Saturday, September 30, 2023

‹‹ኢዴፓ ሁለተኛ ዋና ፓርቲ ሆኖ የመጓዝ ዕድሉ የሰፋ ነው›› ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዶ/ር ጫኔ ከበደ መስከረም 26 ቀን 2006 ዓ.ም. ከተካሄደው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ጠቅላላ ጉባዔን በኋላ የፓርቲው ፕሬዚዳንትነትን ከአቶ ሙሼ ሰሙ ተረክበው ፓርቲውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ በሒሳብ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ዶ/ር ጫኔ፣ ከዚያ በኋላ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተቀበሉ ሲሆን፣ ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ (UNISA) ደግሞ በዴቨሎፕመንታል ስተዲስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ፓርቲው በመጪው ምርጫ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ያዘጋጃቸውን ዕቅዶች፣ በአባልነት ስለሚገኝበት የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ስለፓርቲው ርዕዮተ ዓለምና ከገዥውም ሆነ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ያለውን ልዩነትና አንድነት በተመለከተና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡

 

ሪፖርተር፡- የፊታችን ግንቦት የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ በአጠቃላይ የኢዴፓ የምርጫ እንቅስቃሴና የተሠሩ ሥራዎች ምን ይመስላሉ? ምን ያህል ዕጩዎች ተመዘገቡ?

ዶ/ር ጫኔ፡- በእኛ በኩል ሰፊ ዝግጅት ነው ያደረግነው፡፡ እስካሁን ድረስ ሁሉንም ምርጫዎች እየተሳተፍን ነው የመጣነው፡፡ አሁንም ለመሳተፍ እየተዘጋጀን ነው ያለነው፡፡ ይኼንን የምርጫ ዝግጅት ለማድረግ በምርጫ ቦርድ የምርጫ ማስፈጸሚያ መርሐ ግብር መሠረት በርከት ያሉ ዕጩዎችን አስመዝግበን ለማወዳደር ነው አቅደን የተነሳነው፡፡ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ብዙ ዕጩዎችን አስመዝግበናል፡፡ ከጋምቤላና ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በስተቀር በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ዕጩዎችን ለተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤት አስመዝግበናል፡፡ ከዚህ አንፃር ዝግጅታችንን በሰፊው ጀምረናል ማለት ነው፡፡ ሌላው ለምርጫ ዝግጅት ይረዳን ዘንድ ፓርቲያችን የምርጫ ግብረ ኃይሎችን አቋቁሟል፡፡ በዚያ መሠረት ግብረ ኃይሎቹ የራሳቸውን ሥራ እየሠሩ ነው የሚገኘው፡፡ አንደኛው ግብረ ኃይል የቅስቀሳ ፕሮግራምና ክርክር መድረኮችን የሚመራ ግብረ ኃይል ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በድርጅት ጉዳይ አማካይነት ዕጩዎችን መመልመልና ማስመዝገብ የሚሠራ ሲሆን፣ በዚያም ዙሪያ እስከ ምርጫው መጨረሻ ዕለት ድረስ የሚቀርቡ አቤቱታዎችንና የአፈጻጸም ሥልቶችን በሙሉ የሚከታተል ግብረ ኃይል ነው ያዘጋጀነው፡፡ በዚህም መሠረት ተወዳዳሪዎችን አስመዝግበናል፡፡ የምርጫ ቅስቀሳና የክርክር መድረኮችን የሚመራው ግብረ ኃይል ደግሞ ማኒፌስቶ ማዘጋጀትን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንን ለመጠቀም የሚያስችል መርሐ ግብር አውጥቶ በዚያ መሠረት የምርጫ ቦርድና የመገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ የሚሰጠውን የሰዓት ድልድል እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር በዚያ መሠረት ቅስቀሳውን ለመጀመር እየተዘጋጀ ያለ ግብረ ኃይል ነው፡፡ ሁለተኛ የክትትልና ግምገማ ኮሚቴ ይኖረናል፡፡ በፕሬዚዳንቱ የሚመራ ሆኖ አጠቃላይ ያለውን እንቅስቃሴ በሙሉ የመከታተልና እየገመገመም መፍትሔ የመስጠት ሒደቶችን፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነት መፍጠርና የውይይት መድረኮችን መምራትን ይጨምራል፡፡ ከዚህ አንፃር ሰፊ ዝግጅት እያደረግን ነው የምንገኘው፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢዴፓ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ነው፡፡ ምክር ቤቱ ደግሞ ሲቋቋም አሳካቸዋለሁ ያላቸው ግቦች፣ ዓላማዎችና ዕቅዶች ነበሩት፡፡ ኢዴፓም ይህን ምክር ቤት ሲቀላቀል የሚጠብቀው ለውጥ ወይም መሻሻል ነበርና ምክር ቤቱን ስትቀላቀሉ ያስቀመጣችሁትን ዓላማ አሳክታችኋል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ጫኔ፡- ፓርቲያችን የጋራ ምክር ቤት ሕጉን ከማርቀቁ ጀምሮ እስከ ማፅደቅም ድረስ፣ በኋላም ወደ ተግባር ለመቀየር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ተሳትፎ ነው እያደረገ ያለው፡፡ ከዚህ አንፃር በመርህ ደረጃ ፓርቲያችን የሚከተለው የሊብራል አስተሳሰብ እስከሆነ ድረስና የሊብራል አስተሳሰብ ደግሞ የመጀመርያ መሥፈርት ሕግ ማክበር ነው፡፡ ምን ያህል ሕጉ ተከብሯል? ምን ያህል ሕጉ እየተተገበረ ነው? የሚለውን እየገመገመና እየተቸ በጋራ ምክር ቤቱ በኩል በሚኖረው ውይይት ላይ ይህንን በከፍተኛ ሁኔታ በማቅረብ ሕጎች ወደ ተግባር የሚተረጎሙበትና ሕጎች ሲጣሱ፣ ተጠያቂውን ክፍል የመለየት ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከዚህ አንፃር የጋራ ምክር ቤቱ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ በእኛ በኩል አድርጎልናል ብለን ነው የምናስበው፡፡ በእርግጥ የምክር ቤቱ ግብ የሚሆነው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ የሆነና በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ ምርጫ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚፈጥርበትን ሒደት ማስፈጸም ነው የሚሆነው፡፡ ከዚያም አንፃር የመንግሥት አካላት፣ ባለድርሻ አካላትና በአጠቃላይና የዴሞክራሲ ተቋማት የምንላቸው በሙሉ ምን ያህል ለሰብዓዊ መብት እየሠሩ መሆኑን በሌላ መልኩ ይገመግማል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ በሕግና በሕግ መሠረት መሆን እንደሚገባው፣ ይህንንም እንዲሁ በመረጃ ላይ የተንተራሰ ቅሬታ በማቅረብ ብዙ ጊዜ መፍትሔዎችን አምጥተናል ብለን እናስባለን፡፡ በሌላ በኩል ግን የጋራ ምክር ቤቱ ሕግን የማስፈጸም ነው ትልቁ ሥራው የሚሆነው፡፡ ሕግ ለማስፈጸም ደግሞ የባለድርሻ አካላት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ለይቶ የሚያይና የባለድርሻ አካላት ትክክለኛ ለሰብዓዊ መብትና ለዴሞክራሲያዊ መብት መከበር ምን ያህል መቆማቸውን ይገመግማል፡፡ በዚህ አግባብ ነው ምክር ቤቱን የምንጠቀምበት፡፡ ከዚህም መነሻ ብዙ ጊዜ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሠፈሩ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አሉ፡፡ እነዚህ በሚጣሱበት ወቅት በተለይ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብት ጥሰትን በተመለከተ በአብዛኛው ጊዜ ከመንግሥት አስፈጻሚዎች አካባቢ አንዳንድ ጉድለቶች ይታያሉ፡፡ እነዚህ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እየተጣሱ ነው፡፡ የጋራ ምክር ቤቱን አዋጆችንና ሕገ መንግሥቱን ማጣጣም ስለሚቻልበት ሁኔታ  ሁልጊዜ ትንታኔ ይሠራል፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛ ፓርቲ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ለጋራ ምክር ቤቱ፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ ገዥውን ፓርቲ ፊት ለፊት አግኝተን ውይይት የምናካሂድበት መድረከ በመሆኑ ፓርቲው ተጠቅሞበታል ብለን ነው የምናስበው፡፡ ስለዚህ ግባችንን ከዚህ አንፃር ነው መለካት የሚቻለው፡፡

ሪፖርተር፡- የጋራ ምክር ቤት አባል ያልሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን ስምምነት የፈረሙትንና የምክር ቤቱ አባላት የሆኑ ፓርቲዎችን ‹‹ተለጣፊዎች›› እና ወዘተ የሚሉ ስያሜዎችን በመስጠት ለአጠቃላይ ሰላማዊ ትግሉ የሚያበረክቱት ይህን ያህል አስተዋጽኦ የለም በማለት ይተቻሉ፡፡ ለእንዲህ ዓይነት አስተያየቶችና ትችቶች የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ዶ/ር ጫኔ፡- ለሌሎች ፓርቲዎች የምሰጠው ብዙም አስተያየት ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ተለጣፊ ናቸው ብለው መደምደሚያ የሚሰጡ ፖለቲካ ፓርቲዎች በእውነቱ ከሰላማዊ ትግል መርህ የወጣ አስተያየት የሚሰጡ ናቸው ብለን ነው በእኛ በኩል የምናስበው፡፡ ሁለተኛ የሊብራል አስተሳሰብ እናራምዳለን የሚሉ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው እንዲህ ዓይነት ሐሳብ የሚሰጡት፡፡ የሊብራል አስተሳሰብ የሚያራምድ ሰው ለሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ የመቻቻልና የመግባባት ፖለቲካ፣ ነፃነትና ምቾትን የሚፈልግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ እንዲህ ዓይነት አስተያየት ሲሰጥ የሊብራል አስተሳሰብን በመርህ ደረጃ ያዙት እንጂ በተግባር የሉበትም ነው የምንለው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ወደ ጋራ ምክር ቤቱ ቀረብ ብለው የሚሠራውን ሥራ እስካላዩትና ትንተና እስካልሰጡበት ድረስ እንዲህ ዓይነት አስተያየት መስጠቱ ራሱ በአግባቡ ከሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል እንቅስቃሴ ውጪ ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ በእኛ ፓርቲ ላይ እንዲህ ዓይነት አስተያየቶች መቅረባቸው የተለመደ ነው፡፡ ኢዴፓ ትልቅና አንጋፋ ፓርቲ ነው፡፡ በመላ አገሪቱ ውስጥ ጽሕፈት ቤቶችን ከፍቶ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር የመግባባት ፖለቲካ በዚች አገር ላይ መምጣት መቻል አለበት፡፡ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ለአገር ይጠቅማል ብሎ አባላቱንም ሆነ ደጋፊዎቹን የሚያስተምር ፓርቲ እስከሆነ ድረስ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ተሸክመን ነው የመጣነው፡፡ ወደፊት እየጠሩ የሚሄዱ ናቸው፡፡ ይኼ ትችትና አስተሳሰብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ካሉ የፖለቲካ የትግል ሥልቶች ውጪ ነው፡፡ ያ ማለት ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን አስተያየት ሲሰጡ ከግራ የፖለቲካ አስተሳሰብ የመነጩ ሐሳቦች ገና ያልተቀረፉ መሆናቸውን ነው የሚያሳዩት፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች ምናልባት በአብዛኛው ከዳያስፖራው አካባቢም የሚመነጩ ናቸው፡፡ ከኢሕአፓ ጀምሮ በርካታ የግራ አስተሳሰብ ፖለቲካ አራማጅ የነበሩ በውጭ የሚኖሩ ግራ ዘመም ሰዎች ናቸው እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ የሚያራምዱት፡፡ በአገር ውስጥ ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥም ተፅዕኖ እየፈጠሩ ያሉት እነዚያ ናቸው፡፡ ትችቶችን ሁል ጊዜ እንገመግማለን፡፡ ከዚያ ግምገማ ስንነሳ ግን ነገ በራሳቸው አጋጣሚ መንግሥት የመሆን ዕድል ቢኖራቸው ይህን ዓይነት ፓርቲ የሚያስተናግዱበት ዕድል የተዘነጋ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከመንግሥት ጋር ግንባር ፈጥረህ የምታደርገው የውይይት መድረክ ተለጣፊ ነው የሚያሰኝ ከሆነ፣ እነሱ ምን እያደረጉ እንደሆነ እኛ አይገባንም፡፡ በሕጉ መሠረት በምርጫ ቦርዱ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የሚዘነጉት ይመስለኛል፡፡ እነሱ ምን እያደረጉ ነው? ፈቃድና ዕውቅና አግኝተው በሕግ መሠረት እየተንቀሳቀሱ እንደገና በሕግ መሠረት ከገዥው ፓርቲ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ  የሚነጋገረውን ፓርቲ ሁሉ ተለጣፊ ብለው የሚሄዱ ከሆነ፣ ነገ የዴሞክራሲውን ሒደት የሚያጨልሙት መስሎ ይታየናል፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ አስተሳሰብ በዚህች አገር ላይ መምጣት ካለበት፣ የእኛ ትክክለኛ መስመር ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢዴፓ ብዙውን ጊዜ ለመንግሥት መልካም ሥራዎች ዕውቅና መስጠት አለብን ይላል፡፡ ከዚህ አንፃር ፓርቲው ለመንግሥት ከሚሰጠው ዕውቅና አኳያ ከመንግሥት ወይም ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሚያገኘው ምላሽ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ጫኔ፡- ከገዥው ፓርቲ የግራ ዘመም አስተሳሰቦች ገና ወጥተው አላለቁም፡፡ እነኚህ አስተሳሰቦች እስከ ኮፈናቸው ውልቅ ብለው ካልወጡ በስተቀር በገዥው ፓርቲ በኩል እንዲህ ዓይነቱን ዕድል የመስጠት ዕድሉ አይታይም፡፡ እኛ ግን እስከ መጨረሻው ድረስ ሰላማዊ ትግሉን በተሻለ መንገድ ለማስኬድ ሁልጊዜ ለገዥው ፓርቲ እንዲህ ዓይነት ምቾት ሊሰጡ የሚችሉ አስተሳሰቦችን ማራመድና በተሻለ ወደ እኛ ሊመጣ የሚችልበትን ሐሳብ  ነው ብዙ ጊዜ የምናቀርበው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ ገዥው ፓርቲ የእኛን አስተሳሰብ በተወሰነም ደረጃ ቢሆን እንደሚቀበል፣ ከእኛም ጋር አብሮ አስተሳሰባችንን ዕውቅና ሰጥቶ የፖለቲካ ትግሉ መቀጠል እንዳለበትና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ መቀጠል መካሄድ እንዳለበት በተለያዩ አጋጣሚዎች ይገልጽልናል፡፡ ከዚህ ውጪ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ በሌላ መንገድ የእኛን አስተሳሰብ ከገዥው ፓርቲ የርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ ጋር የማዛመድና የማጣጣል ሁኔታ እንደሚኖር የሚታወቅ ነው፡፡ ስለዚህ ዕውቅና አልሰጠንም ወይም በዚህ መንገድ እየወቀሰን ነው በሚል ቅሬታ ሊኖረን አይችልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መሆናችንን ስለምንገነዘብ ነው፡፡  ነገር ግን በፓርቲነቱ ደረጃ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበን የምንቀሳቀስና ርዕዮተ ዓለማችንን ለሕዝብ አማራጭ የፖለቲካ ፕሮግራም እንደምናቀርብ ገዥው ፓርቲ ዕውቅና ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጊዜ በተለይ ወደ ምርጫ ስንቃረብ በመድረክ ላይ በሚኖረን የክርክር ሐሳቦች ዙሪያ ሕዝብ ሚዛን ላይ እንዲያስቀምጠን የማድረግ ሥራዎች እንሠራለን፡፡ ይኼ በገዥው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚዎች በኩል የሚካሄድ በመሆኑ ይህንን እንደ አንድ ዕውቅና የሚሰጠን አካል ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ከዚያ ውጪ ላሉት ነገሮች ግን የግራ ፖለቲካ አስተሳሰብ ከብዙዎቹ የኢሕአዴግ አባላት ገና ያልወጣ በመሆኑ፣ ነውጥንም አብዮተኝነትንም አጣጥመው የሚጓዙ ብዙ አባላት አሉት፡፡ እነዚህ ነገሮች እስከ መጨረሻው ተቀርፈው እስኪወድቁ ድረስ ትግላችን ይቀጥላል፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅለል ባለ ሁኔታ በፓርቲያችሁና በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መካከል ያለው የአካሄድ፣ የርዕዮተ ዓለምና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አንድነትና ልዩነት እንዴት ይገለጻል?

ዶ/ር ጫኔ፡- በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ምንም ዓይነት አንድነት የለንም፡፡ የተስማማ ርዕዮተ ዓለም የለንም፡፡ እኛ የሊብራል ርዕዮተ ዓለም ነው የምናራምደው፡፡ ገዥው ፓርቲ ደግሞ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ነው የሚያራምደው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቅጂው ሶሻሊዝም ነው፡፡ የሊብራሊዝም መሠረቱ ደግሞ ካፒታሊዝም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሁለቱ በዓለም ላይ በተቃራኒነት ነው የሚጓዙት፡፡ መቼም ቢሆን ስምምነት የላቸውም፡፡ ከዛም ባሻገር ገዥው ፓርቲ አሁን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ በዘለለ ደግሞ ልማታዊ ዴሞክራሲ የሚል ነገር እያመጣ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የጠራ ርዕዮተ ዓለም አይደለም ገዥው ፓርቲ ይዞ የሚሄደው፡፡ የጠራ ርዕዮተ ዓለም ያለመከተል ችግር ደግሞ በኢኮኖሚ ፖሊሲና በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሚኖሩ አስተሳሰቦች በጣም የተለያዩ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በስምምነት ዴሞክራሲና በሶሻል ዴሞክራሲ አስተሳሰቦች ውስጥ ያሉ ነገሮችን ሊብራሊዝም አቅፎ ነው የሚጓዘው፡፡ ሁለተኛ ሊብራል ዴሞክራሲ ይኼኛው መደብ ብሎ የሚከተለው ነገር አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የግለሰብ መብት መከበር አለበት ብሎ ነው የሚጀመረው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግን የመደብ መስመሮችን ነው ተከትሎ የሚሄደው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ገዥው ፓርቲ ብሔር ብሔረሰቦች የሚል የመደብ ሥርዓት ፈጥሮ ነው እየሄደ ያለው፡፡ እኛ ደግሞ ብሔር ብሔረሰቦች መብታቸው ሊከበር የሚችለውና ጥያቄዎቻቸው ሊመለስ የሚችለው የግል መብታቸው ከተከበረና ራሳቸው የሚፈልጉትን ሰው ራሳቸው መርጠው መሾምና የራሳቸውን የብሔር ማንነት መከታተልና መቆጣጠር ሲችሉ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ገዥው ፓርቲ ከዚህ በዘለለ እነዚህ ብሔሮች የመደብ ሥርዓት ናቸው ብሎ የራሱን ሕግና የራሱን ፖሊሲ ጭኖ ይህ ተፈጻሚ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ከዚህ አንፃር ስታየው ሊበራሊዝም የመደብ ጠላት ብሎ የሚፈርጀው አካል የለም፡፡ ኢሕአዴግ ግን የመደብ ጠላት ብሎ የሚፈርጀው አካል አለ፡፡ ለምሳሌ ካፒታሊዝም ሙሉ በሙሉ የኢምፔሪያሊስት አቀንቃኝ ነው ብሎ የሚያስብ እስከሆነ ድረስ የመደብ ጠላቱ ኢምፔሪያሊዝም ነው ማለት ነው፡፡ ካፒታሊዝምን የሚያካሂዱ ሰዎች የመደብ ጠላትነታቸውን በዚያ በኩል ይገልጻሉ ማለት ነው፡፡ ሊብራሊዝም ግን የመደብ ጠላት የሚለው የለውም፡፡ ሁሉም በሰውነት የተፈጠረ ሁሉ ሰብዓዊ ክብሩና ሞገሱ ያለምንም ጣልቃ ገብነት በዚህች ምድር ላይ መኖር አለበት ብሎ የሚያስብ ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ግንኙነነት የለንም፡፡ በአብዛኛው የሚጎላው ልዩነታችን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ግንኙነቶች በአንድ ወቅት ሊጣጣሙ የማይችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ጥምር መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ዕድል በጣም የጠበበ ነው፡፡ በጋራ እናስተዳድር ብለን ብናስብ እንዲህ ዓይነት ልዩነቶች ግንባር ሊያስፈጥሩ የሚችሉ ነገሮች አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ገዥው ፓርቲና እኛ አንድ የምንሆንበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ልዩነታችን በጣም የሰፋ ነው፡፡ ነገር ግን በመንግሥት ደረጃ እንደ መንግሥት መዋቅሮችን ፈጥሮ ሕዝብ እያስተዳደረ ነው፡፡ በሊብራል አስተሳሰብ ገዥ ፓርቲ ብትሆን እነዚህን መዋቅሮችን ተከትለህ ነው የምትሄደው፡፡ ምናልባት በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ሥርጭት በአቅም በደንብ አጠናክረሃቸው ሕዝብ የሚያገለግሉበትን መንገድ ትፈጥራላህ፡፡ መልካም አስተዳደር የሚመጣበትን መንገድ ትፈልጋለህ፡፡ ከሙስና የፀዳ አስተዳደር እንዲፈጠር ታደርጋለህ፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህን ተቋማት እኛም እንደ መንግሥት ብንሆን ተከትለናቸው የምንሄዳቸው ናቸው ማለት ነው፡፡ ሌሎችም የፍትሕ አካላት የምንላቸው በተመሳሳይ ማንነታቸውንና አጠቃላይ የተሳታፊውን አካል በሙሉ ከፖለቲካ ገለልተኛና ነፃ አድርገህ ለሕዝባቸውና ለወገናቸው የሚያገለግሉበትን መንገድ የምታመቻችበት መንገድ ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር ስታየው የመከላከያ ሠራዊትን የማፍረስ ተልዕኮ አይኖረንም ማለት ነው፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር ገዥ ፓርቲ እንደ መሆኑ፣ መንግሥት የሚከተላቸውን ተቋማት የአፈጻጸም ሥልቶችና ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ የሚወጣበትን መንገድ ከፈጠርን፣ ከገዥው ፓርቲ መዋቅሮች ጋር አብረን በተመሳሳይ የምናደርገው ሊሆን ይችላል፡፡ ሊያመሳስለን የሚችለው ይኼ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ገዥው ፓርቲ የሊብራል አስተሳሰቦች ሊመጡ የሚችሉት አሁን መንግሥት እየሄደበት ባለው ባለው አቅጣጫ ዓላማውን ሲያሳካና ይህን የሚያሳኩ የተለያዩ ተቋማትን ገንብቼ ካጠናቀቅሁ በኋላ ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባል፡፡ እናንተ ደግሞ ሊብራል ዴሞክራሲን በምርጫ አሸንፋችሁ ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሳችሁ ነውና አሁን ባለው ሁኔታ ይህ ዕውን የሚሆን ይመስልዎታል?

