Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ወይ ዕዳ ሲኖትራክም እንደ ባጃጅ ተነዳ!

ሰላም! ሰላም! ገና ስለባቡራችን አውርተን ሳንጠግብ “ታላቁ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ቢሰነጠቅ ምን የምንሆን ይመስልሃል?” ብሎ አንዱ ጠየቀኝ። አይገርምም? ቆይ ግን ከዚህ በላይ ሽብርተኝነት አለ? ቀልዴን እኮ አይደለም። ገና ቀና ብለን ሳንጠግብ፣ መሀሉን ዳር ዳሩ መሀል ሲሆን ማየት የሚናፍቃቸውን አንድ ሳንል፣ እሺ እንዴት ብለን ነው መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ የምንሰለፈው? ሆሆ! አለች ማንጠግቦሽ ሆዷን ነገር ሲቆዝራት። ግን የእኛ ጨዋነት አነጋገር ላይ ነው በቃ? ደግሞ ይኼን ያህል ጊዜ ሰላም ናፍቆን፣ ደግ ዘመን አምጣ እያልን በሱሪ ባንገት ትንቅንቅ እርስ በርስ የተላለቅን ሰዎች፣ ዛሬ እፎይታ በዛብን ተብሎ ‘ታላቁ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ መቼ ይሆን አፍሪካን ለሁለት የሚሰነጥቃት’ ብሎ ለወሬ የማይመች ነገር ማንሳት አይገባኝም። ልጆቿ በሥልጣን ሽሚያ፣ በጥላቻ፣ በዘር ልዩነትና በአመለካከት የተሰነጣጠቁት አንሶ እስኪ አሁን!

‘ነገር ከሥሩ’ እንዲሉ ባሻዬ ይኼን የሚለኝን ወዳጄን ስውር የልቦና ሐሳብ ልጎለጉል “እንዴት እንደዚያ ልታስብ ቻልክ?” አልኩት። ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? “እንዴት አላስብም? ‘ቢች’ ይኖረናል በል። በስማችን የሚጠራ ውቅያኖስ ያለን ብለን እንደለመደብን ‹ከአፍሪካ ብቸኛና ቀንደኛ› እያልን እንጎርራለን። ምነው? እንኳን ውቅያኖስ ኖሮን (ባህር በአንድ አገር ስም መጠራቱን የተማረው የት ይሆን? አቤት የትምህርት ጥራት!) በኪራይ ቤትና መኪና እንዴት ነው የምናነጅበው?” ብሎ ያፈጥብኝና ደግሞ ይቀጥላል። እኔ አዳምጣለሁ። “ታዲያ ያኔ አስበው የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን፣ ይቅርታ ፓርቲያችን የምርጫ ቅስቀሳውን ቢች ዳር ሲያደርግ። ከተዋጠልህ አብረህ ዊስኪ እየተራጨህ፣ ያዘጋጀውን ‘ኮክቴል’ ስልቅጥ አድርገህ አብረህ ወደ መሀል ከተማ ስትመለስ ካልተዋጠልህ ደግሞ በሱዳን በኩል ሳትዞር፣ ወደ የመን ሳታይ፣ በገዛ ታንኳችህ ላጥ ስትል። አስበኸዋል?” ብሎኝ አረፈው። ይህንን ሰምቼ ሳበቃ ይኼን ሐሳቡን ለሌላ ሰው እንዳያካፍል ተማፀንኩት። አይ እኛ!

