በሒሩት ደበበ
ባለፈው ሳምንት የሪፖርተር ዕትም አቶ መንግሥቱ መስፍን የተባሉ ጸሐፊ የአገራችን የመገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪ በዕውቀት እንደማይሠራና አገራዊ ፍልስፍናም እንደሌለው አጥብቀው ተችተዋል፡፡ በተለይ ዓለም አቀፉን የዘርፉ ንድፈ ሐሳብ በመጠቃቀስ የእኛ አገር ሚዲያዎችን መሠረታዊ ጉድለት በጅምላም ቢሆን መነካካታቸውና ከሙያ አንፃር ትዝብታቸውን ማስቀመጣቸውን ተረድቻለሁ፡፡ በግሌ የማልስማማባቸው አንዳንድ ነጥቦች አሉ፡፡ በተለይ በግል ስም ሀሉም፣ ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም ሁሉንም በጅምላ በአንድ ቅርጫት መክተታቸው አሳማኝ አይመስለኝም፡፡
አገሪቱ በዴሞክራሲ ጉዞውም ሆነ በሚዲያ ኢንዱስትሪው የተጓዘችበት ጊዜ አጭር ከመሆኑ አንፃር፣ ወደ ማኅበራዊ ኃላፊነትና ብሔራዊ ጥቅም እያተኮሩ ያሉ የግል መገናኛ ብዙኃንን በበጐ ሊጠቀሱ ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ አልባሌ ሥነ ምግባርን፣ የሞራልና የማንነት ክስረትን እንዲሁም የአገር እሴቶች ጉዳትን የሚተቹ የኅትመት ውጤቶችና የሬዲዮ ፕሮግራሞች እንዳሉ አይዘነጋም፡፡ ሙያተኞችም እንኳን ዛሬ ይነስም ይብዛም የመረጃ ነፃነትን ተረጋግቶ መጻፍ በሚያስገድልበት ጊዜም በእሳት ውስጥ ያለፉ ሰዎች ነበሩ፡፡ በፖለቲካ ትንታኔ፣ በምርመራ ዘገባና የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅም የሚጐዱ ድርጊቶችን በሚዛናዊነት የሚያጋልጡና የሚተቹም እንዳሉ የሚታወቅ ነው፡፡
በጥቅሉ የሚዲያ ኢንዱስትሪው በተንሸዋረረ መንገድ እየተገነባ መሆኑ፣ በተለይ ዋና ባለድርሻ አካላት መንግሥትና ዘርፉን የሚመሩት ወገኖች እንዲመረምሩዋቸው የተነሱት ነጥቦች ግን የምስማማባቸውና ጠቃሚ ናቸው፡፡
በእኔ በኩል ለዛሬ ከዚያው ርዕሰ ጉዳይ ጋር በሚስማማ ሁኔታ የአገራችን የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ሙያተኞች የሚፈተኑበትና ለሕዝብ ትዝብት የሚጋለጡበትን የምርጫ ዘገባ ተሞክሮ ላነሳሳ፡፡ መረጃዎቹን ያገኘኋቸው በተለያዩ ጊዜያት በዘርፉ ከተደረጉ ጥናቶች ሲሆን፣ በያዝነው ምርጫ 2007 ወቅት ትምህርት ይሰጣሉ የሚልም እምነት አለኝ፡፡
ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ወሳኝ ሚና የሚጫወት ሲሆን፣ ለስኬታማነቱም ሚዲያ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ዘ ካውንስል ፎር ዴሞክራቲክ ኤሌክሽን (The Council for Democratic Elections) እ.ኤ.አ. በ2004 ባወጣው ሪፖርት አብራርቷል፡፡ ሚዲያዎች የምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉዋቸውን የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጮችን ለኅብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ይሠራሉ፡፡ ራሱ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሒደቱ ሳይስተጓጐል በነፃነት፣ በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ አኳኋን እንዲካሄድ፣ ምርጫ ቦርድና መንግሥትም ተገቢውን የውድድር ሜዳ እንዲፈጥሩ ከመነሻ እስከ መድረሻ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2002 ለሚዲያ ሥነ ምግባር የጋዜጠኛውን ዋነኛ ኃላፊነትን ትውውቅ (Media Ethics: an Introduction to Responsible Journalism) በሚል ርዕስ የታተመው ሥራ በምርጫ ዘገባ ላይ የሚለው አለ፡፡ ‹‹ሚዲያ ትክክለኛ፣ ሚዛናዊና ከአድልኦ የፀዳ ዘገባ ማቅረቡ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ትክክለኛውን ምንጭ መጠቀምና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካል ማነጋገርም ሌላው ጋዜጠኞች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ዓብይ ጉዳይ ነው፡፡ በተቃራኒው ባልተጣራ መረጃ ላይ ተንተርሶ ዘገባዎችን ማቅረብ ኅብረተሰቡን ወዳልሆነ አቅጣጫ ሊመራው ስለሚችል ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤›› ይላል፡፡
ዓለም አቀፍ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ወደ አገራችን መገናኛ ብዙኃንና የምርጫ ዘገባዎች ስንመለስ በርካታ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት የተካሄደ ‹‹የምርጫ ዘገባና ድክመቶቻችን›› (2000) የዳሰሰ ጥናት ላይ የቀረቡትን ጠቃሚ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በ1997 ምርጫ ወቅት የግል ጋዜጦች የተቃዋሚውን ጎራ ያለምንም በቂ ምክንያት በመደገፍ፣ መንግሥትና ገዥው ፓርቲን በተገኘው አጋጣሚ ለማውረድ የተቀናጀ የሚመስል ዘመቻ አካሂደዋል ይላል፡፡ ይህም በተለይ በምርጫ ወቅት ፍፁም ሊዘነጋ የማይገባውን የሚዲያ ገለልተኝነትና ሚዛናዊነት አፈር እንዲበላ አድርጐታል፡፡
እዚህ ላይ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩ ሁሉም ሚዲያዎችም የገለልተኝነትና የሚዛናዊነት ችግር ተንፀባርቆባቸዋል፡፡ በተለይ ከምርጫው ድምፅ መስጫ ዕለት በኋላ የፖሊሲ ለውጥ የተደረገ እስኪመስል ድረስ ክፍተቶች ታይተውባቸዋል ይላል ጥናቱ፡፡
ጥናቱ በስም እየጠቀሰ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ባልጠቅሳቸውም) ካቀረባቸው መድሏዊ ዘገባዎች መካከል የጥቂቶቹን ርዕስ ማሳየት መልካም ይመስለኛል፡፡
- ንቦቹ ተናደፉ! ከ40 በላይ ንፁኃን ዜጐች ተጨፈጨፉ! ከ120 በላይ ቆሰሉ! (ባልተጠራበት ሁኔታ)
- አዲሶቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ከፊታቸው ከባድ ፈተና ይጠበቅባቸዋል! – (ምርጫው ሳያልቅ)
- የተፎካከሩት ‹‹ኢሕአዴግና ሕዝቡ ናቸው›› (የኢሕአዴግ ደጋፊዎችስ?)
እነዚህና በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ሕጋዊ ተቋማትና ምርጫ ቦርድ ላይ የተካሄዱ ስም ማጥፋትና ዘመቻዎች ከፍተኛ ነበሩ፡፡ አንዳንዴ ራሱ የግሉ ፕሬሱ ከተቃዋሚው ኃይል በላይ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የፈጠረው ጫና ከዴሞክራሲያዊ የሚዲያ ዘገባ መርህ ያፈነገጠ ሆኖ ታይቷል፡፡
በጥናቱ እንደተመለከተው የመንግሥትም ሆኑ የግል ሚዲያዎች ከፖለቲካ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሕዝብ ለሚደርስ መልዕክት ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡ እንደ አመቺነቱም የጋዜጣ ዓምድና የአየር ሰዓት በፍትሐዊ ድልድል መስጠት አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ ዛሬ በሥራ ላይ የሌሉት ብዙዎቹ የግል ጋዜጦች ለተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከ85 በመቶ በላይ ሽፋን ሲሰጡ ለኢሕአዴግ (ገዥው ፓርቲ) ከ15 በታች ሽፋን ሰጥተዋል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካለፉት ምርጫዎች ትምህርት የወሰደ ይመስላል፡፡ ለመገናኛ ብዙኃን የምርጫ አዘጋገብ ሥነ ምግባርን እስከ መንደፍ ደርሷል፡፡ እርግጥ ይህ አካሄድ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መሆኑንም ማክዶናል ናፔትራም (1998) “Key Guides to Information Service in Media Ethics)’’ (የሚዲያ ሙያዊ የሥነ ምግባር ደንብ አስፈላጊነት) በሚለው ጥናታቸው ጠቁመውታል፡፡
‹‹ጋዜጠኛ ማንኛውም ሰው ሊኖረው የማይችለው በተለይም የዜና፣ የሐተታ ወይም የፕሮግራምና የዶክመንተሪ አዘገጃጀትና የመረጃ አሰባሰብ ዕውቅት አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪነት በጥብቅ ሊገዛለት የሚገባው ጥብቅ የሙያው ሥነ ምግባር ሊመራው ይገባል፤›› ይላል፡፡
ከዚህ በመነሳት ነው ጋዜጠኛ እንደ አገር ዜጋ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ የሚከበሩለት ቢሆንም፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ውጪ ሙያውን ቢያከናውን ይመረጣል የሚባለው፡፡ በሠለጠነና አደገ በሚባለው ማኅበረሰብ ጭምር በገንዘብና በጥቅም እየተገዙ በተወዳዳሪዎች የሚጠመዘዙ ጋዜጠኞች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ ሌላው ቀርቶ በጥቅም ግጭት ምክንያት ሊጥሉት የፈለጉትን ፓርቲ (ተወዳዳሪ) ጥፋት፣ ክስረት ወይም ኢሥነ ምግባራዊ ድርጊት በማጋለጥ በምርጫ ወቅት ለሕዝብ ይፋ አድርገው ጉቦ የሚቀበሉም አይታጠቁም፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ነው ጋዜጠኝነት ሚዛናዊ፣ ገለልተኝነትንና ነፃ የመሆን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ለሕዝብ ጥቅም (ለሀቅ) የሚቆም የሞራል ባለቤት መሆን ያለበት፡፡ በየትኛውም ዓለም ፓርቲ፣ መንግሥትም ሆነ መሪዎች ኃላፊና ተቀያሪ ናቸው፡፡ የማይለወጠው ሕዝብና አገር ነው፡፡ ስለዚህ የተከበረውን የጋዜጠኝነት ሙያ ለሕዝብና ለአገር ዘብ እንዲቆም ማድረግ ላይ ያሉብን አገራዊ ክፍተቶች ሊወገዱ ይገባቸዋል፡፡
በአገራችን ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው የ2002 ጠቅላላ ምርጫ ኢሕአዴግ በከፍተኛ አብላጫ ድምፅ አሸንፎ አውራ ፓርቲ የመሠረተበት ጊዜ ነው፡፡ በዚያን ወቅት የነበረው የምርጫ አዘጋገብ ሒደት በአንፃራዊነት የሰከነና ከጽንፍና ጽንፍ የፖለቲካ ፍላጐት የወጣ እንደነበር ታይቷል ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ እውነት የሚጠቀሱ ምክንያቶችም አሉ፡፡ አንደኛው ከምርጫ 2002 በፊት የወጣ የዘገባ ሥነ ምግባር ሥራ ላይ በመዋሉ፣ ሙያተኛውም ሆነ የኅትመት ውጤት ባለቤቶች ነገሮችን በሰከነ መንገድ ለማየት ዕድል አግኝተዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ከምርጫው ችግሮች ጋር ነበር ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው በ97 ምርጫ ማግሥት የተፈጠረው ግጭትና ብጥብጥ የብዙዎቹን ሰላም ወዳድ ዜጐች ስሜት የጎዳ ሲሆን፣ ብጥብጥ አንስተው ወዳልተፈለገ መንገድ መሄድ የሚሹ ወገኖችን ከምኅዳሩ አስወጥቷቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ የፓርቲዎቹ በሥነ ምግባር ደንብ መመራትና ሌሎች ሕጐች መውጣታቸውም የለውጡ አካል ተደርጐ ታይቷል፡፡
ይኼው ጥናት የአራተኛውን ብሔራዊ ምርጫ የመገናኛ ብዙኃን አዘጋገብ በበጐ ጅምር ጠቅሷል፡፡ ‹‹ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የምርጫ 2002 ዘገባ በተቻለ መጠን ሚዛናዊ አድርጐ ለማቅረብ የተሞከረበት ነው፡፡ … ከምርጫ 97 ዘገባ ጋር ሲወዳደርም መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን ለመጠበቅ የተደረጉ ጥረቶች አሉ፤›› በማለት ያስረዳል፡፡
ዘንድሮ አምስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መርሐ ግብር ይፋ ከተደረገ አንስቶ የመገናኛ ብዙኃንን አካሄድ አስመልክቶ ያነጋገርኳቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ክፍል ተማሪዎች ነበሩ፡፡ በተለይ በጉዳዩ ላይ የድኅረ ምረቃ መመረቂያ ጽሑፍ እያዘጋጀ እንደሆነ የገለጸልኝ አንድ ዕጩ ተመራቂ በሁለት መንገድ ከፍሎ ይተነትናል፡፡
በመንግሥት ሥር ያሉ የሕትመትም ሆነ የብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን በየዕለቱ ዜናዎቻቸው ለምርጫው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ በተለይ ወቅቱ የቅድመ ምርጫ እንደመሆኑ በመራጮች ምዝገባ ላይ ተከታታይ ሥራ አከናውነዋል፡፡ እንደ ጉድለት የሚታየኝ ግን፣ ለፓርቲዎች የተመደበው የመከራከሪያ ገጽ (የአየር ሰዓት) ሳይጀመር ለገዥው ፓርቲ ‹‹ቅስቀሳ›› የሚመስሉ ዘገባዎች የሚሰጡትን ሽፋን ማቆም ወይም መቀነስ አለባቸው፡፡ በምትኩም ለተቃዋሚ ተፎካካሪዎችም ዕድል ሊሰጡ ይገባል ይላል፡፡
በምሳሌ ሲያስረዳም የባቡር ፕሮጀክት ምርቃት፣ የዓባይ ግድብና የሜጋ ፕሮጀክት ዜናዎች የመንግሥት አፈጻጸሞች ስለሆኑ በመደበኛው አሠራር ይስተናገዳሉ፡፡ የኦሕዴድ ጉባዔ፣ የሕወሓት 40ኛ ዓመት፣ የብአዴን ሰላማዊ ሠልፍ፣ የደኢሕዴን ግምገማ እያሉ ሲዘግቡ መኢአድ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ መድረክ፣ አረና፣ ወዘተ የሚባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ መዘንጋት የለባቸውም በማለት ያስረዳል፡፡
ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝባዊ ውይይት፣ ሰላማዊ ሠልፍም ሆነ ወቅታዊ መግለጫዎች በምሥል፣ በድምፅና በቃላት ብዛት ተመጣጣኝ የሆነ ዕድል በመስጠት ገለልተኝነታቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል በማለኸት ዕጩ ተመራቂው ነግሮኛል በቅርቡ አንድትና መኢአድ የተሰኙት በምርጫው የሚፎካከሩ ፓርቲዎች የውስጥ ችግር ላይ የመንግሥት ሚዲያው ዘገባ ሚዛናዊ አይመስልም ነበር፡፡ ችግሩ በተጨባጭ በፓርቲዎቹ ውስጥ ባሉት መሪዎች የግል ፍላጐት የተፈጠረ መሆኑ እየታወቀ፣ በተለይ ኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (EBC) ለብተናውና ውዝግቡ የሰጠው ተደጋጋሚ ትኩረት ‹‹መፍረሳቸውን የፈለገ አስመስሎታል›› ያሉኝ ብዙዎች ናቸው፡፡ በአስተያየት ሰጪነት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ የሚሉ ሰዎች ገለልተኝነት አጠራጣሪ መሆንና ከምርጫ ቦርድ ውሳኔ በፊት ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ዘገባዎችና ‹‹የሕግ ባለሙያ›› ማብራሪያዎች መቅረባቸውም ተገቢ እንዳልነበሩ ጠቁመዋል፡፡
በግሉ መስክ የተሰማሩ የመገናኛ ብዙኃን የምርጫ 2007 የምርጫ ዘገባንም በሦስት ከፍሎ እንደሚመለከተው ይገልጻል ባለሙያው፡፡ በአንደኛው ጎራ ያሉት ምርጫውን ወቅታዊ የአገር ጉዳይ አድርገው በመዘገብና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ዕድሎችን በመስጠት የሚሠሩ ናቸው፡፡ እነዚህኞቹ በርዕሰ አንቀፃቸው ሳይቀር ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይበጁ የመንግሥት አካላትንም ሆነ የፓርቲዎቹን እንቅስቃሴ በመተቸት የዜጐች የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመመረጥና የመምረጥ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ የሚወተውቱ ናቸው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩት አሁንም የአንድ ወገን መረጃ የሚጫጫናቸው ናቸው፡፡ ስለምርጫው አለመሳካት ከወዲሁ መናገር የሚዳዳቸው፣ የምኅዳር መጥበብ፣ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆን፣ የሕዝቡ ለመምረጥ አለመመዝገብ፣ ወዘተ አጀንዳቸው የሆኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች አይነሱም ባይባልም በተቻለ መጠን በመረጃ ላይ ተመሥርቶ አወዛጋቢ ሁኔታ በማይፈጥር መንገድ በገለልተኝነት ሊመረመሩና ሊጋለጡ ይገባቸዋል፡፡ ከምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሒደት ጋር እምብዛም በማይሄዱ ጉዳዮች (በሕግ ጥላ ሥር ስላሉ ዜጎች፣ የትጥቅ ትግል ጀመሩ ስለሚባሉ ኃይሎችና የቀለም አብዮት ዓለም አቀፍ ታሪኮች ብዙ ማለትም ለሒደቱ የሚጠቅመው ነገር የለም) ይላሉ ምሁሩ፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ምርጫውን ትኩረት የነፈጉት የግል የኅትመት ውጤቶችን ይመለከታል፡፡ ምክንያታቸው ‹‹ጉዳያችን አይደለም!››፣ ‹‹ምን ምርጫ አለ?›› ከማለት ይሁን በገበያው ለሚፈለግ ርዕሰ ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት ለገዥው ፓርቲ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለምርጫ ቦርድም ሆነ ለሕዝብ አስተያየት ትኩረት ያልሰጡና ተሟሙቀው ወደ ምርጫ ዘገባ ያልገቡ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የፍቅር፣ የኪነ ጥበብና የፋሽን መጽሔቶች እንዲሁም የኢኮኖሚና የቢዝነስ ጋዜጦች ሳይቀሩ በምርጫ ዘገባ ላይ ከሚጠመዱበት ሁኔታ አንፃር ትኩረቱ ተቀዛቅዟል፡፡ ከእነዚህ ተርታ የሚሠለፉ ‹‹የምርጫ አዘናጊዎች›› የሚባሉ የኤፍኤም ሬዲዮ የአየር ሰዓቶች ጉዳይም አሳሳቢ እንደሆነ አልሸሸገም፡፡
ኮቮክና ሮዚና ትራል (2001) “The Elements of Journalism” (የጋዜጠኝነት አላባውያን) ሲሉ በጻፉት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ በተለይ በታዳጊው ዓለም የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ገለልተኝነት ይበልጥ ፈተና ላይ የሚወድቀው በምርጫ ወቅት ነው፡፡ የገለልተኝነትና የሚዛናዊነት አቅምና ሥነ ምግባር ማጣቱ የሚመነጨው በተለያዩ ምክንያቶች እንደሆነም ይታመናል፡፡ በቀዳሚነት ከጋዜጠኞች ወይም ከአርታኢያንና ከአሳታሚዎች (ባለቤቶች) ፍላጐትና ዝንባሌ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በሁለተኝነት ከራሳቸው መንግሥታዊ የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኝነትና ብቃት ጋር ይያያዛል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ፍርድ ቤቶች፣ ቅሬታ ሰሚ ተቋማትና ለሕዝብ ተጠሪ የሆኑ ምክር ቤቶች ካልተጠናከሩ የመንግሥት ሚዲያው ብቻውን ተነጥሎ ነፃና ገለልተኛ አቋም ሊገነባ አይችልም ይላሉ ምሁራኑ፡፡
‹‹አንዳንድ የርዕዮተ ዓለም ጫና ማሳደር የሚፈልጉ አገሮች፣ ኤምባሲዎችና መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም በመገናኛ ብዙኃን የምርጫ ዘገባ ገለልተኝነት ላይ የሚያሳድሩት ጫና በምርጫ ወቅት ይበረታል፤›› ያለው ደግሞ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዕጩ ተመራቂ ነው፡፡ በእርግጥም ቀደም ሲል በገለጸው በ1997 ምርጫ ዘገባ ጥናት ላይ አንዱ የገለልተኝነት ፈተና፣ በእጅ አዙር ጋዜጠኛውንና አሳታሚውን ይጫኑና የገንዘብ ድጋፍ ያደርጉለት የነበሩት እነዚህ አካላት መሆናቸው ተረጋግጧል ብሏል፡፡
በአጠቃላይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በአውሮፓ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕግ የተጠበቀና የዜጐች ፖለቲካዊ ሕይወት አካል እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህም የዓለም ትምህርት ተጠናክሯል፡፡ ቤተ መጻሕፍት እንዲበራከቱ፣ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲያብቡና የራሳቸውን የኅትመት ውጤቶች እንዲያወጡ (ዴሞክራሲ እንዲፋፋ)፣ የፖስታና የመልዕክት ልውውጥና ከፍተኛ መሻሻል እንዲያሳይ አድርጓል፡፡ አሁን ደግሞ በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለማኅበራዊ ድረ ገጽና በኦንላይን የመረጃ ፍሰት ዓለም አቀፍ በርን ከፍቷል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በተነሳ ቁጥር ስሙ ሳይጠራ የማያልፈው የሰሜን አሜሪካውን “First Amendment” (1971) ጨምሮ በሌሎች የአውሮፓ አገሮች የሚገኙ የፕሬስ ነፃነት ድንጋጌዎች ይጠቀሳሉ፡፡
አገራችን የሥልጣኔ ዕድሜዋን፣ የነፃነት ታሪኳንና ባለቤትነቷን ጠብቃ የኖረች ቢሆንም፣ ከ20 ዓመታት ወዲህ ደካማ ቢሆንም የዴሞክራሲ ጉዞዋን ጀምራለች፡፡ ምርጫም፣ ፕሬሶችም እየታዩ ነው፡፡ ነገር ግን ዘወትር ከሒደት እየተማሩ፣ ካለፈው እያሻሻሉ፣ ሕዝቡ የተቀበለውና ተዓማኒነት ያለው ምርጫን ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ተጠቃሚ የሚሆነው አገርና ሕዝብ ሳይሆን በየሥፍራው ያደፈጠው ጠላት ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ለማንም ሳይወግኑ ሚዛናዊነታቸውንና ገለልተኝነታቸውን በግልጽ እያሳዩ መሥራት ከቻሉ ለሰላማዊውና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ድርሻ ያበረክታሉ፡፡ ሚዛናዊነትና ገለልተኝነት የሙያው ሥነ ምግባር መለኪያ ናቸውና፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