የአንድ ቅርጫፍ ባንክ አገልግሎት በመስጠት ይታወቅ የነበረውና አሁን ቅርንጫፎችን በመክፈት ላይ የሚገኘው ዘመን ባንክ፣ ኮሜርስ አካባቢ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ሕንፃ፣ ባለ ሰላሳ ፎቅ ሲሆን ሦስት ምድር ቤቶችን ያካተተ ከመሆኑም ባሻገር በ2304 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እየተገነባ የሚገኝ ነው፡፡
የፋናንስ ጎዳና የሚል መጠሪያ ባተረፈው ኮሜርስ አካባቢ ከሚገነቡ የባንክ ሕንፃዎች አንዱ የሆነው የዘመን ባንክ ሕንፃን ዲዛይን ያደረገው ጄዳው አርክቴክቶችና መሐንዲሶች አማካሪ ኩባንያ ሲሆን፣ የግንባታውን የቁጥጥር ሥራ ያከናውናል፡፡ የመሠረት ቁፋሮና ማውጣት ሥራዎች ላይ እንዲሳተፉ አንከር ፋውንዴሽን ስፔሻሊስት ኩባንያ ከባማኮን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ጋር በሽሙር ሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) የመሠረት ሥራውን ከሁለት ሳምንት በፊት መጀመራቸውን ባንኩ አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ እየከፈታቸው ከሚገኙት ቅርንጫፍ ባንኮች በተጨማሪ ሐዋሳን በመሳሰሉ ከተሞችም የባንክ ሥራን ሲቀላቀል ከነበረው አቋም ይልቅ ቅርንጫፎችን እያስፋፋ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