ዶ/ር ጫኔ፡- በእኛ ፓርቲ አሁን በቀጥታ ሊብራል አስተሳሰብ ግብ ነው፡፡ ለምሳሌ ሶሻሊዝም ግቡ ኮሙዩኒዝም እንደነበረው ሁሉ ሊብራሊዝምም የመጨረሻው ግብ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚያ መለስ የምንከተላቸው ሒደቶች አሉ፡፡ የሶሻል ዴሞክራሲ የተወሰኑ እሴቶችና የመግባባት ዴሞክራሲ ሒደቶች አሉ፡፡ የእነሱንም የተወሰኑ ሐሳቦች እንወስድና በአሁኑ ጊዜ ኒዮ ሊበራሊዝም ራሱን እያደሰ የሚሄድ የሊበራል አስተሳሰብ እያደገ የመጣበት፣ በቴክኖሎጂ ዕድገት ምክንያት በሕግ የተገደበ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን የሚደግፍ ነው፡፡ ስለዚህ በሕግ የተገደበ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መሠረት አድርጎ በማኅበረ ኢኮኖሚ ዙሪያ የሚፈጠሩ ችግሮችን መንግሥት የሚፈታበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ዝም ብሎ የሚለቀቅም አይደለም፡፡ ምክንያቱም መካከለኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ ገና ያልተፈጠረ በመሆኑ፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ መፍጠር እስክትችል ድረስ የሶሻል ዴሞክራሲ እሴቶችን ተከትለን መሄድ የግድ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት በሕግ በተገደበ ጣልቃ ገብነት ገብቶ ማኅበራዊ ደኅንነቶችን መጠበቅ አለበት፡፡ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን ማዳረስ ላይ መንግሥት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ መቻል አለበት፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የግለሰቡን መብት ማክበር ከተጀመረ፣ በነፃነት መንቀሳቀሱ ከተጀመረ፣ ሲቪልና የተፈጥሮ መብቶች በሙሉ ለግለሰቡ መሰጠት ከተጀመረ ግለሰቡ በራሱ የማደግ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም የሊበራል ኢኮኖሚ የሚፈቅደው የሊበራል ኢኮኖሚ ሥርዓት ስላለ ያንን መከተል አለብን፡፡ ያንን ከተከተልን ነው መካከለኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ መፍጠር የሚቻለው ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ ግቡ መጨረሻ ላይ ሊብራል አስተሳሰብ የሚለውን ሊያመጣ ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ሊብራል አስተሳሰብ ግባችን ነው እንጂ፣ ከወዲሁ አሁን ለኢትዮጵያ ይመጥናል ተግባራዊ እናድርገው ብንል ከ75 በመቶ በላይ ደሃ ኅብረተሰብ ይዘን አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- ከላይ ኢዴፓ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር ያለውን የበዛ ልዩነትና ጥቂት መመሳሰሎች ተመልክተናል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፓርቲው ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ያለው መመሳሰሎችና ልዩነቶች ምን ይመስላሉ?

ዶ/ር ጫኔ፡- ልዩነት ያለንም አለን፤ ተመሳሳይነት ያለንም አለን፡፡ በእኛ በኩል ኅብረ ብሔራዊ የሆኑና የሊብራል አስተሳሰብ እናራምዳለን የሚሉ ፓርቲዎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ከዚህ አንፃር የሊብራል አስተሳሰብ እናራምዳለን ካሉት ጋር ቅንጅት ፈጥረን የነበረ መሆኑ ምርጫ 97 ላይ የታየ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን በእኛ ፓርቲ የሊብራል አስተሳሰብ ወደ ተግባር ሲገባና ወደ አተረጓጎም ሲሄድ ሊብራል በባህሪው መቻቻልና መግባባትን ይጠይቃል ብለን እናምናለን፡፡ የግለሰብ አስተሳሰብም ቢሆን በፖለቲካ አሠራር ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብለን ነው የምናምነው፡፡ ስለዚህ የግለሰብ መብት አክብረን ልዩነት ካለውም ልዩነቱን ይዘን በአብላጫ ድምፅ የመተዳደርን ባህል ነው ማዳበር የምንችለው፡፡ ይህንንም እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን እነዚህ ኅብረ ብሔራዊ ሆነው ሊብራል አስተሳሰብ እናራምዳለን የሚሉት ፓርቲዎች ግን በመርህ ደረጃ ነው ይዘውት የሚጓዙት፡፡ በአስተሳሰብ ደረጃ  በተግባር ሲተረጉሙት ወይም ሲያደርጉት ግን አላየንም፡፡ ምክንያቱም በእኛ አስተሳሰብ ገዥው ፓርቲ ጠላት አይደለም፡፡ ሌሎቹ ገዥውን ፓርቲ በጠላትነት ነው የሚፈርጁት፡፡ እኛ ግን በጠላትነት ሳይሆን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ መስመሮቹ እንደተሳሳቱበት አንድ አካል ነው የምንወስደው፡፡ እነኚህ መስተካከል አለባቸው ብለን በመረጃ ላይ ተመርኩዘን ሐሳብ ከማቅረብ በስተቀር፣ ለኢትዮጵያ የያዘው ነገር ሁሉ ጥፋት ነው ብለን ፈርጀን አናውቅም፡፡ ይህ ልዩነት አሁንም ቢሆን አለ፡፡ ሌሎች ብሔራዊ ወይም ብሔር ነክ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ ወይም በርካቶቹ ብሔር ተኮር ናቸው፡፡ የብሔር መብት ማስከበር ላይ ነው ትኩረት ያደረጉት፡፡ ስለዚህ በርዕዮተ ዓለም ደረጃ ከገዥው ፓርቲ የተለዩ ናቸው ብለን አቋም አንወስድም፡፡ የሚንቀሳቀሱት የብሔር መብት ለማስከበር ነው፡፡ መብቱ እንዴት ይከበር የሚለውን ለመመለስ የሚደረግ ትንታኔ ምናልባት ከገዥው ፓርቲ ይለይ ይሆናል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ርዕዮተ ዓለማቸው ይኼ ነው ተብሎ መያዝ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ፓርቲዎች ጋር ፍፁም ልዩነት ያለን በመሆኑ ምክንያት ግንባር ፈጥረን ልንሠራ የሚያስችል አካሄድም የለንም፡፡ ይህ ሰፊ ልዩነት በመሆኑ ብሔር ተኮር የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በዚህ ሁኔታ ነው የምናያቸው፡፡ ኢዴፓ ከአሁን በፊት በዚህ ሒደት ከብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተዋህዶ የመጣ ነው፡፡ ኢዴፓ ከኢዲዩ፣ ከኢድሀቅና ከመድህን ጋር ተዋህዶ ነበር፡፡ ስለዚህ ኢዴፓ በአሁኑ ወቅት የአራት ፓርቲዎች ውህድ ነው፡፡ በአመለካከትም በርዕዮተ ዓለምም ከሚመስሉት ፓርቲዎች ጋር ተዋህዷል፡፡ ከሌሎች ጋር እንዲህ  ዓይነት ግንባር መፍጠርና ወደ ውህደት መምጣት ይችላል፡፡ የእኛን አስተሳሰብ ይዘው የሚጓዙና የመቻቻል ፖለቲካንና ብሔራዊ መግባባትን እንደ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካሉ፣ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ ለአገር የሚጠቀም ሐሳብ የሚያፈልቅ እስካለ ድረስ፣ ሕዝብን  አሳትፎና ግንባር ፈጥሮ የሚሠራ ከመጣ አሁንም እንዋሀዳለን፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርቲው በዋንኛነት ከሚያቀነቅናቸው ነጥቦች አንዱ የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሊያዘጋጀው ያቀደው ብሔራዊ መግባባት ላይ አትኩሮት ያደረገ ስብሳባ ነበር፡፡ ጉዳዩ ከምን ደረሰ?

ዶር ጫኔ፡- በር ለመክፈት ያሰብንበት አንድ ኮንፈረንስ ነበር፡፡ ነገር ግን የገንዘብ ችግር አጋጠመንና ከዕጩ ምዝገባ በኋላ በማለት አሸጋግረነዋል፡፡ ያንን ለማድረግ ዕቅዱ እንዳለ ነው፡፡ መቼና በምን መንገድ እናድርገው የሚለው ግን አይታወቅም፡፡ የገንዘብ ምንጩን አሰባስበን አንድ ቀን እናደርገዋለን፡፡ በእርግጥ አጥኚዎቹ ኃላፊነቱን ወስደው ጥናቱን ጀምረዋል፡፡ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት፣ ከገዥው ፓርቲ በኩል ያሉትን ሰዎች ሁሉ የሚያሳትፍ ሲምፖዚየም ነው ብለን ነው ያሰብነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሐሳብን በነፃነት ለመወርወር የሚያስችል አንድ መድረከ ሊፈጠር ይችላል ብለን እናስባለን፡፡ ምናልባት ገዥው ፓርቲ አሁንም ፈተና እየፈጠረብን ያለው ብሔራዊ ዕርቅ በሚለው አስተሳሰባችን ነው፡፡ በእኛ በኩል ብሔራዊ ዕርቅ አንድ የፕሮግራም አካላችን ነው፡፡ ብሔራዊ ዕርቅ መኖር አለበት ነው የምንለው፡፡ ገዥው ፓርቲ የተጣላ ሰው የለም ማንን ከማን እናስታርቃለን የሚል ዓይነት አካሄድ ነው እየተከተለ ያለው፡፡ ስለዚህ ያንን በተወሰነ ደረጃ አለዝበነው ብሔራዊ መግባባት በሚል እንጀምረውና ብሔራዊ ዕርቅ ወደሚለው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ብሔራዊ ዕርቅ ከተባለ በሁሉም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉትን አካላት በመሉ የሚያቅፍ ነው የሚሆነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት የሚለው ግን ተመሳሳይ አጀንዳ ኖሯቸው በአገር ወስጥ ያንን ተመሳሳይ አጀንዳ አዋህደው ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲ ተብሎ በጠላትነት የሚፈረጀውን ነገር በመገደብ፣ ወደ አንድ ለአገር የሚጠቅም አጀንዳ ውስጥ የሚያስገባ ነገር መፍጠር ነው፡፡ ምናልባት ምሁራን በራሳቸው የሚተነትኑበት መንገድ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ያንን ትኩረት ሰጥተን የምናይ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርቲያችሁ ማሳካት ከሚፈልጋቸው ጉዳዮች አንዱ የብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ ዕርቅ ሲባል ማን ከማን ነው የሚታረቀው? የትኛው ችግርስ ነው ዕርቅ የሚፈልገው? ይህን በዝርዝር ተመልክታችሁታል?

ዶ/ር ጫኔ፡- ተሳታፊዎች ይለያሉ፡፡ በዚህች አገር የፖለቲካ ሒደት ሁሉ ያገባናል የሚሉ ብዙ አካላት ናቸው፡፡ በሰላማዊ ትግል የሚንቀሳቀሱ አካላት አሉ፡፡ ለውጥ የሚመጣው በጦርነት ብቻ ነው ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት አሉ፡፡ መሀል ላይ ቆመው ዝም ብለው ምንም ሐሳብ የማይሰጡ ግን በአገር ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት የሚፈልጉ አካላት አሉ፡፡ በድንበር አካባቢ ወይም በሌላ ጦርነቱንም የጀመሩ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነኚህ በሙሉ ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚች አገር ያለፈው ይብቃ የሚል ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በኋላ አገራችንን እንዴት ወደፊት እናራምዳት ነው ጉዳዩ፡፡ በዳይና ተበዳይ አለ፡፡ ስለዚህ በዳይ ተበዳይ የሚለው ነገር የሆነ ቦታ ላይ እስካልቆመ ድረስና መግባባት እስካልተፈጠረ ድረስ፣ ይኼ በዳይ ተበዳይ የሚለው አንዱ አንዱን እየጣለ የአምባገነንት ሥርዓትን ሁል ጊዜ እያስተናገደች የምትሄድ አገር ትሆናለች፡፡ ከዚህ አንፃር ይህ ነገር የሆነ ቦታ ላይ መቆም አለበት፡፡ ሰላም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መምጣት መቻል አለበት፡፡ የድል ሐውልቶች የሚባሉት በመሉ የሰላም ሐውልቶች መባል አለባቸው፡፡ ወንድም ወንድሙን እየገደለ የድል ሐውልት እያልን የምናሞካሽበትና ጀብድ የምንሠራበትን ዓይነት ሥልት አይደለም ተከትለን መሄድ ያለብን፡፡ ብሔራዊ ዕርቅ ከዚህ መለስ ይበቃል ማለት ነው፡፡ ባለድርሻ አካላት እዚህ ጋ ቁሙና ስለአገራችሁ ሰላም ምከሩ ተብሎ ይህንን ሊፈጥር የሚችል ብሔራዊ እርቅን ሊያራምድ የሚችልና አካል ፈጥሮ፣ በዚህ መንገድ ማስቀጠል ማለት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እስከ መጨረሻው ድረስ የማያባራ ዓይነት ቅራኔ እየተፈጠረ እንደሚሄድ የእኛ ፓርቲ ይገመግማል፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርቲያችሁ በመጪው ምርጫ አሸንፎ ቢመረጥ ለሕዝቡ የሚያቀርበው አማራጭ የፖሊሲ ስትራጂ ወይም ፕሮግራም ምንድነው?

ዶ/ር ጫኔ፡- በእኛ ፓርቲ የመንግሥት ለውጥ አይደለም የምንፈልገው፡፡ የምንፈልገው የሥርዓት ለውጥ ነው፡፡ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ሕዝቡ ለኢዴፓ ዕውቅና ከሰጠው መንግሥት ለመመሥረት ይችላል፡፡ መንግሥት ከመሠረተ በኋላ ግን የሥርዓት ለውጡ እንዴት ነው ሊፈጸም የሚችለው የሚለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ በሚያሳትፍ መንገድ እንወስናለን፡፡ የሊብራል ኢኮኖሚና አስተሳሰብ እሴቶቻችንና የዴሞክራሲ እሴቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ መዋቅር መመሥረት እንችላለን ብለን ነው የምናስበው፡፡ ኢዴፓ ሁለተኛ ዋና ፓርቲ ሆኖ የመጓዝ ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡  የሥርዓት ለውጥ ከመጣ ገዥው ፓርቲ እንደ ሁለተኛ ፓርቲ ሆኖ የሚቀጥልበት ዕድሉ የሰፋ ነው ማለት ነው፡፡ የአፈጻጸም ሥልቶች እየተነደፉ አሁን የወጡት አዋጆችና ሕጎች መሬት ላይ ወርደው በትክክል መፈጸማቸውን እያረጋገጠ የሚሄድ ዓይነት የፖለቲካ ሥልት ነው እኛ መንደፍ የምንፈልገው፡፡ የሥርዓት ለውጡን በዚህ መንገድ ነው መተርጎም የሚቻለው፡፡ አለበለዚያ በቀጥታ መንግሥት እንሆናለን ብለን የምናስብ ከሆነ ግን አጠቃላይ ተቋሞችን በሙሉ አፍርሰን ከዜሮ የምንጀምርበት ዕድሉ የሰፋ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ብንሆን የምናደርገው ለተቋማት በሙሉ ከፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ የሆነ አስተሳሰብ ያለው አመራርና ባለሙያ፣ እንዲሁም መልካም አስተዳደር ተዋቅሮለት በሚፈለገው መንገድ ወደ ተግባር የሚቀየርበትን መንገድ ነው ማዋቀር የምንፈልገው፡፡ መንግሥት እየተከተለው ያለውን የሲቪል ሰርቪሱን አካሄድ አሁን ላይ ሆነን ስናስበው ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ አይደለም ብለን ነው የምናስበው፡፡ ከዚህም አንፃር በተለያዩ ጊዜያት ለመልካም አስተዳደር ይሆናሉ ብሎ በሌሎች አገሮች በሳይንስ የተረጋገጡ የአሠራር ሥልቶች ሁሉ ዘርግቶ እንደነበር እናውቃለን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ከወጡና ተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ማዕከል አድርገው መሥራት የሚችሉ ከሆነ፣ በሳይንስ የተረጋገጡ፣ መልካም አስተዳደርን ሊያመጡ የሚችሉና ሥራን ሊያቀላጥፉ የሚችሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች በመንግሥት መዋቅር ሳይሆን በአፈጻጸምና ሕጉን በመተርጎም ላይ የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሕጉ በዚህ መንገድ መፈጸም የሚችልበትን የአፈጻጸም ሥልት ግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ወደ ተግባር መቀየር የሚቻልበት ሒደት አለ ብዬ ነው የማስበው፡፡   

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ኢዴፓ ቢመረጥ አብዛኛዎቹ የመንግሥት ተቋማት ሳይነኩ ይቀጥላሉ ማለት ነው?

ዶ/ር ጫኔ፡- ኢሕአዴግና እኛ ይህ መንገድ ያመሳስለናል ብያለሁ፡፡ እነኚህ የተዋቀሩ ተቋማት በሙሉ መንግሥት እየተከተላቸው ያሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ አፍርሰን የምንገነባበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ ያለው ምንድነው የሚሆነው፣ በሰው ኃይል ከፖለቲካ ነፃ በሆነ መንገድ ገዥ ከሚሆን ፓርቲ የተላቀቀ የሲቪል ሰርቪስ ስትራቴጂ ታቋቁማለህ፡፡ ከዚህ አንፃር ያሉትን በሰው ኃይል ታደራጃለህ፡፡ ሁሉም እንደየአቅሙና እንደየችሎታው የሚሠራ ሠራተኛ ታዘጋጃለህ፡፡ በፖለቲካ ድጋፍ እየገባ አሁን እያበላሸው ያለው ዓይነት አካሄድ ነው መልካም አስተዳደርን ችግር ላይ እየጣለው ያለው፡፡ ስለዚህ በፖለቲካ ሽፋን ወደ ሲቪል ሰርቪሱ እየተገባ አቅም ያለውን ወደ ዳር እያስወጣ ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለ ሒደት መቆም መቻል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዴፓ ከተመሠረተ ረዘም ያለ ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ አንዳንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ  ግለሰቦች በፓርቲው ውስጥ አገልግሎት ሰጥተው ጥፍት ይላሉ፡፡ ለምሳሌ አቶ አብዱራህማን፣ አቶ መስፍን፣ አቶ ልደቱና አቶ ሙሼን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ፓርቲውን በተለያዩ ምክንያቶች የሚለቁት ፓርቲውን  ባላቸው ልምድ በከፍተኛ ሁኔታ ሊረዱ የሚችሉበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ፓርቲው አባላቱን ይዞ መቆየት የሚሳነው ለምንድነው በማለት የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የእርስዎ ምላሽ ምን ይሆናል?

ዶ/ር ጫኔ፡- በእኛ ፓርቲ በኩል ውስጣዊ ዲሲፕሊናችን በጣም ጠንካራ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ላይ ይኼ ነው ይኼ ነው የሚያስብል ነገር የለውም፡፡ የተጠሩት ግለሰቦች ግን ምናልባት አቶ ልደቱ ነባርና ታዋቂ ፖለቲከኛ ነው፡፡ ኢዴፓን እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰና ታላቅ አስተሳሰብ ይዞ ያራምድ የነበረ ግለሰብ ነው፡፡ በደንባችን መሠረት አንድ ግለሰብ በፕሬዚዳንትነት ሁለት ጊዜ ነው መመረጥ የሚችለው፡፡ ሁለት ጊዜ ተመርጦ ዙሩን ጨርሶ በአባልነት እየቀጠለ ነው ያለው፡፡ ከዚያ ባሻገር የብሔራዊ ምክር ቤት አባል ነው፡፡ ከፖለቲካ የራቀበት ሒደት የለም፡፡ እነ አብዱራህማን፣ ሙሼና መስፍን ግን የፖለቲካ ሥራ እየሠሩ የግል ሕይወታቸውን መምራት የሚያስችል የኢኮኖሚ ሒደት አላጋጠማቸውም፡፡ ስለዚህ ሙሉ ጊዜያቸውን የግል ሕይወታቸውን የሚመሩበትን መንገድ እየፈጠሩ ነው የሄዱት፡፡ ፓርቲውን ይህን ያህል እዚህ ደረጃ ላይ ካደረስን ይበቃናል፡፡ የተተካው የፓርቲው አባል ደግሞ ይህንን ይዞ ያራምድ ነው ያሉት፡፡ ወደፊት አቅማችን ሲፈቅድና በኢኮኖሚም ራሳችንን የምንችል ከሆነ ተመልሰን ፓርቲውን የማናገለግልበት ምክንያት የለም፡፡ ከዚህ አንፃር ነው ትርጉም እየሰጡት የሚሄዱት፡፡ ሁሉም ያቀረቡት ነገር ግላዊ የሆነ ምክንያት ነው፡፡ ከፓርቲው ጋር ባላቸው ቅራኔ አይደለም፡፡ ሁሉም የወጡት የራሳችንን ማኅበራዊ ሕይወት መምራት፣ ኢኮኖሚያችንን ማሳደግ፣ ትምህርታችንን ማሳደግ እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡ ፓርቲው ውስጥ ሆነን ግን ይህ ዕድል ተዘግቶብናል ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ የእነሱ አወጣጥ እንጂ በፀብ፣ በቅራኔና በቁርሾ አይደለም፡፡ አቶ ሙሼ በተለይ ማኅበራዊ ተፅዕኖ ነው እንዲርቅ ያደረገው፡፡ ከቤተሰብ ጋር በፈጠረበት ተፅዕኖ ምክንያትና መማር ስለፈለገ ነው፡፡ መማር የምችለው ከዚህ ፓርቲ ወጥቼ ነው ያለው፡፡ ቢሆንም ግን በሐሳብ ይረዳናል፡፡ ተሞክሮውን እያካፈለን ነው፡፡ አሁንም የተለያዩ ነገሮችን ዳሰሳ ያደርግልናል፡፡ ስለዚህ ፓርቲውን ለቋል ማለት አንችልም፡፡ በታዋቂ ፖለቲከኛነቱ እኛን እየረዳን ነው ያለው፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -