Saturday, September 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕዝብ የመንግሥትን አመኔታ የሚፈልግባቸው አራት ነጥቦች

ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ ኖሮት የየዕለት ሕይወቱን መምራት ይኖርበታል፡፡ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ፍላጎት ዘለቄታዊ የሆነ እርካታ እንዲፈጠርለት ሲፈለግ ደግሞ፣ ዋና ዋና የሚባሉ ጉዳዮች መፈተሽ አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንገብጋቢ ተብለው ሊጠቀሱና መፍትሔ ሊፈለግላቸው የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮች በአራት ይጠቃለላሉ፡፡

  1. ሥርዓተ አልባው የግብይት ሥርዓት

የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት መረን ከመለቀቁ የተነሳ የዜጎችን ሕይወት እያናጋ ነው፡፡ በገበያ ሕግጋት እየተመራ ነው የሚባልለት ይህ የግብይት ሥርዓት ጤናማ ካለመሆኑም በላይ፣ በውድድር ላይ ተመሥርቶ የማይከናወን በመሆኑ ሕዝቡን ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት እየዳረገው ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ በተወሰኑ ብልጣ ብልጦችና በመንግሥት ጉያ ውስጥ በተደበቁ ሙሰኞች በመመረዙ ምክንያት፣ በሸቀጦች አቅርቦትና ፍላጎት መካከል መኖር የነበረበት ጤነኛ መስተጋብር ጠፍቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በዋጋ ግሽበት ሕዝቡ እየተመታ ነው፡፡ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ሲጨምር የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ዋጋ ይሰቀላል፡፡ የነዳጅ ዋጋ ሲቀንስ ግን በተመጣጠነ ሁኔታ ቅናሽ አይታይም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሐሰተኛ ሚዛን ሕዝቡ እየተበዘበዘ ነው፡፡ ጥራታቸው የተጓደለና ለአገልግሎት ብቁ ያልሆኑ ምርቶች ገበያው ውስጥ በሰፊው አሉ፡፡ ሕዝቡ በገንዘቡ ማግኘት የሚገባውን እያገኘ አይደለም፡፡ ይህ በሕዝቡ ውስጥ የሚሰማ መፍትሔ የታጣለት ብሶት ነው፡፡ ሕዝብ የመንግሥትን አፋጣኝ መፍትሔ ይጠብቃል፡፡

በመኖሪያ ቤቶች እጥረት ምክንያት በጣም በርካታ ዜጎች በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተከራይተው ይኖራሉ፡፡ ከሚያገኙት አገልግሎት ጋር የማይመጣጠን ከፍተኛ ኪራይ እየከፈሉም በየጊዜው ጭማሪ ይደረግባቸዋል፡፡ በተለይ ለዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል የተገነቡ የኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች ለንግድና ለተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት እየተከራዩ ከፍተኛ ገቢ ስለሚያስገኙ፣ ዜጎች በደላሎችና በአከራዮች ወከባ እየተፈናቀሉ ነው፡፡ የኑሮ ጫናው ሳያንስ በመኖሪያ ቤት እጦት የሚንገላቱ ዜጎችን የሚከላከል ባለመኖሩ፣ ከኪራይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየተፈናቀሉ ለጤና ተስማሚ ባልሆኑ ባረጁ መንደሮች ውስጥ ለመኖር የሚገደዱ በዝተዋል፡፡ በአከራይና በተከራይ መካከል የሚኖረው ግንኙነት በሕግ ማዕቀፍ መመራት ሲገባው፣ ዜጎች የደላላ መጫወቻ እየሆኑ ናቸው፡፡ የሚገነቡት የኮንዶሚኒየም ቤቶች እስኪጠናቀቁ ድረስ እነዚህ ወገኖች ለመንግሥት አቤት እያሉ ነው፡፡ መፍትሔ ይፈለግ፡፡

  1. የታክስ ሥርዓቱ ህፀፆች

ማንም ዜጋ ግዴታውን ተወጥቷል ከሚባልባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ታክስ መክፈል ነው፡፡ የሚከፈለው ታክስ ለመንገድ መሠረተ ልማት፣ ለታላላቅ የኃይል ማመንጫዎች፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለሕክምና ተቋማትና ለተለያዩ አገራዊ ፋይዳዎቸ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ነገር ግን የሚፈለግባቸውን ግብርና ታክስ በወቅቱ ሳይስተጓጎሉ የሚከፍሉ ያሉትን ያህል፣ የታክስ ሥርዓቱን ላልተገባ ዓላማ የሚጠቀሙበት አሉ፡፡ ትክክለኛ ገቢያቸውን በመደበቅ የታክስ ሥወራ ድርጊት የሚፈጽሙት እነዚህ ኃይሎች አገሪቱን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ገንዘቦች ያሳጡዋታል፡፡ በመንግሥትም ሆነ በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ወገኖች በየወሩ የሚፈለግባቸውን ግዴታ ሲወጡ፣ በአክሲዮን ማኅበራት የተደራጁ ባንኮች፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ሌሎች የግል ድርጅቶች ሕጉን አክብረው ታክስ ሲከፍሉ፣ ከፍተኛ ትርፍ እያስመዘገቡ አገሪቱን የሚመዘብሩ ወገኖች አሉ፡፡ ሕዝቡን እያስለቀሱ ነው፡፡

በታክስ ሰብሳቢው መሥርያ ቤት ውስጥ ያሉ ቢጤዎቻቸውን ተገን በማድረግ ለአገሪቱ ትልቅ ፋይዳ ያለውን ሀብት የሚያጭበረብሩ እነዚህ ኃይሎች፣ የጉምሩክ ኬላዎችን በሙስና በማለፍ በኮንትሮባንድ ዕቃ አገሪቱን ያጥለቀልቋታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እነሱ ታክስ ያልከፈሉባቸው ሕገወጥ ሸቀጦች ማለትም ውድ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ አልባሳት፣ መጫሚያዎችና የተለያዩ ምርቶች ገበያው ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋሉ፡፡ በራሳቸው ጥረት ለፍተው ባጠራቀሙት ገንዘብና በባንክ ብድር የሚሠሩ ዜጎች ለኪሳራ ይዳረጋሉ፡፡ የታክስ መረቡ እነዚህን ሕገወጦች ማስገር ካልቻለ አደጋ ነው፡፡ እነሱ በሚፈጥሩት ጫና ምክንያት ሕዝቡ ለጉስቁልና እየተዳረገ በመሆኑ መንግሥት መፍትሔ ይፈልግ፡፡

  1. የመልካም አስተዳደር እጦት

ይህ ርዕሰ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ብዙ የተባለበት ቢሆንም፣ አሁንም ከአሳሳቢነት በላይ የዘለቀ ነው፡፡ ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ምን ያህል አመኔታ አላቸው? ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥቱ ድረስ ለዜጎች አቤቱታ የሚሰጠው ትኩረት ምን ይመስላል? ያለምንም ተጨባጭ ምክንያት ውኃ ለበርካታ ቀናት ለምን ይጠፋል? የኤሌክትሪክ ኃይልም እንዲሁ፡፡ የሞባይል ስልክ ኔትወርክና የኢንተርኔት አገልግሎት ጥራት ችግር የማይቃለለው ለምንድነው? በሚመለከታቸው አካላት የሚሰጠው ምክንያት አጥጋቢ አይደለም፡፡ ችግሮች ተቃለዋል ሲባል ይብስባቸዋል፡፡

ከንግድ ፈቃድ ምዝገባና ዕድሳት ጋር በተያያዘ ያለው እንግልት አልቀነሰም፡፡ የንግድ ስያሜን በተመለከተ የሚታየው ምክንያት አልባ አተካራ ራሱን የቻለ ራስ ምታት ነው፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት አገልግሎት ፍለጋ የሚሄደው ሕዝብ በይፋ ጉቦ አምጣ ይባላል፡፡ የግንባታ ፈቃድ ለመጠየቅ፣ የመሬት ልኬት ለማድረግ፣ መንጃ ፈቃድ ለማደስ ወይም ለማውጣት፣ በመንግሥት ሆስፒታሎች ተራ ይዞ ለመታከም ወይም አልጋ ለመያዝ፣ ወዘተ ሙስና ዋነኛ ቁልፍ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአገሪቱ በአስደንጋጭ ሁኔታ የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ ላለው የተሽከርካሪ አደጋ ከዋነኛ ምክንያቶች መካከል አንዱ ሙስና ነው፡፡ በሙስና የከባድ የጭነትና የሕዝብ  ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃድ እየታደለ ነው፡፡ በርካታ ሕዝብ ደግሞ እያለቀ ነው፡፡ ከፍተኛ የአገር ንብረት እየወደመ ነው፡፡ መንግሥት ምን እያደረገ ነው? ሕዝብ እየጠየቀ ነው፡፡ ለመልካም አስተዳደር እጦት የሆኑ ሕዝብ የሚያማርሩ ጉዳዮች በዝተዋል፡፡ መፍትሔ! መፍትሔ!

  1. የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፈተናዎች

የመንግሥት ሥልጣን የሚገኘው ከሕዝብ በሚገኝ ፈቃድ ነው፡፡ ይህ ዴሞክራሲ በሰፈነባቸው አገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን የሕዝብ ነፃ ፍላጎት ነው፡፡ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የምትችለው ነፃ ኅብረተሰብ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረታዊ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድርና የሕግ የበላይነት መኖር ናቸው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገው ትግል ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ መሆኑን መዘንጋት ነው፡፡

የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚያግዙ በርካታ አንቀጾችን በውስጡ ይዟል፡፡ ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅ የሚፈልጉትን የፖለቲካ አማራጭ እንዲመርጡ ዕድሎችን አመቻችቷል፡፡ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከተፈለገ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ በምርጫው ተወዳዳሪ የሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ በመንግሥት ላይ የሚኖረው ጫና ግን ከፍ ይላል፡፡ በመጀመሪያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች፣ የፀጥታ አስከባሪዎችና የመሳሰሉት አካላት ገለልተኝነታቸውን አስመስክረው ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት፡፡ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምኅዳሩ ሰፍቷቸው በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲወዳደሩ በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ወገን የሕግ የበላይነትን አክብሮ ከተንቀሳቀሰ ሕዝቡ በነፃነት በመምረጥ የሥልጣን ባለቤት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ የመንግሥትንም መተማመኛ ይፈልጋል፡፡ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲኖረው ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ይፈቱ፡፡ ሕዝብ አሁንም ተግባር! ተግባር! ይላል፡፡  

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...