አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር
የኢትዮ-ጂቡቲ 21ኛው የጋራ የሚኒስትሮች ጉባዔ በጂቡቲ በቅርቡ ተካሂዷል፡፡ በዚህ የጋራ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባዔ ከኢትዮጵያ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊዎች ተገኝተው በየዘርፎቻቸው በተወያዩባቸው ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በጂቡቲ ቆይታቸው ከሪፖርተርና ከሌሎች ሁለት የአገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማት ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ ቃለ ምልልሱን ዮሐንስ አንበርብር እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡
ጥያቄ፡- በጋራ የሚኒስትሮች ጉባዔው ላይ ትራንስፖርት ሚኒስቴርን የሚመለከቱት አጀንዳዎች ምንድናቸው? የደረሳችሁበትስ ስምምነት ምንድነው?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- የደረስንባቸው ስምምነቶች በተለይ ከትራንስፖርት ዘርፍ ጋር ተያይዞ የመንገደኞች ትራንስፖርት፣ ማለትም ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞችና በተመሳሳይም ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የመንገደኞች ትራንስፖርትን ለመጀመር የሚያስችል ነው፡፡ የጂቡቲ ትራንስፖርተሮች ወይም የትራንስፖርት ማኅበራት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሕዝብ ትራንስፖርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሥምሪት እንዲጀምሩ የሚያግዝ ስምምነት ነው የተፈራረምነው፡፡ እንግዲህ እንደሚታወቀው በሁለቱም አገሮች ድንበሮች ላይ ከፍተኛ የመንገደኞች እንቅስቃሴ ነው ያለው፡፡ በዚህ ምክንያትም አሮጌውን ባቡር አስጀምረነው ነበር፡፡ አዲሱ የባቡር ፕሮጀክት ሲጀመር የቀድሞው መስመር ከተዘረጋበት ጋር በመገናኘቱ የቀድሞውን አነሳነው እንጂ፣ በቀን ከአሥር ሺሕ በላይ ሰዎች ማመላለስ እንደተቻለ ባለፉት አራት ወራት አይተነዋል፡፡ ምን ያህል የሕዝብ እንቅስቃሴ እንዳለ ነው የሚያሳየው፡፡ አሁን በሁለቱ አገሮች መካከል ብቸኛው የተራንስፖርት አማራጭ የአየር ትራንስፖርትና የግል ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁን ባደረግነው ውይይት የንግድ ትራንስፖርት መፈቀዱ፣ በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ በተጨማሪም ወደ መሀልም ለሚደረግ ጉዞ ከፍተኛ የሆነ እገዛ ነው የሚፈጥረው፡፡
በሁለቱ አገሮች ግራና ቀኝ የሚኖሩ ሕዝቦች በብዙ ነገር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በደም፣ በዝምድናና በተጨማሪም በንግድ የተሳሰሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ትራንስፖርት መጀመር ይህንን የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ትስስር በጣም ነው የሚያጠናክረው፡፡ ማንኛውም ሰው የአቅሙን ያህል ከፍሎ የሚሄድበት አማራጭ ነው፡፡ በሚኒስትሮቹ የጋራ ጉባዔ የተፈራረምነው አንደኛው ስምምነት ይኼ ነው፡፡ ሌሎች አምስት ስድስት ስምምነቶች ቢኖሩም፡፡
