Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክየመጥፋት ውሳኔ በጋብቻ ላይ ያለው ውጤት

የመጥፋት ውሳኔ በጋብቻ ላይ ያለው ውጤት

ቀን:

ከ55 ዓመት በፊት የወጣውና እስካሁን ድረስ በአገራችን ተፈጻሚነት ያለው የፍትሐ ብሔር ሕግ የመጀመሪያ ድንጋጌ ‹‹ሰው ከተወለደበት ቀን አንስቶ እስከሞተበት ቀን ድረስ የሕግ መብት አለው፤›› በማለት የመብትን መጀመሪያና መጨረሻ ጊዜ ወስኗል፡፡ መወለድና መሞት በውል የሚታወቁ ሕጉ እንደቅደም ተከተላቸው ለመብት መጀመሪያና መጨረሻ የወሰናቸው ተፈጥሮአዊ ኩነቶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ሰው ለወትሮው ከሚኖርበት አካባቢ በጠፋ ጊዜ በሕይወት ስለመኖሩና ስለመሞቱ መረጃ የሚጠፋበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ ሕጉ ሰውየው ለረዥም ጊዜያት ከመደበኛ የመኖሪያው አካባቢ በመጥፋትና በሕይወት ስለመኖሩም ምንም መረጃ ባልተገኘበት ሁኔታ የመሞቱ ነገር የቀረበ ወይም የተረጋገጠ ያህል የሚቆጠርበት ሁኔታን ይደነግጋል፡፡ እንዲህ ያለ ሰው በሕይወት አለ ተብሎ በሕግ ያለበትን ግዴታ ለመፈጸም የማይችል ሲሆን፣ ሞተም ተብሎ ግዴታዎች ለሌሎች እንዳይተላለፉ ሊመጣ (ሊመለስ) የሚችልበት አጋጣሚ የተዘጋ ባለመሆኑ ሕጉ ጉዳዩን በጥንቃቄ ይመለከተዋል፡፡

አንድ ሰው የጠፋና ከሁለት ዓመት ወዲህ ወሬውን ያልሰጠ እንደሆነ ማናቸውም ባለጉዳይ ቢሆን የሰውየው መጥፋት በዳኞች እንዲነገር ለመጠየቅ እንደሚችል በአንቀጽ 154 ላይ ሕጉ ደንግጓል፡፡ ይህ የሕግ ሥርዓት የመጥፋት ውሳኔ (Declaration of absence) የሚባለው ሲሆን፣ ሰውየው ለሁለት ዓመት መጥፋቱ ከተረጋገጠና ስለመኖሩ ምንም ዓይነት ማስረጃ ካልተገኘ በዳኞች የሚተላለፍ ፍርድ ነው፡፡ አንድ ሰው የመጥፋት ውሳኔ ከተወሰነበት የመሠረተው ጋብቻ ይፈርሳል፣ ንብረቶቹ በውርስ ለወራሾቹ ይተላለፋሉ፣ ለእርሱ ግላዊ ግዴታ የሚፈጽሙ ወገኖች ግዴታዎቻቸው ይቀራሉ፣ ሆኖም ግላዊ ያልሆኑትን መብቶቹ ወራሾቹ ይጠይቃሉ፡፡ የመጥፋት ውሳኔ ድንጋጌዎች ዓላማ የጠፋውን ሰው መብትና ከሰውየው ጋር ግዴታ የገቡ ሰዎችን ጥቅም ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማስታረቅ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሰውየው ቢጠፋም ሊመጣ የሚችልበት ሁኔታ ያልተዘጋ በመሆኑ ከጠፋው ሰው ንብረት የሚወርሱት ሰዎች ሲመጣ የመመለስ፣ ዋስትና የማቅረብ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ ሰውየው እንደሞተ ሰው የሚቆጠርበት ሁኔታዎች ከሌሉ (ዳኞች ያገኙዋቸው ማስረጃዎች የሞት ማስታወቂያ እንዲነገር የሚያስገድዱ ካልሆኑ በቀር) ሰውየው ሊመጣ ስለሚችል ዋስትና ማስጠራቱና ንብረቱ እንዲመለስለት ማድረጉ አግባብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሰውየው በመጥፋቱ መብታቸው የሚጎዳ ግለሰቦች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ የጠፋው ሰው ልጆች፣ የጠፋው ሰው የትዳር ባልደረባ ወይም ገንዘብ ጠያቂዎች ሰውየው በመጥፋቱ መብታቸው እንዳይጎዳ ሕጉ በሰውየው ንብረት ላይ መብት ይሰጣቸዋል፡፡

የመጥፋት ውሳኔ በፍርድ ቤት ሲወሰን ፍርድ ቤቶቹ ሊከተሏቸው የሚገቡ ሥርዓቶች በፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ ተደንግገዋል፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 154 – 162 ይመለከቷል፡፡ ለመጥፋት ምክንያት የሚሆኑ ሁኔታዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ፣ በጋዜጣ፣ በሬዲዮ ወይም በሌላ የጠፋውን ሰው የመጥራት፣ ሊገኝባቸው በሚችልባቸው ሁኔታዎች ምርመራ የማከናወን ግዴታ ፍርድ ቤቶች የመጥፋት ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት እንዲከተሉዋቸው የተቀመጡ ሥርዓቶች ናቸው፡፡

- Advertisement -

በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው መጥፋትና ጋብቻ ያላቸውን ግንኙነት ነው፡፡ በቤተሰብ ሕግጋቱ እንደተቀመጠው ባልና ሚስት አብረው የመኖር ግዴታ አለባቸው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች አብረው መኖር ካልቻሉ ሕጉ በስምምነት ተለያይተው መኖር እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን የአንዱ ተጋቢ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ ወይም ምንም መረጃ ሳይኖር ሌላኛው ተጋቢ ከመደበኛ መኖሪያው ለሁለት ዓመት ከጠፋ የመጥፋት ውሳኔ ጉዳይ ይመጣል፡፡ ተጋቢውን ለዘለዓለም ጠብቅ ማለት ፍትኃዊ አይሆንም፣ ከጋብቻ የሚያገኛቸውንም ፍሬዎች ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ ጾር በዝቶበት ከሌላ ለመሄድ ቢወስን እንኳን ጋብቻው በሕግ ፊት የፀና በመሆኑ በአመንዝራነት ሊያስጠይቀው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጠፋው ተጋቢ ሊመጣ የሚችልበት ሁኔታ የተዘጋ ባለመሆኑ ንብረቱን በተመለከተ ሕጉ ጥንቃቄ በማድረግ የተወሰኑ ገደቦች በሌላኛው ተጋቢ ወይም በወራሾቹ ላይ ይጥላል፡፡ ለዚህ መፍትሔ እንዲሆን የቤተሰብ ሕጉም ጋብቻ ከሚፈርስባቸው ምክንያቶች አንዱ የመጥፋት ውሳኔ መሆኑን በማስቀመጥ ተጋቢዎች እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ባጋጠማቸው ጊዜ (የትዳር አጋራቸው ያለምንም መረጃ ለሁለት ዓመት ከጠፋ/ች) የመጥፋት ውሳኔ በማስወሰን ጋብቻውን እንዲያፈርሱት ድንጋጌ ቀርጾላቸዋል፡፡

በዚህ የሕግ ድንጋጌ ብዙኃኑ ሲጠቀም አናስተውልም፡፡ አንዳንዶች የትዳር አጋራቸውን ለብዙ ዓመታት እየጠበቁ ይኖራሉ፡፡ ሕጉን ካለማወቅ ወይም በተስፋ ወይም በፀና እምነት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶች ግን ሕጉን አውቀው በጠፋው የትዳር አጋር ላይ የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጥ፣ ጋብቻውም እንዲፈርስ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ስለ ሁለተኛዎቹ ባለትዳሮች የተወሰኑ ነጥቦች እናነሳለን፡፡ የትዳር አጋር በመጥፋቱ የፈረሰ ጋብቻ የትዳር አጋሩ ሲመለስ ይቀጥላል? በመጥፋቱ ጊዜ በሌላኛው ተጋቢ የተፈጸሙ ግብይቶች የጠፋውን የትዳር አጋር ይመለከተዋል? የሚሉትን ነጥቦች የሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 74791 ጥር 17 ቀን 2005 ዓ.ም. የሰጠውን ፍርድ መነሻ በማድረግ እንመለከተዋለን፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ

ወ/ሮ ውቢት ሕሩይና አቶ ዝቋላ ሙሉጌታ ለተወሰኑ ዓመታት በጋብቻ ይኖሩ ነበር፡፡ በ1999 ዓ.ም. ወ/ሮ ውቢት ከትዳር አጋራቸው ጋር ባለመስማማታቸው ከቤት ወጥተው ይጠፋሉ፡፡ ከዚያም በዱባይ አገር መኖር ይጀምራሉ፡፡ ባለቤታቸው ሚስታቸውን ለሁለት ዓመታት ከጠበቁ በኋላ በ2001 ዓ.ም. ፍርድ ቤት በባለቤታቸው ላይ የመጥፋት ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ጠይቀው ፍርድ ቤቱ በጥያቄያቸው መሠረት ወ/ሮ ውበት መጥፋታቸውን በውሳኔው ያረጋግጣል፡፡ ባልየው ለብቻ መኖር በጀመሩበት ዓመታት ግን የወንጀል ድርጊት ፈጸሙ፡፡ ከ2001 ዓ.ም. መጨረሻ እስከ 2002 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ባሉት ጊዜያት ባል ከሌሎች ተባባሪዎች ጋር በመሆን ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና በመገልገል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሐዋሳ ቅርንጫፍ ከሐዋሳ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤት በድምሩ ብር 3,005,002.03 ወጪ ያደርጉና ይወስዳሉ፡፡ የክልሉ ዓቃቤ ሕግም በባልና በግብር አበሮቹ ላይ የወንጀል ክስ በመመሥረት በየካቲት 11 ቀን 2003 ዓ.ም. ጥፋተኛ ተብለው ይቀጣሉ፤ የተጠቀሰውን ገንዘብ እንዲከፍሉ ይወሰንባቸዋል፡፡

የሐዋሳ ከተማ ፋይናንስ የተወሰነለትን ገንዘብ ለመውሰድ አፈጻጸም በፍርድ ቤት ይመሠርትና በባል ስም የተመዘገበ አንድ ቤት እንዲሁም በሚስት ስም የሚታወቅ ሌላ ቤት በሐራጅ ተሸጠው ለአፈጻጸም እንዲውሉ ይጠይቃል፡፡ የአፈጻጸም ፍርድ ቤቱም ንብረቶቹ ተሸጠው ለፋይናንስ እንዲከፈል ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ይህን የሐራጅ ትዕዛዝ የሰሙት ወ/ሮ ውቢት በፍርድ ቤት ይቀርቡና በባላቸው የወንጀል ድርጊት ምክንያት ንብረታቸው እንዲሸጥ መታዘዙ አግባብነት የለውም፣ አንዱ ቤት የጋራ ሌላኛው ደግሞ የግሌ በመሆኑ ለአፈጻጸም ሊቀርብ አይገባውም ሲሉ የተቃውሞ አቤቱታ ለሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀርባሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ ምን አለ?

የሥር ፍርድ ቤቶች አቋም

ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከተው የሐዋሳ ከተማ ፍርድ ቤት መቃወሚያውን ከመረመረ በኋላ ተቃዋሚዋ በስሟ የተመዘገበው ቤት የግሏ መሆኑን ስላላስረዳች ሁለቱም ቤቶች የተጋቢዎቹ የጋራ ናቸው፤ ሆኖም የሐዋሳ ፋይናንስ ገንዘቡ ለጋራ ጥቅም የዋለ መሆኑን ባለማስረዳቱ ተቃዋሚዋ ከሁሉም ቤቶች ያላት ድርሻ ለዕዳው መክፈያነት ሊውል አይገባም ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡

በሐዋሳ ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ጠያቂነት የቀረበለትን ይግባኝ የተመለከተው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበኩሉ ክርክሩን ከሰማ በኋላ ከተጋቢዎቹ ከአንዳቸው በግል የሚጠየቀው ዕዳ የሚከፈለው ከባለ ዕዳው ተጋቢ የግል ሀብት መሆኑ፤ የግል ሀብቱ ዕዳውን ለመሸፈን በቂ በማይሆንበት ጊዜ በጋራ ሀብታቸው መሆኑ ገልጾ የፍርድ ባለዕዳው ንብረት ዕዳውን የሚሸፍን ካልሆነ ከጋራ ሀብታቸው ተሸጦ ለአፈጻጸም ሊውል ይገባል ሲል የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ አሻሽሏል፡፡

የሰበር ችሎቱ ገዥ ፍርድ

የሰበር ችሎቱ በሥር ፍርድ ቤት የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮች ለትንተኔው መሠረት አድርጓል፡፡ ዕዳው በአንዱ ተጋቢ የወንጀል ድርጊት የመጣ መሆኑ እንዳልተካደ፣ ከፍርድ ባለዕዳው ጋር ተጣልተው በ1995 ዓ.ም. ጠፍታ ወደ ዱባይ እንደሄደች፣ በፍርድ ባለዕዳው አመልካችነት በ2001 ዓ.ም. የመጥፋት ውሳኔ እንደተሰጠባት፣ የመጥፋት ውሳኔው ጋብቻውን የሚያፈርስ ምክንያት እንደሆነ፣ ድጋሚ እንዳልተጋቡ፣ ዕዳው የመጣው ከመጥፋት ውሳኔው በኋላ ጋብቻው በፈረሰበት ጊዜ መሆኑን የተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች መሆናቸውን ገልጿል፡፡ የሐዋሳ ፋይናንስ ወ/ሮ ውቢት ከዱባይ መልስ የመጥፋት ውሳኔውን ከነውጤቱ ያሻረች በመሆኑ ፍቺ እንዳልተፈጸመ ስለሚቆጠር ዕዳው በጋብቻ ጊዜ የተፈጸመ ነው ሲል ተከራክሯል፡፡ ሰበር ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ በሰጠው ፍርድ የመጥፋት ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ የሚመለስ ሰው በንብረቶቹ ላይ የነበረውን መብት መልሶ እንደሚጎናጸፍ የሚገልጽ ከመሆኑ በስተቀር ቀደም ሲል ጋብቻ የነበረው ከሆነ ጠፋ በመባሉ ምክንያት ፈርሶ የነበረው ጋብቻ ተመልሶ ሕይወት የሚዘራ ስለመሆኑ የሚጠቁመው ነገር አለመኖሩን ተንትኗል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ይላል ችሎቱ በትንታኔው አመልካች ውሳኔውን ማሻሯ የፈረሰውን ጋብቻ ከፈረሰበት ቀን ጀምሮም ሆነ ከተመለሰበት ቀን ጀምሮ መልሶ የሚያቋቁመው ባለመሆኑ ዕዳው የመጣው ጋብቻው ፀንቶ ባለበት ጊዜ እንደሆነ ይገመታል በማለት ተጠሪው ያቀረበው ክርክር የሕግ መሠረት እንደሌለው ገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት ሰበር ችሎቱ ጋብቻው ከፈረሰ በኋላ የፍርድ ባለዕዳ በግል ያመጣው ዕዳ የተቃውሞ አመልካችን ስለማይመለከት ፍርዱ በፍርድ ባለዕዳ ድርሻ በሆነው በንብረቶቹ ግምት ግማሽ ላይ ብቻ ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል ሲል ገዥ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

በፍርዱ ላይ አጭር ምልከታ

በዚህ ጽሑፍ መነሻ በሆነን ጉዳይ በዋናነት የተነሳው ጭብጥ የመጥፋት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ አንዱ ተጋቢ በግሉ የገባው ዕዳ የጠፋው ተጋቢ የመጥፋት ውሳኔውን እንዲነሳ ካደረገ በኋላ ይመለከተዋል ወይስ አይመለከተውም የሚለው ጭብጥ ነው፡፡ የፍርድ ቤቶቹ ትንታኔም ልዩነት ምንጭ ይህንኑ በመወሰን ላይ ነው፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የመጥፋት ውሳኔው መሻሩ በራሱ ጋብቻው እንዲፀና የሚያደርገው በመሆኑ ከመጥፋት በኋላ የፍርድ ባለዕዳው ያመጣው ዕዳ ሁለቱንም ተጋቢዎች የሚመለከት መሆኑን ተንትኗል፡፡ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ጋብቻው የመጥፋት ውሳኔው በመሻሩ መፅናቱን በመቀበል የዕዳው ባህርይ ላይ ግን ዕዳው ለጋራ ጥቅም የዋለ መሆኑ ባለመረጋገጡ ግማሹን የንብረቱን ክፍል አይመለክትም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል፡፡ የሁለቱን ፍርድ ቤቶች አቋም የሚያመሳስላቸው የመጥፋት ውሳኔ ከተሻረ የፈረሰው ጋብቻ እንደሚመለስ በማሰብ የያዙት አቋም ነው፡፡

ይሁን እንጂ የሁለቱ የሥር ፍርድ ቤቶች ትንታኔ ሕጉን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ የመጥፋት ውሳኔ ጋብቻን የሚያፈርስ መሆኑን ይገልጻል እንጂ የመጥፋት ውሳኔ መሻሩ በጋብቻው ሕልውና ላይ ያለውን ውጤት አይደነግግም፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ በአንቀጽ 170 እና 171 ላይ በግልጽ ያስቀመጠው የጠፋው ሰው ሲመለስ ንብረቶቹ እንደሚመለሱለት ነው፡፡ ጋብቻን በተመለከተ የጠፋው ሰው ሲመለስ ጋብቻው ይፀናል የሚል ድንጋጌም የለም፤ በትርጉምም አይደርስበትም፡፡  የጠፋው ሰው በመመለሱ ጋብቻው እንደገና እንደሚመለስ አድርጎ መተርጎም የሌለ ድንጋጌ መቅረፅ ነው፡፡ ጋብቻው በመጥፋት ውሳኔ ከፈረሰ በኋላ የጋብቻውን ሕልውና የሚወስነው የቤተሰብ ሕጉ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት አንድ ጋብቻ ከፈረሰ በኋላ እንደገና ጋብቻው የሚመለስበት ሁኔታ ተጋቢዎቹ እንደ አዲስ ከተጋቡ ወይም በሌላ አኳኋን አብረው መኖር ሲጀምሩ ነው፡፡ ያም ቢሆን እንደገና ጋብቻው በፈረሰበትና በተጋቡበት ጊዜ መካከል በግለሰቦቹ በግል የተፈጸሙ ግብይቶች የግል ሆነው መቅረታቸው አከራካሪ አይሆንም፡፡

ከዚህ በመነሳት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ፍርድ ሕጉን የተከተለና ፍትኃዊ ነው፡፡ ችሎቱ የመጥፋት ውሳኔ ጋብቻውን እንዳፈረሰው፣ የመጥፋት ውሳኔ መሻሩ በንብረት በኩል ብቻ ውጤት እንደሚኖረው መግለጹ ሕጉን የተከተለ ነው፡፡ የመጥፋት ውሳኔ ከተሻረ በኋላ የቀድሞ ተጋቢዎቹ እንደገና ጋብቻ ካልመሠረቱ በቀር ጋብቻው ወዲያውኑ (Automatically) እንደሚቀጥል የሚገልጽ ድንጋጌ የለም፡፡ በተያዘው ጉዳይ የቀድሞ ባልና ሚስት በመጥፋት ውሳኔ ጋብቻቸው የፈረሰ ሲሆን፣ ሚስት የመጥፋት ውሳኔውን ካሻረች በኋላም አብረው አለመቀጠላቸው፣ ጋብቻም አለመመሥረታቸው በሥር ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ አንፃር ሰበር ችሎቱ ‹‹ሚስት›› እና ‹‹ባል›› የሚሉት ቃላት ከመጥፋት  ወሳኔ በኋላ ተፈጻሚ እንደማይሆኑ በመተንተን ዕዳው የፍርድ ባለዕዳን ብቻ የሚመለከትና በራሱ ንብረት ብቻ የሚፈጸም መሆኑን መግለጹ ፍትኃዊ ነው፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...