻሉ፡፡

እንደ ቤተልሔም ገለጻ፣ ውሳኔ ከተሰጠባቸው 80 ኬዞች በተጨማሪ የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጠባቸው የዲኤንኤ ምርመራዎች በርካታ ናቸው፡፡ ምርመራውን ላለማድረግ የሚጠፉ ሰዎች ቁጥርም ጥቂት አይባልም፡፡ አንዳንድ አፈጻጸም እየጠበቁ የሚገኙ ጉዳዮችም በማዕከሉ ይገኛሉ፡፡ ምርመራው የሚደረገውም በደቡብ አፍሪካ ሲሆን ከ4,000 ብር እስከ 5,000 ብር ወጪ ይጠይቃል፡፡ አብዛኛው ሰውም የመክፈል አቅም ስለማይኖረው ማዕከሉ ሙሉ ለሙሉ ወጪውን የሚሸፍንበት አጋጣሚው ብዙ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

‹‹የዲኤንኤ ውጤት ጥርጣሬዎችን ከሌሎች ማሰረጃዎች በተሻለ ሁኔታ ያስወግዳል፡፡ አስፈላጊነቱም በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ሕጎች ተቀምጧል፤›› የሚሉት አቃቤ ሕግ ሆነው ለአምስት ዓመታት ያገለገሉትና በጥብቅና ሙያ ከተሰማሩ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ በላይ ናቸው፡፡

ምንም እንኳ የዲኤንኤ የምርመራ ውጤት ከባድ ማስረጃ ቢሆንም በአገር ውስጥ ተደራሽነቱ እምብዛም በመሆኑ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ እንደማይውል ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ የዲኤንኤ የምርመራ ውጤት የግድያ ወንጀል ላይ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሟችን ሲያገኙት በወቅቱ የነበሩ መረጃዎች እንደ ፀጉር ብናኝ፣ ደም እና ሌሎችም በጥንቃቄ መወሰድ አለባቸው፤›› የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ለምርመራው የሚያስፈልጉ ነገሮች በጥንቃቄ ሲያዙና ምርመራው ሲደረግባቸው እንዳላዩ ይናገራሉ፡፡

ብዙ ጊዜም በሰዎች የምስክርነት ቃል ላይ በመመሥረት ፍርድ ይተላለፋል፡፡ ነገር ግን የሐሰት ምስክርና ደካማ የመረጃ አሰባሰብ ሒደት ባለበት ሁኔታ በሰዎች የምስክርነት ቃል ላይ ተመርኩዞ ፍርድ መስጠት ፍትሕን ሊያዛባ ይችላል ይላሉ፡፡ እንዲሁም በዲኤንኤ በቀላሉ መረጋገጥ የሚችሉ ጉዳዮችን አላስፈላጊና ኢሰብአዊ የሆኑ ድርጊቶችን በመፈጸም ወንጀል የማጣራቱን ሥራ ኋላ ቀር እንዲሆን መንገድ እንደሚከፍት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አንዳንድ ወንጀሎችን ሰዎች ላያዩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ተጠርጣሪ ተብለው የተያዙ ግለሰቦችን ወንጀለኛነታቸውን አልያም ንፁህነታቸውን ለማረጋገጥ ከባድ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ በዲኤንኤ ምርመራ ጊዜ ሳይፈጅ ይታወቃል፡፡ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ባለመሆናችን ዋጋ እያስከፈለን እንገኛለን፤›› ይላሉ፡፡