 ገና ለገና በተፈጥሮ አደጋ መሬት ለሁለት ተሰንጥቃልን ከሆነልን ከገዢው ፓርቲ ጋር የ‘ቢች ኮክቴል’፣ ካልሆነልን መጥፊያ ወደብ የሚሆነን ባህር ስንመኝ አናሳዝንም? ደግሞ የገረመኝ እንዳልኳችሁ በዚህ የቅስቀሳና የመልሶ ማልማት ዘመን የሸለቆውን መሰንጠቅ እንዴት ብሎ እንደታሰበው ነው። ወደድነውም ጠላነውም ነገሩ በጎም ይሆን ክፉ ይዞ መምጣቱ እንደማይቀር የባሻዬ ልጅ በሰፊው አጫውቶኛል። እንዲያውም አሁን የሚሠሩ ግዙፍ የመንገድ፣ የባቡርና ሌሎችም የግንባታ ሥራዎች ይኼን አንድ ቀን ሳይታሰብ ዕውን ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ አዲስ የመሬት መሰንጠቅና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ክስተት ታሳቢ ያደረጉ እንደማይመስሉትም ሲያጫውተኝ ነበር። ያረግብዋል ያልኩት ሰውዬ ጭራሽ እንደ ጨለማ ነብይ ‘ለምሳሌ’ ብሎ፣ “ከጂቡቲ አዲስ አበባ የሚዘረጋው የባቡር ሐዲድ በየጊዜው ለውጥ ከሚታይበት ታላቁ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ያልተጠበቀ ክስተት ጋር ተገናዝቧል ወይ?” እያለ ሲያደርቀኝ ራሴ ለሁለት ይሰነጠቅ ጀመር። “ኧረ ተወኝ አንተ ሰውዬ! አሁን የሚቀድመው የመሬት ይዞታና ፍትሐዊ ክፍፍል ነውን ወይስ የመሬት መሰንጠቅ  ነው?” አልኩት። አያችሁልኝ? እኔም ሳላስበው ኳስ በመሬት አንከባልላሁ ብዬ ጭራሽ ከሜዳ ውጪ ስጠልዝላችሁ? ጨዋታችንን ሲያዳምጥ የነበረ አንድ አልፎ ሂያጅ (ጥላም ማመን ልንተው ነው እኮ ዘንድሮ) “ወንድሜ ‘ቻፓ’ ይኑርህ! ይኼ ካለህ (በእጁ ምናባዊ ቆጠራ ላይ ነው) እንኳን እዚህ እላይም ቦታ አታጣም፤” ብሎ ሰማዩን ጠቆመኝ። ሆ!ሆ!

‘ምነው ይኼ ሰው በገንዘብ ስካር ወንዱ ከሴቱ ይለይ የተባለበት ዘመን መሆኑን ለማስረዳት ሰማይ ቤት ድረስ ሄደ?’ እያልኩ በኑሮና መሬት አልጨበጥ ባይነት ሳዝን ስልኬ ጮኸች። ሞባይሌን እያየሁ ሞባይል ስልክ ከመጣ የተለወጠውን የኑሮ ዘይቤያችንን ድንገት አሰብኩት። ጭንቅላቴን ወዘወዝኩ። እኔ ያልወዘወዝኩትን ማን ይወዘውዝልኛል? ስታስቡት ግን ያለሞባይል ስልክ መኖር አንችልም ብለን አስበን እናውቃለን? ‘ምን ዋጋ አለው ደስ ባለው ሰዓት ተነስቶ ዘመድ ጥየቃ የሚሄድ ‘ኔትወርክ’ ባይኖረን ነበራ? እንዳትሉኝና ቴሌ ሳቄን ሰምቶ ‘ዌቭ’ አትረብሽ እንዳይለኝ። ወይ እናንተ!

እናላችሁ ስልኬን አንስቼ “ሃሎ?” ስል አንዳንዴ እየደወለ የአገር ቤት ወሬ የማቀብለው ‘ዳያስፖራ’ ወዳጄ “አንበርብር!” ብሎ ጮኸ። “ኧረ ቀስ በል ‘ኔትወርኩ’ በደንብ ይሠራል ይሰማኛል፤” ስለው፤ “እኔስ በሕይወት ያለህም አልመሰለኝ ነበር። ተመስገን!” አለ በረጅሙ እየተነፈሰ። ምን ሊለኝ ነው? እያልኩ “ማለት?” ስለው፣ “ይኼ አይኤስ የሚባል ሰው በላ የአሸባሪዎች ቡድን እንዴት ነው እናንተ ጋ እንቅስቃሴው?” አለኝ፡፡ የዘንድሮ ‘ፌስቡከር’ እኮ አይታመንም። ‘‘አንበርብር ምንተስኖት የአይኤስ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኗል ብለው ‘ፖስት’ አደረጉብኝ እንዴ?’’ እያልኩ በውስጤ፣ “ኧረ እኛ ዘንድ በአሁን ሰዓት የሚወራው ስለኢንቨስትመንትና ስለልማት ነው፤” አልኩት። ታዲያስ! ከዚህ በላይ ፀረ ሽብርተኝነቴንና ልማታዊነቴን የማረጋግጥበት መድረክስ አገኛለሁ እንዴ? እሱን እኮ ነው የማወራችሁ።

