Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበፈጣን መደብር ይገባኛል ጥያቄ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያሳለፈውን ውሳኔ ሰበር ሰሚ...

በፈጣን መደብር ይገባኛል ጥያቄ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያሳለፈውን ውሳኔ ሰበር ሰሚ ችሎት ውድቅ አደረገው

ቀን:

በፈጣን መደብር የይገባኛል ጥያቄ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ይዞታ አስተዳደር የወሰዱትን ዕርምጃ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውድቅ አደረገ፡፡

ፈጣን የችርቻሮ ንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሕጋዊ ባለቤቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴርንና የአራዳ ክፍለ ከተማን ድርጊት ለማስቆም የመሠረቱት የሁከት ይወገድልኝ ጥያቄ ላይ የፌዴራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ ውድቅ አድርጎታል፡፡

የንብረት ይገባኛል ጥያቄው የተነሳው በቀድሞው ሞዝቮልድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤቶች መካከል ነው፡፡ የይገባኛል ጥያቄውን ያነሱት የቀድሞው ሞዝቮልድ ባለድርሻ አቶ ፍቃዱ አምባዬ ተፈራ ሲሆኑ፣ በማኅበሩ ውስጥ የነበራቸው 4,000 አክሲዮን በሕገወጥ መንገድ በመተላለፉ የሞዝቮልድ ድርጅት ከሆነው ፈጣን መደብርና መጋዘን ላይ ድርሻቸው እንዲሰጣቸው በፍርድ ቤት መጠየቃቸውን የክስ ሰነዱ ያስረዳል፡፡

አቶ ፍቃዱ አምባዬ ተፈራ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሳቢያ ከአገር እንዲወጡ ተወስኖባቸው የነበሩ ኤርትራዊ ሲሆኑ፣ ኤርትራውያን ንብረታቸው እንዲመለስ ከተወሰነ በኋላ ንብረታቸውን ለማስመለስ ሲሞክሩ የአክሲዮን ድርሻቸው ያላአግባብ መተላለፉን አስመልክቶ ያቀረቡት ክስ በፍርድ ቤት ግንቦት 4 ቀን 1998 ዓ.ም. ተቀባይነት አግኝቶ ለእሳቸው እንደፈረደላቸው መዝገቡ ያስረዳል፡፡

በዚህም መሠረት የሞዝቮልድ ንብረት ከሆነው ፈጣን መደብር ላይ የአቶ ፍቃዱ አምባዬ የአክሲዮን ድርሻ እንዲመለስ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

ይህንንም ለማስፈጸም አቶ ፍቃዱ አምባዬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤርትራውያን ንብረት አስመላሽ ኮሚቴ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲፈጸምላቸው በጠየቁት መሠረት፣ ንብረት አስመላሽ ኮሚቴው ለአራዳ የግንባታ ፈቃድና ይዞታ አስተዳደር ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን ጽፏል፡፡ በዚሁ መሠረትም ክፍለ ከተማው የፈጣን መደብርና መጋዘን የግንባታ ፈቃድ መሰረዙንና ካርታውንም ማምከኑን ሰነዱ ያመለክታል፡፡

ይህ ተግባር ተገቢ አይደለም በማለት የፈጣን መደብርና መጋዘን ሕጋዊ ባለቤቶች አቶ ፍቃዱ ወርቁ ምሕረት፣ አቶ ሳሙኤል ፍቃዱ ወርቁና አቶ ደረጀ ፍቃዱ ወርቁ የውጭ ጉዳይ ንብረት አስመላሽ ኮሚቴና የክፍለ ከተማው ድርጊት እንዲቆምላቸው ለፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ያቀረቡት የሁከት ይወገድልኝ ጥያቄ፣ በኅዳር ወር 2006 ዓ.ም. ውድቅ መደረጉን ሰነዱ ያስረዳል፡፡ ይህንንም በመቃወም ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀረቡት ይግባኝ የካቲት ወር 2006 ዓ.ም. ውድቅ ሆኖ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ውሳኔ ፀንቷል፡፡

ሁለቱ ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ችሎቱ ባለፈው ጥር ወር ውሳኔውን ሰጥቷል፡፡

በዚህም መሠረት አቶ ፍቃዱ አምባዬ በሞዝቮልድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ላይ አለኝ የሚሉትን መብት በፍርድ ቤት ውሳኔ ለማስከበር ክስ አቅርበው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 31575 ግንቦት 4 ቀን 1998 ዓ.ም. ፍርድ መስጠቱን በመጥቀስ፣ የአፈጻጸም ጥያቄ ማቅረብ የሚችሉት ለንብረት አስመላሽ ኮሚቴው ሳይሆን ውሳኔውን ለሰጠው ፍርድ ቤት መሆኑን ከፍትሐ ብሔር የሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 371 መረዳት እንደሚቻል ችሎቱ አመልክቷል፡፡

በመሆኑም ይህንን ሳያገናዝቡና ሞዝቮልድ የተባለው ድርጅት በ1999 ዓ.ም. በሌላ ፍርድ ቤት መፍረሱ የሚያስከትለውን ውጤት ሳያገናዝቡ፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤትና ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ትዕዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት በመሆኑ እንዲሰረዝ ወስኗል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤርትራውያን ንብረት አስመላሽ ኮሚቴ የሰጠው የአፈጻጸም ውሳኔም በሕግ ከተሰጠው የሥነ ነገር ሥልጣን ውጪ በመሆኑ ሕጋዊ ውጤትና ዕውቅና የሚሰጠው አይደለም በማለት ወስኗል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ የግንባታ ፈቃድና የይዞታ አስተዳደር ከንብረት አስመላሽ ኮሚቴው የተጻፈለትን ደብዳቤ ተመላሽ በማድረግ የፈጸማቸው ተግባራትም ሕጋዊ መሠረት የላቸውም በማለት ወስኗል፡፡

ይህ ውሳኔ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንቦት 4 ቀን 1998 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ የፍርድ ባለመብት የሆኑት አቶ ፍቃዱ አምባዬ ተፈራ፣ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት አለኝ የሚሉትን የአፈጻጸምና ሌላ የመብት ጥያቄ ከማቅረብ የሚገድባቸው አይደለም በማለት ሰበር ሰሚ ችሎቱ ወስኗል፡፡  

  ፈጣን መደብር የሞዝቮልድ አካል ነው ወይስ ራሱን የቻለ ድርጅት ነው በሚለው ጉዳይ ላይ በሰነድ ማጭበርበር ሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶ በፍርድ ቤት ክርክር እየተደረገበት እንደሆነ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...