‹‹ውኃ ወርዶ ወርዶ አቀበት ይዋኛል፣ አትበሳጭ ልቤ የባሰ ይገኛል፤›› አለ የወንዙን ልጅ ትቶ የሰው አገር ሲያድን የመነመነው። ምን በምግብ ዋስትና ራስን ቢችሉ፣ መመንመን አይተወንማ። እና ውዷ ማንጠግቦሽ ራሷን አልችል ብላው፣ ደረቴ ላይ ጣል አድርጋው ሳለ ቅዠት ነው መሰል ብንን አልኩ። ቀን እየባነንን ሌሊት ይቀናናል። እንዲያው እኮ! ስባንን ቀሰቀስኳት። እየተገላበጠች፣ ‹‹ስንት ሰዓት ነው?›› ብላ ጠየቀችኝ። አይገርምም? እስኪ አሁን ጨለማ ቆጠረ አልቆጠረ ምን ይፈይዳል? ‘ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው?’ ይሉናል ደርሰው። እንጃ የእናንተን ብቻ እኔ ሳልደርስባቸው የሚደርሱብኝ እያደር ጨምረዋል። ምናልባት እኔ ሳባርራቸው ወደ እናንተ ከመጡ መልሱ ‹አልነጋም ገና ነው!› ነው። አደራ ከእኔ አልቀዳችሁትም እሺ። ደግሞ ያስኮርጃል ተብዬ ኋላ ጣጣ እንዳታመጡብኝ።
የባሻዬ ልጅ፣ “ማንም አይነካህም አይዞህ። መጀመርያ በኩረጃ እያለፉ ያስመረቁዋቸውን ይከልሱ፤” ሲለኝ ነበር። ማን ተመራቂ ማን አስመራቂ እንደሆነ እሱ ሲያወራ ግራ ገባኝ። ግን እንዲያው አደራችሁን፣ ሌት ከሆነ ሰዓት ማሥላት ምን ይጠቅማል? እ . . ? ሰቅዞ ይዞኝ እኮ ነው የምደጋግምባችሁ። የቀኑን ብርሃን ሳይቀር ይህ የዘመን ጨለማ ከል እያለበሰው የመንገድ መብራት 24 ሰዓት ይብራልን ሳንል አንቀርም ትላላችሁ ትንሽ ቆይተን? “አይ አንበርብር! ‘ዩ አር ቱ ፋር ፍሮም ዘ ሪያሊቲ” ይለኛል ምሁሩ ወዳጄ። “አብራራ!” ስለው፣ “አንተም ቤት ለቤት በቅጡ ያልተዳረሰና የሚቆራረጥ ኃይል እንዴት ሆኖ መንገድ ለመንገድ 24 ሰዓት ሊበራ እንደምታስብ አብራራ፤” ብሎ ይስቅብኛል። ኧረ እኔስ አልስቅም። ቀኑ በጨለማ ኃይል የተያዘበት ምስኪን ይኼን ሁሉ ዕልቂት፣ ይኼን ሁሉ ፍጅት፣ ይኼን ሁሉ የፖለቲካ የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚደረግ የአውሬዎች ሴራ እያየ እንዴት ይስቃል? ማን ነበር፣ ‹‹የሳቅ መቆራረጥ ያስቸገረን በዓለም መንግሥታት የአስተዳደር ብልሹነት ነው፤›› ብሎ ሲደመድም የሰማሁት?