እህሳ? ወዲያው አንድ ተሳቢ ‘ቮልቮ’ ላሻሽጥ ያነጋገርኳቸው ደንበኞቼ ስልክ ‘ዌይቲንግ’ (ዌይቲንግ በአማርኛ ምንድን ነበር? ‘ስቴሽን’ እንበለው ‘ፌርማታ?’ ኧረ የቋንቋ አዋቂ ያለህ?) መግባት ሲጀምሩ፣ “ሄሎ? ይሰማሃል? ሃሎ ሃሎ?” እያልኩ አውቄ ጥርቅም። ደህና ዘጋሁበት ስል ደግሞ ከደንበኞቼ ጋር ያልኳችሁን ተሳቢ ለማየት ወደ ቃሊቲ እየተጓዝን አንደኛው “ይገርማል እኮ!” ብሎ ጀመረ። “ምኑ?” ስለው “ይኼ አይኤስ የሚባል የአረመኔዎች ስብስብ ነዋ። እኔ እምልህ . . . እ፣ ዝም ብለህ ስትጠረጥር ግን የሞሳድና የሲአይኤ እጅ ያለበት አይመስልህም?” ቢለኝስ። የባሰ አታምጣ ማለት ያሻህን አምጣ ማለት ሆነ እንዴ? እንዴት ነው ነገሩ! ከሽብርተኛ ቡድኑ የባሰብን እኮ ሽብሩን የሚያፋፍሙ መላምቶችና አሉባልታዎች ሆኑ እኮ እናንተ። ግራ እየገባኝ “ምን የዓለም ነገር እኮ አስቸጋሪ ሆነ!” ማለት። “ኖኖ! እንደ እሱማ አትበል። መጠርጠር አለብህ አየህ። የምትሰማውን ሁሉ ማመንና መቀበል ማለት ሚዲያና መንግሥታት በነፍስህ ሲጫወቱብህ እንዲኖሩ እጅ ሰጠህ ማለት ነው?” ይለኛል።  አሁን ምርጫ እየደረሰ የሚበጀኝን እንድመርጥ ነፃነት ተሰጥቶሃል እየተባልኩ ‘ሚዲያና መንግሥት አትመን’ የሚለኝን ሰው ምን ልበለው እያልኩ በረዥሙ አሰብኩ። አስቸጋሪ ሆነ እኮ ሁኔታው!

ሥራው ተሳክቶልኝ ‘ኮሚሽኔን’ አየር በአየር ተቀባብዬ ወደ ቦሌ አካባቢ አንድ ልማታዊ ባለሀብት የገነባው መኖሪያ ቤት ለማከራየት ሄድኩ። ወያላው ደርሰሃል ብሎ እንደ ጆቢራ ከወገቤ ቀጥ ብዬ ከተቀመጥኩበት ወንበር አፈናጥሮኝ ስወርድ ያቺ በ‘ቀጭ ቋ’ ስልቷ የማውቃትን ቦሌ ፈልጌ ማግኘት አቃተኝ። እዚህም እዚያም ላስቲክ አንጥፈው በርካሽ ዋጋ ጫማና ልብስ የሚሸጡ ሰልባጅ ነጋዴዎች ዙሪያዬን ወረውታል። አንዱን መንገደኛ አስቁሜ፣ “የት ነው ያለሁት?” ስለው እያሾፈ፣ “ድንበር ላይ ነዋ። ‘ቪዛ’ ከሰጡህ ያውልህ! (የሚነሳ ቦይንግ እየጠቆመኝ) ሌላም አለ አይዞህ። ለትኬት እኔ አለሁ፤” ብሎ ስቆብኝ ተፈተለከ። ይህቺን ካፖርትና ኮፍያ ሲያይ የገጠር ፍንዳታ ነው ብሎ እኮ ነው። “አላወቀም ገጠሪቷ ኢትዮጵያ በመስኖና በማዳበሪያ እየታገዘች ስንት ስማይ ጠቀስ ፎቅ መገንባት የሚችሉ ልማታዊ አርሶ አደሮች እንደሚኖሩባት፤” ብዬ ኋላ ለባሻዬ የዚያን መንገደኛ ማጋለጥ ሳጫውታቸው፣ “እውነቱን ነው! አንተስ ትንሽ ሱሪህን ዝቅ፣ ቡታንታህን ከፍ፣ ይህቺን ኮፍያህን ወደ ኋላ ዞር፣ ካፖርትህን ክንድህ ላይ ጣል አድርገህ አትጠይቀውም ኖሯል?” አሉኝ። “ባሻዬ! በዚህ ዕድሜዬ?” ስላቸው፣ “ለመንዘላዘል ደግሞ ዕድሜ ይጠየቃል? ባይሆን ሰው ለመሆን እሺ!” ብለው ፈገግ አሉ። ቀጠሉና፣ “ግን አንተ ምን ሆነህ ነው ቦሌን ያህል የባለፀጎችና የውቦች መንደር ‘ናት አይደለችም’ ብለህ የምትጠይቅ?” ሲሉኝ መንገድ ለመንገድ ዘወትር ስታዘብ የማልወደውን ቅጥ ያጣ የግብይት ሥርዓት በቦሌ መድመቁ አስገርሞኝ እንደሆነ አጫወትኳቸው። መልስ አያጡ አይደል? “መርካቶን መልሰን እስክናለማ ወይም አዲስ መርካቶ እስክንቆረቁር፣ ሰምሮልን በተራ እስክንደራጅ መቻል ነው። ደግሞ ያ ላስቲክ ምንጣፍ ላይ ጫማና ልብስ የሚሸጠው ሰው ማጅራት መቺ ከሚሆን የሆነውን ሆኖ ሠርቶ ቢበላ አይበጀንም? መንገዱስ ለማን ሆነና የሚሠራው?” ሲሉኝ ይቅር ይበለኝና በህቡዕ ሳይደራጁ እንዳልቀሩ ጠረጠርኳቸው። ማን ይሆን እኔን የሚጠረጥረኝ?!

በሉ እንሰነባበት። ያልኳችሁን ቤት ጆሮውን ልል አሰፍስፌ ደንበኛ ይዤ  ሳመራ ጥበቃው በር ከፈተልኝ። “ምን ፈለግክ?” አለኝ ተቆጥቶ።  እንኳን ሰው ጎመን የማያደቅ የወላለቀ ጥርስ ይዞ እንጂ እንደ ‘ጀርመን ሼፐርድ’ ባቴን ይዞ ቢዘነጥለኝ ሁሉ ደስ ይለዋል። “አይ ቤቱን የሚከራይ ሰው ይዤ መጥቼ ነው ደላላው ነኝ አስታወስከኝ?” አልኩት። “የእኔ ሥራ እዚህ ቤት ከባለቤቶቹ ውጪ ሰው ዝር እንዳይል መጠበቅ እንጂ ማስታወስ አይደለም፡፡ ጥፋ ከዚህ!” ብሎ ሽመሉን አቀባበለብኝ። የሕወሓት የምሥረታ በዓል የሚከበረው ፀብ ለማጋጋል ነው ብለውታል እንዴ? ሰው እኮ አይታመንም! “ተረጋጋ! እሺ ባለቤቶቹን ጥራልን፤” አለው ደንበኛዬ ትዕግሥቱ እያለቀ። “ባለቤቶቹ ተያይዘው አሜሪካ ለ‘ባኬሽን’ ሄደዋል። ከቻላችሁ ድረሱባቸው፤” አለን በምፀት። ‘ጠዋት ደውለውልኝ ያገኘኋቸውን ሰውዬ ከሰዓት ደርሳ የምትውጣቸው፣ ላላቸው የሚጠቀለል ለእኛ ለእኛ የማይገፋ እንዴት ያለ ‘ሃይ ዌይ’ መንገድ ቢኖራት ነው?’ እያልኩ የፈረደባትን አሜሪካ ማማት ስጀምር፣ ሰውዬው ውኃ በመሰለች መርሰዲስ መኪናቸው ከተፍ አሉ። ጥበቃው ምንም ኃፍረት ሳይታይበት ተሽቆጥቁጦ አስገባን። አድህነነ ነው!

እንዲህ ነው እንዲያ ነው ሳንል ደንበኛዬ ከባህር ማዶ ጠቅልለው ለሚመጡት ቤተሰቦቹ ቤቱ መሆን አለመሆኑን አረጋግጦ ሲያበቃ እንደሚከራየው አሳወቀ። ኪሴ ደለብ አለ። ወዲያው የባሻዬን ልጅ ደወልኩለት። ወደ ግሮሰሪያችን ልንጓዝ አስበን በሁዳዴ የመጀመሪያ ሳምንት የብቅል ጭማቂ ስናወራርድ ለመታየት ዋና መሆን የለብንም ብለን ሻይ ቡና እያልን ካፌ ተጎልተን አመሸን። የቀን ውሏችንን እያወራን የጥበቃውን ጉድ ስነግረው፣ “እዚህ አገር ሥልጣን ጌትነት እንጂ አገልጋይነት ተደርጎ እንደማይታሰብ  እያወቅክ ምነው ፈረድክበት?” ብሎ ወደ እኔ ዞረ። “እኮ እንዲህ ያለ ጠባብ ህሊና ይዘን እስከ መቼ?” ስለው፣ “ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች እስኪደጋገሙ! ተመራጭና መራጭ እየተነፋፈቁ መገናኘታቸው እስኪበረታ! ያን ጊዜ ሕዝብ አገልጋዮቹን በተግባራቸው እየመዘነ መጣልን ሲለማመድ፣ ሹመትም መሥሪያ እንጂ መኮፈሻና ጥቅማ ጥቅም ማግበስበሻ እንዳልሆነ እየገባን ሲሄድ ያን ጊዜ እንለወጣለን፤” ብሎኝ የቡና ሲኒውን አነሳ። “ድል ለዴሞክራሲ!” ስለው እየሳቀ በሲኒው ሲኒየን ገጨ። ‘ቡና መሆኑ እንጂ ቺርሱን ምን ለየው?’ አትሉም? ሃሃሃ! ከመለያየታችን በፊት መንገዱን እየተሻገርን ሳለ በሮኬት ፍጥነት የሚወናጨፍ ሲኖትራክ አስበረገገን፡፡ በሩጫ መንገዱን ተሻግረን ዞር ብለን ስናይ ሲኖትራኩ የቆመች ሚኒባስ ላይ ሲወጣባት የቆምንበት መሬት ተንቀጠቀጠ፡፡ የሲኖትራኩ ሾፌር በሩ በርግዶ ሲሸሽ ገና እንቦቆቅላ ልጅ መሆኑን ታዘብን፡፡ ይኼ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ሲኖትራኩን እንደ ባጃጅ እየነዳ የቆመ መኪና ላይ ሲወጣ በዓይኔ በብረቱ አየሁ፡፡ ወይ ዕዳ ከማለት ውጪ ምን ይባላል፡፡ ኧረ የመንግሥት ያለህ! መልካም ሰንበት! ሳምንት!            

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት