በተደጋጋሚ ድሎቿና ክብረ ወሰኞቿ ገናና የሆነችው ገንዘቤ ዲባባ፣ የዓለምን የቤት ውስጥ 5000 ሜትር ሩጫን 14 ደቂቃ 18.86 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመፈጸም ባለፈው ሐሙስ ሰበረች፡፡
ገንዘቤ በስዊድን መዲና ስቶክሆልም የተካሄደውን ውድድር በአገሯ ልጅ መሠረት ደፋር ከስድስት ዓመት በፊት በ14 ደቂቃ 24.37 ሰከንድ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ከ5 ሰከንድ በላይ ማሻሻሏን ራነርስ ዎርልድ በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡ ያለ ቅርብ ተፎካካሪ የመጨረሻዎቹን ሁለት ዙሮች ብቻዋን የሮጠችውን ገንዘቤ ተከትላ ሁለተኛ የወጣችው ብርቱካን ፈንቴ፣ የፈጸመችበት ጊዜ 15፡22.56 ነው፡፡
ገንዘቤ በዓምናው የቤት ውስጥ ውድድር በ15 ቀናት ውስጥ ሦስት የዓለም ክብረ ወሰኖችን በ1500 ሜትር፣ በ3000 ሜትር እና በ2 ማይልስ መስበሯ ይታወሳል፡፡ ዓምና የዓለም የቤት ውስጥ የ3000 ሜትር ሻምፒዮንም ነበረች፡፡