በመንግሥት ግዥዎች ላይ የሚፈጸመውን ሙስና ለመከላል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን የቻለ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አቋቋመ፡፡
ኤጀንሲው በከተማው አስተዳደር ሥር የሚገኙ ተቋማት የሚፈልጓቸውን የካፒታልና አገልግሎት ግዥዎችን ይፈጽማል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፎኢኖ ፎላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተቋቋመውን ኤጀንሲ ሥራ ማስጀመር የሚያስችሉ የሰው ኃይል ቅጥር መመርያዎችና ማንዋሎች እየተዘጋጁ ነው፡፡
የተቋቋመው ኤጀንሲ በዋኛነት ሦስት ዓላማዎች አሉት ተብሏል፡፡ የመጀመሪያው በግዥ ሒደት ሁሉም ድርጅቶች የየራሳቸው ግዥ በሚፈጽሙበት ወቅት የሚባክነው ሀብት ያስቀራል፡፡ በማዕከል ደረጃ ግዥ ቢፈጸም፣ አላስፈላጊ የሀብትና የጊዜ ብክነት በማስቀረት በኩል ከፍተኛ ሚና አለው ተብሏል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ በከተማ ደረጃ እየተካሄደ ያለው ልማት በሚፈለገው ፍጥነት ግዥ ለመፈጸም ይህ ኤጀንሲ አስተዋጽኦው የጐላ ነው ተብሏል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በመንግሥት ግዥዎች ላይ የሚፈጸመውን ሙስና ማስቀረት ነው፡፡
አቶ ፎኢኖ እንዳሉት፣ በዚህ ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 28.8 ቢሊዮን ብር በጀት አለው፡፡ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ ለግዥ ይውላል፡፡ ግዥው የመንገድ፣ የውኃና የተለያዩ ግንባታዎችን ጨምሮ የአገልግሎት ግዥዎችን ያጠቃልላል ብለዋል፡፡
አቶ ፎኢኖ በከተማው አስተዳደር ውስጥ የግዥ የአፈጻጸም ችግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ በጨረታ ግዥ አፈጻጸም ላይ የሚሳተፉ ተጫራቾች፣ አምራቾችን አጫራቾች ሕገወጥ አሠራርን እንዲያስወግዱ ኤጀንሲው ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ባለፉት ወራት በግዥ ሒደት ችግር ፈጥረዋል የተባሉ ወገኖች ከስድስት ወራት እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ከዘርፉ መታገዳቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግዥ ኤጀንሲ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ያቋቋመውን የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ቅርፅ ይዟል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ገንዘብ ሚኒስቴር የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችን ግዥ በማዕከል ደረጃ የሚፈጽም የግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ማቋቋሙ ይታወሳል፡፡