ነሐሴ 8 ቀን 2005 ዓ.ም. በተነበበው ሪፖርተር ላይ ‘‘ከፍተኛ ዋጋ ያለው የሊዝ መብት በተጭበረበረ መንገድ በመሸጥ የተጠረጠሩ ባልና ሚስት ታሰሩ’’ በሚል ርዕስ ሰፊ ሽፋን በተሰጠው የዜና ዘገባ አቶ ጌታቸው ጣሰውና ወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱን አስመልክቶ በተሰጡ ማብራሪያዎች፣ በቀረቡ የተሳሳቱና ሐሰተኛ መረጃዎች በአንባቢው ላይ የተፈጠሩ ብዥታዎች እንዲታረሙ ለማድረግ ትክክለኛውን እውነታ እንደሚከተለው በዝርዝር ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ከሳሽ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾች እነ ጌታቸው ጣሰው በሚል መዝገብ በኮ/መ/ቁ ያቀረበብንን የወንጀል ክርክር መርምሮ በታህሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎት አቶ ጌታቸው ጣሰውንና ወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱን በነፃ የሚያሰናብት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በአቶ ጌታቸው ጣሰው ላይ አንድ የማታለል ወንጀል ክስና በባለቤቱ ወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱ ላይ ሁለት የማታለል ወንጀል ክስ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ የዋስትና መብታችንን በተመለከተ በተደራራቢ ወንጀል ስለተከሰሱ የዋስትና ግዴታቸውን መወጣት አይችሉም በማለት ባቀረበው መቃወሚያ ምክንያት የዋስትና መብታችንን በመከልከል የከፍተኛው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በተለይ አቶ ጌታቸው ጣሰው በአንድ ክስ ብቻ ተከስሼ እያለና የወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱ ክስም በአንድ ጉዳይ ላይ ተመሥርቶ የቀረበ ሁለት ክስ ብቻ ሆኖ ሳለ የተከሰሱት በተደራራቢ ወንጀል ነው የሚለው መቃወሚያ ፍርድ ቤቱን ለማሳሳት የቀረበ መሆኑን በመግለጽ የይግባኝ አቤቱታ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበን ሲያከራክረን፣ ዓቃቤ ሕግ በሥር ፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታ እንደማያዋጣ ሲረዳ ለዘመናት በቤተሰባዊና በጓደኝነት ግንኙነት ከአቶ ድልአርጋቸው በላይ ጋር የምናውቃቸውን ምስክሮች እንደ አዲስ እንደምናውቃቸውና በማባበል ምስክርነታቸውን ልናዛባ እንደምንችል በመግለጽ ተቃውሞ አቅርቦ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም በአብላጫ ድምፅ ተቀብሎት ላለፉት 18 ወራት የዋስትና መብታችን ተከልክሎ በእስር ላይ ሆነን ክርክራችንን አካሂደናል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በየካቲት 3 ቀን 2006 ዓ.ም. አሻሽሎ በአቶ ጌታቸው ጣሰውና በወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱ ላይ ያቀረበው የመጀመሪያው ክስ ተከሳሾች ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን የፍርድ ባለመብት ኢትዮ ሩት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በፍርድ አፈጻጸም ያስያዘውን ንብረትነቱ የአቶ ድልአርጋቸው በላይ የነበረው 543 ካሬ ሜትር የሊዝ ይዞታ መብት ነሐሴ 4 ቀን 1999 ዓ.ም. በፍርድ አፈጻጸም መምሪያ አማካይነት በሀራጅ ሲሸጥ ጨረታው እንዲታፈን በማድረግ የዝምድና ግንኙነት ያላቸው አቶ ቃለሥላሴ በላይ ጨረታውን በ1,065,000 ብር እንዲያሸንፉ በማድረግ አቶ ድልአርጋቸው 5,919,766 ብር እንዲያጡ በማድረግ የማታለል ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው፡፡
አንባቢ እዚህ ላይ በአንክሮት ሊመለከተው የሚገባው ነጥብ የማታለል ወንጀል አለ ለማለት በትንሹ ሊሟላ የሚገባው ነገር አታላይ የሚባል ተከሳሽና ተታላይ የሚባል፣ የንብረት ጥቅሙ የሚጐዳ ተግባር የተፈጸመበት የግል ተበዳይ የሆነ ሰው (ግለሰብ) መኖር ነው፡፡ በዚህ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ ግን ተታላይ የተባለና የንብረት ጥቅሙን የሚጎዳ ተግባር የተፈጸመበት ግለሰብ የለም፡፡ ከተከሳሽ ጋር ግንኙነት ያደረገው፣ ፍርዱን ያስፈጸመው ፍርድ ቤቱ ብቻ ነው፡፡ ከፍርድ ቤቱ ጋር ያለው ግንኙነት የተከናወነው በሰነድ ላይ በተደረገ የመረጃ ልውውጥና በተሰጠ ማረጋገጫ ነው፡፡ እንግዲህ እኔና ባለቤቴ አቶ ድልአርጋቸው በላይን አታላችኋል ተብለን የዋስትና መብታችንን ተከልክለን በእስር እንድንንገላታ የተደረገው በፍርድ ቤት በተካሄደ ጨረታ ላይ በመሳተፋችን ነው፡፡ ይህም ክሱ ምን ያህል ቀላል የሕግ ትርጉምን እንኳ ባላገናዘበ ሁኔታ እንደቀረበ ያሳያል፡፡
አቶ ድልአርጋቸው በላይ በጨረታው ሒደት ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ አልነበራቸውም፡፡ በጨረታው ቦታም ሆነ አካባቢ አልነበሩም፡፡ አቶ ጌታቸው ጣሰውና ወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱ ለፍርድ ቤቱ ፍርድ አፈጻጸም መምሪያ ባቀረብነው መረጃና ማረጋገጫ ላይ ተመሥርተው የፈጸሙት ምንም ዓይነት ተግባር የለም፡፡ ስለሆነም የተታለለ ሰው የለም ማለት ነው፡፡ የተታለለ ሰው ሳይኖር የማታለል ወንጀል ሊኖር አይችልም፡፡
ለፍርድ ቤቱ የፍርድ አፈጻጸም መምሪያ የቀረበ ሐሰተኛ መረጃ ወይም ማረጋገጫ ካለ በሰነዱና በማረጋገጫው ምክንያት ተጠያቂነት ከሚኖር በስተቀር የማታለል ወንጀል የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ፍርድ ቤት በቀረበለት ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔና ትዕዛዝ የሚሰጥ ተቋም እንጂ ሊታለል የሚችል ግለሰብ ባለመሆኑ ነው፡፡
ይህን መሠረታዊ የሕግ ትርጉም ጉዳይ ከተመለከትን አንባቢ ትክክለኛውን ሁኔታ እንዲረዳ ለማድረግ በጨረታው ወቅት የነበረውን እውነት እንደሚከተለው እገልጻለሁ፡፡
የሐራጅ ሽያጭ ጨረታ የተፈጸመው በሕግ ይህንኑ ለማስፈጸም ሥልጣን በተሰጠው አካል ማለትም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም መምሪያ ሐምሌ 3 ቀን 1999 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለሕዝብ በይፋ በታተመ የሐራጅ ሽያጭ ማስታወቂያ አማካይነት ሲሆን፣ የሐራጁ ትዕዛዝ የተሰጠው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 52682 ሰኔ 4 ቀን 1999 ዓ.ም. በተሰጠው ውሳኔ መሠረት ነው፡፡ ማስታወቂያው በሕጉ አግባብ ለ30 ቀናት ክፍት ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ጨረታውም ነሐሴ 4 ቀን 1999 ዓ.ም. በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም መምሪያ የጨረታ አዳራሽ ውስጥ ከጠዋቱ 4፡30 ሰዓት እስከ 5፡30 ሰዓት የተጫራች ምዝገባ ከተደረገ በኋላ 5 (አምስት) ተጫራቾች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡ ይህን እውነታ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ጨረታው በጋዜጣ መውጣቱን፣ በቦታው ላይ ጉብኝት መደረጉንና ጨረታው በፍርድ አፈጻጸም መምሪያ አዳራሽ ውስጥ መከናወኑን መስክረዋል፡፡
