Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ በስድስት ወራት ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ አበድሬያሁ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ከ2.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መሰብሰቡን አስታወቀ

የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በግማሽ የበጀት ዓመቱ 31.8 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱን አስታወቀ፡፡ እንደ ባንኩ ገለጻ፣ ብድሩ የተሰጠው በአገሪቱ ልማት ውስጥ ቁልፍ ቦታ ለተሰጣቸው ታላላቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችና ለተለያዩ የግል ሴክተሮች ነው፡፡

ባንኩ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ቀደም ብለው ከተሰጡ ብድሮች 19.7 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ፣ መልሶ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች በማበደር የተሳካ ሥራ መሥራቱን አስታውቋል፡፡

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ለተሰጣቸው ፕሮጀክቶች የፋይናንስ አቅርቦት ማመቻቸት ዋነኛ ትኩረቱ መሆኑን የገለጸው ባንኩ፣ የብድር አቅርቦቱን በብቃት ለማከናወን እንዲቻል የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ላይ ትኩረት መደረጉን አስረድቷል፡፡

በዚህም መሠረት ለግሉ ዘርፍ የሚደረገውን የብድር አቅርቦት ማሳደግ፣ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለውን የወጪ ንግድ መደገፍና ከፍተኛ አፈጻጸም እንዲኖር በቅርበት መከታተል፣ የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት ማስፋፋት፣ የባንክ ቴክኖሎጂዎችንና አገልግሎቶችን ማስተዋወቅና ይህንን ከፍተኛ ኃላፊነት መወጣት የሚችል የሰው ኃይል መገንባት በዕቅዱ የተያዙ ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውን ገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተቀማጭ ሒሳብ ዕድገትን በተመለከተ ባንኩ ባወጣው የዕቅድ አፈጻጸም ሲያብራራ፣ የተቀማጭ ገንዘብን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ለተያዙ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችል ዕቅድ ተዘርግቶ፣ የባንኩ ዲስትሪክቶችና ቅርንጫፎች ይህንን ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል ብሏል፡፡

በታኅሳስ ወር 2007 ዓ.ም. መጨረሻ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2014 ከነበረበት 193.3 ቢሊዮን ብር፣ ጭማሪ በማሳየት 209.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ አሰባሰብን በተመለከተም፣ በግማሽ ዓመቱ ከተለያዩ ምንጮች የሚሰበሰበውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የተለጠጡ ግቦችን በመያዝ በማዕከል፣ በዲስትሪክትና በቅርንጫፎች ከፍተኛ እንቅስቃሴ መደረጉን ንግድ ባንክ ገልጿል፡፡ የተገኘው ውጤት አመርቂ ነበር ያለው ባንኩ፣ ከ2.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመሰብሰብ የተሳካ አፈጻጸም እንደነበረው አስረድቷል፡፡ በሌላ በኩል ባንኩ ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚደርሱ ክፍያዎችን በተለያዩ መስኮች ለተሰማሩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ፈጽሜያለሁ ብሏል፡፡ ዝርዝሩን ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡

ሁሉንም የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በ“T-24” የኮር ባንኪንግ ሶሊዩሽንስ ሲስተም ውስጥ በማስገባት፣ ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ከሰጣቸው የሥራ መስኮች አንዱ መሆኑን ገልጾ፣ በርካታ የባንኩ ቅርንጫፎችም እርስ በርስ ተገናኝተዋል ብሏል፡፡ የካርድ የባንክ አገልግሎት፣ የሞባይልና የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎቶችን በኅብረተሰቡ ዘንድ ለማሰራጨት የሚያስችሉ ዕቅዶች ከሞላ ጎደል ግባቸውን መምታታቸውን፣ በዚህ መሠረት “ATM” እና “POS” ማሽኖችን ወደ ክፍያ ሥርዓቱ በማስገባት በቅደም ተከተል 597 እና 1,265 ማድረስ መቻሉን ባንኩ በአፈጻጸም ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

ባንኩ ከቴክኖሎጂ በተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመላው የአገሪቱ ክፍሎች በመክፈት፣ የባንክ አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በተግባር የሚያከናውነው መሆኑን ገልጿል፡፡ በግማሽ ዓመቱ 77 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመከፈታቸው ቅርንጫፎቹ በአጠቃላይ 909 መድረሳቸውን አረጋግጧል፡፡

በግማሽ ዓመቱ 1.3 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች ሒሳብ በመክፈታቸው፣ የባንኩ ደንበኞች ቁጥር ከፍተኛ ዕድገት በማሳየቱ በታኅሳስ 2007 ዓ.ም. 9.5 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡ የሴቶች ልዩ የቁጠባ ሒሳብ፣ የወጣቶችና የታዳጊዎች የቁጠባ ሒሳብና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጀምረው ደንበኞች እየተጠቀሙባቸው መሆኑን ባንኩ አስረድቷል፡፡

የባንኩ የሰው ኃይል ልማትን በተመለከተ በግማሽ ዓመቱ 4,058 አዳዲስ ሠራተኞች ቅጥር ተፈጽሞ፣ በአሁኑ ጊዜ የሠራተኞች ቁጥር ከ22 ሺሕ በላይ መሆኑ አስታውቋል፡፡ ለ14,666 ሠራተኞች ቴክኒካዊ፣ ለ3,217 ሠራተኞች ደግሞ ‹‹ዴቨሎፕመንታል›› ሥልጠና መሰጠቱን ባንኩ አውስቷል፡፡

የባንኩ አመራርና ሠራተኞች በተለያየ ደረጃ ባደረጉት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መሠረት፣ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ክንውን ውጤት አመርቂ ሆኖ መገኘቱን ባንኩ አስታውቋል፡፡   

    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች