Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናተዘረፍን ባሉ ተከሳሽ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች አቤቱታ ላይ ማረሚያ ቤት ምላሽ ሰጠ

ተዘረፍን ባሉ ተከሳሽ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች አቤቱታ ላይ ማረሚያ ቤት ምላሽ ሰጠ

ቀን:

‹‹ፍተሻ የሚደረገው የታራሚውን ደኅንነት ለመጠበቅ ነው›› የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር

በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የቀድሞ አመራሮችና ሌሎች ተጠርጣሪዎች፣ በማረሚያ ቤት በሌላ አካል በተደረገ ሕገወጥ ፍተሻ መዘረፋቸውን በሚመለከት ለፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዘርፍ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት አስተዳደር ምላሽ ሰጠ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ የአንድነት አመራሮች የነበሩ ሲሆን፣ አቶ አብርሃ ደስታ የዓረና አመራር እንዲሁም አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ናቸው፡፡ ሌሎች ስድስት ተጠርጣሪዎች በእነሱ የክስ መዝገብ ተካተው ታኅሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በፌዴራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸው በክርክር ላይ ይገኛሉ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና ተከልክለው ታስረው በሚገኙበት ማረሚያ ቤት ታኅሳስ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ለ13 አጥቢያ ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት እስከ ረፋዱ 5፡00 ሰዓት ድረስ፣ ከማረሚያ ቤቱ ውጪ በሆኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላትና የደኅንነት አባላት ናቸው ባሏቸው አካላት እንዲፈተሹ ተደርጐ፣ ገንዘብና ለፍርድ ቤት መከራከሪያ ያዘጋጇቸው የተለያዩ መጣጥፎች እንደተወሰዱባቸው ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

አቤቱታቸውን የሰማው ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዘርፍ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት አስተዳደር አስተዳዳሪ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አምባዬ ህቡዕ የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በጽሑፍና በቃል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አንድ በቀጠሮ ላይ ያለ እስረኛ በቀጠሮ ቀን ወደ ፍርድ ቤት ከማቅረብ ባሻገር፣ በሕግ ቁጥጥር ሥር በሚቆይበት ጊዜ ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮና አካላዊ ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ፣ እስረኞችን በመፈተሽ ደኅንነታቸውን እንደሚከታተል ገልጸዋል፡፡ እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ፣ ማረሚያ ቤቱ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ፍተሻ አካሂዷል፡፡ ፍተሻውን ያደረገው የተጠርጣሪዎች ጠበቃ እንዳመለከቱት ሳይሆን፣ ታኅሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ፍተሻውም የተደረገው በሌሎች አካላት ሳይሆን በማረሚያ ቤቱ የጥበቃ አባላት ነው፡፡ ፍተሻው ዝም ተብሎ የሚደረግ ሳይሆን ኮሚሽኑን ለማቋቋም በወጣ የታራሚዎች መተዳደሪያ መመርያ ቁጥር 01/96 አንቀጽ 28(4)፣ ማለትም የሕግ ታራሚዎች የተከለከሉና የተወገዙ ነገሮች መያዝ፣ መፈጸም ወይም መጠቀም የሚከለክል በመሆኑ፣ በጥበቃ አባላት በሚሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት በእነዚህ ተጠርጣሪዎችም ላይ ፍተሻ መደረጉንና የተገኙ ስለት ነገሮች እንደነበሩ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አምባዬ አስረድተዋል፡፡

አድማና ብጥብጥ የሚያነሳሱ ጽሑፎችን እንዲሁም በአንዳንድ ጠያቂ ቤተሰቦች በፍተሻ የሚታለፉ በጥብቅ የተከለከሉ ሲጋራና ስለት መገኘታቸውንም አክለዋል፡፡ ብርበራና ፍተሻው የተደረገው ከሕግ ውጪ በምሽት አለመሆኑንና ሆን ተብሎ የተቋሙን ስም ለማጥፋት እንደሆነ አስተዳዳሪው አስረድተዋል፡፡

የሕግ ታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞች አያያዝ ደንብ ቁጥር 138/99 አንቀጽ 18፣ ታራሚዎች ከማረሚያ ቤቱ ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር እንዲጻጻፉ ይፈቅዳል፡፡ ለጥበቃ ሥራ ተቃራኒ የሆኑ ተግባራትን እንዳይፈጽሙ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚያዝ በመሆኑ፣ የጽሑፎቹን ይዘት ለማወቅ ሲባል አድማና ብጥብጥ የሚያስነሱ እንዳይሆኑ ለመከላከል የተደረገ በመሆኑ፣ የባለቤቶቹ ስም ተመዝግቦ ሊጣራ እንደሚችል አስተዳዳሪው በመግለጽ፣ ተጠርጣሪዎቹ ‹‹ለፍርድ ቤት ክርክር ለማድረግ ያዘጋጀናቸው መጣጥፎች ተወሰዱብን፤›› ብለው ላቀረቡት አቤቱታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ደንበኞቻቸው ገንዘብ እንደተዘረፉ አድርገው ጠበቃቸው ስላቀረቡት አቤቱታ አስተዳዳሪው ሲመልሱ፣ ‹‹ምንም ዓይነት ገንዘብ አልተወሰደም፡፡ የሕግ ታራሚዎች ከ100 ብር በላይ ገንዘብ መያዝ አይፈቀድላቸውም፤›› ብለው፣ ይኼ ደግሞ በዘፈቀደ የሚባል ሳይሆን የሕግ ታራሚዎች መተዳደሪያ በመመርያ ቁጥር 01/96 ተደንግጐ የሚገኝ በመሆኑ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ከ100 ብር በላይ ይዘው ከተገኙ ለቤተሰብ እንደሚሰጥላቸው ወይም በአደራ እንዲቀመጥ ከማድረግ ውጪ እንደማይወሰድባቸው አስረድተዋል፡፡ በተጠርጣሪዎቹና በጠበቃቸው የቀረበው አቤቱታ የሐሰት መሆኑን በመግለጽ አስተባብለው፣ አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ሌላው ያየው ጉዳይ፣ ዓቃቤ ሕግ አቶ አብርሃም ሰለሞንና አቶ ሰለሞን ግርማ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ክስ አሻሽሎ ማቅረብ አለማቅረቡን በሚመለከት ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ አሻሽሎ እንዳቀረበ ለችሎቱ ተናግሮ፣ ለሁለቱ ተጠርጣሪዎች ክሱን አንብቦላቸዋል፡፡ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በሰጡት አስተያየት ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ችሎት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ክሱ እንዳልተሻሻለ አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ክሱ እንዲሻሻል የታዘዘው ተጠርጣሪዎቹን ማን እንደመለመላቸውና መቼ እንደተመለመሉ (የግንቦት 7 አባል እንደሆኑ) መግለጽ እንደነበር አስታውሶ፣ ማሻሻሉን አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሁለቱንም ወገኖች ካዳመጠ በኋላ መዝገቡን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለየካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...