ጥያቄ፡- ኢትዮጵያና ጂቡቲን የሚያገናኘው አዲሱ የባቡር መስመር በሚቀጥለው ዓመት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተወያያችሁበትና እያደረጋችሁ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- አዲሱ የባቡር መስመር በሚቀጥለው ዓመት በጥቅምት ወር ይጠናቀቃል ብለን እየሠራን ነው፡፡ በጣም ጠንክረን የምንሠራ ከሆነ ምናልባትም ከዚያ ቀደም ብለን ልናጠናቅቀው እንችላለን፡፡ የባቡሩ ግንባታ በሁለት ተከፍሎ ነው እየተከናወነ ያለው፡፡ አንደኛው በኢትዮጵያ ድንበር ነው፡፡ በዚህ በኩል ያለው ፕሮጀክት ከአጠቃላይ ፕሮጀክቱ 85 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው፡፡ በጂቡቲ በኩል ያለው ፕሮጀክት ቀሪውን 15 በመቶ ነው የሚሸፍነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት 85 በመቶ የሚሆነውን በራሱ ድንበር ውስጥ የሚገኘውን መስመር ያሠራል፡፡ እንደዚሁም የጂቡቲ መንግሥት የራሱን ድርሻ ያሠራል ማለት ነው፡፡ በሁለቱም ድንበሮች ላይ የሚገኘውን የባቡር መስመር የሚሠራው ድርጅት በአጋጣሚ አንድ ኩባንያ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የፊዚካል ሥራው ከጂቡቲ ወደብ እስከ ሰበታ ድረስ ያለው አብዛኛው ማለትም 90 በመቶ ተጠናቋል፡፡ አሁን የሚቀሩት የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች ናቸው፡፡ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ መስመር የማምጣት፣ ሐዲዶች የማንጠፍና ሌሎች የማስተካከያና የዲዛይን ሥራዎች ናቸው የቀሩት፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በባቡር መስመሩ ላይ በርካታ ጣቢያዎች አሉ፡፡ የእነዚህ ጣቢያዎች ግንባታ ብቻ ወደኋላ ቀርቶብናል፡፡ 30 በመቶ ላይ ነው ግንባታቸው የሚገኘው፡፡ ነገር ግን በጊዜያቸው የሚያልቁ ናቸው፡፡ ሌላው የኤሌክትሪክ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሥሪያ ቤት ጋር ስምምነት ተፈራርመናል፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ የተለየው በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ የሚገኝ የአገልግሎት ጣቢያ ፕሮጀክት ነው፡፡ በዚህ ድንበር ላይ ብዙ አገልግሎቶች ናቸው የሚሰጡት፡፡ የኢሚግሬሽን፣ የቪዛ፣ የጉምሩክ፣ ሌሎች የደኅንነት ፍተሻዎች የመሳሰሉት ይካሄዳሉ፡፡ በዚህ ረገድ የተስማማነው የተጠቀሱት አገልግሎቶች የሚሰጡበት ማዕከል በጋራ በሁለቱም መንግሥታት እንዲገነባ ነው፡፡ የጂቡቲ ኢሚግሬሽን፣ የኢትዮጵያም እንዲሁም የጂቡቲ ጉምሩክም የኢትዮጵያም አንድ ሕንፃ ላይ በጋራ ሆነው በአንድ ዶክመንት የኢሚግሬሽንንም ሆነ የጉምሩክንም ፕሮሰስ የመጨረስ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ የዚህን ሥራ ጀምረነዋል፡፡ ይህ በራሱ የባቡሩን የምልልስ ፍጥነት የሚጨምርና የትራንስፖርት ዋጋውን ደግሞ በመቀነስ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለን ነው ያሰብነው፡፡
ጥያቄ፡- የባቡር ፕሮጀክት ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን የሚጠይቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አሁን የቀድሞው የባቡር ንብረቶችና ሀብቶች በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- ነባሩ ሐዲድ አብዛኛው ተነስቶ ተቀምጧል፡፡ በነገራችን ላይ ንብረትነቱ የሁለቱም አገሮች ነው፡፡ በድሮው ስምምነት ላይ የሚለው በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ያለው ማንኛውም ንብረት የኢትዮጵያ ይሆናል፡፡ ጂቡቲ ዘንድ ያለው ጂቡቲ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል ያለው አብዛኛው ቢነሳም ለአዲሱ የባቡር ፕሮጀክት ሲሚንቶ ማቅረብ እንዲቻል የተወሰነ የሐዲድ መስመር አለ፡፡ ሌላው ግን በአብዛኛው ተነስቶ ተቀምጧል፡፡ ይህ ንብረት እንደገና ልንጠቀምበት የሚያስችለን ትልቅ ሀብት ነው፡፡ በዚህ ንብረት ላይ ከዚህ ቀደም ዝርፊያዎች ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሞላ ጐደል ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡
ጥያቄ፡- የቀድሞው የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት በይፋ ፈርሷል ማለት ነው?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- አልፈረሰም፡፡ የንብረት ክፍፍልም አላደረግንም፡፡ ስለዚህ በሕይወት አለ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የተፈጥሮ ሞት እንዲሞት ነው የምንፈልገው፡፡ ስለዚህ እየጠበቅን ነው ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ቀደም ብለው እንደገለጹት አዲሱ የባቡር ፕሮጀክት በሚቀጥለው ዓመት ይጀምራል፡፡ አንድ አገር አቋርጦ የሚደረግ የትራንስፖርት አገልግሎት በመሆኑ ኦፕሬሽኑን በተመለከተ የደረሳችሁበት ስምምነት አለ?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- ከባቡር ሥራ በጣም ትልቁ የሚባለው ከመገንባቱ በኋላ ያለው የኦፕሬሽንና የጥገና አገልግሎት ነው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሥራዎች ላይ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ላይ እንዳደረግነው፡፡ ማለትም ሸንዞን ሜትር ግሩፕ እና የቻይና ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በጋራ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራውን ለአምስት ዓመት እንዲሠሩ ነው ኮንትራት የሰጠነው፡፡ የአዲስ አበባ ሰበታ ጂቡቲ መስመርን መጀመሪያ በራሳችን ኦፕሬት እናደርገዋለን የሚል ሐሳብ የለንም፡፡ ሰለዚህ የምናስበው ተመሳሳይ ኮንትራት ሰጥተን ኢትዮጵያውያንን የማብቃት ሥራ ነው የምንሠራው፡፡
በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የባቡር ትራንስፖርት ስኬታማ መሆን ያልቻለው በኦፕሬሽን ችግር ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ መግባት ስለማንሻ ኮንትራት ሰጥተን የራሳችን ሰዎች የማብቃት ሥራ ጐን ለጐን እናካሂዳለን፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርን ከቻይኖቹ ለመረከብ ከሁለት መቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ቻይና ሠልጠነው በአሁኑ ወቅት ተመልሰዋል፡፡ ስለዚህ እኛ በደንብ የትራንስፖርትና የጥገና ሥራውን በደንብ አውቀን ነው የምንረከበው፡፡ ሁለተኛ በብድር የሠራነው ፕሮጀክት ነው፡፡ ስለዚህ ያንን ብር ለቅመን በሥርዓቱ ለብድር ክፍያ ማዋል አለብን፡፡
በመሆኑም ሁሉም ነገር በሚገባ መስመር እስኪይዝ ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተመረጠው ኮንትራት መስጠት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የኢትዮጵያና የጂቡቲ ንብረት ነው፡፡ ስለዚህ ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንደ ኩባንያ ነው ኦፕሬሽኑም ጥገናውም መካሄድ ያለበት፡፡ በጂቡቲ በኩል ባቡር ቢበላሽ ጂቡቲ ይጠገናል፡፡ በኢትዮጵያም በኩል እንደዚያው የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ከሰበታ እስከ የመጨረሻው የወደብ ጣቢያ ድረስ የባቡሩ ኦፕሬሽን ሥራም ሆነ ጥገና በአንድ ተቋም ይሠራል ብለን ነው ያሰብነው፡፡ ነገር ግን ገና በሒደት ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡
ጥያቄ፡- አዲሱ የባቡር ፕሮጀክት በኤሌክትሪክ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ ይህም በመሆኑ በጂቡቲ በኩል ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር እንቅፋት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን በተመለከተ ያደረጋችሁት ውይይት አለ?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- እንዳያችሁት ጂቡቲ የምትጠቀመው ከኢትዮጵያ የሚቀርብላትን የኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡ በተመሳሳይ የተወሰነ ኃይል ለባቡሩ እንድትጠቀም ያው በክፍያ ማለት ነው ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ስምምነቱ የተፈረመው በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኩል በመሆኑ ዝርዝር ጉዳዩን የተመለከተ መረጃ የለኝም፡፡
ጥያቄ፡- ንብረቶችን ከወደብ በማንሳትና ወደ ወደብ በማድረስ ረገድ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር አለ፡፡ እንደሚያውቁት የጭነት ተሽከርካሪዎች በአንድ ጊዜ ብዙ ንብረት ማንሳት አይችሉም፡፡ ደረጃቸውም ተገቢ አገልግሎት ለመስጠት የማያስችል ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን እየሠራችሁ ነው? መንገዱንም አሁን ካለው የመሸከም አቅም በላይ ለማድረግ የታቀደ ነገር አለ ወይ?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- እንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የጭነትም ሆነ የመንገደኞች ተሽከርካሪዎች ታሪክ የቤተሰብ ታሪክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ተሽከርካሪዎች 85 ወይም 87 በመቶ የሚሆኑት አንድ አንድ እየተባለ በቤተሰብ የተያዙ ናቸው፡፡ አንድ ግለሰብ አንድ ሎንቺና ካለው ቤተሰቡን ያስተዳድርበታል፡፡ ይህ ማለት ያለው የተሸከርካሪ ሀብት የተበታተነ ነው ማለት ነው፡፡ በጣም ኋላቀር በመሆኑ ለማስተዳደር በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለዚህም ነው እንግዲህ ማኅበራት የተቋቋሙት፡፡ እነዚህ ማኅበራት በተለያየ መንገድ በተበታተኑ ባለቤቶች የሚተዳደሩ ተሽከርካሪዎችን በማሰባሰብ ፈር ለማስያዝ እየሞከሩ ነው፡፡ ሌላ አገር አንድ ኩባንያ አምስት ወይም ስድስት ሺሕ ተሽከርካሪዎች አሉት፡፡ ይህ ለብዙ ነገር ይጠቅማል፡፡ በእኛ አገር ይህ ችግር አለብን፡፡ በጣም የተወሰኑ ኩባንያዎች ናቸው ሦስት መቶ ወይም አራት መቶ መኪናዎች ያሉዋቸው፡፡ ስለዚህ ይህንን ከመሠረቱ መቀየር አለብን፡፡ አሁን ምናልባት ሰምታችሁት ከሆነ አላውቅም እንደገና እያደራጀን ነው ያለነው፡፡
በድጋሚ ስናደራጅ በመበጣጠሱ ምክንያት የሚፈጠረውን የጊዜና የዋጋ ንረት ማስቀረት በሚቻልበት መልኩ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ በቂ ኢንቨስትመንት አልተደረገም፡፡ ስለዚህ መንግሥትም በዚህ ዘርፍ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት፡፡ የማበረታቻ ነገሮች በመንግሥት እየታሰቡ ነው፡፡ ለምሳሌ ብዙ አትራፊ አይደለም ብለው ባለንብረቶች ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን የማየት፣ የባንክ ብድር አቅርቦትን የማመቻቸት፣ የመኪኖቹን ምልልስ መጨመር የመሳሰሉትን ለመሥራት መቻል አለብን ብለናል፡፡ ትራንስፖርት ዘርፉ በአግባቡ መተዳደር አለበት፡፡ በሹፌሮች ፍላጐት የሚመራ መሆን የለበትም፡፡ አሁን በቅርቡ በጣም በርካታ መኪናዎች ለመግዛት ፍላጐት ያሳዩ አሉ፡፡ የጭነትም የፈሳሽም ተሽከርካሪዎች ማለት ነው፡፡ መንግሥት ለዚህ ብድር የማመቻቸት እየሠራ ነው ያለው፡፡ ሌላው ደግሞ የከተማ ትራንስፖርት ችግርን ለመቀነስ ከቀረጥ ነፃ የተወሰኑ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ መንግሥት የተወሰነ ማበረታቻ እየሰጠ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይህንን እያበረታታን የግል ዘርፉን እየደገፍን ዘመናዊ የሆነ ዘርፍ እንዲሆን እየሠራን ነው፡፡
