Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን የጋራ ኮሚቴ ካርቱም ሊገናኝ ነው

የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን የጋራ ኮሚቴ ካርቱም ሊገናኝ ነው

ቀን:

የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የተቋቋመው የሦስትዮሽ ቴክኒክ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት በኋላ በካርቱም ተገናኝቶ ሊመክር ነው፡፡

ሦስቱም አገሮች እያንዳንዳቸው አራት ባለሙያዎችን ወክለው የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ኃላፊነት፣ ከዚህ ቀደም የዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረባቸውን ሁለት ምክረ ሐሳቦች የሚተገብሩ ዓለም አቀፍ አማካሪዎችን ለመቅጠር ነው፡፡

ይህ ኮሚቴ በጥቅምት ወር በአዲስ አበባ በመቀጠልም በግብፅ ተገናኝቶ ከአምስት አገሮች የተመረጡ ሰባት ዓለም አቀፍ አማካሪዎች፣ የተባሉትን ሁለት ምክረ ሐሳቦች ለማጥናት ፕሮፖዛላቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡

ይሁን እንጂ ለሚዲያ ይፋ ባልሆነ ምክንያት ኮሚቴው መግባባት ላይ መድረስ ባለመቻሉ ወደ ሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች ተመርቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት ኢትዮጵያ የመጡት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤልሰሲ ጉዳዩን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው በስፋት ይመክራሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ በግብፅ ሲናይ በደረሰ የአሸባሪዎች ድንገተኛ ጥቃት ስብሰባውን አቋርጠው መመለሳቸው አይዘነጋም፡፡

ባለፈው ሳምንት የሱዳን የውኃና መስኖ ሚኒስትር በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በእርሳቸው ጋባዥነት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ከግብፅ አቻዎቻቸው ሳሜህ ሽኩሪና ሆሳም አል ሞጋሃዚ ጋር በዝግ በሸራተን አዲስ መምከራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለመገናኛ ብዙኃን ዝግ እንዲሆን በተደረገው ስብሰባ የሱዳን የውኃና መስኖ ሚኒስትር ቢኖሩም፣ ዋነኛ ውይይቱ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ በግብፅ በኩል የቀረበው አዲስ ሐሳብ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ተጠቅማ ውኃውን ለመስኖ እንደማታውልና በግብፅ የውኃ ድርሻ ላይ ጉዳት እንደማይደርስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምስክር በሚሆንበት መድረክ ሁለቱ አገሮች እንዲፈራረሙ ጠይቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ በግብፅ በኩል የቀረበው ሐሳብ በኢትዮጵያ በኩል ውድቅ መደረጉን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን የግብፅ ሕዝብንም ሆነ መንግሥትን የመጉዳት ፍላጐት እንደሌላት፣ ነገር ግን የቀረበው ሐሳብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿን የማልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረ ሉዓላዊ መብቷን የሚጋፉ እንደሆነ እንደተገለጸላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህ ሐሳብ ላይ የሁለቱ መንግሥታት ሚኒስትሮች መግባባት ላይ ባይደርሱም፣ የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሱዳን ተገናኝቶ እንዲወያይ ተሰምተዋል፡፡ በቀጣዩ ሳምንት የዓባይ ቀን በሱዳን የሚከበር መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...