የዓቃቤ ሕግ ምስክር የሆኑትና የግል ተበዳይ የተባሉት አቶ ድልአርጋቸው በላይ ለክሳቸው መሠረት ያደረጉት በጨረታው ላይ የተካፈሉት የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው የሚል የክስ ምክንያትን ነው፡፡ በመሠረቱ የአገራችን ሕግ የአንድ ቤተሰብ አባላት፣ ጓደኛሞች፣ የጋብቻም ሆነ የሥጋ ዝምድና ያላቸው ሰዎች በአንድ ጊዜ በአንድ ጨረታ ላይም ሆነ ከአንድ ምንጭ በተገኘ ገንዘብ ጨረታ ሊሳተፉ እንደማይችሉ የሚከለክል አይደለም፡፡ ይህን የሚከለክል ሕግም ሆነ የጨረታ መመርያ እንዲሁም አሠራር የለም፡፡
በተቃራኒው በአገራችን ያለው የዳበረ ልምድ የሚያስረዳው በግልጽ ጨረታ ላይ ተጫራቾች ጨረታን ለማሸነፍ ተደራጅተው በመግባት ሌሎች ተጫራች ሰዎች በራሳቸው ሐሳብ በጨረታው ላይ የሚያደርጉትን ውድድር በማያሰናክል ሁኔታ መጫረትና መወዳደር የሚችሉ መሆኑን ነው፡፡ ተጫራቾች ወደ ጨረታ አዳራሹ ከመግባታቸው በፊት ማናቸውንም ዓይነት አደረጃጀት ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ከጨረታው አዳራሽ ውጪ ያለው እንቅስቃሴ በሙሉ የጨረታው አካል አይደለም፡፡ ተጫራቾች ወደ ጨረታ አዳራሽ ከገቡ በኋላ ግን ሐሳብ መለዋወጥም ሆነ መነጋገር አይችሉም፡፡ ምክንያቱም በጨረታው አዳራሽ ውስጥ የሚደረገው ግንኙነት የጨረታው አካል በመሆኑና የጨረታውን ፍትሐዊነት ሊያዛባና ሊያሰናክል ስለሚችል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ተጫራቾች ከጨረታ አዳራሽ ውጪ በፈጸሙት ማናቸውም ሕግን የተከተለ ነገር ጨረታውን አፈናችሁ ተብለው ሊጠየቁ አይችሉም፡፡
የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችም ቢሆኑ አቶ ጌታቸው ጣሰውና ወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱ በጨረታው አዳራሽ ውስጥ የጨረታውን ሒደት የሚያሰናክል ድርጊት ፈጸሙ ብለው አልመሰከሩብንም፡፡ ይልቁንም የግል ተበዳይ የተባሉት ግለሰብ ጨረታውን ለማስፈረስ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበው ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን ውድቅ አድርጐ የጨረታውን ሕጋዊነት አፅድቆታል፡፡ ይህ የሚያሳየው የጨረታው ሒደት ጨረታውን በሚመራውና ለመቆጣጠር እንዲሁም ስህተት ተፈጽሞም ሲገኝ ለማረም በሕግ ሥልጣን በተሰጠው ፍርድ ቤት ሕግን በተከተለ ሁኔታ የተከናወነ መሆኑን ነው፡፡
አንባቢ የበለጠ ጉዳዩን እንዲረዳው አንድ ትኩረት የሚደረግበት ነጥብ ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ ጨረታ ላይ የአቶ ድልአርጋቸው በላይ ተወካይ የሆኑት ወንድማቸው አቶ ታምራት በላይ ተገኝተው የነበረ ሲሆን፣ በጨረታው ቬርባል ላይ ስለጨረታው ትክክለኛነትና ስለአሸናፊው ሰው ማንነት እንዲሁም አሸናፊ የሆነው ሰው ስላሸነፈበት የገንዘብ መጠን ማረጋገጫ የሆነውን ሰነድ በአካል ተገኝተው፣ አይተውና አረጋግጠው ፈርመውበታል፡፡ እንግዲህ እኛ የተከሰስነው የአቶ ድልአርጋቸው በላይ ወንድም አቶ ታምራት በላይ ይህን በፊርማቸው ያረጋገጡትን ነገር አሁን ፍርድ ቤት ቀርበው ክደው በመመስከራቸው ነው ማለት ነው፡፡
ሌላው አንባቢ ሊረዳው የሚገባው ነጥብ በዓቃቤ ሕግ ክስ ላይ ምስክር ሆነው ያቀረቡት፣ ጨረታው በተካሄደበት ወቅት የአቶ ቃለሥላሴ በላይ የቅርብ ጓደኛ የነበሩ አሁን ግን በመካከላቸው ቅራኔ የፈጠሩት አቶ አሰፋ በየነ የተባሉት ምስክር ከእኔና ከባለቤቴ ጋር ከጐናችን ቁጭ ብለው በዚህ ጨረታ ላይ ተሳትፈው የተሸነፉ ተጫራች ቢሆኑም፣ ለፍርድ ቤት ቀርበው ሲመሰክሩ ከደቡብ ክልል በደሌ አካባቢ ካላቸው ትልቅ እርሻ ላይ ተነስተው ሌሊቱን በሙሉ መኪናቸውን ሲነዱ አድረው በጨረታው ቦታ ላይ መሬቱን ለመግዛት ለመጫረት የመጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለጨረታ የቀረበው መሬት ስፋት ስንት እንደሆነ፣ የጨረታው መነሻ ዋጋ ስንት እንደሆነ፣ ለመጫረት በሲፒኦ ማስያዝ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ስንት እንደሆነ፣ መሬቱ ለምን አገልግሎት ሊውል እንደሚችልና በጨረታ ሊወዳደሩበት የመጡበት ዋጋ ስንት እንደሆነ እንደማያውቁና በጨረታው ቬርባል ላይ ምንም ሳይረዱ መፈረማቸውን ገልጸዋል፡፡ እንግዲህ አንባቢ እዚህ ላይ አንድ በፒኤችዲ ደረጃ የተማረ፣ በአገራችን በከፍተኛ የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሰማራና በአዲስ አበባ ከተማ የትልቅ ሆቴል ባለቤት የሆነ ሰው እንዲህ ዓይነት ስህተት እንዴት ሊሳሳት ይችላል የሚል ጥያቄ በማንሳት በእርግጥ ስህተት ነው ወይስ ሆን ተብሎ ቅሬታ የፈጠረበትን ሰው ለመጉዳት በማሰብ የተሰጠ ምስክርነት ነው የሚለውን በመመዘን እውነታው የቱ ጋር እንዳለ ግንዛቤ እንዲወስድ እጠይቃለሁ፡፡
ዓቃቤ ሕግ የአቶ ድልአርጋቸው በላይ የሊዝ ይዞታ 1474 ካሬ ሜትር ነው በማለት በክሱ ላይ የገለጸ ቢሆንም፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለጨረታ የወጣው በጨረታ ማስታወቂያው ላይ የተገለጸው በካርታ ቁጥር ድ0007/97 የሚታወቀውና በጉብኝት ወቅት በአካል ለተገኘን ተጫራቾች በሙሉ የተገለጸልን የመሬት ልኬት 543 ካሬ ሜትር ብቻ ነው፡፡ ጨረታውም የተካሄደው በዚህ መሬት የሊዝ ይዞታ መብት ላይ ብቻ ነው፡፡
እኔ አቶ ጌታቸው ጣሰውና ባለቤቴ ወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱ በጨረታው ውስጥ የነበረን ተሳትፎ ግልጽ ነው፡፡ ከጨረታው በኋላ ያለው ጉዳይ በጨረታው ያሸነፈውን ግለሰብ የሚመለከት እንጂ በጨረታው ተሸንፈን የወጣነውን ሰዎች የሚመለከት አይደለም፡፡
ይልቁንም ፍርድ ቤቱ ለተጫራቾች ባወጣው ግልጽ የጨረታ ማስታወቂያ እንደማንኛውም ተጫራች መሥፈርቱን እኔና ባለቤቴ ወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱ አሟልተን የጨረታውን መነሻ ዋጋ አንድ አራተኛውን ከንብ ባንክ ኡራኤል ቅርንጫፍ በCPO እና በጥሬ ገንዘብ እያንዳንዳችን 264,169.50 ብር አሠርተንና አስይዘን ቦታውንም በአካል ጭምር በመጐብኘት የተጫረትንበት ማስረጃ በሰነድ ተደግፎ በቀረበበት ሁኔታ በማታለል ወንጀል መከሰሳችን ተገቢ አልነበረም፡፡
የግል ተበዳይ የተባሉት አቶ ድልአርጋቸው በላይ በክሱም ሆነ በምስክርነት ቃላቸው ላይ 1474 ካሬ ሜትር እንደተወሰደባቸው የተገለጸው ፈጽሞ ከሐቅ የራቀ ነው፡፡ ግለሰቡ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጋር ከተፈራረሙት የሊዝ ውል በቀላሉ ለማየት እንደሚቻለው የሊዝ ውል ስምምነት የተደረገው፣ የሊዝ ክፍያ የተፈጸመው፣ ካርታ የተሰጠውና የይዞታ ርክክብ የተደረገው በሊዝ ይዞታነት በተፈቀደላቸው 543 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ብቻ ነው፡፡