በቀደምለት ባሻዬን ወደ ቤተስኪያን ልሸኛቸው ከቤት ወጣሁ። ሰዓታቱ ሳይጀመር ለመድረስ እየተጣደፉ ይራመዳሉ። አካላቸው ቢዝልም አዕምሯቸውን ንቁ ነውና አንዳንዴ አነቅፏቸው ወይ ወለም ብሏቸው እንዳይወድቁ ስለምሠጋ፣ “ቀስ ይበሉ እንጂ ባሻዬ፣ ይደርሳሉ፤” አልኳቸው። ኋላ ፈገግ ብለው፣ “ሂድና ለእነዚያ ችኩሎች ንገራቸው። እኔ ብቸኩልም በሁለት እግሬ ነው። ምነው ባለ አራት እግሮቹ አይታዩህ?” ብለው ማዶ ሲጠቁሙኝ አንድ ቪትዝ መኪና እንደ ካርቶን ተጨማድዳ፣ አንድ አይሱዙ ደግሞ የፊት መስታወቱ ረግፎ አየሁ። “አሁን እኮ ሰላም ነበር፣ ከመቼው?” ብዬ ክው አልኩ። “ለመዋደድ ስንዝር ለፀብም እንዲያው ነው ያለውን ባለቅኔ አታውቀውም እንዴ? ሰው ከንቱ ሁሉ ነገር ቀሪ መሆኑ በምን ቋንቋ ቢነገረው፣ እንዴት ባለ ልምድ ቢያየው እንደሚገባው እንጃ። ረግፎ ለመቅረት ይኼ ሁሉ አበሳ፣ ይኼ ሁሉ ሩጫ፣ ይኼ ሁሉ ስደት አይገርምህም ግን አንበርብር? መጽሐፉ እኮ ‹ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ› የሚለው ያለ ምክንያት እንዳይመስልህ። በሟች በላይ የቋሚ አበሳ ነው ከባዱ። ግን እኛ ነገር ካላለፈ አልገባን ብሏል፤” ብለው የዕርምጃችንን ዙር አቀዘቀዙት።
“ምነው ባሻዬ አመመዎ እንዴ?” ስላቸው፣ “እንዴት አያመኝ አንበርብር? በየቀኑ ጥፋት መቁጠር እንዴት አያመኝ? በየቀኑ አስከሬ መሸኘት እንዴት አያመኝ? በየቀኑ ውሸት ማንገሥ፣ ሀቅ መውገር እንዴት አያመኝ?” ብለው ሲያፈጡብኝ ማረጋጊያ ዘዴና የምገባበት ጠፋኝ። ውሎ አድሮ የባሻዬ ሕመም ተጋባብኝ መሰለኝ የደመ ነፍስ ሩጫ፣ የስሜት ውዥንብር የሚነዳው ሆታና እልልታ እየደገሰ የሚያስገብረን አካልና አዕምሮን መቁጠር እኔንም ታከተኝ። ጥቂት ማንቀላፋት፣ ጥቂት ደግሞ መንቃት፣ ደግሞ ማንቀላፋት፣ ደግሞ መባነን፣ እኮ እስከ መቼ?
ጨዋታን ጨዋታ ያጫውተዋል። እጄ ላይ ባለሁለት መኝታ ክፍል ኮንዶሚኒየምን ቤት ስላለ እሱን የሚገዛ ደንበኛ ለማግኘት እታትራለሁ። እዚያ እደውላለሁ። እዚህ ሰው አስቁሜ አናግራለሁ። የማልሆነው ነገር የለም። ቤቱ የሚገኘው ከሠፈሬ ቅርብ አካባቢ ስለነበር ምሳ ሰዓት ሲደርስ ወጪ ቁጠባ ቤቴ ሄጄ ልመገብ አስቤ አዘገምኩ። መቼም ውዷ ማንጠግቦሽ ቆቅ ናት፡፡ ቤቱን አበባ አስመስላ፣ ቡና አቀራርባ፣ ምሳ አዘጋጅታ ትጠብቀኝ ኖሯል። በነገራችን ላይ የኑሮዬን ቋጠሮ መንግሥት ብቻ ይፈታዋል ብላችሁ ለምታስቡ ላጤዎች የማስተላልፈው መልዕክት፣ ቶሎ አግቡና ከመንግሥት አናት ላይ ውረዱ የሚል ነው። እንኳን ኑሮ ሥልጣንም ለብቻ ያንገፈግፋል። ይኼን የክፍል አለቃ ሆናችሁ የምታውቁ በደንብ ትረዱኛላችሁ!
እና ምሳዬን እየሰለቀጥኩ ሳለሁ አንድ ወዳጄ ደውሎልኝ በአስቸኳይ ሊያገኘኝ እንደፈለገ አሳውቆኝ ቤት ና አልኩት። እንደመጣ፣ “ምንድነው?” ብዬ ያጣደፈውን ጉዳይ ስጠይቀው፣ “ዕቁብ መጣል ልንጀምር ስለሆነ፣ ከእኛ ጋር መጣል ጀምር ብዬ ነው፤” አለኝ። የዘንድሮ ወጣት የኑሮን ብልኃትና አያያዙን አላውቅበት ብሎ ሲንገታገት እንደሚያበሽቀው ሁሉ፣ ሲያውቅበት ደግሞ እንዴት አንጀት እንደሚያርስ አልነግራችሁም። “ጥሩ ነዋ ለመሆኑ ስንት ነው?” ማለት። “በሳምንት አሥር አሥር ሺሕ ነው!” ሲለኝ ጉሮሮዬ ላይ ቆሞ አልወርድ ያለውን እህል ለመግፋት ሁለት ብርጭቆ ውኃ (ያውም በሌለ ውኃ) ጨረስኩ። “እንኳን እኔ ይኼን ያህል ገንዘብ በሳምንት የመጣል አቅም ሊኖረኝ፣ የሚጥል የቅርብ ወዳጅም አላውቅም። ይገርማችኋል ጭራሽ እኛ ሠፈር ተርፎት ዕቁብ መጣል ይቅርና እንቁላል የምትጥል ዶሮም አናውቅም። ከተረጋጋሁ በኋላ፣ “ለመሆኑ ሠርቼ ነው ዘርፌ ነው በሳምንት አሥር ሺሕ ብር የምጥለው?” ስለው ቅር ብሎት ተነስቶ ሄደ። አይገርማችሁም? አገርህን ዕወቅ ይሉኛል ሠፈሬን በቅጡ ሳላውቅ። ኧረ እንዴት ያለ የብልፅግና ዘመን ሆኗል ግን!
ያልኳችሁን ቤት አሻሽጬ ጨረስኩ፡፡ የቱንም ያህል ያሰብነው ቢሳካ የወጠንነው ቢሰምር ያለጤና ምንም ዋጋ እንደማይኖረው በጣም እንዳልገባኝ ስሆን አንዳንዴ አፍራለሁ። ለነገሩ ዛሬ ማፈር የሚባለው ነገር ተረስቷል አይደል? ‘እያዩት ከማይበሉት ሰዎች ተርታ አያስቆጥራችሁ!’ ሲባል አሉ አላሳፍር ብሏል። ዘመኑ በልተን እንሙት ባዩ ነዋ የሚመራው። መብላቱንስ ይብሉ። ካልተባላን ብለው የሚያስጨንቁን ነገር አይደብርም?! ባሻዬ ባለፈው ከዕድር ስብሰባቸው ሲመለሱ ባገኛቸው፣ “አቤት! እግዚኦ አንተ ፈጣሪ!” እያሉ ሲጓዙ አገኘኋቸው። እጆቻቸውን ወደ ሰማይ አንስተው ረቂቅ ትዝብታቸውን ለአምላካቸው ይኸው ብለው እንደ ንድፍ የሚያሳዩት ይመስላሉ። “ምነው ባሻዬ?” ስል እንደ ልማዴ፣ “እንዲያው ማን ይሆን ጤነኛ ዘንድሮ አንበርብር? ሰው ሁሉ ጉዱን ከኋላው ቀብሮ ነው ለካ የሚኖር?!” ሲሉኝ ምን ሰምተው እንደሆነ አልጠየቅኳቸውም።
ምድረ ሙሰኛ እንደ ቀበሮ ካለበት ጉድጓድ እየታደነ ለሕግ መቅረብ በጀመረበት ሰሞን የምን ጥያቄ ማብዛት ነው እሱ? ያውስ በጥልቅ እየታደስን? ይልቅ የገረመኝ የእኛ የሰው ልጆች ባህሪ ነው። በስርቆትና በሕገወጥ መንገድ ዘመናችንን በሙሉ ለምን የተደላደለ ነገር ይዘን ለመኖር እንደምንደክም ሳስበው ብቻዬን ገርሞኝ እስቅ ጀመር። ወደው አይስቁ እኮ ነው! ስለዚህ አመራማሪ ስለሆነ የእኛ የሰው ልጆች ባህሪ ከባሻዬ ጋር ስንጨዋወት፣ “ይኼ አሁን የምትለኝ ነገር ከጥንትም ከእነ አዳም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለ አመል ነው። ቀናው እያለ ጠማማውን፣ ፊት ለፊቱ እያለ ጓሮውን፣ ብርሃን እያለ ጨለማ ጨለማውን መሄድ ነው የምንወደው። እንደው እንዴት ያለ ባህሪ ነው ግን?” ብለውኝ ራሳቸው እጅግ ገርሟቸው ሳቁ። በዚህ መሀል ስለ ሰው ልጅ በሥልጣኔ መገስገስና መራቀቅ ለማሰብ ሞከርኩ። ጨርሶ የሚዋጥልኝ ነገር አልሆነም። ሰው ሰውን የሚጥልበትን ገደል እየማሰ፣ ለሰውነቱም፣ ለአዕምሮውም፣ ጤና የማይሰጠውን የሕዝብ ገንዘብ እየቀማ፣ የአገርን ኢኮኖሚ ለማድማት የማይገባበት ሲገባ ስታዩ እውነት 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነን ወይስ የጋርዮሽ ዘመን ላይ ትላላችሁ እኮ! እያወቁ አለቁ ነው በደፈናው የእኛ ነገር!
