Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢትዮጵያና ኖርዌይ ወረርሽኝን ቀድሞ በጋራ ለመከላከል ተስማሙ

ኢትዮጵያና ኖርዌይ ወረርሽኝን ቀድሞ በጋራ ለመከላከል ተስማሙ

ቀን:

ኢትዮጵያ፣ ከዓርባ ዓመታት በላይ በጤና፣ በትምህርት፣ በልምድ ልውውጥና በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ስትሠራና ስትረዳ ከቆየችው ኖርዌይ ጋር፣ በዓለም ሊከሰቱና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሊያጠፉ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ወረርሽኞችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ከስምምነት ደረሰች፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ከሐሳቡ ጠንሳሽ፣ ከኖርዌይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዩ መልዕክተኛና ካለፉት 47 ዓመታት ወዲህ በአለርት በሚገኘው አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት (አህሪ) ካገለገሉት ዶ/ር ቶሬ ጐዳል ጋር ውይይት የተደረገበትና ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. የተደረሰው ስምምነት፣ ከዚህ በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉና ዓለም አቀፍ ሥርጭት ይኖራቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ወረርሽኞችን ለመከላከል የሚያስችል የስርፀትና የምርምር ሥራ ለመሥራት ያስችላል፡፡

በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ የመጡት የኖርዌይ ልዑል አልጋ ወራሽ ሃኮንና ልዕልት ሜቲ ሜሪት በተገኙበትና በአለርት ማዕከል በተዘጋጀ የጤና፣ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ኮንፈረንስ ላይ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ከበደ ወርቁ እንዳሉት፣ ከኖርዌይ ጋር የተደረሰው ስምምነት ከዚህ ቀደም በወረርሽኝ መልክ የተከሰቱ በሽታዎች እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱ ተስፋፍተው ብዙ ሰዎችን እንዳያጠፉ፣ በወረርሽኝ መልክ ተከስተው ብዙዎችን የሚያጠፉ በሽታዎችን መከላከልና ጉዳት ያደርሳሉ ተብለው የተለዩ በሽታዎት ላይ ምርምር ማድረግ፣ አቅም መገንባት፣ ክትባት ማምረትና በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉ ኅብረተሰቦች ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡

በስምምነቱ መሠረት አህሪ እና ሌሎች ከፍተኛ የምርምር ተቋማት ከ‹‹ኮዋሊሽን ፎር ኢፒደሚክ ፕሪፔርድነስ ኢኖቬሽንስ›› (ሲኢፒአይ) ጋር አብረው የሚሠሩ ሲሆን፣ ይህም የልምድ ልውውጥ ለማድረግና ለተቋማቱ አቅም ለመገንባት እንደሚያስችል ዶ/ር ከበደ ተናግረዋል፡፡

ብዙ የኖርዌይ ተቋማት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሠሩ መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ከበደ፣ በሒደቱ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት የድጋፎቹ ተቋዳሽ እየሆኑና አቅማቸው እየተገነባ ሄዷል ብለዋል፡፡

አለርትም ሆነ አህሪ ሲመሠረት የኖርዌይ መንግሥትና ንጉሣዊ ቤተሰብ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውን በማስታወስ፣ የትብብር ስምምነቱ በአለርት ማዕከል ላይ መሠረት አድርጎ ለሌሎች ማዕከላትም የሚጠቅም ይሆናል ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1970 ጀምሮ በአለርት አህሪ መሥራት የጀመሩት ዶ/ር ቶሬ ጐዳል፣ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ በጀት በማሳደግ ለውጥ እያመጣች መሆኗን፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዕድገት ትኩረት መስጠቷና አህሪ ለባዮቴክኖሎጂ መስፋፋት የሚሠራው ሥራ በኢትዮጵያ ካዮዋቸው እመርታዎች የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአህሪ ዳይሬክተር፣ ዶ/ር ታዬ ቶሌራ በበኩላቸው፣ የምርምር ተቋሙ በ47 ዓመት ውስጥ ቀድሞ ለሁለት ዓመት ይወሰድ የነበረው የሥጋ ደዌ መድኃኒትን በስድስት ወር እንዲወሰድ የሚያስችሉ ሦስት ዓይነት መድኃኒቶች ላይ ሙከራ አድርጎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ ማዋሉን፣ መድኃኒት በተላመደ ቲቢ ላይ የሚሰጠውን መድኃኒት ለስድስት ወር ብቻ መስጠት ይቻላል ወይ? በሚለው ላይ ሙከራ እየተደረገበት መሆኑን፣ በወባ፣ በኤችአይቪና በሌሎች በሽታዎችም ምርምር እንደሚያደርግና ለጤናው ዘርፍ እመርታ በምርምሩ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

አህሪ 20 በመቶ በጀቱን ከኖርዌይ መንግሥት የሚያገኝ ሲሆን፣ አብዛኛው ድጋፍ ቴክኒካል መሆኑ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...