ግለሰቡ 1474 ካሬ ሜትር እንደተወሰደባቸውና በዚህ ምክንያትም በሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ጉዳት እንዳደረሰባቸው የገለጹበት ሁኔታም ፈጽሞ ሐሰት ነው፡፡ ምክንያቱም የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር መምሪያ ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች አፈጻጸም መምሪያ በቁጥር ቂ.ክ.መ.አ. 153821/9 ሚያዝያ 22 ቀን 1999 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ የግለሰቡ ይዞታ ወይም ኪራይ 543 ካሬ ሜትር ብቻ መሆኑን፣ በቦታው ላይም ምንም ዓይነት ግንባታ አለማካሄዳቸውን እንዲሁም 845,342.40 ብር ከባንክ ወለድ ውጪ እንደሚፈለግባቸው ገልጿል፡፡ ከዚህ በቀላሉ ማየት እንደሚቻለው ግለሰቡ መሬቱን በሊዝ ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ የአንድ ብር የልማት ሥራ እንኳ ሳይሠሩበት በመቆየታቸውና የመንግሥት ዕዳንም በጊዜው ባለመክፈላቸው የመሬቱ ይዞታ በመንግሥት ዕዳ የሚፈለግ እንጂ በዓቃቤ ሕግ ክስ ላይ እንደተገለጸው 5,949,766.00 ብር ሀብትን በመሸጥ ትርፍ ለማግኘት መሞከር መንግሥታችን በግልጽ የሚያወግዘው የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ነው፡፡ ይህም የዓቃቤ ሕግ ክስ መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ከሚከተለው የፖሊሲ አቅጣጫ አንፃር ያልተቃኘ ስለመሆኑ በቂ ማሳያ ነው፡፡
በሊዝ ሕጉ መሠረት በሊዝ ይዞታ ላይ ምንም ዓይነት ግንባታ ወይም የልማት ሥራ ያልሠሩ ሰዎች ይዞታው ከእጃቸው ሲወጣ ያላቸው መብት የፈጸሙት የሊዝ ክፍያና ክፍያ ከፈጸሙበት ጀምሮ እስከ አስተላለፉበት ጊዜ ድረስ ያለው የባንክ ወለድ፣ በይዞታው ላይ የተካሄደ የግንባታ ሥራ ካለ የዚሁ የግንባታ ወጪ ግምት፣ የሊዝ መብቱ በመተላለፉ የተገኘ የዋጋ ልዩነት አምስት በመቶ ክፍያ ብቻ ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ የሊዝ መብቱ በመተላለፉ የሚገኘው ተጨማሪ ገቢ በሙሉ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት በመሆኑ ምክንያት ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን በሕግ የተወሰነ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር የአቶ ድልአርጋቸው በላይን ጉዳይ ስንመለከት ግለሰቡ በገቡት የሊዝ ውል መሠረት የከፈሉት ገንዘብ 211,335.60 ብር ብቻ ሲሆን፣ በቦታው ላይ ምንም ዓይነት ግንባታም ሆነ የልማት ሥራ አላከናወኑም፡፡ በመሆኑም በሊዝ የመጠቀም መብታቸው ሲሸጥ በሕጉ መሠረት ያላቸው መብት ይህን የከፈሉትን ገንዘብ ከባንክ ወለድና አምስት በመቶ ጭማሪ ጋር ማግኘት ብቻ ነው፡፡ በሕጉ መሠረት ግለሰቡ ማግኘት የነበረባቸው የከፈሉት 211,335.60 ብር የባንክ ወለድና የዋጋው ልዩነት አምስት በመቶ ተደምሮ የሚገኘው የገንዘብ መጠን ማለትም በድምሩ ከ270,000.00 ብር የማይበልጥ ገንዘብ ነው፡፡ ቀሪው ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ መሆን ሲገባው ከሕግ ውጪ ለዕዳቸው መክፈያነት እንዲውል በተደረገው ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ መደረግ የነበረበትን 853,664.40 ብር ለግላቸው በመውሰድ በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብለን እናምናለን፡፡
ዓቃቤ ሕግ ግን ይህን ግልጽ ሁኔታ ወደ ጐን በመተው ግለሰቡ በሌላቸው የሊዝ ይዞታ በአካባቢው ሕግ መሠረት ለልማት ሥራ በሊዝ የተሰጠ መሬትን ከፍተኛ ዋጋ በማነጻጸሪያነት በመጠቀም በግለሰቡ ላይ ጉዳት ደርሷል በማለት ያቀረበው ክስ የመንግሥትን ጥቅም ታሳቢ ሳያደርግ የቀረበ መሆኑን ያሳያል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱ ላይ ያቀረበው ሁለተኛ ክስ ተጠርጣሪዎቹ ባላቸው የዝምድና የጥቅም ትስስር አቶ ወንድአፍራሽ ፍቅሩ የአቶ ድልአርጋቸው በላይ ወኪል ሆነው በሚሠሩበት ጊዜ ውክልናቸውን ተጠቅመው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 1474 ካሬ ሜትር የሊዝ ውል ፈጽመዋል የሚል ነው፡፡ ይህን አስመልክቶ የቀረበውን ክስም ሆነ በጋዜጣው የወጣው ዘገባ ሐሰት መሆኑን እንደሚከተለው እገልጻለሁ፡፡
ነሐሴ 30 ቀን 1997 ዓ.ም. የተፈረመው የሊዝ ውል በግልጽ እንደሚያመለክተው፣ አቶ ድልአርጋቸው በላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በሊዝ ተፈቅዶላቸው በሊዝ ሕጉ መሠረት 20 በመቶ የሊዝ ቅድሚያ ክፍያ በመፈጸም ካርታ የተሠራላቸውና የተሰጣቸው ለ543 ካሬ ሜትር ብቻ ነው፡፡ ቀሪው በክሱ ላይ የተገለጸው 931 ካሬ ሜትር ምንም ዓይነት የሊዝ ውል ያልተፈረመበት፣ የሊዝ ክፍያ ያልተፈጸመበትና ካርታ ያልተዘጋጀለተ ነፃ የመንግሥት መሬት ነው፡፡ ይህንን አቶ ድልአርጋቸው በላይ ከአስተዳደሩ ጋር ያደረጉትን የሊዝ ውልና የሊዝ ክፍያ የፈጸመባቸውን ሰነዶች በማየት ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ይህን እውነታ ወደ ጐን በመተው የአቶ ድልአርጋቸው 931 ካሬ ሜትር የሊዝ ይዞታ ከሕግ ውጪ እንደተወሰደባቸው በማድረግ በባለቤቴ በሁለተኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱና በሦስተኛ ተከሳሽ ላይ ያቀረበውን ክስ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሐምሌ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ክሱ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም በማለት ከክሱ በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡
እዚህ ላይ አንባቢ በአንክሮ ሊመለከተው የሚገባው ነፃ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት የሆነ መሬትን አስመልክቶ ለመወሰን በሕግ ሥልጣን የተሰጠው የክፍለ ከተማው አስተዳደር በሕግ መሠረት ከኢትዮ ሩት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የሊዝ ውል ተዋውሎ፣ የሊዝ ክፍያ አስከፍሎ፣ አዲስ ካርታ ሠርቶ ለማኅበሩ ይዞታውን ያስረከበና በዚህ ሒደት ውስጥ የማታለል ወንጀል ተፈጽሞብኛል የሚል ቅሬታ ያላቀረበ መሆኑን ነው፡፡
የንግድ ማኅበሩ ከአስተዳደሩ ጋር በሕግ መሠረት ባከናወነው ሕጋዊ ተግባር አቶ ድልአርጋቸው በላይ ተታልዬ የፈጸምኩት ተግባር ነው በማለት ክስ ሊያቀርቡ ስለማይችሉ፣ ይህን አስመልክቶ የቀረበው ክስና ዘገባ እውነታውን መሠረት ያላደረገ ነው፡፡ ከአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ጋር ሕግን በተከተለ ሁኔታ በተደረገ ውል በሌላ ግለሰብ ላይ የሚፈጸም የማታለል ወንጀል ሊኖር እንደማይችልና ለውሉ ሦስተኛ ወገን የሆነ ሰው ተታለልኩኝ ሊል የማይችል መሆኑን ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው የሚገነዘበው ሐቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ እኔ አቶ ጌታቸው ጣሰውና ባለቤቴ ወ/ሮ ሸዋነሽ መንግሥቱ አላግባብ በቀረበብን ክስ ቤታችንና ሥራችን ተዘግቶ የዋስትና መብታችንን ተከልክለን ለ18 ወራት በእስር ላይ እንድንቆይ የተደረገ ቢሆንም፣ ጉዳዩን የመረመረው ፍርድ ቤት በወንጀል የሚያስጠይቃቸው ተግባር አልፈጸሙም በማለት በነፃ ያሰናበተን በመሆኑ በመጨረሻ ፍትሕ ማግኘታችንን አንባቢ እንዲረዳልን እንጠይቃለን፡፡
(ጌታቸው ጣሰው)