Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ተመልሼ የመጣሁት ለደንበኞች በሙሉ ቤቶቻቸውን ሠርቼ ለማስረከብ ነው›› አቶ ኤርሚያስ አመልጋ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር መሥራችና የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኤሚርያስ አመልጋ፣ ወደ አገር ቤት ተመልሰው እንዲመጡ በሕግ ያለመጠየቅ ጥበቃ በማግኘታቸው ምክንያት፣ ባለፈው ሐሙስ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት  ከነበሩበት ዱባይ የተመለሱት አቶ ኤርሚያስ ከሪፖርተር ጋር በስልክ ባደረጉት አጭር ቃለ ምልልስ፣ ከመንግሥት ጋር በመሆን የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለደንበኞች በሙሉ ቤቶችን ሠርተው ለማስረከብ መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ የአክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያ ደንበኞች በተቻለ መጠን በፍጥነት መኖሪያ ቤቶቻቸው ተገንብተው እንደሚረከቡ ገልጸው፣ ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው የሚፈልጉ ካሉም መብታቸው የተከበረ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ወደ አገር ቤት የተመለሱት በቅድሚያ የሪል ስቴት ደንበኞችን ቤቶች ገንብተው በማጠናቀቅ ማስረከብ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የሚከናወነው ከመንግሥት ጋር በሚደረግ የተቀናጀ ጥረት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ለጊዜው ከዚህ በላይ ዝርዝር መረጃ እንደማይሰጡ ያስታወቁት አቶ ኤርሚያስ፣ በቅርቡ ለቤት ደንበኞችና ለባለአክሲዮኖች መግለጫ እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡

አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሁለት ሺሕ ያህል ለሚሆኑ ደንበኞች ቤቶችን ገንብቶ ማጠናቀቅና ማስረከብ መሆኑን ተናግረው፣ የሌሎች ኩባንያዎቻቸው ጉዳይም ከዚሁ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለሁሉም መፍትሔ ይፈለግለታል ብለዋል፡፡

‹‹አሁን በመመለሴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 18 ቀን 2013 ከአገር ወጥቼ በዕለቱ ፌብሩዋሪ 18 ቀን 2015 ነው የተመለስኩት፡፡ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝቼ ከተነጋገርኩ በኋላ ሥራዬን በፍጥነት እጀምራለሁ፡፡ ከዚያም አጠቃላይ ሒደቱን በተመለከተ መግለጫ እሰጣለሁ፡፡ አሁን ዋንኛ ትኩረቴ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ከመንግሥት ጋር በመተባበር ማጠናቀቅ ነው፡፡ በአገሬ ልማትም መሳተፍ ፍላጎቴ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ከንግድ ሚኒስቴርና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር በሳምንቱ መጀመርያ ላይ ተገናኝተው በዝርዝር ዕቅዶቻቸው ላይ እንደሚነጋገሩ ታውቋል፡፡

ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ዕትም አቶ ኤርሚያስ በቅርቡ እንደሚመለሱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ እሳቸው ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ የተደረገው መንግሥት በሕግ ያለመጠየቅ ጥበቃ ስለሰጣቸው ሲሆን፣ ይህንን ጥበቃ ያገኙትም  ከአገር ከወጡ በኋላ ከመንግሥት ጋር ባደረጉት ረጅም ጊዜ የፈጀ ድርድር ነው፡፡

አቶ ኤርሚያስ ለአክሰስ ሪል ስቴት ደንበኞች ለመገንባት ቃል ገብተውባቸው የነበሩ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው በሚፈለገው ሁኔታ ሊከናወን ባለመቻሉ፣ ከአገር ወጥተው በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዱባይ ከተማ ላለፉት ሁለት ዓመታት ቆይተዋል፡፡ በተደረገው ድርድር እንዲመለሱ ከተደረገ በኋላ በዋናነት በጅምር የቀሩ ቤቶችን በማጠናቀቅና አዳዲስ ግንባታዎችን በማከል ለደንበኞች ያስረክባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም የሥራ ክንውን ዝርዝር ዕቅዶች መዘጋጀታቸው ይነገራል፡፡

አክሰስ ሪል ስቴትን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት በመንግሥት አማካይነት መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አቶ ኤርሚያስ አሁን ተመልሰው በመምጣቸው ከመንግሥትና ከቤት ደንበኞች ተወካዮች ጋር በመሆን ሥራውን ዳር ያደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በመንግሥት እንዲቋቋም የተደረገው የቴክኒክ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም ባደረገው ጥናት፣ አክሰስ ሪል ስቴት በራሱና በሌላ ሦስተኛ ወገኖች እጅ የሚገኙ መሬቶች አሉት፡፡ የቤቶች ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችለው አቅምም አለው ተብሏል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ከአገር ከመውጣታቸው በፊት በተለያዩ ወገኖች ክሶች የቀረቡባቸው ሲሆን፣ ከፕሮጀክቶቻቸው ጋር በተገናኘ በገቡት ውል መሠረት ባለመፈጸማቸው ጥያቄ ሲቀርብባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች