Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

መቼም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን ላይ የተለያዩ ነገሮች እናያለን፣ እንሰማለን፡፡ ሊገርሙን፣ ሊያስተምሩንና ሊያበሳጩንም ይችላሉ፡፡ እስቲ እኔም ሰሞኑን ወደ ሥራዬ በሐይገር ባስ ስሄድ ያየሁትን ላካፍላችሁ፡፡ ከሳሪስ አቦ ተነስቶ ወደ መገናኛ በሚሄደው ሐይገር ባስ ውስጥ ተቀምጫለሁ፡፡ የቆሙም ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እኔ ወደ ውጭ እያየሁ ስለነበር ከጐኔ ከተቀመጠችው ልጅ ሌላ ያስተዋልኩት አልነበረም፡፡

በተለምዶ ‹‹ማሞ›› የሚባለው አካባቢ ስንደርስ ሐይገሩ ቆሞ ሰው ይጭናል፡፡ ወያላው (ረዳቱ) መሀል ላይ ያለውን መስታወት ከፍቶ ‹‹ሼባው ጋሼ እስቲ ወደኋላ ተጠጉ›› ሲል ሰማሁ፡፡ ወያላው እንደዚያ ከማለቱ ወዲያው ሰውየው ‹‹አልጠጋም›› ሲል አንቧረቀ በአካባቢው የተቀመጥን ሰዎች ሁሉ ዘወር ዘወር ብለን ተመለከትነው፡፡ ሰውየው ጐልማሳ የሚባል ሲሆን፣ ፀጉሩ ገባ ያለና ሽበትና ጥቁር የተቀላቀለበት ገብስማ የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ 

ወይ ብስጭት? ሰውየው ከቤቱ ተበሳጭቶ ነው የወጣው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለው? በሚያስብል አኳኋን፣ ‹‹አንተ የለማኝ ልጅ፣ እናትህ እንደዚህ ትሁን፣ ቆይ ስወርድ አገኝሃለሁ፤›› እያለ ከንፈሩን ይነክሳል፡፡ ልክ እንደዚህ ሲል ሳየው ደግሞ ልጆች ሆነን ትምህርት ቤት ‘ቆይ ወደ ቤት ስንሄድ አገኝኸለሁ’ የምንባባለውን አስታወሰኝ፡፡ ሁኔታው በጣም ይገርማልም ያስቃልም፡፡ እኔማ ሳቄን መቆጣጠር አቅቶኝ ከትከት ብዬ ለቀቅኩት፡፡ ወዲያው እኔን ተከትለው በአካባቢዬ የነበሩትም በሳቅ ተቀላቀሉኝ፡፡

- Advertisement -

ሰውየውን መለስ ብዬ አየት አደረግኩትና ይኼ ሰው እንደዚህ ተናዶ በጥፊ እንዳይሞላብኝ ብዬ ደግሞ ወዲያው ዝም አልኩ፡፡ ሌሎቹን ሰዎች ሳይ ጭንቅላታቸውን ይወዘውዛሉ፡፡ አብሮት ያለው ሰውዬ ራሱ በጣም ነው ያፈረው፡፡ ግራ ገብቶት፣ ‹‹አንተ ተው እንጂ እንደዚህማ መሆን የለብህም እሱ እኮ ሽበትህን አይቶ ነው እንደዚያ ያለህ፤›› ይላል፡፡

‹‹ኧረ ቆይ ልውረድለት አጋድሜው ከአፈር ጋር ስቀላቅለው ያኔ ሽማግሌነቴን ያያል፤›› ይላል ሰውየው፡፡ ያ አብሮት ያለ ሰው በጣም ግራ ገብቶት እንዴት ብሎ ያረጋጋው? ‹‹ይኼውልህ አንዳንድ ሰው ዝም ብሎ ሰይጣን ውስጥ ይከታል በቃ ተረጋጋ፤›› ይላል፡፡

ከኋላ ሌላ ሰው ወረደና ያ የተበሳጨ ሰው ቁጭ አለ፡፡ ወደኋላ ተጠግታ የቆመች አንዲት ሴት፣ ‹‹እንዴ ይኼ ሰውየ ምን ሆኗል? ዕድሜ ፀጋ ነው አባባ ቢባል ምን ችግር አለው? እስቲ ለዚያ ያድርሰው፤›› ትላለች፡፡ ሌላኛው ተሳፋሪ ደግሞ፣ ‹‹የእኔ ታናሽ ወንድም ሙሉ ፀጉሩ ጥጥ ነው፡፡ እኔ ታናሼ ነው ስል ማንም አያምነኝም፡፡ እንኳን ታናሼ የታላቄ ታላቅ ነው የሚመስለው፡፡ ይኼ እኮ እንደዚህ አያበሳጭም፤›› አለች፡፡

ትንሽ ቆይቶ ሁሉም በራሱ ሐሳብ ጭልጥ አለ መሰለኝ ወዲያው ሐይገር ባሱን ፀጥታ ሞላው፡፡ እኔም ቦሌ ደርሼ ወረድኩ፡፡ ሰውየው መገናኛ ነው የሚሄደው መሰለኝ ቁጭ ብሏል፡፡ እውነት እንደፎከረው ሲወርድ ልጁን ከአፈር ይቀላቅለው ይሆን? ምነው ሰው ትዕግሥት አጣ? በዚህ ወቅት የተረዳሁት ነገር ቢኖር በትንሽ ነገር መደሰት መቻልና ትዕግሥተኛ መሆን ለሕይወታችን ዋና ቁልፍ ነገሮች ይመስሉኛል፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ? ቸር እንሰንብት፡፡

(ሔለን፣ ከሳሪስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...