በስህተት ወንጀለኛ ተብለው የታሠሩ ንፁኃንን በዲኤንኤ ውጤት  ነፃ ማውጣት እንደሚቻል የሚናገርሩት አቶ ሙሉጌታ፣ የተሳሳተ መረጃዎች በማጠናቀር ፍትሕ የተጓደለባቸው ፍርደኞች እንዳሉ ያምናሉ፡፡ በተመሳሳይም መረጃ በማጣት የሚዘጉ በርካታ ክሶችን በዲኤንኤ ውጤት ፍትሕ እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ተደራሽ ባለመሆኑ እና በውጭ አገር የሚደረገውን የምርመራ ወጪ የመሸፈን አቅሙ ያላቸው ሰዎች ቁጥር ውስን በመሆኑ ብዙዎች ተጎጂ እንደሚሆኑ  ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ወይዘሮ ቤዛ ብርሃኑ የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ ለአምስት ዓመታት በዳኝነት ሥራ አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በጥብቅና ሙያ ተሰማርተዋል፡፡ የዲኤንኤ ምርመራ በሕግ ክትትል ላይ ስለላለው አስፈላጊነትና በተደራሽነቱ ላይ  ምን እንደታዘቡ ጠይቀናቸዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ምንም እንኳ አንዱ ማስረጃ ከአንዱ ባይበልጥም ዲኤንኤ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ በተለይም የቤተሰብ ሐረግ ለማጣራት የመጨረሻው አማራጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ‹‹እናትነት እውነት አባትነት እምነት›› በሚለው አባባል መሠረትም አባትነትን የማረጋገጡ ኃላፊነት በእናት ጫንቃ ላይ ያርፋል፡፡ የመካካዱ ሁኔታ ጥግ ሲደርስ የግድ የዲኤንኤ ምርመራ ይታዘዛል፡፡ ብዙዎቹ እናቶችም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ውስን በመሆኑ፣ ምንም እንኳ የኋላ ኋላ ግለሰቡ ያወጡትን ወጪ የሚሸፍን ቢሆንም ከሩቁ ይሸሹታል፡፡ ነባራዊ ሁኔታውንም ሲገልጹ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው ምርመራውን የሚያደርጉት›› ይላሉ፡፡

አገልግሎቱ ውስን በመሆኑ በግለሰቦቹ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የበኩላቸውን እንደሚጥሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ቤዛ፣ ‹‹አንዳንዴ የሚካደው ልጅ ገጽታ ከአባቱ ጋር ተመሳሳይ ይሆናል፡፡ ምስክሮች የሚሰጡት ቃልም በእርግጥ አባት ስለመሆኑ አሳማኝ በሚሆንበት ጊዜ ግለሰቡን በማግባባትና በማውጣጣት አባትነቱን እንዲያምን አደርጋለሁ፤›› ይላሉ፡፡

የአቅማቸውን ጥረው ነገሮች እንዳሰቡት የማይሆንበት ጊዜ ጥቂት እንዳልሆኑም ቴክኖሎጂው በአገር ውስጥ ተደራሽ ባለመሆኑ የሚያስከትለው ችግር ከፍተኛ እንደሆነ በመግለጽ መንግሥትና የግል ባለሀብቶች ኃላፊነታቸውን  ሊወጡ አንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

የዲኤንኤ ምርመራ ከሕግ ማስረጃነት ባለፈ በጤናው ላይ ያለው አስተዋጽኦ ጉልህ ነው፡፡ ሆኖም ግን በዘርፉ ያለው ውስን ዕውቀትና ተደራሽነት የዲኤንኤ ማወቅ ጥቅም አላጎላውም፡፡ ነገር ግን አበረታች ጅምሮች እየታዩ ነው፡፡ ቴክኖሎጂውን ወደ አገር ውስጥ በማስገባቱ ረገድ ጥረቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ካለው ውስን ግንዛቤና ሌሎችም ጉዳዮች አንፃር ተገቢውን ሥራ መሥራት አለመቻሉን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ዶ/ር ዘውዱ ተረፈወርቅ የኤምአርሲ ኢትዮ ላቦራቶሪ ሞሎኪዩላር ዲያግኖስቲክስ ባለቤት ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዲኤንኤ ላብራቶሪ አገልግሎት ተደራሽነቱ ዜሮ ነው፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤም ገና አላደገም፡፡ ቀሪው ዓለም የደረሰበትን ጠቃሚ ቴክኖሎጂ ባለመጠቀም በጤናም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ወደ ኋላ ለመቅረት ምክንያት ሆኗል፡፡

ይህንንም ሁኔታ ከግምት በማስገባት ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ ከጥቂት ወራት በፊት የዲኤንኤ ላቦራቶሪ ከፍተዋል፡፡ ነገር ግን ‹‹ተጠቃሚው ከአቅም በላይ የሆነ ሕመም ገጥሞት በሐኪም ካልታዘዘ በስተቀር ሆነ ብሎ ዲኤንኤውን አይመረመርም፤›› ይላሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከሕግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች እስካሁን ወደ ላቦራቶሪው የመጣ ጉዳይ አለመኖሩን ገልጸው፣ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በውጭ አገር ከሚጠየቀው ዋጋ በግማሽ እናም ከዚያ በታች ቀንሰው ለማገልገል ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...