በሉ እስኪ እንሰነባባበት። ምንም እንኳ የሚሰማውና የሚታየው የመኖር ትጥቃችንን ሊያስፈታ ቢታገለንም ይህችን ያህል መተንፈሳችን አልጎዳንም። እሱም ተራው ደርሶ አትቁም እስኪባል ቋሚ ምን ይሆናል አትሉኝም? አዎ! ተስፋ ሳለ ምን ይሆናል። ባሻዬ ምን ሲሉኝ ነበር መሰላችሁ? “እሱ ኑር እስካለ ድረስ ብታጣ፣ ብትራቆት፣ ብትታረዝ ምን ማድረግ ትችላለህ? ‘እሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድርም’ ትላለህ። ዳሩ እሱ የከፈተውን ጉሮሮ አረመኔ ሲቆርጠው ዝም እያለ አስቸገረ። ግን መታገስ ነው። ሃይማኖትህ ምንም ሆነ ምን መሠረቱ ትዕግሥትና ፍቅር መሆን አለበት። ይኼውልህ ምሳሌ፣ አንድ የቆሎ ተማሪ ‘በንተ ስለማርያም’ ይላል ጭራሮ አጥር ጥግ ቆሞ። ውስጥ ያሉ እናት ሰምተው ‘ተሜ አትቁም’ ይሉታል። ‘እመ እኔ መቼ ቆሜ በእኔ ተመስሎ እኮ ፈጣሪ ነው የቆመ፤’ ቢላቸው፣ ‘ከምኔው አንተ ዘንድ ደረሰ? አሁን ሌማቴ ባዶ መሆኑን ከፍቼ አሳይቼ ሳልከድነው?’ አሉት።
ተሜ ተራውን፣ ‹‹ነው? እንግዲያስ ልቀመጥ፤›› ብሎ ተማሪነቱን ተወው ይባላል። የሚለመን ሳይኖር ለምን ልለምን ብሎ እኮ ነው። አይ ተሜ! ‘ከሰነፍ ተማሪ፣ ከገንዘብ ቀርቃሪ፣ ከሸምጣጣ ሱሪ ይሰውርህ’ የሚባለው ይኼኔ ነው። ስንፍና የጥበብና የተግሳፅ ጠላት ናት። አየህ ዓለም በማጣት፣ በማግኘት፣ በመውጣት፣ በመውረድ፣ በሞትና በሕይወት ጋጣ ስትከፋፈል ታግሶ ለሰነበተ፣ ቆሞ ለታዘበ፣ ታክቶ ላልተቀመጠ የማስተዋልን የዕውቀትን ብርሃን ታበራለት ዘንድ ነው። ጅብ ቸኩሎ ምን ነከሰ? ቀንድ አትለኝም? ምንድነው እኔን ብቻ የምታስለፈልፈኝ? አዎ! ሁሉን ታግሰን እኛው በእኛው እዚሁ ተደቋቁሰን ይህችን ምድር ብናርሳት ታጠግበናለች። ‘ወንድሜ ፊት ነሳኝ’ ብሎ ሰው የአባቱን ርስት ጥሎ ከሄደ ያው ባርነት፣ ያው የባዳ በደል ነው የሚጠብቀው። አፉን የከፈተ ባህር ነው የሚውጠው። አይደለም? መቻል ያሳልፋል። መቻል ያሰነብታል። በአጭር አነጋገር የታገሰ ፅልመትን ብርሃን ያለብሳል፡፡ መልካም ሰንበት!