የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች በተያዘው የምዕራባውያን ዓመት የሚጠናቀቁ መሆናቸውን ምክንያት በማድረግ ቀጣዮቹን የልማት ግቦች የተባበሩት መንግሥታት እየቀረፁ ይገኛል፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት በተለይ በታዳጊና ድሃ አገሮች ዘንድ ሲተገበሩ የቆዩት የልማት ግቦች የታሰበውን ለውጥ ሊያስገኙ ሳይችሉ ቢገባደዱም፣ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ተስፋ የሚጣልባቸው ለውጦችን አሳይተዋል፡፡
ከእነዚህ አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የልማት ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ ልታሳካቸው ትችላለች ከሚላቸው የልማት ግቦች ውስጥ የድህነት ቅነሳና ከአምስት ዓመት በታች ያሉ የሕፃናት ሞት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ግቦች በምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ከተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ አስቀድማ ማሳካቷን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ይገልጻሉ፡፡
ከ15 ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አገሪቱ ከድህነት ወለል በታች ይኖሩ ከነበሩት 46 ከመቶ ሕዝቦች ውስጥ አሁን ላይ በግማሽ በመቀነስ 24 ከመቶ መድረሳቸውን ዶክተር አብርሃም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የአምስት ዓመት የልደት በዓላቸው ሳያከብሩ ከሚሞቱ ሕፃናት ውስጥ ቢያንስ የሁለት ሦስተኛ ሟቾችን ቁጥር መቀነስ በምዕተ ዓመቱ የተቀመጡ የልማት ግቦች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ግብ ያሳካችው የልማት ግቦቹ መጠናቀቂያ ጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ሁለት ዓመት ሲቀረው ነው፡፡ በትምህርት ሽፋንም አገሪቱ ያሳቸው ለውጥ በዩኤንዲፒ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡
እነዚህን ውጤቶች መነሻ በማድረግ ከሁለተኛው የምዕተ ዓመት የልማት ግቦች ወይም ዘላቂ ‹‹የልማት ግቦች›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን ግቦች ፋይናንስ ለማድረግ የሚረዳውን ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ መመረጧን በማስመልከት ዶክተር አብርሃም መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የልማት ፋይናንስ- ፋይናንሲንግ ፎር ደቨሎፕመንት›› ተብሎ የሚታወቀውን ኮንፈረንስ በወርኃ ክረምት ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሔድ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡ ኮንፈረንሱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት ጋር እያዘጋጀ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