መንገድን በተመለከተ የእኛ የመንገድ ክብደት የመሸከም ደረጃ ከሌሎች አገሮች ያነሰ ነው፡፡ መንገዱ የሚችለው ተሽከርካሪ ነው መሄድ መቻል ያለበት፡፡ አንደኛ መንገዱም ይጐዳል፣ ተሽከርካሪውም እንዲሁ፡፡ ሁለት ጉዳት ነው የሚሆነው፡፡ መንገድ ሲሠራም ሆነ ሲጠገንም በጣም ውድ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እያሰብን ያለነው የመንገዱን የመሸከም አቅም ማስተካከል ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን የድሬዳዋ-ደወሌ መንገድ ኮንትራት ተሰጥቶ ሥራው ተጀምሯል፡፡ ይህ አንዱ የፍጥነት መንገድና ኮንክሪት እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ ከ40 ቶን በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ለማሰማራት ነው የምንፈልገው፡፡
ከአዳማ-አዋሽ ሌላ ተጨማሪ የፍጥነት መንገድ በሚቀጥለው ዓመት ለመጀመር አስበናል፡፡ ስለዚህ ይህንን መስመር አዲስ አበባ-ደወሌ ድረስ ለመግጠም ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ በደወሌም ሆነ በጋላፊ በኩል ያለውን መስመር የተሻለ የመሸከም አቅም ያለው ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ በተመሳሳይም ከ300 በላይ ከፍተኛ ዕቃ የማንሳት አቅም ያላቸው ሰፋ ያሉ ተሽከርካሪዎች ከፈረንሳይ ተገዝተው ሊገቡ ነው፡፡
ጥያቄ፡- እነዚህ ተሽከርካሪዎች በመንግሥት ነው ወይስ በግል ባለሀብቶች የተገዙት?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- በመንግሥት አመቻችነት በተለያዩ ማኅበራት ነው የተገዙት፡፡ ከፈረንሳዩ ሬኖ ኩባንያ ነው የተገዙት፡፡ እንደ ኮሜት፣ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የመሳሰሉ ድርጅቶች ናቸው የገዟቸው፡፡ ስለዚህ መንገዶችንም እያስተካከልን፣ ዘመናዊና ከፍተኛ ዕቃ የሚያነሱ ግዙፍ ተሽከርካሪዎችንም እያስገባን ነው ያለነው፡፡
ጥያቄ፡- የአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ ከታቀደ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ዕውን ይሆናል ማለት ይቻላል?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- በሚቀጥለው ዓመት ይጀመራል ብለን ነው የምናስበው፡፡ ያው ገንዘብ እያፈላለግን ነው ያለነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው አቅማችን የመንገድ ሥራ ለብቻችን የምንሠራው አይደለም
ጥያቄ፡- የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- የሞጆ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ በተወሰነ ደረጃ ፋይናንስ በማግኘቱ ከሞጆ-መቂ ያለው ክፍል ተጀምሯል፡፡ ፕሮጀክቱን የሚሠራው ኪንግናም የተባለው የኮሪያ ኩባንያ ነው፡፡ ገንዘቡም የተገኘው ከዚያው ነው፡፡ ከዝዋይ-አርሲ ነገሌ እንዲሁም ከአርሲ ነገሌ-ሐዋሳ እንዲሁም ከመቂ-ዝዋይ ድረስ ላለው የፍጥነት መንገድ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ጨረታ ወጥቷል፡፡
ጥያቄ፡- የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት የከተማዋን ችግር በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ሚና የሚኖረው ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ ደካማ የትራፊክ ማኔጅመንት ስላለ የባቡሩ መምጣት ችግር ሊፈጥር ይችላል ይባላል፡፡ ለምሳሌ ባቡሩ በየጣቢያዎቹ የሚያራግፋቸውን ተሳፋሪዎች ተቀብሎ ወደሚፈለገው አካባቢ ትራንስፖርት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ካልተዘረጋ መልሶ አጣብቂኝ ውስጥ መግባት ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ረገድ የታሰበ ነገር አለ?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ኦፕሬሽን ሥራ በቀጥታ አይመለከተኝም፡፡ ነገር ግን የትራንስፖርት ሚኒስትር እስከሆንኩ ድረስ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ በአዲስ አበባ የታሰበው መልቲ ሞዳል የትራንስፖርት ሥርዓት ለመዘርጋት ነው፡፡ ባቡር፣ የፈጣን የአውቶብስ ትራንስፖርት፣ ታክሲና ብስክሌትን የሚያቀናጅ ማለት ነው፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሥር የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አደራጅተናል፡፡ አሉ የተባሉ የትራንስፖርትና የትራፊክ አስተዳደር ባለሙያዎችን ከአገር ውስጥም ከውጭም አቀናጅተን እየተጠና ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ባቡር የት ነው የሚሄደው? በዚህ መስመር በርካታ ሰዎች የትኛው ጣቢያ ላይ ነው የሚወርዱት? እነርሱን ተቀብሎ የሚያደርሰው የሕዝብ ትራንስፖርት ታክሲ ነው? ወይስ ፈጣን አውቶብስ ነው የሚሆነው? የሚለው በጥልቀት እየተጠና ነው፡፡ ፕሮጀክቱም በዓለም ባንክ፣ በሌሎች ተቋማትና ትራንስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ የሚደገፍ ነው፡፡
ጥያቄ፡- አሁን ባለው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛው ችግር የትራፊክ ማኔጅመንት ነው ይባላል፡፡ በቂ የሚባል የትራንስፖርት አቅርቦትና የመንገድ ኔትወርክ ቢኖርም፣ በትራንስፖርት አስተዳደሩ ላይ ባለው ክፍተት ነው ችግሩ ከፍተኛ የሆነው የሚሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?
አቶ ወርቅነህ ገበየሁ፡- ይህ ብቻ ምክንያት አይደለም፡፡ እውነት ነው የትራፊክ አስተዳደር ችግር አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ካለው ነዋሪ 60 በመቶው እግረኛ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ አራት ሚሊዮን አካባቢ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ነው 60 በመቶው እግረኛ መሆኑን ነው በጥናት ያረጋገጥነው፡፡ አብዛኛው እዚያው ሠፈር ውስጥ ወይም ወደ ትምህርት ቤት የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ አሁን እያገለገልን ያለነው ትራንስፖርት የሚጠቀመውን 40 በመቶ የሚሆነውን ነው፡፡
እኛ አገር ውስጥ ለዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ በአጠቃላይ ወደ 500 ሺሕ ተሽከርካሪዎች ናቸው ያሉት፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ ያለው አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ታክሲ፣ አውቶብስና የመሳሰሉት ወደ 300 ሺሕ እና 400 ሺሕ ተሳፋሪዎችን ያነሳሉ፡፡ አሁን ባቡር ሲገባ ከ300 ሺሕ እስከ 350 ሺሕ ተሳፋሪዎችን ያነሳል፡፡ የግል መኪኖች ወደ 100 ሺሕ ተሳፋሪዎችን ያነሳሉ፡፡ በጠቅላላ ያለንን አቅም ተጠቅመን፣ የሲቪል ሰርቪስ አውቶብሶችንና አሁን ልንገዛቸው ያሰብናቸውን 500 ተሽከርካሪዎች ጨምረን ያለን ተሳፋሪዎችን የማንሳት አቅም አንድ ሚሊዮን ነው የሚሆነው፡፡ ገና ከ40 በመቶው ውስጥ እንኳን 500 ሺሕ ሰው አዲስ አበባ ውስጥ መኪና ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ የፍላጐትና የአቅርቦት ችግር በደንብ ነው ያለው፡፡ የትራፊክ አስተዳደር ችግር እንዳለ ሆኖ ዋነኛው ግን ከላይ የገለጽኩት ነው፡፡